በአገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች የመልካም አስተዳደር ችግር አለ..................የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

አዳማ ሚያዝያ 15/2006 አገልግሎታቸው ከህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ጋር የተቆራኘ አራት የአዲስ አበባና ፌደራል መስሪያ ቤቶች ላይ ባደረገው ቁጥጥር ለመልካም አስተዳደር ማነቆ የአሰራር፣አደረጃጀትና የህግ ክፍተት ችግር መታየቱን የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
መልካም አስተዳደር ማስፈን ለሰላም፣ለልማትና ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ የመንግስት ተቋማት ተጠያቂነት፣ግልጽና ጥራት ያለው የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ህብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚያነሳው ቅሬታ አጥጋቢ መፍትሔ መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተቋሙ ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ የመንገዶችና ውሃ ፍሳሽ ባለስልጣን፣በኢትዮ ቴሌኮምና ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፓሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ባደረገው ቁጥጥር በጅምር የሚገኝ የአንድ መስኮት አገልግሎት፣የጋራ ፎረም በመመስረት ለህብረተሰቡ ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ቋሚ ኮሚቴው በጠንካራ ጎን ተመልክቶታል።
በተቋማቱ ላይ ተቀናጅቶ ለአንድ ዓላማ መስራት ላይ ሰፊ ክፍተት ከማግኘቱም ሌላ በእያንዳንዳቸው የአመራር፣ የአደረጃጀትና የህግ ማዕቀፍ ክፍተት መኖሩን አረጋግጫለሁ ብሏል ተቋሙ ።
በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ግንባታ ሲካሄድ የውሃ፣ የቴሌና መብራት መስመሮች በወቅቱና በአግባቡ ተነስተው አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው ተቋማቱ የህዝብ ብሶት የሚያስተናግዱበት ሁኔታ በስፋት መፈጠሩን የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ሠራዊት ስለሺ አስታውቀዋል።
በከተማው ለሚከናወኑ የመሰረተ ልማት አውታሮች መጓተት በህግ የተደገፈ የጊዜ ገደብ በስራ ተቋራጮች፣በአማካሪዎችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ባለመኖሩ የህዝቡ ብሶትና ቅሬታ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አልቻለም ብለዋል።
የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን የውሃ መስመሮች ብልሽት በወቅቱ ያለመጠገን፣የውሃ ቆጣሪ ለማስገባት የቤት ካርታ መጠየቅ፣ በአንድ ግቢ ከሁለትና ሶስት በላይ ቆጣሪ ማስገባት፣ወርሃዊ የቢል ክፍያ ጊዜ ካለፈ ቅጣቱ አግባብ ያለመሆኑና በአንዳንድ ቆጣሪ አንባቢዎች ላይ የሚታየው የስነ ምግባር ጉድለት ተቋሙ ያገኘው ችግር መሆኑን ገልጠው ችግሩ መሰረታዊ የውሃ ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ከመሆኑ ባለፈ የባለስልጣኑን ገቢ የሚያቀጭጭ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፓሬሽን የህዝብ ብዛት በሌለበት አካባቢ የሀይል ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ተክሎ አገልግሎት መስጠቱ አሰራሩ ላይ ፍትሃዊና ግልጽነት የጎደለ ከመሆኑም ሌላ ሠራተኞቹ፣ባለሙያዎችና አመራሮች የስራ ተነሳሽነት ማነስ በስፋት የሚስተዋል ችግሮች ናቸው ብሏል።
በኢትዮ ቴሌኮም ከዋናው መስሪያ ቤት ባለፈ በየደረጃው በሚገኙ ሪጅኖች መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ በአደረጃጀቱ ላይ ሰፊ ክፍተት መታየቱ ተረጋግጧል ብለዋል።
በመደበኛና ሞባይል ስልኮች አገልግሎት መቋረጥ፣ የህዝብ አቤቱታን ተከታትሎ መፍትሔ የሚሰጥ አካል በተቋሙ በቋሚነት ያለመመደብ ፣ 994 ጊዜያዊ ምላሽ መስጫ ስርዓት የተዘረጋ ቢሆንም ቅሬታ ተቀባይ በወቅቱ ምላሽ ያለመስጠት ፣በርካታ ውሳኔዎች ወደ ዋናው መስሪያ ቤት መውሰዳቸው በኢትዮ ቴሌኮም የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶችና ውሃ ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ተወካይ አቶ ሲሳይ ወልደአጥናውና አቶ አለማየሁ ሸዋንዳኝ እንደገለጹት ተቋሙ በቁጥጥር ጥናት ያገኘው የመልካም አስተዳደር ማነቆ፣ የአደረጃጀትና የህግ ክፍተት ይገኝበታል።
ከህብረተሰቡ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎች መኖራቸውን ገልጸው በተቋማቱ የህዝቡ የቅሬታ መንስኤ የሆኑትን በመለየት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ተቋሙ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአንድ ግቢ ከሁለት በላይ ቆጣሪ እየገባ ነው የተባለው ትክክል እንዳልሆነና በአንድ ሰነድ አንድ ቆጣሪ ብቻ እንደሚገባ አቶ አለማየሁ ገልጠው ይህ ሆኖ ከተገኘ ተገቢ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱና ከመመሪያ ውጪ የሚከናወን ግዠ ተቀባይነት የሌላቸውና በህግ የሚያስጠይቁ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ተወካይ አቶ ተስፋዮ ደሳለኝና የኢትዮ ቴሌኮም ተወካይ አቶ አለም በዜ እንደገለጹት  በፌደራልና በክልሎች የህብረተሰቡን አገልግሎት አሰጣጥ ዕርካታ ለመመለስ መዋቅሩንና አደረጃጀቱን ከመፈተሽ ጀምሮ በርካታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር ደረጃ የኢንተርኔት ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት በአንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርጾ የተቋሙን ጉድለቶች ለማስተካከል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መግባቱን የገለጹት ተወካዩ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው እልባት ሲያገኝ በክልሎችም ተመሳሳይ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
በአዲስ አበባ መንገዶች፣በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን፣በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮርፖሬሽንና ኢትዮ ቴሌኮም ላይ በተደረገው የቁጥጥር ግኝት ውጤት ላይ የተካሄደው ምክክር የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።
ምንጭ፦http://www.ena.gov.et/index.php?option=com_k2&view=item&id=3328%3A%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8C%88%E1%88_%E1%8C_%E1%88%8E%E1%89%B5-%E1%88%B0%E1%8C%AA-%E1%88%98%E1%88%B5%E1%88%AA%E1%8B%AB-%E1%89%A4%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%88_%E1%8A%AB%E1%88_-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%8B%B3%E1%8B%B0%E1%88_-%E1%89%BD%E1%8C_%E1%88_-%E1%8A%A0%E1%88%88%E1%8B%A8%E1%88%85%E1%8B_%E1%89%A5-%E1%8B%95%E1%8A%95%E1%89%A3-%E1%8C%A0%E1%89%A3%E1%89%82-%E1%89%B0%E1%89%8B%E1%88_&Itemid=249&lang=am#.U1gPzPldX4U

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር