ዋሊያዎቹ ሰኞ ከሊቢያ ጋር ይጫወታሉ

በአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ዋንጫ (ቻን) የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራል፡፡
ፌዴሬሽኑም ዛሬ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ምድብ የተደለደለው የጋና ብሔራዊ ቡድን ባለፈው ሰኞ ምሽት ደቡብ አፍሪካ ገብቷል፡፡
በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ተቀምጦ ከሁለት ሳምንት በላይ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ባለፈው ዓርብ ወደ ናይጄሪያ አምርቶ በማግስቱ ቅዳሜ ከናይጄሪያ አቻው ጋር ተጫውቶ 2ለ1 ተሸንፎ እሁድ ታኅሣሥ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. አዲስ አበባ መመለሱ ይታወሳል፡፡ 
በመጪው ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2006 ዓ.ም. በኬፕታውን ስታዲዮም አስተናጋጅ ደቡብ አፍሪካ ከሞዛምቢክ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል፡፡ ባቻን ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጥቂት አገሮች ውጪ ያሉት ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሩንና የመሳሰሉት የሚሳተፉት በሁለተኛ ቡድናቸው ስለመሆኑ ሲነገር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ 
የዋሊያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ ሰውነት በኬንያ አስተናጋጅነት በቅርቡ በተከናወነው ሴካፋ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ፣ በእሳቸው አገላለጽ ለነባሩ ብሔራዊ ቡድን ተተኪ ያሉዋቸውን ተጨዋቾች ይዘው እንደሔዱ፣ ነገር ግን በውሳኔያቸው ሳይጸኑ መቅረታቸው ሲያስተቻቸው ሰንብቷል፡፡ 
አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ሊጎች ከሚጫወቱት በደቡብ አፍሪካ ጌታነህ ከበደ፣ ከሱዳን አዲስ ሕንጻና ሽመልስ በቀለ እንዲሁም በግብጽና በቤልጄም ክለቦች ሲጫወት ከቆየው ሳላዲን ሰይድ በስተቀር የቀሩትን ሙሉ በሙሉ አካትተው መሄዳቸው ተቃውሞውን አባብሶታል፡፡
አሰልጣኙ ደጋግመው እንደሚናገሩት አሁን ባለው በአገሪቱ ሊግ ነባሮቹን የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሊተኩ የሚችሉ አሉ፡፡ ይህ የአቶ ሰውነት ቢሻው አባባል በስፖርት ቤተሰቡ በተለይም በሙያተኞች ዘንድ ይሁንታን ሳይሆን ተቃውሞን እንዳተረፈላቸው የተለያዩ ዘገባዎች እያመላከቱ ይገኛል፡፡ እንዲያም ሆኖ አሰልጣኙ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሊቢያ ጋር በፍሪ ስቴት ስታዲየም ያደርጋሉ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር ጥር 9 ቀን እና የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ከጋና ጋር ጥር 13 ያከናውናሉ፡፡
በሁለተኛ ቡድኑ የተዋቀረው የጋና ብሔራዊ ቡድን ለዘጠኝ ቀናት በናምቢያ ዊንድሆክ ከተማ ልምምዱን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሰኞ ምሽት ደቡብ አፍሪካ መግባቱ ተዘግቧል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር