ስለከሸፈው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ጥራዝ አንዳንድ ነጥቦች

በተስፋዬ ንዋይ
 መነሻ
የአገራችንን የአጭር ጊዜ ታሪክ በጥልቀት ለሚመለከት ታዛቢ እጅግ በጣም የሚያሰቅቅና አፍ የሚያሲዘን ጉዳይ የተወሰኑ የዕውቀት ገመዶች የጥፋት ብርሃን ማስተላለፊያ በመሆናቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በተጨባጭ እውነት ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊ ትንታኔ በበቂ ሁኔታ የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ይህ መሠረታዊ ሀቅ ንቅንቅ ወደማይል አለትነት የደረሰ ይመስላል፡፡ ይህን ችግር ከመሠረቱ የሚፈጥረው ደግሞ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ተብሎ በጽሑፍም ሆነ በቃል የሚተረተረው ሐሳብ እውነታን መሠረት ያላደረገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ፣ ግብዓትና ዓላማ ተብሎ የቀረበ ወይም እየቀረበ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ መምታታት አገሪቷን አንድ አስማሚ የሆነ ታሪክ የሌላት የሚያስመስላት ብቻ ሳይሆን የግልን የፖለቲካ ዓላማ ማካሄጃ መድረክ እንዲሆን ዕድል ፈጥሯል፡፡ 

የአገራችን የታሪክ ሒደትና ውጤት ላይ በእውነት (Authentic) ላይ የተመሠረተ የታሪክ ዕድገት በአገሪቷ ተመዝግቦ  ያለመኖሩ አንድ ችግር ሆኖ፣ እነዚህ በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ታሪኮችን ከእውነት በላይ አድርጎ በመውሰድ ምሁራዊ ትንታኔዎችን በእነሱ ላይ መስጠት ሌላው አበሳጭ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን እንድል ያደረገኝ በቅርቡ በገበያ ላይ ውሎ የተሰራጨውን  “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ጥራዝ አንብቤ ከጨረስኩኝ በኋላ ነው፡፡ ይህ ጥራዝ የተጻፈው መስፍን ወልደማርያም በሚባሉ ግለሰብ (እኚህ ግለሰብ ፕሮፌሰር የሚል ማዕረግ የደረቡ ቢሆንም በመጽሐፉ ላይ ስላወለቁት እኔም ትቼዋለሁ) ሲሆን፣ በዚህ አጭር በማይባል ጥራዝ ጸሐፊው ያሉዋቸውን አስተሳሰቦችና ከአስተሳሰቦቹ ጀርባ ያሉትን መነሻዎች በሚገባን ቋንቋ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጥራዝ የታጨቁት ሐሳቦች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፣ በዚህች አጭር ጽሑፍ ለመመልከት የምፈልገው በጥራዙ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በሚያጣፍጡ ወይም በሚመርዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ማን ነች? ማን ነበረች? ምን ዓይነት ሥልጣኔ ነበራት?  
ኢትዮጵያ ማን ነች? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ምናልባትም አገር ነች ይሆናል፡፡ ጥያቄው በአዕምሮ ውስጥ ያለውን የሐሳብ ማስተላለፊያ ገመድ የሚያጨማትርና የሚያጨናንቅ ደረጃ ላይ የሚደርሰው፣ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አገር ነበረች? የሚለውን ጥያቄ ስናክልበት ነው፡፡ ጡዘቱን ለመጨመር ኢትዮጵያ በታሪክ የሚታወቅ ምን ዓይነት ሥልጣኔ ነበራት? የሚለውን እንጨምርበት፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ጥራዝ ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ ባለቤት መሆኗን በመግለጽ ሥልጣኔዎቻችን ወይም ጥበቦቻችን አሁን ያሉበትን ደረጃ እንካችሁ ይሉናል፡፡ እንዲህ በማለት፣ “የአክሱም ሐውልት፣ የላሊበላ ከድንጋይ የተፈለፈሉ ቤተ ክርስቲያኖች፣ የጎንደር ቤተ መንግሥት የሠራ ሕዝብ ከደሳሳ ጎጆ ጋር ተቆራኝቶ ለብዙ ምዕት ዓመታት የቆየበት ምክንያት ምንድነው? የድንጋይ ሥራ ጥበብ ከሽፎ የቀረበት ምክንያት ምንድነው?” ገጽ (9) እያሉ ይቀጥላሉ፡፡

ጸሐፊው እነዚህን መሰል ጎርጓሪ የቁጭት ጥያቄዎችን ከደረደሩ በኋላ መሠረታዊ የሚሏቸውን ምክንያቶች በገጽ (23) ላይ ወደ መደርደር ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች በመጀመሪያ ረድፍ ላይ የመቀመጥ ዕጣ ፈንታ ያጋጠማቸው ከሕግና ሥርዓት አንፃርና በአስተዳደር በኩል ያሉትን ችግሮች ነው፡፡ መፍትሔ ብለው የሚያስቀምጧቸውም ሐሳቦች ከእነዚሁ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ጸሐፊው “ኢትዮጵያ” የሚለውን “ታላቅ”  ስም ወስደው በብዙ የጥራዙ ገጾች የደረደሩትና የኢትዮጵያ ታሪክ ከሸፈበት ብለው የገለጹት “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ላይ ብቻ የታጠረ ነው፡፡ ይሁንና ጸሐፊው በጥራዛቸው ከገለጹት “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪክ መክሸፍ አንፃር በመጀመሪያ ሌሎች የጥበብ ወይም የሥልጣኔ ውጤቶች አሁንም ሆነ ድሮ በምናውቃት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖራቸው ወይም አለመኖራቸው ያለመግለጻቸው፣ ለጥራዛቸው የመጀመሪያው የክሸፈት አረንጓዴ ምልክት መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪክ ከሸፈ ብለው የሚገልጹት ታሪክ (ከሸፈ ብለን መስማማት ከቻልን) በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሚገኘውን ጥበብ ነው፡፡ ስለዚህ የሰሜኑን “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪክ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ መመልከት የተንሸዋረረ ምሁራዊ የታሪክ ትንታኔ ከማለት ውጭ ሌላ ማለት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሀቁን ወደ ምድር ለማውረድ ያህል እውነት የትኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ነው የከሸፈው? የኢትዮጵያ ታሪክ “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪክ ብቻ ነው ወይ? የኢትዮጵያ ታሪክ ብለው ጸሐፊው የበየኑትን ሥልጣኔስ ማን ነው ያከሸፈው? መክሸፉን ከመበየን በፊት አክሻፊውን ማሳየት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ታሪክ ጸሐፊው እጅግ ከማጥበባቸው የተነሳ ከከሸፈው “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪክ አንፃር ብቻ ቃኝተውታል፡፡ ጸሐፊው በአገራችን የሰሜኑ ክፍል የነበሩት እሳቸው “የድንጋይ ሥራ ጥበብ” ታሪኮች ብለው የገለጹዋቸው ሥልጣኔዎች መክሸፋቸውን ሲገልጹ፣ በአገሪቱ የነበሩ ሌሎች “የጥበብ ታሪኮች” ለምሳሌ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓትና ሌሎችም ስለመክሸፋቸውና አለመክሸፋቸው የነገሩን አንድም ነገር የለም፡፡ ይህ በዚህ ጥራዝ ሳይታቀፍ ለምን ታለፈ? ወይስ የኦሮሞ፣ የወላይታ፣ የሲዳማና የመሳሰሉት የጥበብ/የሥልጣኔ ታሪኮች እንደ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ታሪኮች አይታዩም? ጥራዙ ለዚህ መልስ የለውም፡፡ ይህም ጥራዙን የከሸፈ ያስብለዋል፡፡

የትኛውን ታሪክ ጸሐፊ/ተንታኝ እንመን?
ይህን ነጥብ ይበልጥ ለማብራራት ከጥራዙ የተወሰኑ ሐሳቦችን እንምዘዝ፡፡
“የታሪክ ባለሙያው የአንድን ኅብረተሰብ ወይም ሕዝብ ታሪክ በሚመዝንበትና የታሪኩን አካሄድ በሚገልጽበት ጊዜ እሱ ራሱ የት ሆኖ ነው? መጀመሪያውኑ እሱ ራሱ የታሪኩ ባለቤትና የታሪኩ ምንጭ የሆነው ኅብረተሰብ ወይም ሕዝብ ክፍል አካል ይሆናል፡፡” ገጽ (53) 
“በታሪክ ትምህርት በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ አልታደለም፣ የጥንቶቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ታሪክን የሚጽፉበት ቋንቋ ግዕዝ ነበር፣ ሁለተኛም ንጉሠ ነገሥቶችን ለማወደስ ነበር፡፡ ስለዚህ በቋንቋውም ሆነ በዓላማው የነገሥታቱ ታሪክ /ዜና መዋዕል/ የተጻፈው ለሕዝቡ አልነበረም፡፡ ዓላማውም ውስን በመሆኑ ቋንቋውም ውስን ነበርና የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ በገዛ ራሱ ታሪክ ጨለማ ውስጥ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡” ገጽ (76)

ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን ለማወቅ እጅግ በጣም የሚጓጉ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ ይህም የመነጨው አገራችን እውነተኛ (Authentic) ታሪክ ያልነበራት ስለሆነ ነው የሚለውን የጸሐፊውን ዕይታ ይህ ጸሐፊም በመጠኑ የሚቀበለው ነው፡፡ ጥያቄው ግን እውነተኛ ያልሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ የትኛው ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ የሚሰጠው ትንታኔ ነው፡፡ ጸሐፊው በመጀመሪያው ሐሳብ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት የታሪክ ባለሙያ የመወሰን ወይም አገር የመቅረፅ ሥልጣኑን በመጠቀም የማኅበረሰቡም አባል በመሆኑ ለማኅበረሰቡ መሥራት እንዳለበት አስቀምጠዋል፡፡ ይመስለኛል የእርስዎ የታሪክ ትንታኔም ለታሪክ ጸሐፊው ያስቀመጡትን ገመድ (ለማኅበረሰቡ የመሥራት) በጥሰው የወጡ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የነበሩ የታሪክ ጽሑፎች (ዜና መዋዕሎች) የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨለማ ውስጥ ያደረጉና ለነገሥታት ብቻ የተጻፉ የሕዝብ ታሪክ ያለመሆናቸውን በገለጹበት ብዕር፣ አፍታም ሳይቆዩ የተለያዩ አፄዎችን ዜና መዋዕሎች እንደ እውነተኛ ታሪክ በመውሰድ በመጠኑም ምክንያታዊ ይሆናሉ የሚባሉትን ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፊዎችን ያለ ርህራሔ በቀለም አርጩሜ ይገርፏቸዋል፡፡ ለምሳሌ ጸሐፊው የፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት “Church and State In Ethiopia” መጽሐፍ በተቹበት ነጥብ ላይ፣ አምደ ፅዮንን “ጀግና” ብለው ካሞገሱ በኋላ እኚህ ንጉሥ በዜና መዋዕላቸው እንዲገባላቸው ያስደረጉትን “እንዘ ንጉሥ አነ ላዕለ ኵሉ ተንባላት ዘምድረ ኢትዮጵያ” በመውሰድ ይህም ማለት “ለክርስቲያኑም ሆነ ለእስላሙ ኢትዮጵያዊ ከአምደ ፅዮን በቀር ሌላ ንጉሥ የለውም ማለቱ ነው፤” በማለት፣ “ኢትዮጵያ አንድ አገር ነበረች ማለት ነው” ብለው ከደመደሙ በኋላ፣ “ታደሰ የእስላም አገረ መንግሥት ወይም የክርስቲያን አገረ መንግሥት የሚለውን ከየት አመጣው?” በማለት የዜና መዋዕሉን ትክክለኛነት በማጠንከር የታሪክ ምሁሩን ትንታኔ አፈር ድሜ ያበሉታል፡፡ ይህ የጸሐፊው ትንታኔና አንድምታ ጸሐፊው ዜና መዋዕሎችን (የግራኝ መሐመድ ዜና መዋዕልን ጨምሮ) ለሚፈልጉት ዓላማ እስካገለገላቸው ድረስ ሲጠቀሙበት ትንታኔያቸው በንጉሥ ተነግሮት ዜና መዋዕልን ከሚደርሰው ጸሐፊ ትዕዛዝ ያልተለዩ መሆናቸውን ነው፡፡ 

በሌላ በኩል የጸሐፊው የመስመር ዘላቂነት ወይም ኢ-ዘላቂነት ግራ የሚያጋባው ስለ ውጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎች ያላቸው ምልከታ ነው፡፡ ጸሐፊው በጥራዛቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ማደግ የጀመረው የውጭ ሊቃውንት መግባት ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ መሆኑን መግለጻቸውን ዘንግተው ይመስል በሌላ ቦታ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡፡ “የውጪ አገር የታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ በመምጣት የተለያዩ ጥናቶችን የሚያደርጉት ለእንጀራ መብያቸው” ገጽ (59) ሲሉ፣ በሌላ ቦታ ደግሞ “… ስለ ቋንቋዎች፣ ስለዘር፣ ስለባህል፣ ስለታሪክ፣ በጠቅላላ በሕዝቡ መሀል ስላለው የሃይማኖትና ቋንቋ፣ የኑሮና ሌላው ልዩነት ላይ የውጭ አገር ሊቃውንት የሚያተኩሩት ለምንድነው?” (ገጽ 56)፡፡ እዚህ ላይ ጸሐፊውን መጠየቅ የምፈልገው እነዚህ የተባሉ ልዩነቶች ላይ የውጭ ሊቃውንት ማተኮራቸውን ለምን ጠሉት? ልዩነቶቹ የሉም ለማለት ነው? ወይስ ልዩነቶቹን ለማጥፋት የተደረጉትን አገዛዛዊ ደባዎችና ወንጀሎች ይፋ ያወጡታል ብለው ፈርተው ነው? ዋናው ነገር የውጭም ሆኑ የአገር ውስጥ ሊቃውንት የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ ለማንም ሳይሉ ለእውነት ብለው መጻፋቸው ነው እንደ ነጥብ መወሰድ ያለበት።

ጸሐፊው የውጭ ጸሐፊዎችን ከዚህ በላይ ባለው መልስ ቢተቹዋቸውም ሥራዎቻቸውን እንደ አስፈላጊነቱ በመቀያየር ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ጸሐፊው ኢትዮጵያ በ11ኛው ክፍለ ዘመን የእስላሙም የክርስቲያኑም አገር ነበረች በማለት ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ የጻፈውን ትሪሚንግሀም “Islam In Ethiopia” በሚለው መጽሐፍ እንደ ትክክለኛ የታሪክ ጸሐፊ ወስደው፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የወሰዱትን አቋም ለመተቸት እንዲህ ይሉናል፡፡ “ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው ከኢትዮጵያዊው የተሻለ ኢትዮጵያዊ አመለካከት ሊኖረው እንደሚችል ጥሩ ማስረጃ ነው፤” ገጽ (100) በሚል ደምድዋል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ይህን ጉዳይ የገለጹበትን መጽሐፍ ከማሳተማቸው ከ20 ዓመታት በፊት የትሪሚንግሃም መጽሐፍ መታተሙ በጉዳዩ ላይ ፕሮፌሰሩ የተሻለ ዕይታ እንዳላቸው ለመገመት ብዙም የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ጸሐፊው ግን አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ፣ ለታሪክ ተመራማሪም ትልቁ ሰርተፊኬት ያልነበረችውን ኢትዮጵያ ነች ብሎ ማቅረብ ነው። እንዲህማ ከሆነ ከመነሻው ዜና መዋዕልን መተቸቱ ለምን አስፈለገ? ዜና መዋዕል ኢትዮጵያን የሚጠቅም ጥራዝ ነው ብለን መስማማት ከቻልን ማለት ነው፡፡

ጸሐፊው የሚፈልጉትን ሐሳብ ትሪሚንግሃም በማጠናከሩ ወጣ ገባ እያሉ ቢያወድሱትም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የተለያዩ መጣጥፎችን ያዘጋጀውን ዶናልድ ሌቪንን ከመተቸት ግን አልተዘናጉም፡፡ ይህ ተመራማሪ ባዘጋጀው አንድ የጥናት ውጤት “Wax And Gold:Tradition and Innovation In Ethiopian Culture” ላይ በደረሰበት መደምደሚያ፣ “በስሜት የተሳሰረና አንድነት ያለው የአማራ ኅብረተሰብ የለም” (ገጽ 59) የሚለውን  አጥብቀው ኮንነውታል፡፡ እኔ ሌቪን የደረሰበትን መደምደሚያ ባልቀበለውም፣ ጸሐፊው እሳቸው ስለሚያስቡትና ስለሚፈልጉት “የኢትዮጵያ ታሪክ” ቲፎዞ የሚሆኑ የውጭ አገርም ሆነ የቤተ መንግሥት ዜና መዋዕሎችን ሳያኝኩ ውጠው፣ ኢትዮጵያን በሌላ መንገድ የሚያሳዩ ጥራዞችን  ደግሞ በተበጣጠሰ መልኩ መተቸታቸው እኛን በጥራዝ ለመጋት የሞከሩት የታሪክ ትንታኔ ስለመክሸፉ እንጂ ስለመተኮሱ አያሳይም፡፡

ኢትዮጵያ መቼ ዘመናዊ አገር ሆነች? 
ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት የሕዝቦች አንድነትና ልዩነት ታሪክ ያላት አገር መሆኗ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጉዳዩ ጥያቄ የሚያጭረው ይህ የኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ እንደ አገር ለነገሥታት የተጻፈ ታሪክ ነው? ወይስ የተለያዩ ሕዝቦች ታሪክ ነው? እንደ አገር ለነገሥታት የሚል ታሪክና እንደ ሕዝቦች ያለ ታሪክ ይለያል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መሠረታዊ ናቸው፡፡ በትንሹ ሙቀቱን ለመጨመር ኢትዮጵያ አገር ነበረች ስንል አገር ስለመሆን የሚያሳዩ መስፈርቶችና ምልክቶች ምን ነበሩ? ምንድን ናቸው? ጸሐፊው የአሁኑን ጥያቄ ለመመለስ ዳድቶአቸዋል። እንዲህ እያሉ “አገር” የሚለውን ቃል ወስደው ከዜና መዋዕል ደግሞ “አገረ መንግሥት” የሚለውን ወርሰው ይህም በእንግሊዝኛው (State) ነው ይሉናል፡፡ በዚህም መሠረት “አገር ማለት በአንድ ዓይነት ሕግና በአንድ መንግሥት ጥላ ሥር የሚተዳደሩ ሰዎች/ሕዝብ ባለመብት የሆኑበት የኑሮአቸው መሠረት የሚያደርጉት በወሰን የተከለለና የማይደፈር መብታቸውን ጨምሮ የሚገልጽ ኅብረት ነው” ይሉናል (ገጽ 80)፡፡ ከዚህ ትርጉም አንድ አገር አገር ለመባል የሚከተሉትን ነጥቦች መሟላት አለባቸው፡፡

-    በአንድ ዓይነት ሕግ የሚመራ ሕዝብ
-    በአንድ መንግሥት ጥላ ሥር የሚተዳደሩ ሰዎች
-    ሕዝቦች ባለመብት የሆኑበት/ኑሮአቸውን መሠረት የሚያደርጉበት መብት
-    የተከለለና የማይደፈር መሬት ያላቸው
-    ኅብረት ያላቸው ሕዝቦች
ጸሐፊው እነዚህ መስፈርቶች ላይ በመመሥረት ኢትዮጵያ የመንን ለመርዳት በሄደችበት ጊዜ እንኳን አገር ነበረች ይሉናል፡፡ የአገርን ሁኔታ ለመለየት ደራሲው የወሰዷቸው እነዚህ መስፈርቶች በ18ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ (Modern State) አገሮችን ለመግለጽ በጀርመናዊው የማኅበረሰብ ፈላስፋ ማክስ ዌበር የተቀመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ መስፈርቶች በእንግሊዝኛው “Territory, People/Nation, Soverginity” በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ ጸሐፊው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በአስቀመጣቸው መስፈርቶች መሠረት ኢትዮጵያ አገር ነበረች የሚያሰኝ አንድምታ ያለው ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ በዚያ ወቅት የተከለለና የማይደፈር መሬት የቱ ነበር? በዚያ ወቅትስ ኢትዮጵያ በአንድ ዓይነት ሕግ የሚመራ ሕዝብ ነበራት ለሚሉት ጥያቄዎች ማስረጃችን ምን ይሆን? ይህን ያሉትን ሕግስ ማን አወጣው? መቼም ፓርላማ እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጸሐፊው በመጽሐፉ ውስጥ ያስገቡዋቸው በተለያዩ ግለሰቦች የተዘጋጁ የተለያዩ ካርታዎች እርስ በርስ የተምታቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያሳዩት እውነታ ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻና 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በፊት የተከለለች አገር (Territional State) አለመሆኗን ነው፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው በምን ስሌት ነው ምዕራብ አውሮፓውያን ዘመናዊ መንግሥትን ለመግለጽ የተጠቀሙባቸውን መስፈርቶች ወደኋላ 1,200 ዓመታት በመውሰድ፣ ኢትዮጵያን እንደ ዘመናዊ አገር ለመግለጽ የሞከሩት በውሸት የተጋገረ ታሪክ ከጠቃሚነቱ ይልቅ መርዝነቱ ያይላል።

በዚያን    ጊዜ ኢትዮጵያ ባህላዊ አገር (Traditional State) ነበረች፡፡ በዚህም መሠረት አሁን በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦች በሚሰፍሩበት አካባቢ የራሳቸው የሆነ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መዋቅር ያላቸው ነበሩ፡፡ በንግድ፣ በጦርነት፣ በግጦሽ መሬት ፍለጋ፣ በጋብቻና በመሳሰሉት ምክንያቶች እርስ በርስ በመቀራረብ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የተለዋወጡበት፣ የተወራረሱበትና የነበሩዋቸውንም የማንነት መገለጫዎች ጠብቀው፣ በችግርም ወቅት አብረው አንድ ሆነው የኖሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ የሆኑ አካባቢያዊ መንግሥታት በኢትዮጵያ የነበሩ ሲሆን፣ በአንዱ ማኅበረሰባዊ መንግሥት በተወሰነ የታሪክ ሒደትና አጋጣሚ አንድ ማኅበረሰብ ገዢ ወይም ራሱ ተገዢ የነበረበት ሁኔታ ነበር። እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው ነው እነዚህ ማኅበረሰቦች አሁን በምናውቃት የተከለለች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየትና ታሪኮቻቸውን ለመንከባከብ የበቁት፡፡

መንደርተኛ ማን ነው?
ጸሐፊው በጥራዛቸው እንዲህ ይሉናል፡፡ 
“መንደርተኛ ማለት ከመንደር በማይወጣ አስተያየት፣ ከመንደር በማይወጣ አስተሳሰብና ከመንደር በማይወጣ ስሜት መመራት ነው፤” ካሉ በኋላ መነሻውን ሲበይኑ “የመንደርተኝነት መሠረት ምንድን ነው ዘር ነው፤ ቋንቋ ነው፤ ሃይማኖት ነው፤ ባህል ነው፤ መንደርተኝነት ብሂል ምንድነው ብሎ አይጠይቅም፡፡ መነሻውም መድረሻውም የመንደሩ ቋንቋ፤ የመንደሩ ሃይማኖት፤ የመንደሩ ብሂል ከሌላው ሁሉ የተሻለና የበለጠ ነው የሚል ጠባብ አስተያየት ነው፤ መነሻውም ሆነ መድረሻው ልዩነትን ማጉላት ነው፤” ገጽ (170 እና 171) ይሉናል፡፡ 

ይህንና መሰል “የመንደርተኝነት” ጥራዝ ጀባ ያሉን ጸሐፊ ሰው የራሱን ዘር፣ የራሱን ቋንቋ፣ የራሱን ባህል ከሌለው አስበልጦ በመመልከቱ “መንደርተኛ” ብለው ይፈርጁታል፡፡ እስቲ አንባቢያን ለራሳችንና ለህሊናችን ለሚቀጥሉት ጥያቄዎች መልስ እንስጥ፡፡ የራሱን ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት ከሌላው አስበልጦ የማይመለከት ማኅበረሰብ በዚህ ምድር ላይ አለ? አለ ከተባለ ለምን እንደዚያ ሊመለከት ቻለ? ሰው በተፈጥሮ የዕድገት ሒደት የእናትና የአባቱ ማኅበረሰብ የሚናገረውን ቋንቋ፣ ያለውን ባህልና ሃይማኖት ለማወቅና ለመተግበር ቅርብ ነው ወይስ የሌላውን? በቅርብ ማወቁ የራሱን እንዲያስበልጥ ያደርገዋል ወይስ የሌላውን? የሌላው ከእሱ ስለመብለጡ መስፈርቱ ምነድን ነው? ከእሱ ስለመብለጡ የመወሰን ሥልጣንስ የማን ነው? የባለቤቱ ወይስ የእኔ ይበልጣል ባዩ? በመወሰን ሥልጣን የኔ የበላይ ነው የሚባል ከሆነ ጉዳዩ የተቀባዩን ባህል ማነስ ሳይሆን የሰጪውን ትምክህት የሚያሳይ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ከአሁን በፊት የነበሩት አገዛዞች “መንደርተኝነትን” በማጥፋት አገርን ለመገንባት (Nation Building) ባደረጉዋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉንም “የመንደርተኝነት አስተሳሰብ” እንዳላጠፉት የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገዢዎች የሌሎች ማኅበረሰቦችን የመንደርተኝነት አስተሳሰብን ለማጥፋት የከፈሉትን ዋጋ ያህል የተወሰነ ማኅበረሰብን የመንደርተኝነት አስተሳሰብ ሕጋዊና ተቋማዊ ለማድረግ ጭምር ከፍለዋል፡፡ ግልባጩ ሲታይ ማኅበረሰባዊ መንደርተኝነት የሚጠላው መንግሥታዊ ድጋፍ ያለውን መንደርተኝነት ለማስፋፋት ተብሎ ነው፡፡

የመንደርተኝነት አስተሳሰብ (የራስን የማክበር የሌላውን ያለማቅለል አስተሳሰብ ልበለው) የግጭት መነሻ መሆን የሚያቆመው መንግሥት ለሁሉም ማኅበረሰብ አስተሳሰቦች ዕውቅና መስጠት ሲችል ነው፡፡ ይህን ማድረግ ባልቻሉ አገሮችና መንግሥታት ይህ አስተሳሰብ የማኅበረሰብን ቅራኔ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካኖች የመንደርተኝነት አስተሳሰብን ከፖለቲካና ከመንግሥት አስተዳደር ለማራቅ ብዙ መንገድ ቢሄዱም፣ በአሁኑ ጊዜ ይህን አስተሳሰብ ከመንግሥት መዋቅር ማፅዳት አልቻሉም፡፡ ለዚህም ነው በአሜሪካ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት አስተዳደር ውስጥ ጥቁር ከነጭ እኩል ክብርና መስተንግዶ የማያገኘው፡፡

ጸሐፊው የመንደርተኝነት አስተሳሰብን አምርረው እንደሚጠሉ ቢገልጹም እሳቸው ስለራሳቸው ያነሷቸው ፉከራዎች መንደርተኝነታቸውን ያሳብቃል፡፡ ጠራዡ  እንዲህ ይላሉ፡፡ “በአሜሪካ አገር ተማሪ ሆኜ ለአባቴ ስልክ ለማስገባት ወደ ቴሌፎን ኩባንያው ሄድሁ፤ በሥራ ላይ የነበረችው ሴትዮ ሙሉ ስምህን ጻፍልኝ አለችኝና ጻፍሁት፡፡ በቴሌፎን ማውጫው ላይ የሚገባው ስምህ ማርያም ነው አለችኝ ---- ክርክሩ ቀጠለ ---- ስምህ የሚጻፈው ወልደማርያም መስፍን ተብሎ ነው አለችኝ፡፡ ሲስተርዬ ስሜን የማውቀው እኔ ነኝ፤ ማን እንደሆንህና ማን ተብለህ እንደምትጠራ አታውቅም ካልሽኝ እኔ የምነግርሽን አድርጊ ብዬ ክርክሩ ቆመ፡፡” (ገጽ 60) ይሉናል፡፡ ጸሐፊው በሰው አገር ፊደል ለመቁጠር ሄደው ከአሜሪካውያን የስም አጠራር ባህል ውጭ “የኔ ሐሳብ ትክክል ነው” ማለት ለምን አስፈለጋቸው? ሌሎች ኢትዮጵያውያን ይህን ያለማድረጋቸውን ሲኮንኑ “መንደርተኝነታቸውን” አያሳይም እንዴ? በእርግጠኝነት እሳቸው ለአሜሪካዊቷ መንደርተኛ ናቸው፡፡

ጸሐፊው ይህ የመንደርተኝነት አስተሳሰብ ተጣብቷቸው ሳለ መንደርተኝነትን እንድንተው የሚያስገድዱን መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ ሊጠቃቅሱልን ሞክረዋል፡፡ እነዚህን ምክንያቶች ሲያስቀምጡ፣ “ትክክለኛው የሰው ልጆች ዕድገትና የታሪክ አካሄድ ትውልድ ከመንደርተኝነት ጠባብ አስተያየት ወጥቶ ወደ ዓለም አቀፍ ኅብረት ለመሸጋገር ያለው ከፍተኛ ጥረት ነው፡፡” (ገጽ 173) ይህንን ትንታኔ በሁለት መልኩ ማፍታታት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው የሰው ልጅ ዕድገት ወደ ዓለም አቀፋዊ ኅብረት እንዲሸጋገር ያደረገው ምንድነው? የተለያዩ ማኅበረሰብ ሐሳቦች ገበያ ላይ ቀርበው ከእነዚህ ውስጥ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን የሐሳብ ቡፌ አንስቶ ነው? ወይስ ይህ የሐሳብ ቡፌ ጥሩ  ስለሆነ መመገብ አለብህ። አለበለዚያ! ተብሎ ነው? ለዚህ ነው ትክክለኛ የሰው ልጆች ዕድገትና የታሪክ ሒደት ጸሐፊው ወዳስቀመጡት ደረጃ እስካሁን ያላደረሰን፡፡ ምዕራብ አውሮፓውያን ዘመናዊ አገርን ለመመሥረት ተገጣጣሚ የባህልና የፖለቲካ ማኅበረሰብ (Nation State) መኖር እንደ ወሳኝ ሐሳብ በመውሰድ አገር የመገንባት ሥራዎችን ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሄደውባቸዋል፡፡ አሁን ላይ ሆነን ተገጣጣሚ የባህልና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባት ችለዋል ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ እነዚህ አገሮች  እንደዚህ ዓይነት ማኅበረሰብ መገንባት አልቻሉም ነው፡፡ 

በተለይም ይህን መሰል ተገጣጣሚ የባህልና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለአንድ ዘመናዊ አገር ወሳኝ መነሻ ነው ብላ ብዙ በሠራችው ታላቋ ብሪታኒያ በአሁኑ ወቅት በአራት (አይሪሽ፣ ኢንግሊሽ፣ ዌልሲሽ፣ ስኮቲሽና ብሪቲሽ) በሚባሉ የፖለቲካና የባህል ማኅበረሰቦች ተከፋፍላ ትገኛለች፡፡ ይህን እሳቤ አገር ለመገንባት ተሳክቶላቸዋል በሚባሉት የተወሰኑ አገሮች (ፈረንሳይና ኢጣሊያንን) ማንሳት ይቻላል፡፡ ግንባታው የተፈጸመው የተወሰነ የባህል ማኅበረሰብን በማጥፋት (Ethnocide) ነበር። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በመጥፋት ጎዳና ላይ ያሉት ማኅበረሰቦች (ለምሳሌ ባስክ፣ ኦኪታንያንስና ኮሪሲካንስ) ቢሆኑም እያቆጠቆጡ መሆናቸውን የሚያሳየው፣ አገር ለመገንባት ማኅበረሰብ (ጎሳ) መግደል የሚለው ብሂል ጊዜው ያለፈበትና የከሰረ የፖለቲካ ዘዴ መሆኑን ነው፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ዓለም ወደ አንድ ማኅበረሰብ እየሄደች ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ወደዚያ ለመሄድ እንድንችል የመንደርተኛ አስተሳሰብ እንተው ስንል፣ የእኔ ጥያቄ የማንን መንደርተኝነት ለመቀበል? የነጭ አሜሪካውያንን? ወይስ የቻይኖችን? እነዚህ አገሮች በስልት ወይም በስሌት እያስፋፉ ባሉት መንደርተኛ አስተሳሰብ አይደለም እንዴ ዓለም እየታመሰች ያለቸው? ስለዚህ ጸሐፊው በስድብ መልክ ያስቀመጡት አመለካከት በራሱ መጥፎ አይደለም። መጥፎ መሆን የሚጀምረው የራስን የመንደርተኝነት አስተሳሰብ በኃይልና በንቀት በሌላው ማኅበረሰብ ላይ ለመጫን የሚደረግ እንቀስቃሴ ሲኖር ነው።

ጸሐፊው ሌላው በጥራዛቸው ያነሱት ጉዳይ የመንደርተኝነትን አስተሳሰብ ነፃ አገር ከመመሥረት ጋር በማስተሳሰር ያቀረቡት ትንታኔ ነው፡፡ የሶማሊያ መንግሥትን ጸሐፊው የኮነኑበት አግባብ ይበል የሚያስብል ነው፡፡ በዚህ ላይ ብቻ ቢያቆም ጥሩ ነበር፡፡ ግን እንዲህ ይላል፡፡ “የሶማሊያ መንግሥት የመንደርተኝነት አስተሳሰብን ለሶማሊኛ ተናጋሪዎች ኢትዮያውያን ብቻ ሳይሆን ለኦሮምኛ ተናጋሪዎች፣ ለትግርኛ ተናጋሪዎች፣ ለአፋርኛ ተናጋሪዎች” (ልብ በሉ ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣አፋሮች አላሉም) (ገጽ174) ሰብኳል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እነዚህ ማኅበረሰቦች ለብሔር ጥያቄ ትግል ከሶማሊያ መንግሥት ስለመማራቸው ማረጋገጫው ምንድን ነው? ሶማሊያ አገር ተብላ ከመታወጁ በፊት እነዚህ ማኅበረሰቦች የራሳቸው የማንነት መገለጫ ነበራቸው፡፡ የእነዚህ ማኅበረሰብ የማንነት መገለጫዎች በኢትዮጵያ በነበሩ ገዥዎች ሶማሊያ አገር ከመሆና በፊት ተደፍጥጠውባቸዋል፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቦች በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች የተደፈጠጡባቸውን የማንነት መብቶች ለማስመለስ ሶማሊያ አገር ከመሆኗ በፊት ትግል ጀምረው ነበር፡፡ እነዚህ ማኅበረሰቦች በገዥዎች የተደፈጠጡባቸውን መብቶች ለማስመለስ የንቃተ ልቦና እንክብል ከሶማሊያ መንግሥት ለመቀበል የሚያስፈልጋቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ ጉዳይ የእነዚህንና የሌሎችን ሕዝቦች የትግል ታሪክ መሻር ነው፣ አይቻልም እንጂ። በተጨማሪም እነዚህ ማኅበረሰቦች ነፃ አገር ለመመሥረት ካላቸው ፍላጎት ጋር በማገናዘብ ያቀረቡት ጉዳይ አሁን አገሪቷ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ጥራዙ የከሸፈ ብቻ ሳይሆን፣ የአሁኑን የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበና እንዲሁ ወደ ገበያ የተወረወረ  ነው፡፡

መደምደሚያ
“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚለው ጥራዝ ታሪክን ከፖለቲካ ጋር አላግባብ በማሳከርና በማጋባት ለራስ ዕይታ የሚጠቅምን አለቅጥ ወደላይ በማንሳት፣ የማይበጅን ደግሞ በማንሸራተት ቁንጽል “የጥንታዊት” ኢትዮጵያን “አንድነት” ወይም ዘመናዊ አገርነት በብዕር ለማምጣት የተሞከረበት የጉልበት ሥራ ነው፡፡ ጸሐፊው በጉዳዩ (በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ታሪክ) ላይ ያላቸው ዕውቀት ጥልቀት ያለው መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እዚህም እዚያም ተወርውረው የሚገኙ ቢሆንም፣ የሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ታሪክ ‘አውቀው በንቀት ወይም ሳያውቁት በትምክህት’ ሳይገልጹት አልፈዋል። ምናልባት ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ነው ብለው የጠቀሱትን ሥልጣን የግል መሆንንና የሚገራበትን፣ ሥልጣን የሚሠለጥንበትን ሥርዓት አለማበጀቱ ነው ያሉትን ችግር ለመቅረፍ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ለምሳሌ ኦሮሞዎች በገዳ ሥርዓት) የነበራቸውን የሥልጣን ምንነትና ዕይታ ታሪክ ቢያጠኑ ለኢትዮጵያ ችግር መነሻው ሌላ እንደሆነ ያገኙት ነበር። በዚህም ምክንያት ጸሐፊው ለኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ ምክንያት ብለው በቀረቡዋቸው ሐሳቦች እውነተኛ፣ ሚዛናዊ፣ አካዳሚያዊ ብቃት ያለውና አስማሚ (አቀራራቢ) ትንታኔ ግን ሊያቀርቡ አልቻሉም፡፡ በሌላ በኩል ጽሑፉ በተዘጋጀበት ጊዜ በተለይ ስለመንደርተኝነት ጉዳይ የተገለጸውና የታተመበት ወቅት በዓለምም ሆነ በአገራችን ብዙ ለውጦችና ኹነቶች የተስተናገዱበትና የተስተዋሉበት ቢሆንም፣ ጥራዙ በጉልበት የወጣ ይመስላል። በዚህም ምክንያት ጥራዙ የዓለምን የጊዜ አቆጣጠር ወደኋላ መመለስ ካልተቻለ በቀር ይህን ያህል ተጨባጭ ፋይዳ ያለው አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ጥራዙ የአገራችንን የታሪክ ዑደት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት የራሳችንን ግንዛቤ እንድንይዝ ለማድረግ ያለው ዕድል የጠበበ ቢሆንም፣ በጽሑፋቸውና ጥቂት በሚባሉ “ደጋፊዎቻቸው” ውስጥ እየሟሸሽ ያለውን “የገናናዋን” ቁንጽል “ኢትዮጵያ” እሳቤ ለመረዳት በመጠኑ ስለሚረዳ አንብቤ በመጨረሴ ብዙም አልተቆጨሁም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው seenaafergaa@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
ምንጭ፦http://www.ethiopianreporter.com/index.php/other-sections/law-and-politics/have-your-say/item/681-%E1%88%B5%E1%88%88%E1%8A%A8%E1%88%B8%E1%8D%88%E1%8B%8D-%E2%80%9C%E1%88%98%E1%8A%AD%E1%88%B8%E1%8D%8D-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B0-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%89%B3%E1%88%AA%E1%8A%AD%E2%80%9D-%E1%8C%A5%E1%88%AB%E1%8B%9D-%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%8A%90%E1%8C%A5%E1%89%A6%E1%89%BD

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር