ማህበራትና ዩኒየኖች በምርት ገበያው እንዴት መሳተፍ ይችላሉ?

የፌደራል የኀብረት ሥራ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚጠቁመው በአገራችን እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ 26ሺ 672 የኀብረት ሥራ ማህበራት አሉ፡፡ እነዚህ ማህበራትም በድምሩ ከነጥብ89 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሏቸው መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ማለት ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 13 በመቶ ገደማ ያህሉ ቢያንስ የአንድ ማህበር አባል ሆኗል ማለት ሲሆን፣ በጾታ ተዋፅኦ ሲታይም 85 በመቶ ወንዶችና 15 በመቶ ሴቶች በእነዚህ ማህበራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በድምሩ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያላቸው የኀብረት ሥራ ማህበራቱ ከነጥብ 1ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አባላትና ሌሎች ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኀብረት ሥራ ማህበራቱ ተደራጅተው 177 ያህል ዩኒየኖችን መሥርተዋል፤ ዩኒየኖቹ በበኩላቸው የአባል ማህበሮቻቸውን ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የተደራጁ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በተለይም በግብርና ግብይት ዘርፍ ዩኒየኖች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አገራዊ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመት ወዲህ የግብርና ኀብረት ሥራ ዩኒየኖች ማዳበሪያ ከውጭ በማስመጣት ተግባር ላይ ተሠማርተው የአገሪቱን የማዳበሪያ ፍላጐት 70 በመቶ ያህል የሚሸፍን ግብይት ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሞላ ጐደል የአገሪቱ የማዳበሪያ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በማህበራትና ዩኒየኖች አማካይነት ከውጭ እየተገዛ በመቅረብ ላይ ነው፡፡
በቡና ምርትና ግብይት ዘርፍም እንዲሁ ጠንካራ የቡና ገበሬዎች የኀብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ተመሥርተው የአባሎቻቸውን ጥቅም የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸው ድርሻም ቀላል በማይባል ደረጃ ዕድገት እያሳየ ሲሆን ባለፈው የምርት ዘመን ከቡና የወጪ ንግድ የ21 በመቶ ድርሻ የነበራቸው ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ይርጋጨፌና ካፋ የጫካ ቡና አርሶ አደሮች የኀብረት ሥራ ዩኒየኖች ነበሩ፡፡ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ይርጋጨፌና ካፋ የጫካ ቡና አርሶ አደሮች የኀብረት ሥራ ዩኒየኖች በዘርፉ የአገሪቱን ንግድ ሩብ ያህል ድርሻ ይዘው በመንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ልምዳቸውን እያዳበሩ የአባሎቻቸውንም ጥቅም ማስጠበቅ ችለዋል፡፡ እነዚሁ ዩኒየኖች ዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ያገኙ ሲሆን፣ የተፈጥሮ ጣዕም ቡናና የልዩ ቀጥተኛ ሽያጭ ዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬታቸው ከመደበኛው ግብይት በላይ የገቢ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችልና የአገሪቱን የቡና ምርትም ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና እንዲኖረው ለማድረግ ዕድል ፈጥሮ ላቸዋል፡፡ ዩኒየኖቹ በዓለም አቀፍ ቡና ገዥ ኩባንያዎች ዘንድ አስተማማኝ አጋርና በስፋት የሚያቀርቡ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ የቡናን ተፈጥሯዊ ምንጭ በላቀ ደረጃ የዘርፉ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የቡና እውነተኛ ጣዕም እውቅና እንዲያገኝ አስችለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ በአርአያነት ሊጠቀስ ከሚችለው ከዚህ ተግባር በተቃራኒው ግን በአገር ውስጥ ግብይት ሠፊው አርሶ አደርና ማህበራት በኋላ ቀሩ የገበያ መዋቅር ምክንያት ተጐጂ ሆነው መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ባካሄደው ጥናት መረጃ የሰጡ መሠረታዊ ማህበራትና ዩኒየኖች በልማዳዊው ግብይት እንደሚያጋጥሟቸው ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል ወቅታዊና ትክክለኛ የገበያ መረጃ አለማግኘት፣ ከነጋዴዎች ጋር የግብይት ውል አለመከበር ችግር፣ ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ፣ የምርት ጥራት መጓደልና ከግሉ ዘርፍ ነጋዴዎች በኩል የሚታይ ተገቢ ያልሆነ የገበያ ውድድር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የገበያ መረጃ እጦት የአካባቢ ነጋዴዎች እንደፈለጉ ዋጋና የምርት መጠኑን እንዲወስኑ በማድረግ አምራቹ የድካሙን ዋጋ ለሌላ ወገን አሳልፎ እንዲሰጥ አስገድዶት ቆይቷል፡፡ የምርት ሰብሳቢዎችና ነጋዴዎች በተሳሳቱና ህገወጥ ሚዛኖች በመጠቀምም የአርሶ አደሩን ምርት ያለአግባብ እንደሚገዙ ነው ጥናቱ ያረጋገጠው፡፡ ልማዳዊው ገበያ ያልተደራጀና በአነስተኛ የግብይት ተግባራት የተወሰነ እንደመሆኑ በተራዘመው የግብይት ሰንሠለት ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች ደላሎች ናቸው፤ የግብይት ሂደቱ ለጥራት መጓደል መንስኤ መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡ ይልቁንም በቡና ግብይት ዙሪያ ህገ ወጥ ንግድ ጐልቶ ይታይ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልፃሉ፡፡
በልማዳዊው ገበያ ማህበራትና ዩኒየኖች ከግለሰብ ነጋዴዎች ጋር ተወዳድረው ምርት ለመገበያየት ይቸገራሉ፡፡ ምክንያቱም ግለሰብ ነጋዴዎች አርሶ አደሮችን የሚያማልሉባቸው የተለያዩ መደለያዎች ስላሏቸውና የተሳሳተ የገበያ መረጃ በመስጠትም ስለሚቆጣጠሯቸው መሆኑን ይነገራል፡፡ ግለሰብ ነጋዴዎቹ ያላቸው የገበያ ትስስር ጠንካራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ከማህበራት የተሻለ የገበያ መረጃ የማግኘትና ቀጣይ ለውጦችን የመገመት ዕድል መጠቀም ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማህበራትና ዩኒየኖች እንደግለሰብ ነጋዴዎች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ቀልጣፋና ተለዋዋጭ (Flexible) አይደሉም፤ የጋራ ውሳኔና የተጠና ህጋዊ ግብይት ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡ ይህም ግለሰብ ነጋዴዎች ዋጋ ሰብሮ ለማግባት ሲያስችላቸው ማህበራትና ዩኒየኖችን ግን ፈጣን ውሳኔን በሚጠይቁ ጉዳዮች እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሁንና ማህበራትና ዩኒየኖች ደግሞ ከግለሰብ ነጋዴዎች የተሻለ የግብይት ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው አዎንታዊ ጐኖችም አሏቸው፡፡ ከነዚህም መካከል፡-
ማህበራትና ዩኒየኖች የተሻለ የምርት አቅርቦት ምንጭ አላቸው፤ አባሎቻቸው ከሽያጭ ተገቢ ዋጋ ለማግኘትና የትርፍ ተካፋይ ለመሆን ጭምር ምርታቸውን ለማህበራቸው መሸጥን ይመርጣሉና
ለአባሎቻቸው የመጋዘን አገልግሎት ስለሚሰጡ ተጠቃሚ ናቸው
ከአካባቢ ነጋዴዎች ጋር ሲነፃፀርም የተሻለ የካፒታል ክምችት አላቸው፡፡
ከአካባቢ ነጋዴዎች የተሻለ ለምርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡
በተለይ በቡናና ሰሊጥ አምራች አካባቢዎች ያሉ ማህበራትና ዩኒየኖች ምርት በዱቤ ለመግዛት የሚችሉበት ሁኔታ ስላለ ከፍተኛ የምርት ክምችት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል፡፡
በቡና ግብይት ከአካባቢ ነጋዴዎች የተሻለ ዋጋ ለማቅረብ የሚችሉበት ዕድል አለ።
በቡና ምርት ግብይት ውስጥ ዩኒየኖች በቀጥታ ለውጭ ገበያ የማቅረብ፣ የተፈጥሮና የዝርያ ቡናን የመሸጥ፣ ፍትሐዊ ግብይት ከሚያካሂዱ ድርጅቶች ጋር የመሥራት ዕድል አላቸው፡፡
በአጠቃላይ አብዛኞቹ ማህበራት የካፒታል እጥረት፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ማነስ፣ ከግሉ ዘርፍ ጠንካራ ፉክክር፣ የመጋዘን እጥረት፣ ወዘተ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ያስገደዷቸው መሆኑን ሲገልፁ፣ ይኸው ሁኔታ በዘመናዊው የምርት ገበያ ለመሳተፍም አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ነው የሚጠቁሙት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለዘመናዊ የምርት ግብይት ሥርዓት ጠቀሜታ ተገቢውን ግንዛቤ አለማግኘትና ግንዛቤው ያላቸውም በተግባር የሚገለጽ እንቅስቃሴ ያለማድረግ ችግር ይጠቀሳል፡፡ ይህም ማለት ዩኒየኖቹ በሥራቸው ለሚገኙ አባል ማህበራት ዕውቀታቸውን በማካፈል ረገድ ክፍተት መኖሩን ይጠቁማል፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣንም የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባሩን በስፋት ማዳረስ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ከግንዛቤ ማነስ ባሻገር በምርት ገበያው ግብይት የሚካሄድባቸው የግብርና ምርቶች በዓይነት አነስተኛ መሆን፣ የምርት ገበያው መጋዘን ርቀት፣ የምርት ገበያው የአባልነት መስፈርቶች መብዛትና ጠንካራነት፣ የአንዳንድ ዩኒየኖችና ማህበራት ምርት በግዥ አለመሰብሰብ፣ ወዘተ ጉዳዮችም ይጠቀሳሉ፡፡
ይሁንና የምርት ገበያው አሠራር ለማህበራትና ዩኒየኖች አመቺና ጠቃሚ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የምርት ገበያው ከፍተኛ የምርት ክምችት (አቅርቦትየሚፈለግ መሆኑ፣ የካፒታልና ዋስትና መጠንን በመስፈርትነት መጠየቁ፣ የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን መጠቀሙ፣ የውክልና (አገናኝነትአሠራርን መከተሉና የመሳሰሉት ሁኔታዎች ማህበራትና ዩኒየኖች ከምርት ገበያው ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/economy

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር