በልማትና በወረራ መካከል የሚዋልለው የእርሻ መሬትና የአርሶ አደሩ እንባ

በቶፊቅ ተማም    
የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አንድ አካል በማድረግ የጀመረው ሰፋፊና ለም የእርሻ መሬቶችን ለውጭ አገር ባለሀብቶች በስፋት መስጠት መጀመሩ,
ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ ካስነሱበት የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች አንደኛው ሆኖ በመዝለቅ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ተቃውሞው ከተለያዩ አካላት እንደቀጠለ ቢገኝም፣ በመንግሥት በኩል ያሉ ቅሬታዎችን ከመፍታት ይልቅ የሚነሱት ችግሮች በአብዛኛው መሠረት ቢስ ናቸው ሲል እየሞገተ ነው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት ርቀት በጣም እየሰፋ ከመጣ የቆየ ሲሆን፣ መንግሥት ትችቶችን በተለመለከተ በሚያቀርበው ምክንያት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ልማት የማያስደሰታቸው አካላት ትችት ነው ሲል ቢያጣጥልም፣ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡
መንግሥት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በውጭ ባለሀብቶች እንዲለሙ የማድረጉ አቅጠጫ ዋነኛ ዓላማ አገሪቱ ካላት 112 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ ከ 60 እስከ 70 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂና አመራር ቢያገኝ ሊለማ የሚችል መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካትና ሰፊ መሠረተ ልማትና ሰፊ የሆነ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ፣ እነዚህን ሰፋፊ መሬቶች ለማልማት የሚያስችል ካፒታል፣ ዕውቀትና ከፍተኛ አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የአገሪቱን ድንግል መሬት (Prime Soil) በቅናሽ ዋጋ በሊዝ በማከራየት ለባለሀብቶች ቢሰጥም፣ የባለሀብቶቹ ኢንቨስትመንት የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ብዙ የተባለላቸው የቻይና፣ የህንድና የሳዑዲ ኩባንያዎች ያስመዘገቡት ውጤት አናሳ መሆኑ ሲሆን፣ ለዚህም ካሩቱሪ የተባለው ኩባንያ ያደረሰውን ኪሳራ ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በውጭ ባለሀብቶች እየተተገበሩ ያሉ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ስኬታማ አለመሆን ያስከተላቸውን ጉዳቶችና ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደረጓቸውን ጥቂት ምክንያቶች በአጭሩ ለማዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
የመሬት ወረራ
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አከራካሪ እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የመሬት ወራራ በኢትዮጵያ አለ ወይስ የለም የሚለው ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል የውጭ ባለሀብቶች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው እያለሙ እንጂ መሬት ሊቀራመቱ ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም፡፡ ይህም ኢትዮጵያን አይመለከትም  ቢልም፣ ግዙፎቹ የውጭ ኩባንያዎች የታሰበውን ያህል ለውጥ አለማምጣታቸውን የተመለከቱ የተለያዩ አካላት በእነዚህ መሬቶች ላይ  የሚካሄደው ልማት የመሬት ወረራ (Land Grab) አስከትሏል በማለት ይከራከራሉ፡፡ የመሬት ወረራን ያቀላጠፉ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡
መንግሥት መሬቱን በሚሰጥበት ወቅት ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማለትም ምን ያህል መሬት በሊዝ እንደሚያከራይ፣ ለምን ዓይነት የእርሻ ልማት እንደሚውል፣ ውሉ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ለኅብረተሰቡ ከማሳወቅ ይልቅ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ስለሚፈጽም ይህ የመሬት ወረራ ዓይነተኛ ባህሪ ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡
ሌላውና አሳሳቢው ችግር ከአርሶ አደሮች መፈናቀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መንግሥት ለእነዚህ የውጭ ባለሀብቶች በተሰጠው መሬት ምክንያት መንግሥት  አርሶ አደሮችን ከእርሻ ቦታቸው በማንሳት ወደ ሌላ ሥፍራ ቢያዘዋውራቸውም፣ ለእነዚህ ‹‹ልማታዊ ስደተኞች›› ላላቸው አርሶ አደሮች የትምህርት፣ የጤና፣ የውኃ፣ በቂ የሆነ ተለዋጭ መሬት በማቅረብ ረገድ እንዲሁም መሬቱን የተረከቡት ባለሀብቶች ለአካባቢው መሠረተ ልማት እናሟላለን ብለው የገቡትን ቃል ኪዳን የተገበሩበት ደረጃ ሲታይ እጅግ አናሳ ሆኖ መገኘቱ የመሬት ወረራ እየተፈጸመ ነው የሚለውን የሚያጠናክር ተግባር ሆኗል፡፡
ሌላው ከላይ እንደጠቀስኩት የግልጽነት አለመኖር ማሳያ የሚሆነው ለውጭ ባለሀብቶች የተሰጠው መሬት ስፋት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት 400 ሺሕ ካሬ ሜትር ብቻ ነው ቢልም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ግን እስከ ሦስት ሚሊየን ካሬ ሜትር ገደማ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በአገራችን በአርሶ አደሩ ከተያዘው መሬት ውስጥ ከ30 በመቶ ያህሉ በውጭ ባለሀብቶች እጅ መውደቁ አይቀርም ሲሉ የግብርና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡   
በዚህ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ስለንብረት ባለቤትነት በሚገልጸው  አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር 3 የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ በውጭ ባለሀብቶች በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሳይሆን ሲቀር እየታየ ባለው ከፍተኛ የመሬት ብክነት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ ቁጥር 3 እየተጣሰ ነው ለማለት ያስደፍራል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡
የምግብ ዋስትና
እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች የአገሪቱን የምግብ ዋስትናን (Food Security) ለማረጋገጥ የሚኖራቸው ሚናን ስንመለከት፣ በተለይ ባለሀብቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ምክንያት በማድረግ የሚያመርቷቸውን የምግብ እህሎች ወደ አገራቸው በመላክ፣ የአገራቸውን የምግብ እህል እጥረት ለመቅረፍ እንዲሁም ለመደጎም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህም በራሱ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚመረተውን የምርት ዓይነት በተመለከተ ምርጫው የውጭ ባለሀብቶች ሥልጣን በመሆኑ፣ የአገሪቱን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ አስተዋፅኦ እጅግ አናሳ ይሆናል፡፡ በባለሀብቶች የሚመረቱ ምርቶች በኛው አርሶ አደሮች የሚመረቱ ከሆኑና ባለሀብቶቹ በትላልቅና በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች በመታገዝ አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በትንሽ ማሳና በኋላቀር አስተራረስ የሚያመርተውን አርሶ አደር ከገበያ ውጪ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ይህም አርሶ አደሩን ክፉኛ ተጎጂ ያደርገዋል፡፡
ሌላው የአርሶ አደሩ ችግር ደግሞ ባለሀብቶቹ ለእርሻ ልማት የሚጠቀሙበትን ውኃ ከአካባቢው ወንዞች በከፍተኛ ደረጃ ስለሚወስዱ፣ በአካባቢው ያለው አርሶ አደር ለከፍተኛ የውኃ እጥረት በመጋለጥ የውኃ ዋስትናው (Water Security) አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
 የሥራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር
መንግሥት እንዳሰበው እነዚህ ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ ባይሳካላቸውም ቅሉ፣ ለገበሬው ሰፋ ያለ የሥራ ዕድልን ማለትም ከግብርናው ጋር የተያያዙና  ከግብርና ውጪ ባሉ የሥራ መስኮች (On and off Farm Employment) ይፈጥራሉ ቢልም፣ አብዛኞቹ ባለሀብቶች ለሚያመርቱዋቸው እህሎች ሠራተኞችን ከራሳቸው አገር ያስመጣሉ፡፡ ሌላው እርሻው የሚከናወነው ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመጠቀም በመሆኑ የሰው ኃይል አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ እጅግ አናሳ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥት የእኛ ባለሀብቶች ሊማሩበትና ተከትለው ሊያድጉበት የሚችሉበትን የሰፋፊ እርሻዎች አስተዳደር፣ ከውጭ ባለሀብቶች ይቀስማሉ ብሎ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ ቢሰንቅም፣ የውጭ ባለሀብቶች ስኬታማ መሆን አለመቻላቸው የሰነቀውን ተስፋ መና ያስቀረው ይመስላል፡፡
ተጠያቂነትና የአካባቢ ጥበቃ
መሬት ወስደው ለማልማት የመጡት ባለሀብቶች ሥራቸውን ቢያቆሙ ለሥራቸው ሲሉ ላፈናቀሏቸው አርሶ አደሮች የሚከፍሉትን ካሳና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ የሚሆኑበት ግልጽ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ባለሀብቶች ለእርሻ ተግባራቸው በማሰብ የሚመነጥሩት ከፍተኛ ጥብቅ ደን የሚያስከትለው የአካባቢ መራቆት (Deforestation)፣ የአፈር መከላትና መሸርሸር (Soil Degradation and Erosion) የሥነ ምኅዳር መዘባት የአገሪቱን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ወደኋላ ከመጎተቱም ባሻገር፣ በደን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ እንስሳትና አዕዋፍ ለስደት እየዳረገም ይገኛል፡፡
ክትትልና ግምገማ
መንግሥት መሬት የተረከቡ ባለሀብቶችን በየሦስት ወሩ ክትትል በማድረግ የካምፕ አያያዛቸውን፣ የማሽኖችን ሁኔታ፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅና ምን ያህል መሬት እንዳለሙ ጥብቅ ክትትል አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡ የባለሀብቶች ውጤታማ አለመሆን ሲታይ በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው ክትትልና ግምገማ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ በሌላ በኩል የባለሀብቱን የካፒታል አቅምና የልማቱ የአካባቢ ተፅዕኖ ፕሮጀክቱ ብቃት ክትትል ማድረጊያ ዕቅድ ሳይዘጋጅ መሬት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን አንዳንድ ዓለም አቀፍ የግብርና ጥናት ባሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
 በመጨረሻም መንግሥት አሁን እየሄደበት ያለውን አካሄድ ቆም ብሎ በማሰብ አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ሊመግቡን ያልቻሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በአግባቡ ተጠቅሞ እንዲመግቡን ማስቻል፣ የመሬት ወረራን ሊያስቀር የሚችል ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት፣ ጠንካራ የክትትልና የግምገማ ሥርዓት በመተግበር፣ በውጭ ባለሀብቶች ምክንያት ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጠ ያለውንና በቅርብ በመሆን ችግሩንና ብሶቱን የሚቀርፍለት በማጣት እያነባ ያለውን አርሶ አደር ችግር መፍታት፣ በተለይ ለመንግሥት ፋታ የማይሰጥ የቤት ሥራ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tofick2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡
ምንጭ፦ሪፖርተር ጋዜጣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር