የሐዋሳ ሐይቅን «ደህንነት ለመጠበቅ ተኝተን አናድርም» - የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ዮናስ ዮሴፍ

የሐዋሳ ሐይቅን ከብክነት ለመከላከል የከተማው ነዋሪም ሆነ በአካባቢ
ጥበቃ ላይ የተሠማሩ አካላት ሚናቸውን ማጐልበት ይጠበቅባቸዋል፤
ለመጥለቅ የዳዳችው ጀምበር ሙሉ ለሙሉ ከእይታ ከመሰወሯ በፊት ከአድማሱ ጥግ ሆና የፈነጠቀችው ነፀብራቅ የሐይቁን ውበት አጉልቶታል። አእዋፍ ከእንቅስቃሴያቸው እየተገቱ በሐይቁ አካባቢ በሚገኙ ትልልቅ ዛፎች ላይ መቀመጥ ጀምረዋል፤ ድምፃቸውም ብዙም አይሰማም። በነፋሱ ኃይል በሚገፋው የሐይቁ ውሃ ላይ ሆነው ጥቂት አዕዋፋት ወዲያ ወዲህ ይላሉ። በሐይቁ እምብርት ላይ በርቀት ሲታዩ የነበሩት ጀልባዎችም ወደ ሐይቁ ዳር እየተፋጠኑ ናቸው።
ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች በሐይቁ ዙሪያ ታድመዋል።
የዲላ ከተማ ነዋሪው አቶ ሳሙኤል ንጉሴ በንግድ ሥራቸው ምክንያት ወደ ሃዋሳ ከተማ ይመላለሳሉ። ቢያንስ በወር አንዴ ብቅ እንደሚሉም ነው የሚናገሩት። «ፍቅር የሆነውን የሃዋሳ ሐይቅ ሳልጎበኝ በጭራሽ አልመለስም» ይላሉ። ወሩን ሙሉ በሥራቸው ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና በሐይቁ በሚያደርጉት የደቂቃዎች ቆይታ እርግፍ አድርገው አስወግደው በአዲስ መንፈስ እንደሚመለሱም ነው የሚናገሩት።
ወይዘሮ ማርታ አክሊሉም ልክ እንደ አቶ ሳሙኤል ወደ ሐይቁ ሲመጡ እፎይታ ይሰማቸዋል። «በሐይቁ ዳር ዳር ሆቴሎች መኖራቸው መልካም ነው» የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ አልፎ አልፎ የሚያስደምጡት ሙዚቃ በሐይቁ ዳርቻ ላይ እፎይ ብሎ መቀመጥ የሚፈልግን ሰው ምቾት እንደሚነሳነው የገለጹት። «በሐይቁ ዙሪያ ያለው ተፈጥሮአዊ ትዕይነት ብቻ በራሱ በቂ ነው» ባይ ናቸው።
ለከተማዋ ውበት አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዘው የሐዋሳ ሐይቅ ደህንነቱን ለመጠበቅ «ተኝተን አናድርም» ይላሉ የከተማው ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ። ባለፈው ዓመትም በሐይቁ ላይ የመከረ ጉባዔ ተካሂዷል። በጉባዔው ላይም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎች በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ፕሮፌሰሮች ቀርበዋል። በመድረኩ ከተገኘውም ጥቅል ሐሳብ «ሐይቁን ከብክለት መከላከል አንዱ ነው» ያሉት ከንቲባው፤ ከከተማው ሁሉም አቅጣጫ የሚመጣውን ፍሳሽና ደለል ለማስቀረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
«ሐይቁ የዓለማያ ሐይቅ ዕጣ ሳይገጥመው ከወዲሁ ርብርብ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባራችን አድርገን በመውሰዳችን በ2005 .ም የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት በከተማ ደረጃ አቋቋመን እየሠራን ነው» የሚሉት ከንቲባው፤ በሐይቁ ዙሪያ ያሉ ተፋሰሶችን በማልማት እንዲሁም የከተማውን ፍሳሽ ለማስወገድ ሠፊ ሥራ መካሄዱንም ይናገራሉ።
አቶ ዮናስ እንደሚሉት፤ ባለፈው ዓመት 13 ሚሊዮን ብር ዘንድሮ ደግሞ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ለሐይቁ ስጋት ናቸው በተባሉ ችግሮች ላይ ለመሥራት እንቅስቃሴ ተደርጓል።
«እንደ ዓለማያ ሐይቅ ድንገት ከአጠገባችን ጠፍቶ የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ሐይቁን ለመታደግ ጠንክረን በመሥራት ላይ እንገኛለን» ያሉት ከንቲባው፤ በድጋሜም ከኢትዮጵያ ሐይቅ ጠፋ የሚል መርዶ መደመጥ እንደሌለበትም ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ፤ ሐይቁን ለመታደግ የከተማው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር እያደረገ ሲሆን፤የክልሉና የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም አጋር ድርጅቶችም የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈራ ማተቤ እንደሚሉት፤ ለሐይቁ ሥጋት ናቸው በሚል የተፈረጁትን በተለይ ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁትን ኬሚካሎች ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ከተቋማቱ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው። እንደ እነ ቢ ጂ አይ እና ፔፕሲ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ቢሆንም «አፈትልኮ ሊወጣ የሚችል ኬሚካል ይኖራል» በሚል በእዚህም ላይ እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ከከተማው የሚወጣው ፍሳሽ ወደ ሐይቁ እንዳይቀላቀል በሦስት አቅጣጫዎች በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታልና አሞራ ገደል አካባቢ ማጥለያ ረገረግ መሬት እየተዘጋጀ መሆኑን አብራርተው፤ ሦስተኛው ደግሞ በእቅድ ላይ መሆኑን ይጠቁማሉ።
የከተማው ባህል ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት ገነነ «የሐዋሳ ሐይቅ ደረቀ ማለት የሐዋሳ ከተማ ማለት ነው፤ ሐይቁ የከተማው ሳምባ ነው» ይላሉ። ሁሉም ሐይቁን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቀው የተፈጥሮ ሀብት እንደሆነም ነው የገለጹት። ሐይቁ እንደ ዓለማያ ሐይቅ ጠፍቶ ከመቆጨት በፊት «ሳይቃጠል በቅጠል» የሚለውን ብሂል ይዞ መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
በኢትዮጵያ ስም ጥሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ይህ ሐይቅ የተለያዩ የአሳ ዝርያዎች፣ ጉማሬዎች፣ አርጃኖዎችና የመሳሰሉት የሐይቅ ውስጥ እንስሳና የተለያዩ የተክል ዓይነቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ገባር ወንዙም ጥቁር ውሃ ብቻ መሆኑ ይታወቃል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/news/7016-2013-12-26-07-12-26

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር