በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተነሳው ቃጠሎ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አላደረሰም

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመገንባት ላይ ባለው ህንፃ ላይ ከትናንት በስቲያ ምሽት የእሳት አደጋ ቃጠሎ ተነስቶ በአካባቢው ህብረተሰብና በተለያዩ አካላት በተደረገው ርብርብ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መልሰው ደጀኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ከትናንት በስቲያ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ በሴት ተማሪዎች ማደሪያ አካባቢ እየተገነባ ባለ አንድ ህንፃ ላይ ባልታወቀ መንስኤ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ተነስቶ ከሁለት ሰዓታት በላይ በፈጀ ርብርብ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር አፋጣኝ እርምጃ በመውሰዱ ቃጠሎው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ተችሏል። ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን ተማሪዎቹን የማረጋጋት ሥራ መሥራቱን አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር በላይነህ በቀለ በበኩላቸው፤ እሳቱን ለማጥፋት የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዋናነትም ከአካባቢው ህብረተሰብ፣ ከተማሪዎች፣ ከሃዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ከፖሊስ ኮሚሽንና ከሻሸመኔ እሳት አደጋ መከላከል እንዲሁም በአካባቢው መንገድ ሥራ ላይ ከተሰማሩ አካላት ድጋፍ የተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎ አደጋውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከሁለት ሰዓታት በላይ መፍጀቱን ኮማንደር በላይነህ ተናግረው፣ ይህም ሊሆን የቻለው ቃጠሎው የተከሰተበት ህንፃ በግንባታ ላይ ስለሚገኝና እሳቱን በፍጥነት በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቸጋሪ ስላደረገው በመሆኑ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በተጠንቀቅ ላይ የነበሩ የፌደራል መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በቃጠሎው ወቅት ተማሪዎችና አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና የአካባቢው ፀጥታና ሰላም እንዲከበር ርብርብ ያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቃጠሎውን መንስኤና በአጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን የማጠራት ሥራ እየሰራ ሲሆን፣ በቅርቡም ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ኮማንደር በላይነህ አስታውቀዋል፡፡
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/national-news/7148-2014-01-02-09-23-21

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር