መከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊቱን ወቅታዊ የብሔር ተዋጽኦ ለፓርላማ ይፋ አደረገ፤ ሲዳማን እና ወላይታን በብዛት የያዘው ደቡብ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል



ሰሞኑን የመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊቱን ወቅታዊ የብሄር ተዋጽኦ ለፓርላማ ይፋ ያደረገ ሲሆን ለዘመናት በሰራዊቱ ውስጥ በቁጥርም በጥራትም የበላይነት እንደያዘ የሚነገርለት የትግራይ ክልል በኣማራ ክልል የተተካ መሆኑን ታውቋል።

በደቡቦች በመመራት ላይ በሚገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰራዊቱ የደቡብ ክልል በቁጥር እያደገ የመጣ ሲሆን፤ በብዛት ሲዳማን እና ወላይታን እንደያዘ የተገመተው የደቡብ ክልል በኣሁኑ ጊዜ በብዛት ሁለተኛ ደረጃ ይዟል።  ለዝርዝር ዜናው ከስር ይመልከቱ፦

foto ከድረገጽ
በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት የአገር መከላከያ ሠራዊት የብሔር ተዋጽኦን ለማመጣጠን እየሠራ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና በሁለተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ አደረጉ፡፡ 
ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ሚኒስቴርን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት ነው የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ እየተመጣጠነ መምጣቱን የገለጹት፡፡  
በሚኒስትሩ ሪፖርት መሠረት ከአጠቃላይ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት የአማራ ብሔር ተዋጽኦ 30.3 በመቶ በመሆን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በአንደኛነት ሲመራ የቆየ ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. 29.46 በመቶ በመሆን በቀዳሚነት እየመራ ይገኛል፡፡ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተዋጽኦ ደግሞ በ2006 ዓ.ም. 25.05 በመቶ በመሆን በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የኦሮሞ ብሔር በ2004 ዓ.ም. በ25.2 በመቶ የሁለተኛነት ድርሻ ይዞ የነበረ መሆኑን፣ በ2006 ዓ.ም. ግን ወደ 24.45 በመቶ በመውረድ የሦስተኛ ደረጃን እንደያዘ በሪፖርቱ ውስጥ ሰፍሯል፡፡ 
ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ እንዳስረዱት፣ የደርግ መንግሥት ወድቆ የኢሕአዴግ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ የአገር መከላከያ ሠራዊት አካል የሆነውን ኃይል ከነጥንካሬው እንዲቀጥል ለማድረግ የብሔር ተዋጽኦውን የማስተካከሉ ሥራ በጥንቃቄና በሒደት እየተተገበረ ነው፡፡
በ1989 ዓ.ም. የትግራይ ብሔር በሠራዊቱ ውስጥ የነበረው ተዋጽኦ 40 በመቶ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት ከሠራዊቱ አመጣጥና አመሠራረት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ግን የትግራይ ብሔር ተዋጽኦ ወደ 17.47 በመቶ በመውረድ በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በ1989 ዓ.ም. የደቡብ ሕዝቦች ተዋጽኦ 9.8 በመቶ የነበረ መሆኑን፣ በሒደት በተወሰደ ማስተካከያ 25.05 በመቶ ድርሻ መያዙን ገልጸዋል፡፡ 
‹‹የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች 70 በመቶ የሚገኙበት የደቡብ ክልል በሠራዊቱ ውስጥ ያለው ተዋጽኦ ከ9.8 በመቶ ወደ 25.05 ሲያድግ፣ የሠራዊቱ ብሔር ተዋጽኦ እየተመጣጠነ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ሌላ ማረጋገጫ ልናመጣለት አንችልም፤›› በማለት ለፓርላማው አስረድተዋል፡፡ 
የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ ቀደም ሲል ከነበረበት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት እየተሻለ ቢመጣም ሙሉ በሙሉ ተስተካክሏል ማለት እንዳልሆነ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሱት ደግሞ ክልሎች የሠራዊት ምልመላ ላይ በቂ ትኩረት የማይሰጡ መሆኑን ነው፡፡ በተለይ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ተዋጽኦ የሚፈልገውን ያህል መድረስ አለመቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ 
በ2006 ዓ.ም. በሠራዊቱ ብሔር ተዋጽኦ መሠረት የአፋር ክልል 0.48 በመቶ፣ የጋምቤላ 0.98 በመቶ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ 0.96 በመቶ፣ የሶማሌ 1.14 በመቶ እና የሐረር ደግሞ 0.01 በመቶ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ የሠራዊቱ አመራር አካላት የመተካካት ሥራንም በተመሳሳይ ሁኔታ ነባሩ ኃይል ያሉትን መልካም እሴቶች በማይበርዝ ወይም በማያጠፋ መንገድ እየተከናወነ ነው፡፡ የመተካካት ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በድምሩ 568 ከፍተኛ አመራሮች በመተካካት ሒደቱ የተሰናበቱ መሆናቸውን፣ በምትካቸው ደግሞ 930 ከፍተኛ አመራሮችን ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት የሠራዊቱ አመራሮች የብሔር ተዋጽኦን አላመለከተም፡፡ በተጨማሪም ሪፖርቱን ተንተርሶ በምክር ቤቱ አባላት አንድም ጥያቄ አልቀረበም፡፡ 
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ. በግንቦት 2012 መቀመጫውን እንግሊዝ ካደረገው የሮያል አፍሪካን ሶሳይቲ ዳይሬክተር ታዋቂው ጋዜጠኛ ሪቻርድ ዳውደን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በሠራዊቱ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች በጣም አናሳ ቢሆኑም ይህ በከፍተኛ አመራር ደረጃ እንደማይንፀባረቅ ገልጸው ነበር፡፡ 
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 87 ላይ የመከላከያ መርሆዎች ቀዳሚ ንዑስ አንቀጽ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡     

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር