ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ስድስት የቡና ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

-በተጭበረበረ ሰነድ የተላከ ቡና የተሸጠበት ዶላር የደረሰበት እየተመረመረ ነው
በቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ችግሮች ላይ ለመምከር በተጠራው ስብሰባ ላይ ስድስት ታዋቂ የቡና ላኪዎች የችግሩ መስንዔዎች ናቸው በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡
ባለፈው ሐሙስ በንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ሰብሳቢነት በተካሄደው ስብሰባ 86 ከፍተኛ ቡና ላኪዎች ብሶት የተሞላበት ግልጽ ውይይት ማካሄዳቸውን ስብሰባውን የተካፈሉ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የቡና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ደካማነት መንስዔ ናችው የተባሉት ስድስት ታዋቂ ቡና ላኪዎች በግልጽ ጣት እንደተቀሰረባቸውና በመጨረሻም ይቅርታ መጠየቃቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ስድስቱ ቡና ላኪዎች ሙለጌ፣ ሆራ ትሬዲንግ፣ ትራኮን ትሬዲንግ፣ ከማል አብደላ ቡና ላኪ፣ ለገሰ ሸሪፍ ቡና ላኪና አልታ አግሪ ቢዝነስ ናቸው ተብሏል፡፡ 
እነዚህ ቡና ላኪዎች ላይ የቀረበው ቅሬታ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በውድ ዋጋ ቡና እየገዙ በዓለም ገበያ በርካሽ ይሸጣሉ የሚል ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ይህንን የሚያደርጉት በውድ ገዝተው እየከሰሩ የሚሸጡት ከውጭ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቡ  ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲጠቀሙበት ስለሚፈቀድ ነው ተብሏል፡፡ ነጋዴዎቹ በዚህ አካሄድ በቡናው ንግድ የከሰሩ ቢመስልም፣ ከውጭ በሚያስገቧቸው የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች እንደሚያካክሱ ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ከበደ እነዚህን ጉዳዮች በስብሰባው ላይ ሲያነሱ ከቡና ላኪዎች ቅሬታ ቀርቦላቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ስድስት ቡና ላኪዎች ቡና በውድ ዋጋ እየገዙ በርካሽ ሲሸጡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በርካታ የቡና ነጋዴዎች ትክክለኛ ዋጋ በጨረታ አቅርበው ማሸነፍ ባለመቻላቸው ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ የለም፡፡ ዕርምጃ ባለመውሰዱም የቡና ንግድ በትክክለኛው መንገድ ለመሥራት አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩንና በዚህም ተጠያቂው ንግድ ሚኒስቴር ነው የሚል ነው፡፡ 
ባለፉት ሰባት ወራት  የቡና አፈጻጸም በደካማነቱ ተመዝግቧል፡፡ መንግሥት በዚህ ዓመት 200 ሺሕ ቶን ቡና ተልኮ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት አቅዷል፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሰባት ወራት ይላካል ተብሎ ከታቀደው ገቢ 40 በመቶ ክፍተት አለ፡፡ በመጠን ደግሞ 30 በመቶ ጉድለት ታይቷል፡፡ በየጊዜው የቡናን ንግድ ከማሻሻል ይልቅ እየተበላሸ ነው የሚሉት የዘርፉ ተዋናዮች፣ ኢትዮጵያ በቡና ብትታወቅም፣ በየጊዜው ከደረጃ በታች የሆነ ቡና ለገበያ እየቀረበ የዘርፉ ገጽታ እየተበላሸ ይገኛል ይላሉ፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቡና ጣዕሙ በዓለም  ተወዳዳሪ የሌለው ቢሆንም፣ በዋጋ ግን ከቡና አቅራቢ አገሮች የመጨረሻው ርካሽ እንዲሆን ተደርጓል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከውጭ የተለያዩ ሸቀጦችን ኢምፖርት የሚያደርጉ ነጋዴዎች ከቡና ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ ከውጭ ለሚያስገቡት ሸቀጣ ሸቀጥ ግዥ የሚጠቀሙበት በመሆኑ ትኩረታቸው ወደ አገር ለሚያስገቡት ሸቀጣ ሸቀጥ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላ ይህንን አሠራር እንደማይታገሱትና ሚኒስቴሩ ፈቃድ ከመንጠቅ ጀምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ  ማስጠንቀቃቸው ታውቋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ከዚህ በተጨማሪ በተጭበረበረ ሰነድ ቡና ከአገር እንደሚወጣ እንደተደረሰበትና የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይህንን ጉዳይ እየመረመረ መሆኑ ተወስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሰጠ ተደርጐ በተዘጋጀ ፎርጂድ ሰነድ 120 ሺሕ ኩንታል ቡና ወደ ውጭ ተልኳል፡፡ ቡናው የተሸጠበት ዶላርም ወደ ኢትዮጵያ እንዳልገባና እዚያው እንደቀረ ተገልጿል፡፡ ይህን ወንጀል የፈጸመውን አካል የፀረ ሙስና ለማወቅ ኮሚሽኑ ምርመራውን እያካሄደ ነው ተብሏል፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በስድስት ወራት ሪፖርቱ ቡናን በማስተዳደር በኩል ንግድ ሚኒስቴር ችግር እንዳለበት ጠቅሷል፡፡ ኮሚሽኑ እንዳለው በቡና ላኪ ድርጅቶች ላይ በቂ ክትትልና ቁጥጥር አለማድረግ፣ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሳይሰጥ ቡና ወደ ውጭ አገር ለመላክ፣ በድርጅቶች ላይ ወቅቱን የጠበቀ የቡና ክምችት ቆጠራ አለማካሄድ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ ቡና ኤክስፖርት በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ አለመውሰድ፣ ወዘተ የሚሉት ችግሮች ይገኙበታል፡፡ ሚኒስትሩ ይህ ዓይነቱ ግልጽነት የተሞላበት ስብሰባ በየሁለት ወሩ እንደሚደረግ ማረጋገጫ መስጠታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
በዚህ ስብሰባ ላይ 86 ቡና ላኪዎች፣ የክልል ባለሥልጣናት፣ የብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡  ከስድስቱ ቡና ላኪዎች በተጨማሪ ሁለት ቡና ላኪዎች ታግደዋል፡፡ የታገዱት ቡና ላኪዎች አልፎዝና ሙሉነህ ካሳ ቡና ላኪ ናቸው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር