በሃርቤ ጎና ወረዳ በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ቀርከሃ ልለማ ነው

ፋብሪካው በሲዳማ ዞን በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ቀርከሃ ለማልማት ዝግጅት እያደረገ ነው
በኢትዮጵያዊ ባለሀብትና በአሜሪካ የልማት ድርጅት ትብብር የተቋቋመው «አፍሪካን ባንቡ» የተሰኘው የቀርከሃ ፋብሪካ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቀርከሃ ጣውላ በማምረት ወደ ጀርመንና የተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመላክ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የአፍሪካ ባምቡ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ ዱሪ የፋብሪካውን በይፋ ስራ መጀመር አሰመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲዳማ ዞን አርቤጎና ወረዳ ውስጥ በ250 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይኸው የቀርከሃ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በየአመቱ 140 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ለማስገባት አቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከምርቱ 52 በመቶውን ወደ ጀርመን ለመላክ ስምምነት ፈጽሟል፡፡
«በሀገሪቱ የደን ሽፋን ካለፉት 40 አመታት ወዲህ እየተመናመነ በመምጣቱ የእንጨት ጥሬ እቃ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ አጋጥሟል» ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ በየአራት ዓመቱ ራሱን በሚተካው ቀርከሃ ይህን የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱን በመሸፈን ከቀርከሃ ጣውላ እንደሚመረት ነው ያስታወቁት። ከሀገሪቱ የደን ሽፋን ከ50በመቶ በላይ የሚሆነው ቀርከሃ መሆኑንም አስታውቀዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የፋብሪካው ዋነኛ ጥሬ ዕቃ የሆነውን ቀርከሃ በሲዳማ ዞን አርቤ ጎና ወረዳ በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም50 ሺ ችግኞችን በማፍላት ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ይገኛል። በየአመቱም አርሶ አደሮቹ የሚያመረቱትን ቀርከሃ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ እየገዛ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡አርሶ አደሮቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቀርከሃ ለማምረት ያስችለው ዘንዳም 10 የኤክስንቴሽን ባለሙያዎችን በማሰልጠን ለሁለት ሺ አርሶ አደሮች ስልጠና እንዲሰጡ የሚያደርግም ይሆናል፡፡
ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር ለ400 ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል። ከእነዚህም ሠራተኞች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውን ቀሪዎቹ ደግሞ የውጭ ዜጎች ይሆናሉ፡፡ከውጭ በሚመጡት ባለሙያዎችና ከጀርመንና ቻይና ባስመጣቸው መሳሪያዎች አማካኝነትም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚካሄድና ይህም የላቀ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ የልማት ድርጅት የማህበራት ምክትል አስተዳዳሪ ሚስተር ማርክ ፌይርስቲን በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ለፋብሪካው ግንባታ ከጀርመን ከስዊድንና ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራቱን አመልክተዋል፡፡ ፋብሪካው በዋናነት ከብክለት ነፃ የሆነ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም በመሆኑ ሀገሪቱ ለተያያዘችው የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጀርመን የፋብሪካውን የጣውላ ምርቶች ለመላክ ስምምነት መደረጉን ሚስተር ማርክ ተናግረው፣ በቀጣይም ምርቶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃን እንዲጠብቁ በማድረግ ወደ አሜሪካና ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የወጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ድጋፍ የሚደረግለት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን አርቤ ጎና ወረዳ በቀጣይም ድርጅቱ በሁለተኛ ምእራፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዷል፡፡
ምንጭ፦ http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/national-news/7808-2014-02-03-07-21-07

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር