በሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከመልካም ተሞክሮ ባሻገር ጥቃቅን ችግሮችም አይናቁ

ወደ ሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ግቢ ስዘልቅ ሞቃታማ አየሯን የምትረጨውን ፀሐይ ተቋቁመው በየትምህርት መስካቸው ተግባራዊ ልምምድ የሚያደርጉ ተማሪዎች እዚህም እዚያም ሲታትሩ ታይተውኛል። በስተቀኝ በመንገድ ሥራ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች አፈሩን እየደለደሉና እየጠቀጠቁ ጥራት ያለው መንገድ እንዴት መሥራት እንደሚቻል ተግባራዊ ልምምድ ሲያደርጉ፤ በስተግራ ደግሞ በኮብል ስቶን ሥራ እና በቅየሳ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች በየሙያቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሶች ታጥቀው ሙሉ ትኩረታቸውን በልምምዱ ላይ አድርገው ይታያሉ።
ከተማሪዎቹ መካከል ወደ አንዱ ጠጋ ብዬ «ሥልጠና እንዴት ነው?» የሚለውን የጋዜጠኛ ጥያቄዬን አስቀደምኩ። ተማሪው አራርሶ ወልዴ ይባላል። የመጣው ከሀዲያ ዞን ሾኔ ከሚባል አካባቢ ነው። የሦስተኛ ዓመት የመንገድ ሲቪል ዎርከ ሠልጣኝ ሲሆን፤ በኮሌጁ በነበረው ቆይታ በክፍተትና በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀሱ ጉዳዮችን እንዲህ በማለት ይገልጽልኝ ጀመር « ባለፉት ዓመታት የመምህራን እጥረት ነበር። በሳምንት አምስት ቀን መማር ቢኖርብንም አንዳንድ ቀን መምህራን እየጠፉ ትምህርት የማናገኝበት ቀን ነበር። ይሁን እንጂ ያሉት መምህራን ጊዜያቸውን በመሰዋት ትምህርት እየሰጡን ክፍተቱን ለመሙላት ይጥሩ ነበር። አንዳንድ ለተማሪ ፍቅር የማይሰጡ መምህራንም ነበሩ። ተማሪ ሊያጠፋ ይችላል መምህር መቻል፣ መምከርና ትምህርቱን በአግባቡ መስጠት መቻል አለበት። »
ሠልጣኝ አራርሶ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ሰባ ከመቶ ተግባር ተኮር እንዲሆኑ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሚሰጠው ሥልጠና በኮሌጃቸው በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን ይናገራል። ሰላሳ በመቶ የሚሆነውን ሥልጠና በክፍል ከተማሩ በኋላ ቀሪውን በተግባር ይሰለጥናሉ። በእነርሱ የሥልጠና ዘርፍ የተሟሉ የተግባር ትምህርት መስጫ ቁሶች እንዳሉም ይናገራል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቀደም ብሎ ትኩረት እንደማይሰጠው የተናገረው ሠልጣኝ አራርሶ አሁን ግን አመለካከቱ መቀየሩን ይናገራል። «ከውጭ ሲታይ የጉልበት ሥራ የሚሠራ ይመስላል። እኛ ሠልጥነን ስንመረቅ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ ተማሪዎች በማይተናነስ ሁኔታ አገራችንን እናገለግላለን። ሠልጣኞች እንደ ትንሽ ነገር ሳይመለከቱት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ እጠይቃለሁ» የሚለው አራርሶ ወደ ፊት በሙያው ተደራጅቶ በሠለጠነበት የሙያ ዘርፍ በሚፈጠረው የሥራ መስክ የመሰማራት ራዕይ መሰነቁን ይናገራል።
በኮሌጁ በአይ ሲ ቲ ማኔጅመንት የደረጃ አምስት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ፎዚያ መሀመድ የመምህራንን እጥረት በተመለከተ ሰልጣኝ አራርሶ ያነሳውን ችግር ትጋራለች። «የመምህራን እጥረትና አንዳንዴ በክፍል ውስጥ ያለመገኘት ችግር አለ » የምትለው ሰልጣኝ ይሁንና ተማሪዎች፣መምህራንና አስተዳደሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ውይይቶች ስለሚያደርጉ ጉድለቶቹ ቀስ በቀስ እየተወገዱ መሆኑን ትናገራለች።
በኮሌጁ ተማሪዎች በአንድ ለአምስት የትምህርት ልማት ሰራዊት ተደራጅተው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለመማር ማስተማሩ ሂደት መሳካት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው የምትለው ሰልጣኝ ፎዚያ አደረጃጀቱ ሲጀመር ግን ከሚቃወሙት ተማሪዎች መካከል አንዷ እሷ እንደነበረች ታስታውሳለች። «አምና የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ሲጀመር ከሚቃወሙት ተማሪዎች መካከል አንዷ እኔ ነበርኩ። እኔ ቀድሜ ከሄድኩኝ ከኋላ ያለውን እስክጎትት ጊዜ ይወስዳል የሚል አመለካከት ነበረኝ። አሁን ነው ያለማወቄን ያወቅሁት» የምትለው ፎዚያ አሁን ግን በእሷ የተነሳ ሁለት ወይም ሦስት ተማሪ የተሻለ ውጤት ካመጣ የተማረ የሰው ኃይል እየጨመረ እንደሚሄድና ቡድኑ ውስጥ የተለያየ እውቀት ያላቸው ተማሪዎች ስለሚኖሩ እውቀት መጋራት እንደሚያስችል መገንዘቧን ትናገራለች።
በኮሌጁ በአንዳንድ የትምህርት ክፍሎች ያለው የግብአት እጥረትና በደረጃ ከተከፋፈለ ወዲህ ተማሪዎች በተያዘላቸው ጊዜ ትምህርታቸውን ያለመጨረስ ችግር ስላጋጠማቸው እነዚህ ቢስተካከሉ መልካም መሆኑን የምትናገረው ፎዚያ ሰልጣኞች ከትምህርት በኋላ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የተጀመረውን ቁጠባም በመልካም ጎኑ ታነሳለች።
«እያንዳንዱ ተማሪ ብር እንዲቆጥብ ተብሏል። ይህ ተማሪው ትምህርት ጨርሶ ሲወጣ ሥራ ከመጠበቅ በራሱ አቅም እንዲንቀሳቀስ ያስችለዋል። እኛ ሃያ ከመቶ ብንቆጥብ መንግሥት ቀሪውን በብድር አሟልቶልን ተደራጅተን ሥራ ለመጀመር የሚያስችል አሰራር ተጀምሯል» የምትለው ፎዚያ እሷና የክፍል ጓደኞቿ ከአሁኑ ብር መቆጠብ የጀመሩ ሲሆን፣ በሙያቸው የራሳቸውን ሥራ ለመስራት ተዘጋጅተዋል።
በኮሌጁ የተማሪዎች መሰረታዊ አደረጃጀት ሰብሳቢና በኢንዱስትሪያል፣ኤሌክትሪካልና ማሽን ድራይቭ ሰልጣኝ የሆነው ያሬድ መንግስቱ የሚሰጠው ትምህርት ሰባ ከመቶ በተግባር ላይ ያተኮረ መሆኑ ሰልጥነው ሥራ የሚጠብቁ ሳይሆን ሥራ የሚፈጥሩ እጆች ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ይናገራል። «ትምህርቱ ወደ ተግባር ማተኮሩ ሁሉም ሰልጣኝ ጭንቅላት ውስጥ ተምሮ ሥራ ለመጠበቅ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ የመሆን ሃሳብ እንዲቀረጽ አድርጓል። ትምህርት ቤቱም ያሳደረብን አመለካከት ይሄ ነው። የተማሪዎች ተወካይ እንደመሆናችን በሁሉም የስልጠና ዘርፎች ተማሪዎችን እናወያያለን። ሁሉም ጋ ተመሳሳይ አመለካከት ነው ያለው። »
በተቋሙ የአንድ ለአምስት የትምህርት ልማት ሰራዊት አማካይነት እየተጠናከረ የመጣው ቁጠባ ተማሪዎች ስልጠናውን አጠናቅቀው ሲወጡ ሥራ ለመፍጠር አቅም ይሆናቸዋል የሚል አመለካከት እንዳለው ያሬድ ይናገራል።
የሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ ፍስሐ ሐሪሶ ተቋሙ በ1990 ዓ .ም በመላው ኢትዮጵያ 25 በክልሉ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሲመሰረቱ በሰባት የስልጠና ዘርፎች ትምህርት መጀመሩን ያስታውሳሉ። በወቅቱ 300 አካባቢ የሚደርሱ ተማሪዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከትምህርት ቤት ከሚመጡ ተማሪዎች ይልቅ ትኩረት ያደረገው ሥራ አጥተው ቁጭ ያሉ ወጣቶች ላይ ነበር። በሂደትም ከአስረኛ ክፍል ጨርሰው የሚመጡ ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል። በአሁኑ ወቅት 37 በሚሆኑ ሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። በቀኑ መርሐ ግብር እስከ 6ሺ የሚደርሱ ሰልጣኞች ሲኖሩ በማታው ደግሞ ሺ የሚሆኑ ሰልጣኞች ይገኛሉ። ከከተማው አስተዳደር ጋር በትብብር በሚሰጡ አጫጫር ስልጠናዎች ከሚሳተፉት ሰልጣኞች ጋር እስከ 10ሺ የሚደርሱ ተማሪዎች በኮሌጁ ይስተናገዳሉ።
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚሰጠው ስልጠና ሰባ ከመቶ በተግባር እንዲታገዝ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከኢንዱስትሪው ጋር በመተሳሰር የተግባር ልምምድ ለመስጠት ቢታሰብም በአካባቢው ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ ተቋማት ተሟልተው አለመገኘታቸውን በችግርነት ያነሱት ዲኑ በተቋሙ አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢንዱስትሪዎች ለሥራው አዲስ በመሆናቸውና ግንዛቤው ባለመስፋቱ በአግባቡ ያለማስተናገድ ችግር ነበር። አሁን ግን ይህ ችግር በሚደረጉት ውይይቶች ተፈትቷል የሚሉት አቶ ፍስሐ በተለይ በከተማው የሆቴል ዘርፍ ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ብዙ ሰልጣኞች ለተግባራዊ ልምምደ በሄዱበት ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። «በከተማው የሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች ላይ ከተቋሙ የወጡ ሰልጣኞች ተቀጥረው እየሰሩ ነው። ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ነው።»
ከሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞች በሥራ ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩ ከሚሰጣቸው የሥራ ፈጠራ ስልጠና በተጨማሪ ለሥራ መነሻ የሚሆን የገንዘብ እጥረት እንዳያጋ ጥማቸው ቁጠባ መጀመሩን ኃላፊውም ይናገራሉ። «ሰልጣኞች በአንድ ለአምስት አደረጃጀታቸው ለሥራ የሚሆን ብር ይቆጥባሉ። ስለ ቁጠባ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከኦሞ ማይክሮ ፈይናንስና ከአካባቢው ባንክ በመጡ ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል። የተሻለ ገንዘብ የቆጠቡትን ለማበረታታት የግቢውን መዝናኛ እንዲሰሩበት ተሰጥቷቸዋል። »
በኮሌጁ የተከሰተውን የመምህራን እጥረት በተመለከተ ወቅቱ ግንባታ የተስፋፋበት በመሆኑ ወደእዚያ እንደሚፈልሱ የሚናገሩት አቶ ፍስሐ የለቀቁ መምህራን እስኪቀጠሩ ክፍተቶች ይፈጠራሉ ብለዋል። መፍትሄውንም በተመለከተ « በ 'ደረጃ የሚገኙ መምህራንን በብዛት በመቅጠር ወደ ላይኛው ደረጃ በማሳደግ ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከርን ነው» ያሉት የኮሌጁ ዲን «ሁሉም መምህራን አስፈላጊውን ምዝና ወስደው በማለፍ የሚሰሩ በመሆናቸውና ክፍተቶች እየተለዩ በመሞላታቸው የስልጠና ሥርዓቱ መሻሻል እያሳየ ነው። በዚህም የተማሪዎች የምዘና ውጤት መሻሻል በማሳየቱ ባለፈው ዓመት 70 ከመቶ የሚሆኑት ተገቢውን ውጤት አምጥተው አልፈዋል» ብለዋል።
በሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደ ኮምፒዩተርና ሌሎችም ለመማሪያ የሚያገለግሉ የመማሪያ ግብአቶች እጥረት እንዳለ ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠር ነው ይላሉ አቶ ፍስሐ። « በኮሌጁ በርካታ ሰልጣኞች በመኖራቸው መሳሪያዎቹ ጫና ስለሚበዛባቸው ብልሽት ይገጥማቸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ግን በርካታ ግዢዎች በመፈጸ ማቸው እጥረቶችን ለመፍታት ተችሏል።»
ኮሌጁ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚሰራ የሚናገሩት አቶ ፍስሐ በሐዋሳ ሦስት ክፍለ ከተሞችና በሲዳማ ዞን በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ለተደራጁ ማህበራት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በመደረግ ላይ ነው ይላሉ። በዚህም ክህሎታቸው ተለይቶ ስልጠና ይሰጣቸዋል። የቴክኖሎጂ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። የሥራ አመራር ስልጠናና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚደረግ ድጋፍ ይሰጣል። የብረት መቁረጫና የተለያዩ ቁሶችን በመጠቀም ከሰል የሚያመርት ማሽን እንደ አብነት የሚጠቀሱ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የተሸጋገሩት ቴክኖሎጂዎች ናቸው።
የሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት፤ ብቃት ያለውና በሥራ ክቡርነት የሚያምን ዜጋ ለማፍራት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እውን በማድረግ ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የጎላ ድርሻ የሚያበረክት አርዓያነት ያለው ተቋም የመሆን ራዕይ ሰንቆ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ነው። በተማሪዎች የሚነሱትን ጥቃቅን እንከኖች በማረም የሚታሰበው ግብ ላይ ለመድረስ የተቋሙ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለበለጠ መትጋት ይጠበቅባቸዋል።
ምንጭ፦ ኣዲስ ዘመን ጋዜጣ http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/society

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር