ሲዳማውያን በቅርበት ልከታተሉት የምገባ የመሬት ምዝገባ አዋጅ ጸደቀ፤ ኣዋጁ ኣንድ ወጥየኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል

የፍትሕ ሚኒስትሩ የተቃወሙት የመሬት ምዝገባ አዋጅ ይሁንታ ተቀባይነት አገኘ፤ ኣዋጁ ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ይዘት ኣለው
 
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የከተማ መሬት ምዝገባ አዋጅን ለማፅደቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የይሁንታ ጥያቄ በፍትሕ ሚኒስትሩና በሌሎች ሁለት አባላት ተቃውሞ አፀደቀ፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑት የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፦የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መሬትን ብቻ መመዝገብ የሚመለከት ሳይሆን፣ ከመሬት ጋር ተያያዥ የሆኑ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አብሮ መመዝገብ የሚያካትት በመሆኑና ይህ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ባለመሆኑ ይሁንታው መጠየቁን ጠቁመዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቀረበለት የከተማ መሬት ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ የተለያዩ አንቀጾች ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ይዘት ያለው በመሆኑና አንድ ወጥ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲባል ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ የጠየቀው፡፡ 
ረቂቅ አዋጁ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች መሬትንና በመሬት ላይ ያሉ ቋሚ ይዞታዎችን የመመዝገብ፣ የባለቤትነት መብትና የመጠቀም መብት ዕውቅናና ዋስትናን የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶችን አጠቃቀምና አጠባበቅ የተመለከቱ ሕጐች የማውጣት ሥልጣን ለሕዝብ ተወካዮች ቢሰጥም፣ ክልሎች ደግሞ በፌዴራል መንግሥት የሚወጣውን ሕግ መሠረት በማድረግ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አላቸው፡፡
የቀረበው የመሬት ምዝገባ ረቂቅ አዋጅ በተወሰነ ሁኔታ የክልሎችን ሥልጣን የሚጋፋ ቢሆንም፣ አንድ ወጥ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ይህንን አዋጅ በማፅደቅ ተግባራዊ ለማድረግ ክልሎች የሚወከሉበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ እንዲሰጠው፣ የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ጠይቆ ነበር፡፡ 
በዚህ የይሁንታ ጥያቄ መሠረት ባለፈው ሐሙስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን በማካሄድ በአብላጫ ድምፅ በሦስት ተቃውሞ ለረቂቅ አዋጁ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡ 
የቀረበውን የይሁንታ ጥያቄ በዋናነት የተቃወሙት የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ ለረቂቅ አዋጁ ድጋፋቸውን ገልጸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የመላኩን አስፈላጊነት ግን ተቃውመዋል፡፡
‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ የተጠየቀበት ምክንያት ትክክል አይደለም የምልበት ምክንያት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(5) ላይ የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ሕግ እንደሚያወጣ በግልጽ ስለተቀመጠ ነው፤›› በማለት ምክንያታቸውን አስረድተዋል፡፡ 
በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቁን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይሁንታ ሳይጠይቅ በራሱ የሥልጣን ክልል ውስጥ ሆኖ ማፅደቅ ይችላል ብለዋል፡፡ 
የፍትሕ ሚኒስትሩ በተጨማሪነት የጠቀሱት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 52(1) መ ነው፡፡ ‹‹ይህ አንቀጽ የፌዴራል መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት ክልሎች መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራሉ ይላል፡፡ ስለዚህ ክልሎች መሬትን ለማስተዳደር የፌዴራል መንግሥት የሚያወጣውን ሕግ እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠበቅ ይገባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ 
ስለዚህ የመሬት ምዝገባን በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ የተካተቱት አንቀጾች የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን በመሆናቸው ረቂቅ አዋጁ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብ ሳይገባው መፅደቅ እንደሚችል ተከራክረዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ውስጥ ከተካተቱት አንቀጾች የተወሰኑት በተለይ አንቀጽ 49 በተወሰነ መንገድ የክልሎችን ሥልጣን ስለሚነካ፣ በመሆኑም እዚህ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት የተወሰኑ ማስተካከያዎች በማድረግ ማፅደቅ ይችላል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑት የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላዚዝ አህመድ በሰጡት ምላሽ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መሬትን ብቻ መመዝገብ የሚመለከት ሳይሆን፣ ከመሬት ጋር ተያያዥ የሆኑ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አብሮ መመዝገብ የሚያካትት በመሆኑና ይህ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ባለመሆኑ ይሁንታው መጠየቁን ጠቁመዋል፡፡
ከመሬት ውጭ ያሉ ቋሚ ንብረቶችን አብሮ መመዝገብ የረቂቅ አዋጁ ፍላጐት ነው ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ ይህ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በማከልም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(8) መሠረት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ግን አሁንም በአቶ አብዱላዚዝና በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት የተነሱ የተለዩ ሐሳቦችን አልተቀበሉም፡፡
ሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጠው ሥልጣን የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በመለየት ሕግ እንዲወጣላቸው ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀረበው ረቂቅ የመሬት ምዝገባ አዋጅ ከፍትሐ ብሔር ውጪ የወንጀል ሕጐችንም የያዘ በመሆኑ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ 
በመጨረሻም በሚኒስትሩ ጭብጥና አቶ አብዱላዚዝ ባነሱት ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ በአብላጫ ድምፅ ረቂቅ አዋጁ ይሁንታ አግኝቷል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር