የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁንጥጫ በርትቷል

ፎቶ ሪፖርተር ጋዜጣ
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ግቦች መሠረት በማድረግ የተጀመሩ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ ፈርጀ ብዙ ግንባታዎች በሚካሄዱበት አገር ውስጥ ለዓመታት አስቸጋሪ የነበሩ ኋላ ቀር የአገልግሎት ዘርፎች የሚፈጥሩትን ችግር እያየን ነው፡፡ ከኋላ ቀር አሠራርና አኗኗር ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት መሰናክል ሲሆኑበትም ይታያል፡፡ እነዚህን መሰናክሎች እንዲህ ማየት የግድ ይላል፡፡ 
1.የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ 
ምንም እንኳን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ማጠቃለያ ላይ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አቅም አሥር ሺሕ ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል ቢባልም፣ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች የሚገኘውን ከሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል በቅጡ ማሰራጨት አልተቻለም፡፡ ለትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሳካት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ትላልቅና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በኃይል መቆራረጥና እጥረት ምክንያት ማምረት እየተቸገሩ ናቸው፡፡ 
ከፍተኛ ኢቨስትመንት የፈሰሰባቸው የተለያዩ የንግድ፣ የማምረቻና የአገልግሎት ተቋማት በኃይል መቋረጥ ምክንያት ለኪሳራ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ የባንክ ብድር መመለስ እስኪያቅታቸው ድረስ ምርት እየተስተጓጐለባቸው ነው፡፡ የተመረተውን ምርት መሸጥ አልተቻለም፡፡ ሆቴሎች ለጄኔሬተርና መሰል የኃይል አማራጮች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ በኢንቨስትመንት አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት እያጋጠመ ነው፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በቢሮዎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በመሳሰሉት ከግለሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ሕፃናትን መመገብና መንከባከብ የማይቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ እንኳ ቢታይ በዚህ ኑሮ ውድነት ምግቦች ለብልሽት እየተዳረጉ ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለውን ጫና በመቀነስ ቢቻል የተመጣጠነ አገልግሎት እንዲገኝ መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከሳምንት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እየተቋረጠ ዕድገት እንዴት ይጠበቃል? ቁንጥጫው ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡    
2.የቴሌኮም አገልግሎት አሳሳቢነት 
በዚህ ዘርፍ እየታየ ያለው ችግር እጅግ በጣም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ በሞባይል ስልክ ላይ ኑሮአቸውን ከመሠረቱ ዜጐች ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድረስ እሮሮ በዝቷል፡፡ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ጥራት መጓደልና ጨርሶውንም መጥፋቱ የአገሪቱን ገጽታ እያበላሸው ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተጓጐለው የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድም ሆነ በዲፕሎማቶች አካባቢ ቁጣ እየቀሰቀሰ ነው፡፡ 
በተለይ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ እስኪረሳ ድረስ ችግሩ ተባብሷል፡፡ የሞባይል ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት በአግባቡ ለተጠቃሚዎች መድረስ ባለመቻሉ አገሪቱ በከፍተኛ የመሠረተ ልማት ግንባታ ውስጥ ስለመኖሯ እያጠራጠረ ነው፡፡ የሚመለከተው ተቋም ችግሩን ከማንም በላይ ተገንዝቦ አጣዳፊ ዕርምጃ መውሰድ ካልቻለ ይህ ዘርፍ የጐን ውጋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ 
የኢትዮ ቴሌኮም አዲሱ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ መጠናቀቅ እንደሚገባው ሁሉ፣ ከዚህ ቀደም የተሠራው ደግሞ በአግባቡ አገልግሎቱን እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነት ሊታሰብበት ይገባዋል፡፡ በጥራት ችግር ምክንያት የልማት እንቅፋት በመሆን ላይ ያለው የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት መንግሥትን፣ የግሉ ዘርፍን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትንና ሌሎችንም ጭምር መከራ እያበላ ነው፡፡ እንጀራቸውን ከዚህ አገልግሎት ጋር ያስተሳሰሩ ዜጐች ደግሞ ከማንም በላይ እየተጐዱ ናቸው፡፡ አስቸኳይ የሆነ መፍትሔ የግድ ነው፡፡ ቁንጥጫው በዝቷል፡፡        
3.የውኃ አቅርቦት መስተጓጐል
የውኃ አገልግሎት መስተጓጐል እያደረሰ ያለውን ችግር ከመግለጽ በላይ በጉልህ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ በየቦታው ለበርካታ ቀናት የውኃ አገልግሎት ሲቋረጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ይከሰታል፡፡ በቤተሰብ፣ በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ በመፀዳጃ ቤቶች፣ በፋብሪካዎችና በተለያዩ ተቋማት ላይ የሚደርሰው ችግር የብሶት ምንጭ እየሆነ ነው፡፡ 
የውኃ አገልግሎት አቅርቦት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እየደረሰ ያለው መስተጓጐል ዜጐችን ለእንግልት እየዳረገ ነው፡፡ ለተለያዩ ተግባራት ይውል የነበረው የሰው ኃይል ውኃ ፍለጋ ሲንከራተት ማየት ያሳዝናል፡፡ ኢንቨስተሮች በውኃ እጦት ምክንያት ማምረት ሲያቅታቸው፣ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ሆቴሎች በውኃ ድርቅ ሲመቱ፣ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ሲቸገሩ ማየት አስተዛዛቢ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም የውኃ አገልግሎት መስተጓጐል መቀረፍ አለበት፡፡ ችግሩ ከሚታሰበው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ቁንጥጫው በርትቷል፡፡   
4.የትራንስፖርት አገልግሎት መጓደል 
ለቀላል ባቡርና ለመንገዶች ግንባታ ሲባል በበርካታ ሥፍራዎች ነባር መንገዶች ተዘጋግተዋል፡፡ ወትሮም እንደነገሩ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለታክሲና ለአውቶቡስ ጥበቃ ተሠልፎ ሲታይ ያስደነግጣል፡፡ በስንት መከራ የሚገኝ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚፈለገው ጊዜ የተባለበት ቦታ አያደርስም፡፡ መንገዶች በመዘጋጋታቸው ምክንያት ሠራተኞች በተወሰነላቸው ሰዓት በሥራ ገበታቸው ላይ መገኘት አይችሉም፡፡ 
በመንግሥት የተለያዩ ተቋማት፣ በባንኮች፣ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በሆቴሎች፣ በንግድ መደብሮችና በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ዜጐች የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ለመስጠት ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ሌላው ቀርቶ የትራንስፖርት አቅርቦት ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ በተፈለገው ሰዓት የሥራ ገበታቸው ላይ እየተገኙ አይደሉም፡፡ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ዜጐች ጭምር በሰዓታቸው ተገኝተው አገልግሎት መስጠት እየተሳናቸው ነው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ትልቅ ለውጥ ይታይበታል ቢባልም፣ አሁን ያለውን ችግር ለማቃለል ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ተገልጋዩ ሕዝብ ቁንጥጫው ጠንክሮበታል፡፡     
5.በነዳጅ ዋጋ ምክንያት ኑሮ አልቀመስ እያለ ነው 
በተለያዩ ጊዜያት ጭማሪ የሚደረግበት ነዳጅ ከምግብ ጀምሮ የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ እያስከተለ ነው፡፡ መንግሥት ግሽበትን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር እየናረ ያለው የኑሮ ውድነት ዜጐችን እያስመረረ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ዓለም አቀፉን ገበያ የተከተለ መሆኑ በሚገባ መጤን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዘመን መንግሥት ነዳጅን ሊደጉም ይገባዋል የሚል መከራከሪያ ባይኖርም፣ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑ አቅርቦቶች ለኅብረተሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የሚደርሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡ ሰሞኑን በተለይ በቤንዚንና በናፍጣ ላይ የተደረገው ጭማሪ ለዋጋ ንረት የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ ከወዲሁ ዜጐች ጭንቀት ውስጥ እየወደቁ መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ገበያው ውስጥ ሰው ሠራሽ እጥረቶችና የዋጋ ንረቶች ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ችግሩን ያስተውሉ፡፡ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ይታሰብባቸው፡፡ ቁንጥጫው ከማሳመም በላይ እየሆነ ነውና፡፡ 
በበርካታ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም፣ በአሁኑ ጊዜ በአገልግሎቶች መስተጓጐል ምክንያት ሕዝቡ እየተንገላታ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ የልማት ዕቅዶች ተይዘው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ተብሎ ባይታሰብም፣ ችግሮች አፍጥጠው አስመራሪ እስኪሆኑ ድረስ ዝም ማለት ወይም ‹‹መስዋዕትነት መከፈል አለበት›› በሚል ችላ ማለት አይገባም፡፡ አገሪቱ ወደ ዕድገት እየተጓዘች ነው ሲባል የዕድገቱ ፍሬ በትንሹም ቢሆን መታየት አለበት፡፡ ቁንጥጫው በበዛ ቁጥር ተስፋ ቢስነት አየሩን ይሞላዋል፡፡ ያለ ተስፋ የሚደረግ ጉዞ ውጤታማ አይሆንም፡፡ በፍርድ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎችና ኅብረተሰቡ አገልግሎቶችን በሚፈልግባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ችግሮች ሲጠራቀሙ ብሶት ይፈጥራሉ፡፡ ብሶት ሲፈነዳ ደግሞ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማንም አያጣውም፡፡ ቁንጥጫው ከመጠን በላይ እየበዛ ነው፡፡ ቁንጥጫው ይብቃ! 

http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/itemlist/user/58-%E1%89%A0%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A3%E1%8B%8D%E1%88%AA%E1%8D%96%E1%88%AD%E1%89%B0%E1%88%AD

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር