የእርግዝና ወቅት መድኃኒቶች አግባባዊ አጠቃቀም

በምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን
በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ወራት ሀምሳ ከመቶ በላይ የጸነሱ እናቶች በእርግዝና በሽታ (Morning Sickness) ይሰቃያሉ፡፡ በሽታው ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ከሚከሰት የሆርሞኖች መጠንና ዓይነት መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት
ችግር መሆኑን በዘርፉ የተሠሩ ምርምሮችና የተጻፉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በሽታው አብዛኛውን ጊዜ የጎላ የጤና ችግር በጽንሱም ሆነ በእናትየዋ ላይ የማያስከትል ቢሆንም የብዙ እናቶችን ምቾት ግን ይነሳል፡፡ የበሽታው ክብደትና ቅለት ከእናት እናት የሚለያይ ሲሆን በአንዳንድ እናቶች በአጭር ጊዜ በቀላሉ ታይቶ የሚጠፋ ሲሆን፣ በአንዳንዶች ደግሞ የምግብ ፍላጎት በማሳጣት፣ የተመገቡትንም በተደጋጋሚ በማስመለስ በከፍተኛ ደረጃ ሊያውክ ይችላል፡፡ የበሽታው ምልክቶች በአብዛኛው ጠዋት ጠዋት ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነት ችግር በአብዛኛው ጠዋት ጠዋት ይታይ እንጂ በማንኛውም ሰዓት ሊከሰት ይችላል፡፡ የማቅለሸለሽና የማስመለስ ስሜት በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የሚወሰንም ነው፡፡ በተለይም መጥፎ ሽታ ባለበት፣ ምግብ ሲያበስሉ፣ በጉዞ ወቅት ወዘተ ሊነሳና ሊባባስ ይችላል፡፡
እናቶች በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ማቅለሽለሽና ማስመለስን ለመከላከል እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ለምሳሌ በጉዞ፣ በካንሰር፣ በቀዶ ሕክምና ወዘተ የሚመጣ ማቅለሽለሽና ማስመለስን ለመከላከል የሚያግዙ መድኃኒቶችን (Antiemetic) ከመድኃኒት ቤቶች ገዝተው በራሳቸው ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡
እናቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ ማቅለሽለሽንና ማስመለስን ለመከላከል የሚያግዙ መድኃኒቶችን በራሳቸው ገዝተው ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ይመከራል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት በእርግዝና ወቅት በተለይም በመጀመሪያ ጥቂት ወራት አብዛኛው የጽንሱ የአካልና የአእምሮ ምሥረታ ሒደት የሚካሄድበት ጊዜ ስለሆነ ምንም ዓይነት መድኃኒት አለመጠቀም በእጅጉ ስለሚመከር ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት አብዛኛዎቹ የፀረ ማቅለሽለሽና ማስመለስ መድኃኒቶች በእርግዝና ጊዜ ቢወሰዱ የሚያመጡት የተሟላ የደኅንነት መረጃ ስለሌላቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የእርግዝና በሽታው የእናትየዋንና የጽንሱን ጤና በአደጋ ላይ የሚጥልና ለከፍተኛ ረሃብ ካጋለጣት በደም ሥር ከመመገብ እስከ መድኃኒቶችን መጠቀም ሊያስገድደን ይችላል፡፡ በመጀመሪያዎቹ የእግርዝና ወራት የሚከሰት የማቅለሽለሽና የማስመለስ ችግርን ለመከላከል እናቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ የፀረ ማቅለሽለሽና ማስመለስ መድኃኒቶችን ከመጠቀም በመቆጠብ የሚከተሉትን የመድኃኒትም ሆነ ያለ መድኃኒት ሕክምና አማራጮች ቢጠቀሙ ይመከራል፡፡ 
ሀ. ያለመድኃኒት ሕክምና አማራጮች፡-
አነስተኛ፣ ካርቦሀይድሮት ይዘት ያላቸውና የጮማነት ይዘት የሌላቸው፣ ደረቅ ምግቦችን ትንሽ ትንሽ ቶሎ ቶሎ መመገብ፣
ጠዋት ጠዋት ከመኝታ እንደተነሱ ደረቅ ብስኩት ወይም ኩኪስ መመገብ ወይም ደረቅነት ያላቸው ሌሎች አነስተኛ ምግቦችን መመገብ
አብዝቶ ፈሳሽ መውሰድ
አዘውትሮ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ
ምግብ አለማብሰልና ምግብ ከሚበስልበት አካባቢ መራቅ (እንዳይሸት)፣ ሲመገቡም እንፋሎት የማይወጣ በአግባቡ የቀዘቀዘ ምግብ መመገብ
በአውቶቡስ ረዥም መንገድ አለመጓዝ
የዝንዥብል ሻይ መጠቀም ወዘተ.
ለ. የመድኃኒት ሕክምና አማራጮች፡-
ቫይታሚን ቢ6፡- ለጽንሱ አካላዊና አእምሮአዊ ዕድገት እርጉዝ እናቶች በቀን 1.9 ሚሊ ግራም ቫይታሚን ቢ6 ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዴት የሚለው በውል ባይታወቅም በቀን ከ25 ኪሎ ግራም - 200 ኪሎ ግራም ቫይታሚን ቢ6 መውሰድ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ማቅለሽለሽና ማስመለስን በብዙ እናቶች ይከላከላል፡፡ ይህ ቫይታሚን ጭማሪ ስለሆነ እርጉዝ እናቶች ቢወስዱት በጽንሱም ሆነ በእናትየዋ ላይ የሚያመጣው ችግር የለውም፡፡ ስለሆነም በዚህ መድኃኒት የሚፈወሱ እናቶች እንደ መጀመሪያ አማራጭ ቢጠቀሙ መልካም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ሐኪምን በማማከር ከመድኃኒት ቤቶች ማግኘት ይችላሉ፡፡
ሜቶክሎፕራሚድ፡- 10 ሚሊ ግራም በየስምንት ሰዓት ልዩነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ይህ መድኃኒት ድብርትን ሊያስከትል ስለሚችል ንቁነትን ከሚጠይቁ ተግባራት መኪና እንደማሽከርከር መቆጠብን ይጠይቃል፡፡ መድኃኒቱ ሌሎች አማራጮች መፍትሔ የማይሰጡ ከሆነ ብቻ በሐኪም ክትትል መሰጠት ይኖርበታል፡፡ 
ክሎርፕሮማዚን (Chlorpromazine)፡ ይህ መድኃኒት በመጀመሪያዎች የእርግዝና ወራት የሚመጣ ማቅለሽለሽና ማስመለስን ለመከላከል 25 ሚሊ ግራም በየስድስት ሰዓት ልዩነት መውሰድ ይችላሉ፡፡ ይህን መድኃኒት ሌሎች የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሉት ከአራተኛው የእርግዝና ወራት ጀምሮ እናቶች እንዳይወስዱ ይመከራል፡፡ 
ኦንዳንሴትሮን (Ondansetrone) እና ግራኒሴትሮን (Granisetron) የተባሉ መድኃኒቶችን እርጉዝ እናቶች መውሰድ የለባቸውም፡፡ 
በአጠቃላይ እርጉዝ እናቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ የፀረ ማቅለሽለሽና ማስመለስ መድኃኒቶችንም ሆነ ሌሎች መድኃኒቶችን ባለሙያን ሳያማክሩ መውሰድ የለባቸውም፡፡ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ማቅለሽለሽና ማስመለስን ለመከላከልም ያለ መድኃኒት ሕክምና አማራጮችን የመጀመሪያ ምርጫቸው ከዚያም ቫይታሚን ቢ6 እንደ ሁለተኛ አማራጭ ከዚያም በባለሙያዎች ምክርና ክትትል ወደ ሌሎች የመድኃኒት አማራጮችን ቢጠቀሙ ይመከራል፡፡ 
ከአዘጋጁ፡- ባለሥልጣኑን በኢሜል አድራሻው daca@ethionet.et ማግኘት ይቻላል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር