የፕሬዚዳንቱን ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን የሚቀንስ አዋጅ ቀረበ






ሪፖርተር ጋዜጣ 12March2014 -

 መጋቢት 3, 2006 ዓ.ም.


-የፓርላማ አባላት ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንዲጣጣም ጠይቀዋል
የአገሪቱ ፕሬዚዳንትን ለሕግ ታራሚዎች ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን የሚቀንስ አዲስ ‹‹የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት›› ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀረበ፡፡ አንዳንድ የፓርላማው አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል በማለት እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱን ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 71 (7) ‹‹ፕሬዚዳንቱ በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል›› በማለት ይደነግጋል፡፡
በ1996 ዓ.ም. የወጣው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጅም በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጠውን ይቅርታ የማድረግ ሥልጣን ያጠናክረዋል፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ፕሬዚዳንቱ የይቅርታ ቦርድ የውሳኔ ሐሳብን መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የቀረቡ መረጃዎችን ፕሬዚዳንቱ በራሱ መመዘን ለሕግ ታራሚዎች ይቅርታ እንዲያደርግ ወይም እንዲከለክል ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ይቅርታ ያገኘ ታራሚ በሕጉ መሠረት የተጣለበትን ጥሶ የተገኘ ከሆነ በይቅርታ ቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ የሰጠውን ይቅርታ የማንሳት መብት በዚሁ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ለፕሬዚዳንቱ ተሰጥቷል፡፡ 
ባለፈው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ የይቅርታ ቦርድን የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ ይቅርታ ይሰጣል፤›› ሲል በረቂቁ ክፍል ሁለት አንቀጽ 4 (1) ላይ አስቀምጧል፡፡ በማከልም ቦርዱ ለፕሬዚዳንቱ የሚልከው የውሳኔ ሐሳብ ይቅርታ የተወሰነላቸውን ታራሚዎች በመተለከተ ብቻ ነው፡፡
 በቦርዱ ውሳኔ አቅራቢነት ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል የሚሰጠውን ይቅርታ የመሰረዝ መብት አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቢኖረውም፣ ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን በፕሬዚዳንቱ የተሰጠ ይቅርታ ተጥሶ ወይም የተጭበረበረ መሆኑ ሲረጋገጥ ቦርዱ ያለፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በራሱ እንዲሰረዝ ያደርጋል ይላል፡፡ ‹‹ቦርዱ ይቅርታ የሚሰጣቸውን ሰዎች ብቻ ለይቶ ለፕሬዚዳንቱ ስለሚያቀርብ ፕሬዚዳንቱም በቦርዱ የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ብቻ ይቅርታ ስለሚሰጡ የይቅርታ መሰረዝን በተመለከተ ወደ ፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ ተገቢነት የለውም፤›› በማለት ከረቂቅ አዋጁ ጋር የተያያዘው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
የተሰጠ ይቅርታ ዋጋ የሚያጣባቸው ምክንያቶች ሁለት መሆናቸውን፣ እነዚህም የተሰጠው ይቅርታ በተጭበረበረ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነና ይቅርታው ሲሰጥ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ከተጣሰ የሚሉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የሚሰጠውን ለታራሚዎች ይቅርታ የማድረግ ኃላፊነት ይጋፋል በማለት አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ረቂቅ አዋጁ መስተካከል እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በቦርዱ ውሳኔ ይቅርታ ይሰጣሉ በማለት ረቂቅ አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ባይቀበሉትስ? ይህ ማለት ውሳኔው ያለቀው እታች ነው ማለት ነው በማለት የረቂቅ አዋጁን ድንጋጌ ተችተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሰጠውን ይቅርታ ቦርዱ ያለፕሬዚዳንቱ እውቅና ማንሳት እንደሚችል የሚገልጽ ድንጋጌ መካተቱ ተገቢ አለመሆኑን አባላቱ ገልጸዋል፡፡
 ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱ ይቅርታ የመስጠት ሥልጣን እንዳስፈላጊነቱ አግባብ ላለው የክልል መንግሥት አካል በውክልና መስጠትና የይቅርታ ጥያቄዎችን የሚመረምረው ቦርድም በተመሳሳይ በክልል ለሚቋቋሙ ቦርዶች ውክልና ሊሰጥ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ በተለየ ሁኔታ ይቅርታን የሚያስከለክሉ ወንጀሎችን ይዘረዝራል፡፡ ሙስና፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ግብረ ሰዶም፣ ሽብርተኝነት፣ አደገኛ ዕፅ ማምረት፣ ማዘዋወር፣ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም፣ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸም የጠለፋና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ቢሆንም መንግሥት የይቅርታ ዓላማን ያሳካል ብሎ ካመነበት በረቂቅ አዋጁ ይቅርታን የሚያስከለክሉ ወንጀሎች ምክንያት ሆነው ሊቀርቡ እንደማይችሉ ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡
 በተጨማሪ መንግሥት በሚያወጣው ደንብ መሠረት በሚዘረዘሩ ሌሎች ወንጀሎች ይቅርታ የማይጠየቅባቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ የፓርላማው አንዳንድ አባላት ከላይ የተጠቀሰውን ድንጋጌ፣ ረቂቅ አዋጁ ይቅርታ የሚከለከልባቸውን ወንጀሎች መዘርዘር ከጀመረ በኋላ ሌሎች ወንጀሎች ደግሞ በሚወጣ ደንብ እንዲዘረዘሩ ማለቱ ግራ እንደሚያጋባቸው፣ የወንጀል ዓይነቶቹን  ሙሉ በሙሉ መዘርዘር ወይም ይቅርታ የሚያስከለክልባቸውን መርህ ብቻ ማስቀመጥ ነው በማለት እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ለሚመራው የፓርላማው የሕግ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ተመርቷል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር