የተንከባለሉ የማንነት ጥያቄዎች

ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ዛሬ ሥራ ላይ ከዋለ 19ኛ ዓመቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥሙም በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመምራት የሚያስችል ሰነድ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎች ሕገ መንግሥቶች በሕዝቦች መካከል የተገባ ቃል ኪዳን አይደለም፡፡ ይልቁንም በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የተገባ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት ለተሰጣቸው ለእነዚህ ቡድኖች ሕገ መንግሥቱ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፡፡ 
 ከአንድነት ባልተናነሰ ሁኔታ ልዩነትና የማንነት ጥያቄ በሕግም ሆነ በተግባር ድጋፍ እንደሚሰጠው ይገመታል፡፡
የሕገ መንግሥቱን የተለያዩ አንቀጾች በማየት የማንነት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አላቸው ከማለትም በላይ እነዚህ አንቀጾችና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መርህን በማንገብ ታግሎና አታግሎ በአሸናፊነት ሥልጣን የያዘው፣ በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱም ወሳኝ ሚና ያለው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለተግባራዊነቱ ታማኝና ቁርጠኛ ነው የሚል ግምትም በብዙዎች ዘንድ ሥር የሰደደ ነበር፡፡ 
ይሁንና በተግባር ኢሕአዴግ የመገንጠልን፣ ክልል የመሆንና የማንነት ጥያቄዎችን በተለያዩ ጊዜያት ላነሱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰጠው ምላሽ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ መሠረት የሆነው መርህ በሥራ ላይ ያለውን የመንግሥት ቅርፅ እንዲለውጥ በሚያስችል ሁኔታ እንዲተገበር ፍላጎት እንደሌለው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ 
በቅርቡ ለህትመት የበቃው ‹‹የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄና የማዕከላዊ መንግሥታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ ፬ኛ እስከ ኢሕአዴግ›› የተሰኘው የዓለሙ ካሳና የሲሳይ መንግሥቴ መጽሐፍ የራያ ሕዝብ ማንነት ጥያቄን ለማስተናገድ ሕወሓትና ብአዴን እየሠሩ ያሉትን ጥፋት በዝርዝር የሚተርክ ነው፡፡ የራያ  ሕዝብ ፍላጎት፣ ታሪክ፣ ማንነትና ሥነ ልቦናዊ አንድነት ከግምት ውስጥ ሳይገባ በተለይ የሕወሓት አመራሮች የነበራቸውን የሥልጣን የበላይነት በመጠቀም ለራሳቸው ጥቅም የሚያዳላ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው፣ ከፊሉ ራያ ወደ ትግራይ እንዲካተት ሲደረግ ከፊሉ ደግሞ በአማራ ክልል ውሰጥ እንዲቆይ ስለመደረጉ ያስረዳሉ፡፡ 
ወደ አማራ ክልል የተካተተው የራያ ሕዝብ አማርኛ ተናጋሪና በብዙ መልኩ ከአጎራባች የአማራና የአገው ብሔር ሕዝቦች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ባህል፣ ወግና ሥርዓት ያለው መሆኑን የሚጠቁሙት ሁለቱ ጸሐፊያን በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ተካቶ የሚገኘውና አማርኛ፣ ኦሮሚኛና አገውኛ ቋንቋዎችን ተናጋሪ የሆነው ከፊሉ የራያ ሕዝብ ግን በቋንቋው እንዲጠቀም ስላልተደረገ ራያ የሚለው የማንነት መገለጫ ጠፍቶ፣ የራያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባህልና ወግ በትግራይ ባህልና ማንነት ተውጦ እንዲቀር እየተደረገ ስለመሆኑ ይከሳሉ፡፡ በተጨማሪም ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መልካም ስም ያለው ሕወሓት ለክልሉ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ለማግኘት በማሰብ ውሳኔውን የወሰነ ስለመሆኑም ይከሳሉ፡፡ ከፊሉ ራያ ወደ ትግራይ ክልል የተቀላቀለው የቋንቋን መመሳሰል ወይም መቀራረብ እንደ አንድ ብቸኛ መስፈርት አድርጎ በመውሰድ የተወሰነውም ሕገ መንግሥታዊ መስፈርትንና የቀደሙ ተግባራዊ ተሞክሮዎችን ያገናዘበ አለመሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡ 
በተመሳሳይ የወለኔ ሕዝቦች ደሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች የማንነት ጥያቄያቸው ተገቢ ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለና በሒደቱም የአመራሮች መታሰር፣ የአባላት መሰደድ እንዲሁም ግድያ ጭምር ስለመፈጸሙ ለሪፖርተር መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ወለኔ ጉራጌ እንዳልሆነና የተለየ የራሱ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) የማንነት ዕውቅናን ለማግኘት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን እንደሚያሟላ የሚገልጹት የፓርቲው አመራሮች ጥያቄአቸው በጉራጌ ዞን ምክር ቤትና በደቡብ ክልል ምክር ቤት ምላሽ ባማግኘቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ ብለው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተዘግቧል፡፡  
ከላይ ከተገለጹት ሁለት ምሳሌዎች በተጨማሪ በአማራ ክልል የቅማንት የማንነት ጥያቄ፣ በደቡብ ክልል የቁጫ የማንነት ጥያቄን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማንነት ጥያቄው ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም፡፡ በሕግ የተቀመጠው የማንነት ጥያቄ ምንነትና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገው ሥነ ሥርዓት ግልጽ መሆኑን የሚጠቁሙ ምሁራን፣ የማንነት ጥያቄዎቹ አላግባብ የሚንከባለሉት በፖለቲካ ምክንያቶች መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ 
ይሁንና የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጾችና የተለያዩ ሕጎች ከክልሎች ሕገ መንግሥት ጋር ተዳምረው ሲነበቡ የማንነት ጥያቄዎቹ አዎንታዊ ምላሽ እንዳያገኙ የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ሌሎች ይከራከራሉ፡፡ 
የቡድን የማንነት ጥያቄዎች ከሕገ መንግሥቱ መሥራቾች ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንዱን ቅርፅ/ስያሜ መያዝ እንዳለባቸው ይጠበቃል፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ደግሞ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚተረጉመው እንደሚከተለው ነው፡፡ ‹‹ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡›› 
እነዚህ መሥፈርቶች በተናጠል በቂ ስለመሆናቸው ወይም ደግሞ ሁሉም አንድ ላይ መሟላት እንዳለባቸው ግልጽ መግባባት እንደሌለ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎችን በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ መሥፈርት በራሱ ሲታይም ከቋንቋ መሥፈርት ውጪ ያሉት ተጨባጭ ያልሆኑና የተለያዩ ትርጉሞችን የሚጋብዙ ናቸው፡፡ 
በሕገ መንግሥቱ አንቀት 39(4) ላይ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት በሥራ ላይ የሚውልበት ሥነ ሥርዓት በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በአንቀጽ 47(3) ላይ የማንኛውም ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ሥራ ላይ የሚውልበት ሥነ ሥርዓትን በዝርዝር አስፍሯል፡፡ 
በኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአንቀጽ 39 አግባብ እስካሁን ጥያቄ አላቀረቡም፡፡ ክልል የመመሥረት ጥያቄም ገፍቶ መጥቶ የነበረው በሲዳማ ብሔር ብቻ ነው፡፡ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ሐምሌ 6 ቀን 1997 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የሲዳማ ብሔር በዞን ደረጃ የሚገባውን መብት እየተጠቀመ አለመሆኑን በታሪክ፣ በአስተዳደር በደል፣ በሕግና በፌዴራል አወቃቀሩ ያሉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን በመጥቀስ የአሥሩም ወረዳ ምክር ቤቶች ክልል የመሆን ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት እንዲቀርብ ተፈራርመው አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ የዞኑ ምክር ቤት ክልል የመሆን ጥያቄው በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በተሻሻለው የ1994 ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 5 እና 6 መሠረት እንዲፈጸም ውሳኔ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ 
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉዳዩን በመስከረም ወር 1998 ዓ.ም. ለሕዝበ ውሳኔ መርቶት ነበር፡፡ ይሁንና የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ሚያዝያ 26 ቀን 1998 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የሲዳማ ተወላጅ በሆኑ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተደረገው ውይይት ጥያቄው ወቅታዊና ጠቃሚ አለመሆኑን በመረዳት መወሰኑን በመጥቀስ፣ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ያቀረበውን ጥያቄ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡ 
በመገንጠልና በክልል የመሆን ጥያቄ ያለው የተወሰነ ልምድ ወደ ማንነት ጥያቄ ሲሸጋገር ግን አገሪቱ ጥያቄዎችን ከአራቱም አቅጣጫ ማስተናገዷን መረዳት ከመቻሉም በላይ፣ ከላይ በመግቢያችን ላይ የተገለጸው የራያ ጥያቄም የልሂቃኑ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም ጥያቄ ከሆነ መጠናከሩ አይቀሬ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ያለውን የሕግ ክፍተት ለመሙላት በስልጤ የማንነት ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሌሎች የማንነት ጥያቄዎች ጭምር ተግባራዊ የሚሆኑ መሥፈርቶችን አውጥቷል፡፡ የደቡብ ክልልና የኦሮሚያ ክልል የባህረ ወርቅ መስመስንና የደንጣ ቡድን ክችንችላ የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ስልጤን እንደ ምሳሌ ተጠቅመዋል፡፡ 
ስልጤ እንደ ምሳሌ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በቁጥር ሕ/ተ/ም-ፌ 15/40/3/1 ጥር 17 ቀን 1992 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ የአንድ ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ መወሰን ያለበት ማን ነው? የሚወሰንበት ሥነ ሥርዓት ምን መሆን አለበት? በማለት አቅርቦ በዚህ ላይ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡ 
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 35(5) መሠረት ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ተብሎ ለመፈረጅ መሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች ያሟላ አካል ዕውቅና ይሰጠኝ እንዲሁም ከዚሁ ጋር የተያያዙ መብቶች ይከበሩልኝ የሚል ጥያቄ ሲያነሳ፣ ለጥያቄው መልስ የሚሰጠው አካል ማን እንደሆነ በቀጥታና በግልጽ የሚመልስ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሌለ መሆኑን አጣሪ ጉባዔው ስለመገንዘቡ ገልጿል፡፡ 
ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደር ዓላማው ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር በሚያዋቅሩበት ጊዜ በቅድሚያ የማንነትን ጥያቄ መወሰን እንደሚጠበቅባቸውና የሕገ መንግሥቱ አወቃቀር ለክልሎች በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ፣ የማንነት ጥያቄ በክልሉ ውስጥ የሚነሳ ጉዳይ እንደመሆኑ የክልሉን ውሳኔ ማግኘት የግድ እንደሚሆንም አጣሪ ጉባዔው አክሎ አስገንዝቧል፡፡ ከስልጤ የማንነት ጥያቄ በመነሳትም ማንነቴ ይታወቅልኝ በማለት በአንድ ማኅበረሰብ የሚቀርብ ጥያቄ በቅድሚያ ቀርቦ መስተናገድ የሚባው ጥያቄው በተነሳበት ክልል ምክር ቤት መሆን እንዳለበትም አመልክቷል፡፡ 
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 62(3) ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚወስን ይደነግጋል፡፡ አጣሪ ጉባዔው ይህ ሥልጣን የማንነት ጥያቄን እንደሚጨምር አስረድቷል፡፡ 
አጣሪ ጉባዔው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንነት ጉዳይ ላይ ተሳትፎው የሚመጣው ጥያቄ አቅራቢው ማኅበረሰብ በሚገኝበት ክልል ምክር ቤት የአፈጻጸም ጉድለት አለ የሚል ወይም ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ አልተፈጸመም የሚል ቅሬታ ሲነሳ፣ በዚህና በተመሳሳይ ምክንያቶች ጥያቄውን ባቀረበው ማኅበረሰብና በክልሉ ምክር ቤት መካከል ልዩነት ሲኖር እንደሆነም አብራርቷል፡፡ 
የማንነት ጥያቄ የሚያቀርበው ማኅበረሰብ ጥያቄውን በጽሑፍ ማቅረብ እንዳለበትና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(5) የተዘረዘሩት መስፈርቶች የተሟሉ ስለመሆናቸው ማሳየት እንዳለበትም አጣሪ ጉባዔው አመልክቷል፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም ጥያቄውን ተቀብሎ አንቀጽ 39(5) መሥፈርቶችን ያገናዘበ ጥናትን መሠረት በማድረግ ለሕዝብ ውሳኔ እንዲያቀርብ የሚጠበቅ መሆኑንም ጉባዔው አብራርቷል፡፡ ሕዝበ ውሳኔው ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ጥያቄውን ያቀረበው ማኅበረሰብ አባላት በቀጥታ የሚያሳትፉበት፣ ነፃ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት እንዲሁም ገለልተኛ ታዛቢዎች በተገኙበት አግባብ ሊከናወን እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡ 
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥትና ክልሎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ የማንነት ጥያቄው በቀረበ በምን ያህል ጊዜ ይወሰን የሚል ጭብጥ በአጣሪ ጉባዔው ያለመካተቱን በማመልከት በሕገ መንግሥቱ የመገንጠል ጥያቄ በቀረበ በሦስት ዓመት፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄ ደግሞ ጥያቄው በቀረበ በአንድ ዓመት ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ የሚያደራጅ ከሆነ፣ የማንነት ጥያቄ ክልል ከመመሥረት ጥያቄ አንፃር ሲታይ ያነሰ ጊዜ የሚበቃው መሆኑን መገንዘቡን ጠቁሟል፡፡ የመወሰኛ ጊዜው ስድስት ወር ቢሆን የሚል የውሳኔ ሐሳብም የኮሚቴው አባላት አቅርበዋል፡፡ 
ማንነትን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያለባቸው በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው ወይስ በወኪሎቹ? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተም በጉዳዩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውይይት ሲያደርግ፣ የያኔው የደቡብ ክልል ተወካይ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የማንነት ጥያቄን ለማስተናገድ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ስለሌለ ወደ ክልሉ ጉዳዩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢልክም፣ ክልሉ በተጨባጭ በዚህ መንገድ መሄድ አለበት የሚል ሁኔታ ስለሌለ አካሄዱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ገልጸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ለአንድ ክልል እሆናለሁ ለሚል አካል የጊዜ ገደቦችና የአካሄድ ሥነ ሥርዓቶች እንደተቀመጡ ሁሉ ለማንነት ጥያቄም ቢሆን በሕገ መንግሥቱ መቀመጥ እንዳለበትም አስገንዝበው ነበር፡፡ 
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በአብላጫ ድምፅ የስልጤ የማንነት ጥያቄ ወደ ክልሉ ተመልሶ እንዲታይ፣ ክልሉ መልሶ ይየው ሲባልም የተቀመጡትን አቅጣጫዎች ተከትሎ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪው አካል ራሱ ሕዝቡ እንደሆነ ወስኗል፡፡ በተጨማሪም ሕዝቡ ራሱ እንዲወስን እያንዳንዱ ሰው ቀርቦ ለማንነቱ ሐሳቡን በሚስጥር ድምፅ የሚሰጥበት፣ ሌሎች አካላትም ነፃ ሆነው ሒደቱን የሚታዘቡበት አግባብ እንደሚመቻችም ወስኗል፡፡ 
የማንነት ጥያቄ ማን ያቀርባል የሚለውን በተመለከተም ጥያቄውን ማንም ሊያቀርብ እንደሚችል ሆኖም ጥያቄው ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ መሆን አለመሆኑ በሒደት በሚሠሩ ሥራዎች የሚወሰኑ፣ የሚነጥሩና የሚለዩ መሆናቸውን፣ የማንነት ጥያቄ ውሳኔ የሚገኝበት ጊዜም ቢበዛ ከአንድ ዓመት እንደማይበልጥና የስልጤ ጥያቄም በዚሁ አግባብ መወሰን እንዳለበት፣ ለዚህም ወደ ክልሉ ተመልሶ ያለፈው አካሄድ ይህንን አካሄድ መሠረት ያደረገ መሆኑ ተፈትሾ የሚደረግ ማስተካከያ ካለ ተደርጎ የመጨረሻውን ውሳኔ እንዲያገኝ የሚለውን ሐሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ32 የድጋፍ ድምፅ በ23 የተቃውሞ ድምፅ ወስኗል፡፡ ይህ አካሄድና የመፍትሔ ሐሳብ ለሌሎች ተመሳሳይ የማንነት ጥያቄዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም በመግለጽ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ይደመድማል፡፡ 
ውሳኔ የሚጠብቁ ጥያቄዎች 
የስልጤ የማንነት ጥያቄ ከላይ የተገለጹትን ተጨማሪ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ቢያስቀምጥም ከዚያ በኋላ የመጡ የማንነት ጥያቄዎችን በወቅቱ ለመመለስ ስለመቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ የደቡብ ክልልና የኦሮሚያ ክልል በስልጤ ውሳኔ መሠረት የባህረ ወርቅ መስመስንና የደንጣ ቡድን ክችንችላን የማንነት ጥያቄዎች እንዲመልሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመወሰኑ ውጪ ለሌሎች የማንነት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ በክልሎች የተሰጠበት ሁኔታ የለም፡፡ 
የአማራ ክልል የቅማንትን የማንነት ጥያቄ እስካሁን መመለስ አልቻለም፡፡ የደቡብ ክልልና የኦሮሚያ ክልል የጉጂን ጥያቄ እንዲሁ አልመለሱም፡፡ የአፋርና የኢሳ ጥያቄ ከዘመናት በኋላም መፍትሔ በዘላቂነት አልተሰጠውም፡፡ ደቡብ ክልል የመንጃን፣ የቁጫና የከፊቾን ጥያቄ አሁንም ምላሽ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ በ1986 ዓ.ም. የተካሄደው ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ 84 የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ዝርዝር ያሳያል፡፡ በ1999 ዓ.ም. የተካሄደው ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ ደግሞ ቁጥሩን 85 ያደርሰዋል፡፡ ይሁንና በ1986 ዓ.ም. የነበሩና በ1999 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ ያልተካተቱ አምስት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ በ1999 ዓ.ም. ስድስት አዳዲስ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ስለመጨመራቸው መናገር ይቻላል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደሚወከሉ በሕገ መንግሥቱ በግልፅ ቢቀመጥም፣ በአሁኑ ጊዜ 76 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ በምክር ቤቱ ውክልና አላቸው፡፡ ይህ የሕዝብ ቆጠራና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና አለመናበብ የሚያሳየው ነገር በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ነው፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑትና በተለያዩ የምርምር ሥራቸው ታዋቂ የሆኑት ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ የማንነት ጥያቄ በሁለት መልኩ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የመገንጠል፣ ክልል የመሆንና ማንነታቸውን በውስን መልክዓ ምድር (ዞን፣ ወረዳ፣ ልዩ ወረዳ፣ ቀበሌ) አማካይነት መብታቸውን በመጠቀም ይገለጻል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካዊ ስምምነት በመፈጸም የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በመሆንና የተሻለ የፖለቲካ ሥልጣን በማግኘት ይገለጻል፡፡ ዶ/ር አሰፋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስልጤ ውሳኔ ሁሉንም የማንነት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ የማንነት ጥያቄዎች የኢኮናሚና የፖለቲካ ሥልጣን ፍትሐዊነት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ በሕግ የተቀመጠውን ሥነ ሥርዓት ለሁሉም ጉዳዮች ወጥ በሆነ መልኩ መጠቀም አይቻልም፡፡ ይሁንና የማንነት ጥያቄዎቹ ገፍተው ሲመጡ ሥነ ሥርዓቱን የማክበር አዝማሚያ ያለ ቢሆንም በአብዛኛው የፖለቲካ መፍትሔ ለመስጠት ነው መንግሥት የሚሞክረው፡፡ በአማራ ክልል ያለውን የቅማንት ጥያቄ ለምሳሌ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከረ ነው፡፡ መጀመሪያ የቅማንት ጥያቄ የማንነት ሳይሆን የሃይማኖት ነው የሚል አዝማሚያ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ሃይማኖትን የማንነት አካል አድርጎ ነው የሚያየው፡፡ ይሁንና አሁን አማራ ክልል ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን እያጠናው መሆኑን አስታውቋል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ስለአንድ ቡድን ማንነት የሚደረገውን ጥናት ማነው ሊያጠናው የሚገባው የሚለው ነው፡፡ ለጥናቱ የተሻለ የሚሆነው አካል ጥያቄ አቅራቢው ነው ወይስ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው አካል?›› በማለትም ዶ/ር አሰፋ አብራርተዋል፡፡ 
ዶ/ር አሰፋ ለማንነት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ የዘገየ መሆኑን ጠቁመው የሕዝብ ውሳኔ መፍትሔም የተሻለ ቁጥር ያለውን አሸናፊ ስለሚያደርግ ዘላቂ መፍትሔም ስለመሆኑ እንደሚጠራጠሩ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አንቀጽ 39(5) ላይ የተቀመጡ የተለያዩ መሥፈርቶችን ለዓላማቸው በሚመች ሁኔታ በመተርጎም ልሂቃኑ የሚያነሱት ጥያቄ በትክክል የዚያ ማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ጉዳይ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡ ያኮረፉ የፖለቲካ መሪዎች ሕዝቡን በማንነት ጥያቄ ስም ለራሳቸው አጀንዳ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ያመለከቱት ዶ/ር አሰፋ፣ የርዕሰ ጉዳዩ ተመራማሪዎች እነዚህን መሪዎች “Political Entrepreneurs” እንደሚሏቸውም ጠቁመዋል፡፡ 
ሳራ ቮን በደቡብ ክልል የተነሱ የማንነት ጥያቄዎች ከመሠረታዊ (Primordial) የማንነት ጥያቄ ይልቅ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን መሣሪያ (Instrumental) መሆናቸውን በሚተነትነው ሥራዋ፣ የፖለቲካ ልሂቃኑ የቡድኖችን ማንነትና ፍላጎት በሚመቻቸው መልኩ ያለአግባብ እንደገና በመተርጎም በክልሉ የሚነሱ ከላይ ሲታዩ የ‹ብሔር› የሚመስሉ ፖለቲካዊ ግጭቶችን በማንነት ስም እንደሚፈጥሩ በማመልከት ከዶ/ር አሰፋ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሳለች፡፡ 
አቶ እንዳልካቸው ገረመው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄን ከአናሳዎች መብት ጥበቃ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡ የአናሳዎች የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ጥበቃ ጥያቄ በተመሳሳይ ለማንነት ጥያቄም መነሻ መሆኑን ያመለከቱት አቶ እንዳልካቸው አናሳዎች ማንነታቸውን የመጠበቅ፣ ህልውናቸውን የማረጋገጥና ያሏቸውን መብቶች የማስፋፋት ፍላጎት የነፃነታቸው አካል ሲሆን እነሱን ባቀፈው አካባቢያዊ አገዛዝ የመሳተፍ የጋራ ፍላጎትም እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ 
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(1) ላይ የማንነት ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚመለስ መሆኑ መጠቀሱን የጠቆሙት አቶ እንዳልካቸው፣ የማንነት ጥያቄው እንዴት ይመለስ ለሚለው ጥያቄ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(4) ላይ ክልሎች በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙዋቸው የአስተዳደር እርከኖች የማዋቀር ሥልጣን ስለሰጠ፣ ውሳኔው የክልሎች እንደሚሆን በማስገንዘብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የስልጤን ውሳኔ በዚህ ረገድ የወሰነው ጉዳዮችን ወደ ክልሎች የመመለስ ውሳኔ ትክክለኛ አሠራር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
ይሁንና እንደ ዶ/ር አሰፋና ሳራ ቮን ሁሉ አቶ እንዳልካቸው የማንነት ጥያቄ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆኑ ተጨማሪ ምክንያቶችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡ አዲስ ማንነት ማለት ተጨማሪ በጀትና ሀብት የሚጠይቅ ተግባር በመሆኑ በኢሕአዴግ ዘንድ በበጎ ጎኑ እንደማይታይ አመልክተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ፍላጎት የለውም ማለት ፓርቲው በመላው ኢትዮጵያ ካለው ተፅዕኖ አንፃር በተመሳሳይ ለሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ክልሎች ደካማ የሆነ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ማድረጉንም ያስረዳሉ፡፡ ይህ ችግር ክልሎች ሕገ መንግሥቶቻቸውን ሲያሻሽሉ ካካተቱዋቸው የማንነት ጥያቄዎች እንዴት እንደሚመልሱ በገለጹበት መንገድ እንደሚስተዋልም አቶ እንዳልካቸው አስገንዝበዋል፡፡ 
ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ “Federalism: New Frontiers in Ethiopian Plitics” በተሰኘ ሥራቸው ክልሎች በኢኮኖሚ በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው የማንነት ጥያቄን በነፃነት በመመለስ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመጋጨት ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ይህ ችግር የተከሰተው ኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍል ለፌዴራል መንግሥት ያዳላ በመሆኑ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ በተለያዩ ሥራዎቻቸው ይህን የፕሮፌሰር አሰፋን ሥራ በመሞገት በተግባር የሚታየው የክልሎች የወሳኝነት ሚና ደካማ መሆን ከሕገ መንግሥቱ ዲዛይን ጋር የተገናኘ ሳይሆን በተግባር የመጣ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ 
ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ የሚከበረው 8ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ መሰል በዓሎች አንፃር በፌዴራል ሥርዓቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ስኬቶች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ መገመት ቢቻልም፣ በተግዳሮቶቹ ላይ (ለምሳሌ በሚንከባለሉ የማንነት ጥያቄዎችና ዘላቂ መፍትሔ አወሳሰድ ዙሪያ) መወያየትና ስምምነት ላይ መድረስ ሕገ መንግሥቱን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ ለማድረግ አስፈላጊ ዕርምጃ መሆኑን ብዙዎች ይመክራሉ፡፡ 
ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ http://www.ethiopianreporter.com/index.php/politics/itemlist/user/46-%E1%88%B0%E1%88%88%E1%88%9E%E1%8A%95%E1%8C%8E%E1%88%B9

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር