ለሞጆ - ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ግንባታ የጨረታ ሂደት ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 21 ፣2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን  ከሞጆ -መቂ እና ከአርበር ረከቴ -ገለምሶ ያለውን የ113 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ለመጀመር የሚያስችለውን የጨረታ ሂደት ጀመረ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከሞጆ- ሀዋሳ ያለውን የፈጣን መንገድ ግንባታን በአራት ተቋራጮች ከፋፍሎ ለማሰራት አቅዷል።
ከሞጆ  እስከ መቂ፣ ከመቂ እስከ ዝዋይ ፣ ከዝዋይ እስከ አርሲነገሌ እና ከአርሲነገሌ   እስከ ሃዋሳ  ተብሎም መንገዱ ተከፋፍሏል።
ለነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ መንግስት አራት ከሚሆኑ አለም አቀፍ አበዳሪ  ድርጅቶች በብድር ያገኘውን ከ173 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት ትናንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቆታል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደሚሉት፥ ከነዚህ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች በቀዳሚነት ወደ ግንባታ ሂደት የሚገባው ከሞጆ- መቂ ያለው ነው።
56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው ለዚህ መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ ልማት ፈንድ ያገኘው ከ126 ሚሊየን የአሜርካን ዶላር በላይ የገንዘብ ብድር ትናንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ አጽድቆታል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የገንዘብ ብድሩ ከአበዳሪው መገኘቱን እንዳረጋገጠ፥ እስከሚጸድቅ ሳይጠብቅ ወደ ጨረታ ሂደት መገባቱን ነው አቶ ሳምሶን የተናገሩት።
ከመቂ - ሃዋሳ ያለውን መንገድ ለመገንባት የአለም ባንክ፣ የኮርያ መንግስትና የቻይና  ኤግዚም ባንክን  የመሳሰሉ  አበዳሪዎች ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ለመስጠት ይሁንታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።
የሞጆ ­- ሃዋሳ የመንገድ ግንባታ ከነባሩ ሙሉ በሙሉ ሳይገናኝ ራሱን ችሎ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የነዚህ መንገድ ግንባታ ከሃዋሳ - ሞያሌ በመገንባት ላይ ካለው መንገድ ጋር ተያይዞ ከጎረቤት ሃገር ኬንያ ጋር የሚኖርን ግንኙነት ይበልጥ ያቀላጥፈዋል ተብሎ የታመነበት ሲሆን፥  በነባሩ መንገድ በየጊዜው የሚከሰተውን የትራፊከ አደጋ  እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ያስቀራል ብለዋል።
218 ኪሎ ሜትር  ርዝመት ያለው የሞጆ ሀዋሳ  ፈጣን መንገድ በአጠቃላይ 13 ነጥብ 6 ቢሊዮን  ብር  ይፈጃል  ተብሎ  ተገምቷል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር