የጉቦ ነገር በኢትዮጵያ

መንግሥት በሚፈጽማቸው ግዢዎች የውጭ ኢንቨስተሮች ጉቦ እንጠየቃለን አሉ

በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ላይ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች በሙስና ላይ ስላላቸው አመለካከት ለማወቅ በተደረገ ረቂቅ ጥናት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚፈጽማቸው ግዥዎች እስከ 80 በመቶ ጉቦ እንደሚጠየቁ ተመለከተ፡፡ 
ይህ አስደንጋጭ ነው ሲሉ ረቂቅ ጥናቱን ያካሄደው ሰላም ዴቨሎፕመንት አማካሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አመነ ዲያነ ገልጸዋል፡፡ አቶ አመነ እንደሚሉት፣ ለጥናቱ ከተጠየቁት 350 ኢንቨስተሮች መካከል አንድ መቶ ብር ለሚያወጣ ግዥ 80 በመቶውን ጉቦ የሚጠይቁ አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምላሽ የሰጡት ግን ውስን ቁጥር ያላቸው ቢሆንም ሁኔታው አስደንጋጭ ነው ብለዋል፡፡ 
ባለፈው ሐሙስ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለቤትነት ሰላም ዴቨሎፕመንት አማካሪ ድርጅት ባካሄደው ጥናት ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በሒልተን ሆቴል በተካሄደው በዚህ ውይይት ለተካሄደው ጥናት ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የተጠየቁት ኢንቨስተሮች ከ42 አገሮች የተወከሉ ናቸው፡፡
እነዚህ ኢቨስተሮች እንደሚሉት ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ወደ መንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት ጉቦ ይጠየቃሉ፡፡ 
ከዚህ በተጨማሪም የመረጃ ማረጋገጫ ለማግኘትና ፈቃድ ለማውጣት የሚወስደው ጊዜ መሻሻል ቢታይበትም፣ አሁንም መስተካከል እንደሚቀረው አመልክተዋል፡፡ 
በተካሄደው ውይይት ላይ በጥናቱ ጐልተው ከታዩት ውስጥ አነስተኛ ሙስና ገዝፎ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ትላልቅ የሙስና ድርጊቶች በሰፊው የሚነገርላቸው በመሆናቸው ሊጤን እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡ 
በጥናቱ ሕግና መመርያ፣ የቢሮክራሲ ማነቆዎችና ቢዝነስ ለመሥራት ያለው ቅለትና የሙስና ችግሮች አጽንኦት ተሰጥቷቸው ቀርበዋል፡፡ 
በሦስቱም መስኮች ችግር መኖሩ በረቂቅ ጥናቱ የተመለከተ ሲሆን፣ በመድረኩ መንግሥት ቀጣይ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ተጠይቋል፡፡ 
በወቅቱ እንደተጠቀሰው የመረጃ ማረጋገጫና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ያሉ መጓተቶች እንዲታረሙ፣ ያልተገቡ የግዥና የአገልግሎት ክፍያዎች በወቅቱ መታረም እንዳለባቸው፣ በገቢዎችና ጉምሩክና በውጭ ምንዛሪ አካባቢ ያሉ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ከመነገሩም በተጨማሪ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በአገሪቱ በስፋት ስለሚታይ እጥረት ባለበት አካባቢ በሙሉ ሙስና ስለሚኖር ቁጥጥሩ ሊጠብቅ እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡
በለፈው ረቡዕ ዕትም ‹‹የውጭ ኢንቨስተሮች የመንግሥት ተቋማት ለሙስና ተጋልጠዋል አሉ›› በሚል ርዕስ የውጭ ኢንቨስተሮች በተለያዩ የሙስና ጉዳዮች ላይ የሰጡዋቸውን አስተያየቶች መዘገባችን ይታወሳል፡፡  
ምንጭ፦ http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/4863-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%A5%E1%89%B5-%E1%89%A0%E1%88%9A%E1%8D%88%E1%8C%BD%E1%88%9B%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%8C%8D%E1%8B%A2%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%8B%8D%E1%8C%AD-%E1%8A%A2%E1%8A%95%E1%89%A8%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%88%AE%E1%89%BD-%E1%8C%89%E1%89%A6-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%A0%E1%8B%A8%E1%89%83%E1%88%88%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%88%89      

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር