የጥራት ደረጃ ያጭበረበሩ ሁለት ቡና ላኪዎች በሕግ ሊጠየቁ ነው

-ሌሎች ስድስት ላኪዎች በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል
-ራሱን የቻለ የመጋዘን አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ሊቋቋም ነው
ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቡና ምርት የጥራት ደረጃ በማጭበርበር የወደቀ የጥራት ደረጃ ያለው የቡና ምርት ከአገር ለማስወጣት የሞከሩ ሁለት ቡና ላኪዎች በሕግ እንዲጠቁ መወሰኑን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የውጭ ንግድ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥት የወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው በቡና ላኪዎቹ ላይ ስለተወሰነው ዕርምጃ ያሳወቁት፡፡
በንግድ ሚኒስቴር ቀጥተኛ ክትትል የሚደረግባቸው የግብርና ምርቶች የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ሥርዓት አፈጻጸምና ውጤታማነት ላይ በ2004 ዓ.ም. በኦዲት የታየ ችግር በመኖሩ፣ ቋሚ ኮሚቴው ችግሩ በምን ዓይነት መንገድ እየተቀረፈ መሆኑን ለማወቅ ነው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የጠራው፡፡
በ2004 ዓ.ም. ታዩ ከተባሉት ችግሮች መካከል ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች የጥራት ደረጃ ጉድለት አገሪቱን በእጅጉ እየጐዳ መሆኑን፣ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገዙ የግብርና ምርቶች የኪሎ ጉድለት እንደሚታይባቸው፣ ግዥውን የፈጸሙ ላኪዎች የገዙትን የግብርና ምርት በጥራት ደረጃው እንደማያገኙት፣ ወደ ውጭ እንዲላክ የተዘጋጀ ቡና ዋጋ ውጭ አገር ተሽጦ ከሚገኘው ገቢ የሚንር መሆኑ በ2004 ዓ.ም. በዋና ኦዲተር ጄኔራል የተደረገው የክዋኔ ኦዲት ያስረዳል፡፡
ችግሩን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለፈው ረቡዕ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የተጠየቁት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ያዕቆብ፣ አብዛኞቹ ችግሮች መለየት መቻላቸውንና መቀረፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ጥቂት የሚባሉ ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ቡና ላኪዎች የቡና ገበያውን እያዛቡና እያጭበረበሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ሁለት ቡና ላኪዎች ከጥቂት ወራት በፊት ለመላክ ያዘጋጁት ለውጭ ገበያ የተዘጋጀና የሚያስፈልገውን ደረጃ የሚያሟላ የቡና ምርት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሠርተፍኬት ቢያሳዩም፣ ተጭኖ ከአገር ሊወጣ የነበረው የቡና ምርት ግን የወደቀ ደረጃ ያለው መሆኑን በመግለጽ ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉን ገልጸዋል፡፡
የእነዚህ ሁለት ቡና ላኪዎች ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በሕግ እንዲታይ የተላለፈ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይ አንዱ ቡና ላኪ የወደቀ ደረጃ ያለውን የቡና ምርት ለመላክ የተጠቀመበት መንገድ የተለየ በመሆኑ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን እንደያዘው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የኤክስፖርት ደረጃ ያለው የቡና ምርት ከአገር ውስጥ የሚገዛበት ዋጋና በውጭ ገበያ የሚሸጥበት ዋጋ እንዳይጣጣም የተለያዩ ማጭበርበሮችን የፈጸሙ ሌሎች ስድስት ላኪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
የግብርና ምርቶች የጥራት ችግር ሙሉ በሙሉ መቀረፍ አለመቻሉን አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል፡፡ የሻገተና የበሰበሰ ቦሎቄ ወደ ህንድ ተልኮ ከፍተኛ ቅሬታ በህንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ መቅረቡን አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊትም የበሰበሰ ዝንጅብል ከሞሮኮ ወደ ጂቡቲ ወደብ መመለሱን፣ በተመሳሳይ ከጥቂት ወራት በፊት ሲንጋፖር የተላከ ዝንጅብል የበሰበሰ በመሆኑ ወደ ጂቡቲ መመለሱን፣ ከሩሲያ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ የተበላሸ ጥራጥሬ መመለሱን ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ የጥራት ደረጃው የተበላሸ ምርት ከአገር የሚወጣው የሚኒስቴሩን የገቢና ወጪ ምርቶች ቁጥጥር ክፍልን አልፎ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የጥራት ችግር እያለባቸው ምርቶቹ ከአገር የሚወጡት ከተቆጣጣሪዎች ጋር በቅንጅት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን የሚገልጹት ሚኒስትር ዴአታው፣ ለጥራት ጉድለቱ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
ለአብነት ካነሱት ውስጥ በአገሪቱ ያለው የመጋዘን አገልግሎት የተፈለገውን ደረጃ መጠበቅ የሚያስችል አለመሆኑን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ላብራቶሪዎች በመጋዘኖቹ አለመኖርና ሌሎችንም ምክንያቶች ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም በአገር አቀፍ ደረጃ የመጋዘን አገልግሎት መስጠት የሚችል ራሱን የቻለ የመጋዘን አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እንዲመሠረት በመንግሥት ተወስኖ ጥናት መጀመሩን፣ አቶ ያዕቆብ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከብራዚልና ከደቡብ አፍሪካ የተወሰዱ ልምዶች የሚያሳዩት አገሮቹ ራሱን የቻለ የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት እንዳላቸው፣ ይህንንም ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ጥናት በመሠራት ላይ ነው ብለዋል፡፡
ጥናቱ ተጠናቆ አገልግሎቱ ሲጀመር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥር ያሉ መጋዘኖች ወደሚመሠርተው ተቋም እንደሚተላለፉም ገልጸዋል፡፡
በሕግ እንዲጠየቁ የተወሰነባቸው ሁለት ቡና ላኪ ድርጅቶችና ሌሎች ማስጠንቀቂያ የደረሳቸውን ላኪዎችን ማንነት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለማወቅ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ 
ምንጭ፦http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/itemlist/user/52-%E1%8B%AE%E1%88%90%E1%8A%95%E1%88%B5%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%89%A0%E1%88%AD%E1%89%A5%E1%88%AD
 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር