በሀዋሳ በተለያዩ ዘርፎች ዉጤታማ የሆኑ ሴቶች ተሸለሙ

ሀዋሳ መጋቢት 5/2006 በሃዋሳ ከተማ የላቀ እንቅስቃሴ ላበረከቱ ሴቶችና በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ፡፡
በኢትዮጵያ ለ38ኛ ጊዜ የተከበረውን  የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተደረገው ሽልማት በሁሉም የትምህርት ደረጃ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላመጡ 31 ሴት ተማሪዎች ለትምህርታቸው አጋዥ የሆኑ መጽሓፍት ተበርክቶላቸዋል።
በሃዋሳ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ለሴት ተማሪዎች ልዩ የትምህርት ድጋፍ  ያደረጉ  ሞዴል ሴት መምህራን በከተማው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች  ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ተቀብለዋል።
በከተማው በተለያዩ የልማት ቡድን በመደራጀት ውጤታማ የሆኑ 16 የልማት ቡድኖችም የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተረክበዋል፡፡
በቅርቡ በተጀመረው የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በስምንቱም ክፍለ ከተሞች አበረታች ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
ከተሸላሚ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዝናሽ ዘንባባና ተማሪ አብጊያ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት ሴቶች ባለፉት ስርዓት ከነበረው ጭቆናና አድሎአዊ አሰራር ተላቀው በልማትና በመልካም አስተዳደር እኩል ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡ እጅግ ያኮራናል ብለዋል፡፡
የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ  ጉዳይ መምሪያ  ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ገረመው  እንደተናገሩት በከተማው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ  አቅም ለማሻሻል የብድር አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በርካታ ሴቶች በማህበር ተደራጅተውና ሃብት አፍርተው ወደ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውንና ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፦ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር