የመላው ደቡብ ክልል ስፖርቶች ውድድር በሲዳማ ዞን አሸናፊነት ተጠናቀቀ

አርባምንጭ የካቲት 23/2006 በደቡብ ክልል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የስፖርቱን መስክ ከሌሎች የልማት ፕሮግራሞች ጋር አቀናጅቶ በማስኬድ ውጤታማ ስራ መከናወኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዳሴ ዳልኬ ገለጹ።

ባለፉት 2 ሳምንታት በአርባምንጭ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የመላው ደቡብ ክልል የልዩ ልዩ ስፖርቶች ውድድር በሲዳማ ዞን አጠቃላይ አሸናፊነት ትናንት ተጠናቋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዳሴ ዳልኬ በስፖርት ውድድሩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በስፖርቱ መስክ ባስቀመጣቸው ግቦች መሰረት ስኬታማ ውጤቶች አስመዝግቧል፡፡
በእግር ኳስ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ስፖርት የአምራቹን ኃይል የአካል ብቃት ለማጎልበትና ጤንነቱን ለመጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገልጹት ርዕስ መስተዳድሩ  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህል ልውውጥ በማሳደግና ገጽታን በመገንባት የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ ለሁለንተናዊ ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ይበልጥ ለማጠናከር በየደረጃው የሚገኘው አመራር የስፖርት ቤተሰቦችን በማቀናጀት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም አሳስበዋል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መዝርድን ሁሴን በበኩላቸው ላለፉት 2 ሳምንታት በተለያዩ ድማቅ ስነስርዓቶች ታጅቦ ሲካሄድ የቆየው የመላው ደቡብ ስፖርቶች ውድድር ተተኪ ስፖርተኞችን ለይቶ ለማዘጋጀት ማስቻሉን ገልጸዋል።
በውድድሩ ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ ከ14 ዞኖችና ከ4 ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ከ3ሺህ500 በላይ  ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን በዚህም  የክልሉ ብሄሮች ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ ፣ባህልና ሌሎች እሴቶችን ለመለዋወጥ አስችሏል፡፡
በትናንቱ የፍጻሜ ፕሮግራም ላይ በወንዶች እግር ኳስ ለዋንጫ ያለፉት ሲዳማና  ወላይታ ዞኖች ተጫውቶ ወላይታ 3 ለባዶ በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።
በሴቶች እግር ኳስ ሲዳማ ዞን ጌድኦን 4 ለ3 ፣በቅርጫት ኳስ በወንዶችና ሴቶች ጉራጌ ዞን አሸንፈው ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በቦሊቦል ወንዶች ቤንቺ ማጂና ከምባታ ጣምባሮ ፣ በሴቶች ደግሞ ከምባታ ጣምባሮና ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ በመውጣት ተሸልመዋል፡፡
በቼስ ውድድር በሁለቱም ጾታ ሐዋሳ ከተማ አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ችሏል፡፡
በብስክሌት ውድድር በወንዶች ስልጤ፣ ሐዋሳና ጉራጌ ከ1ኛ እስክ 3ኛ በመውጣት የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኙ በሴቶች ሐዋሳና ስልጤ አሸንፈዋል፡፡
በአትሌቲክስና ቦክስ ጋሞ ጎፋ ፣ሐዲያና ወላይታ ዞኖች ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት እንደ ቅደምተከተላቸው የወርቅ፣ የብርና ነሐስ ሜዳሊያ  ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በአጠቃላይ በተካሄደው 17 ዓይነት የስፖርት የስፖርት ውድድሮች ሲዳማ ዞን 32 ወርቅ፣ 23 ብርና 18 ነሐስ በድምሩ 73 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ውድድሩን በበላይነት አጠናቅቀዋል።
ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር 18 ወርቅ፣ 19 ብርና 10 ነሐስ በድምሩ 47 ሜዳሊያ በማግኘት 2ኛ ደረጃና ሀዲያ ዞን ደግሞ 10 ወርቅ 5 ብርና 17 ነሐስ በማግኘት 3ኛ ደረጃ ወጥቷል።
በባህር ዳር ከተማ በቅርቡ  በሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ስፖርቶች ውድድር ላይ የደቡብ  ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችም ተመርጠዋል።
በፕሮግራሙ  መዝጊያ ስነ ስነርዓት ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉና የፈዴራል የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር