የቡና ዘርፍን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ድርጅት ሊቋቋም ነው

ባለቤት የሌለውን የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ባለቤት እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገኙበት ልዑካን ቡድን የሌሎች አገሮች ልምድ በመቅሰም ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ቡናን በበላይነት የሚመራ መንግሥታዊ ተቋም ይቋቋማል ተብሏል፡፡ 
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራ ልዑካን ቡድን ብራዚልና ኮሎምቢያ በመጓዝ፣ አገሮቹ የቡናን ዘርፍ እንዴት እንደሚመሩ ልምድ ቀስሞ ተመልሷል፡፡ 
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ፣ በጠቅላይ  ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የፖሊሲና የዕቅድ አፈጻጸም ቁጥጥር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ያሉበት የልዑካን ቡድን ጓቴማላና ኮስታሪካ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ ለመቅሰም ተጉዟል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ምን ዓይነት አደረጃጀትና አሠራር ይኑረው የሚለውን ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረትና ዩኤስአይዲ በየራሳቸው መንገድ ጥናት እያስጠኑ መሆናቸው ታውቋል፡፡
እነዚህ ጥናቶች ሲጠናቀቁ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያገኝ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ባለፉት ዘመናት የቡና ዘርፍ በተለያዩ አደረጃጀቶች ተመርቷል፡፡
ቀደም ሲል ቡና ቦርድ፣ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ቀጥሎም የቡናና ሻይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ የቡናን ዘርፍ ሲመሩት ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ወጥ በሆነ መንገድ ዘርፉን የሚመራ ተቋም ባለመኖሩ ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት መጓዝ ሳይችል እንደቀረ ባለሙያዎች ያብራራሉ፡፡
መንግሥት ዘግይቶ የቡናን ዘርፍ የሚመራ አንድ ጠንካራ ተቋም ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ላይ በመድረሱ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች የሚመራበትን መንገድ እንዲቀይሱ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል፡፡
ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ከኢትዮጵያ ኋላ ተነስተው ከፍተኛ እመርታ ያስመዘገቡ ከፍተኛ የቡና ላኪ አገሮችን ልምድ ለመቅሰም በሚል ባለሥልጣናቱ ወደ ላቲን አሜሪካ አገሮች አተኩረዋል፡፡ 
በቡና ዘርፍ ለዓመታት የቆዩ ነጋዴዎች እንደሚሉት፣ የቡና ዘርፍ ኃላፊነቶች ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በመበታተናቸው እየተጎዳ ነው፡፡ መንግሥት ቢዘገይም እንኳ አንድ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩ መልካም ቢሆንም፣ ከመንግሥት ወገን ጥናቱን እያጠና ያለው አካል የቡና ነጋዴዎችንና ገበሬዎችን በይፋ መረጃ እንዳልጠየቀ ነጋዴዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሚቋቋመው መንግሥታዊ ተቋም ገበሬዎችን የሚደግፍ፣ ሰፋፊ እርሻዎችንና የቡና ንግድን በአጠቃላይ የሚደግፍና የሚከታተል መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/itemlist/user/49-%E1%8B%8D%E1%8B%B5%E1%8A%90%E1%88%85%E1%8B%98%E1%8A%90%E1%89%A0

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር