የኢኮኖሚ ዕድገቱ ባለ አንድ አሃዝ ሆኖ እንደሚቀጥል የተመድ ሪፖርት ይፋ አደረገ

ሪፖርተር ያቀናበረው ይህ የሥዕል መግለጫ፣ የላይኛው መስመር በያመቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚወክል ሲሆን የታችኛው መስመር ደግሞ ዓመቱን እ.ኤ.አ. ይጠቁማል)
-የዋጋ ግሽበት እያንሰራራ ወደ ሁለት አሃዝ ማምራቱ ይጠበቃል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ቀናት በፊት ይፋ ያደረገው፣ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታና መጪውን ጊዜ የተነበየበት የዘንደሮው ሪፖርት፣ (World Economic Growth Situation and Prospects) የዓለምን ኢኮኖሚ ዕድገት በየቀጣናው ተንትኗል፡፡ 
በዚህ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የኢኮኖሚዋ ዕድገት ትልልቅ ከሚባለው ጎራ ቢሰለፍም፣ በመንግሥት የታቀደውን መጠን ሆኖ አልተገኘም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በአንድ አሃዝ ተወስኖ፣ ከስድስት ዓመት በፊት ከነበረበት የ12 ከመቶ ዕድገት በግማሽ ያህል እየወረደ መምጠቱንና በዚሁ መጠን እንደሚቀጥልም ትንበያው ይጠቁማል፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ6.4 ከመቶ ያልበለጠ ዕድገት እንደሚኖርም ይጠበቃል፡፡ በአንጻሩ የዋጋ ግሽበትም (ምርትና አገልግሎቶች በአጠቃላይ የሚያሳዩት የዋጋ ጭማሪ) እያንሠራራ እንደሚቀጥልና ወደ ሁለት አሃዝ እንደሚጠጋ ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡ 
መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት የሚጠብቀው የአገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ- ጂዲፒ) በዝቅተኛው ዕርከን 11 ከመቶ፣ በከፍተኛው የዕድገት ጣሪያ ደግሞ 14 ከመቶን እየረገጠ እንደሚጓዝ ነበር፡፡ ሆኖም ከመንግሥት በወጣው መረጃ እንኳ ከታየ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከታሰበው በታች በስምንት ከመቶ ክልል ውስጥ እያደገ ይገኛል፡፡ 
ካስቀመጠው ውጥን በታች ዕድገቱ መጓዙ ያሳሰበው መንግሥት፣ በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፋቸው መግለጫዎቹም ካሰበው በታች የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበባቸውን ዓመታት አካክሶ፣ ቀድሞ ሲመዘገብ የቆየውን ኢኮኖሚ ዕድገትና ፍጥነት እንደሚያጋግል፣ ባቀደው መሠረትም ዕድገቱ እንደሚቀጥል ሲናገር ቆይቷል፡፡ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀመር ባሰበው መጠን ማስኬድ የተሳነው ቢሆንም፣ የዋጋ ግሽበቱን በአንጻራዊነት ከአሥር በመቶ በታች አቆይቶት ከርሟል፡፡ ተመድ ባስቀመጠው ትንበያ መሠረት፣ በኢትዮጵያ የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት አምና ከነበረበት የ6.9 ከመቶ ዕድገት በዚህ ዓመት ወደ 6.5 ከመቶ ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ ለመጪው ዓመት የአገሪቱ የአምስት ዓመት ዕቅድ የሚያበቃበት ጊዜ ሲሆን የአገሪቱ ዕድገት ግን 6.4 ከመቶ (አፍሪካን ኢኮኖሚክ አውትሉክ የተባለው ሪፖርት ይባሱን ወደ 6.3 ከመቶ ዝቅ ያደርገዋል) ላይ እንደሚወሰን ይጠቃበል፡፡ በመንግሥት የሚጠበቀው ዕድገት ግን ቢያንስ 11 ከመቶ እንደሚደርስ ነው፡፡
ተመድ ሌላው ይፋ ያደረገው መረጃ የአገሪቱ ዋጋ ግሽበት መረጃን ነው፡፡ እስካሁን በአንድ አሃዝ ተጠብቆ የቆየው አገሪቱ ግሽበት፣ በዚህ ዓመት 9.5 ከመቶ እንደሚደርስ ተተንብዩዋል፡፡ በመሆኑም እያንሰራራ እንደሚመጣ ያስታወቀው ተመድ፣ በኢትዮጵያ ይኖራል ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት መንስዔ የሚያደርገው የአገሪቱ ግብርና ዘርፍ የሚኖረውን ሚና ነው፡፡ አገልግሎት ዘርፉንም በኢትዮጵያ ይኖራል ተብሎ ለሚጠበቀው የኢኮኖሚ ዕድገት ቀዳሚ ባለ ድርሻ ይለዋል፡፡ 
በተለይ በአገልግሎት ዘርፉ የሚኖረው የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ኢኮኖሚው ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ በማሳረፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ያለው ተመድ፣ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ዕድገት በመጠኑ ብልጫ ያለው ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ በመንግሥት የሚፈለገው የኢኮኖሚ ዕድገት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመራ ቢሆንም፣ ለዚህ ዓይነቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዞ የሚያበቃው ጎዳና ላይ አለመሳፈሩን ነው ተመድም ሆነ ሌሎች አካላት የሚስማሙት፡፡ 
ይህ ሆኖ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚኖረው የዘንድሮው የኢኮኖሚ ዕድገት በአማካይ ወደ 6.4 ከመቶ እንደሚያድግ ሲጠበቅ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የተመዘገበው ስድስት ከመቶ ዕድገት እንደነበርም አስታውሷል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ለሚመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት መንስዔው፣ በኬንያ ይመዘገባል ተብሎ ተስፋ የተደረገው የሸማቾች የፍጆታ መጨመር አንዱ ነው፡፡ ታንዛንያ የተፈጥሮ ጋዝ ኢንቨስትመንትና ፍጆታ ላይ የምታሳየው ግስጋሴ ለምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት ጅምላ ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተመድ አስታውቋል፡፡ 
ተመድ በአፍሪካ የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ከዓለም አኳያ የበለጠ እንደሚሆን ቢታውቅም፣ በመላ አህጉሪቱ የሚታየው የጦርነት ሰደድ፣ በውስጥም በውጭም የሚስተዋለው አደጋ አፍሪካ የምትገኝበትን የዕድገት መሰላል ሊያወዛውዙ የሚችሉ ስጋቶች መሆናቸውን አሳይቷል፡፡ በሊቢያ ተከስቶ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ብቻውን መላው አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎች ላይ ሳይቀር በጉልህ የሚንጸባረቅ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ በሌሎች ምዕራባዊ አፍሪካ አገሮች የሚታዩ የማዕድን ፍለጋ ግኝቶችና የነዳጅ ፍለጋዎች ለአፍሪካ ዕድገት ተስፋ ቢጣልባቸውም ከስጋት አላስጣሉም፡፡ 
ምንጭ፦http://www.ethiopianreporter.com/

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር