የኮፒ ፔስት ጉዳይ ወዴት እየወሰደን ይሆን?..............እንዳለ ደበላ ሀዋሳ ኢዜአ

ዘወትር ከሚቀመጡባት የዛፍ ጥላ ስር ዛሬም እንደወትሯቸው ተቀምጠዋል። በተለመደው ሁኔታ ከፊት ለፊታቸው ካለች ሰባራ የእንጨት ባለመደገፊያ ወንበር ላይ የተቀመጡ ደምበኛቸው የመጡበትን ሁኔታ እየገለጹላቸው ነው። 
እርጅናና ኑሮ ያጎሳቆለው እጃቸው ቢንቀጠቀጥም እንደወትሮ አስኪሪፕቶ ጨብጦ ከባለጉዳያቸው የሚነገራቸውን ዋና ዋና ሀሳብ በያዟት እንደርሳቸው እድሜ የተጎሳቆለች የምትመስል ማስታወሻ ቢጤ ደብተር ላይ ጫር ጫር ያደርጋሉ። 
እንግዳቸው የመጡበትን ጉዳይ አስረድተው እንደጨረሱ ሻምበል ቢተው በተለመደ ሁኔታ በመካከሉ ካርቦን የገባበት የታጠፈ ወረቀት አውጥተው መጻፍ ጀመሩ። 
የመጀመሪያውን ጨርሰው ሌላ ሁለተኛ ካርቦን በመካከሉ የገባበት ወረቅት አውጥተው ያለ ምንም የሀሳብ መቆራረጥ በሚንቀጠቀጥ እጃቸው በማስታወሻ ላይ የጫሩትን ሀሳብ መልከት እያደረጉ የቃላት ዝናብ በወረቀቱ ላይ ያዘንቡ ጀመር። 
እንደጨረሱ የጻፏቸውን ሁለት ገጽ ወረቀቶች በየተራ አንብበው እንደጨረሱ ለደንበኛቸው አስፈረሙበትና ቴምብር ለጥፈው በክላሰር በማድረግ ሰጧቸው።
 ለዚህ አገልግሎታቸው ከደንበኛቸው የክላሰሩንና የቴምብሩን ዋጋ ሳይጨምር የተቀበሉት 20 ብር ብቻ ነው። 
ዛሬ ዘመናዊው አለም በፈጠራቸው የጽሁፍ ማሽኖች ሳቢያ የምንጽፋቸው ጽሁፎች ለራሳችንም የማይገቡና ግራ የሚያጋቡ እየሆኑና በኮፒ ፔስት የተሞሉ ጽሁፎች ተበራከተው በመጡበት ወቅት ራፖር ጸሀፊው ሻምበል ያለምንም መመሳሰልና ኮፒ ፔስት የባለጉዳዮቻቸውን ሀሳብ አዳምጠው ያለምንም የሀሳብ መቆራረጥ ለሁሉም በሚገባ መልኩ ያለማቋረጥ ይጽፋሉ። 
የደረስንበት የቴክኖሎጂ አለም ስራችንን ቀልጣፋና በአጭር ጊዜ እንድናከናውን የረዳን ቢሆኑም ኢንተርኔትና ፌስ ቡክ አድራጊና ፈጣሪ በመሆን ከአዕምሯችን አፍልቀን እንዳንጽፍ እንቅፋት እየሆኑብን የመጡ ይመስለኛል። 
በወጣትነት እድሜያችን ልባችን በፍቅሯ ለተነደፈላት ቆንጆ ፍቅራችንን ለመግለጽ የምንጽፋቸው ደብዳቤዎች በገጽ ብዛታቸው ምንያህል እንደነበሩ እስቲ ወደኋላ መለስ ብለን በሀሳብ እንቁጠራቸው። 
ለዛውም በአንድ ደብዳቤ ብቻ ተጽፎ የሚያልቅ ሳይሆን ደጋግመን የምንጽፋቸው ደብዳቤዎች ሀሳብን አሳክቶ በመጻፍ የነበረን ልምድ ዛሬ ከኢንተርኔትና ቀደም ሲል ከሰራናቸው በኮፒ ፔስት ተተክተዋል። 
ዛሬ ዛሬ ያ ሀሳብን አሳክቶ የመጻፍ ልምዳችንን በኮፒ ፔስት ተነጥቀናል  ለአመታት የደከምንለት የከፍተኛ ትምህርት ቆይታ የመመረቂያ ጽሁፍ ለመጻፍ እንኳን የሚያስችል ዕውቀት አላስጨበጠንም እንዴ? 
የመመረቂያ ጽሁፎቻችን ኮፒ ፔስት ማመልከቻዎቻችን ኮፒ ፔስት ዜናዎቻችን ኮፒ ፔስት እየሆኑብን ተቸገርን። ሀሳባችንን አሳክተን የተሟላ መልዕክት ለመጻፍ ያቃተን ለምን ይሆን? 
በጸሀፊነት ሙያ ከሰላሳ አመት በላይ ያገለገሉት አንድ ጸሀፊ እንዲህ አሉ ያኔ እንደዛሬ ኮምፒውተር ሳይኖር በፊት በታይፕ በምንሰራበት ወቅት አለቆች እንዲጻፍላቸው የሚፈልጉትን ጉዳይ አርቅቀው ይሰጡን ነበር ተመሳሳይ ጉዳይ እንኳን ቢገጥማቸው አዲስ ጽሁፍ አርቅቀው ይሰጡንና እንጽፍ ነበር። 
ዛሬ ይህ የለም ባለፈው የሰጠሁሽና የጻፍሽውን የሶስት ወር እቅድ ከኮምፒውተር ፋይል ውስጥ ኮፒ ፔስት አድርገሽ እንዚህን ቁጥርና ስሞች በመቀየር አውጭልኝ ማለትና እኛም አዲስ ነገር ከመጻፍ ይልቅ ከፋይላችን ፈልገን ስም ቀን ርዕስና ቁጥር ቀይሮ ከመስጠት ያለፈ ስራ የለብንም ብዙ ጻፉ ብንባል ምን ይውጠን ይሆን? አሉኝ። 
የምንሰራቸው ሳምንታዊ ወርሃዊ አመታዊ ዕቅዶች የመመረቂያ ጽሁፎች ዜናዎች ሁሉም ያከናውንነውን ስራና ያለንን መረጃ መሰረት አድርገን ሀሳብ አፍልቀን በአዲስ መልክ የምንጽፋቸው ጽሁፎች ሳይሆኑ ቀደም ሲል የተሰሩ መሰል ስራዎችን በመኮረጅ እየሆነ ከመጣ ቆየት ብሏል። 
ከአስራ አራት ዓመት በፊት የፈረንጆቹን ሚሊኒየም ለመቀበል ደፋ ቀና በሚባልበት ወቅት ላይ አንድ አስደንጋጭ ወሬ ተሰምቶ ነበር ኮምፒውተሮች እስከ 1999 ብቻ የሚያገለግሉ በመሆኑ 2000 ሺህ ላይ አገልግሎት መስጠት ያቆማሉ በዚህ ሳቢያ በውስጣቸው ያለ ፋይል በሙሉ ይጠፋል ተብሎ ሩጫ በዝቶ ነበር። 
ያኔ ሲዲና ዲቪዲ ፍላሽና ሌሎች ከፍተኛ መረጃ የመያዝ አቅም ያላቸው ቴክኖሎጂዎች ባለመኖራቸው በፍሎፒ መረጃዎችን ለማስቀረት የነበረው ሩጫና ጥቅም ላይ የዋለው የፍሎፒ መጠን በአንዳንድ ተቋማት በወረቀት አትሞ ለማስቀረት የወጣው የወረቀት መጠን ተቋማቱን የፍሎፒና የወረቀት ፋብሪካ አስመስሏቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። 
ያሁሉ ግር ግር ኮምፒውተር መስራት ካቆመ መረጃ እንጣለን ተብሎ ታስቦ ይሆን እንዴ? ዛሬ ላይ የኮፒ ፔስቶቻችን መብዛት ያን ጊዜ የነበረው ሩጫ ዛሬ ኮፒ ፔስት የምናደርገው ነገር እንዳናጣ ታስቦ ይሆን እያልኩ ማሰብም ጀምሪያለሁ። 
"የህይወት ጉዟችን ፈጥኗል። የአዳዲስ ግኝቶች ፈጣራ ግስጋሴም ለጉድ ሁኗል። ትናንት የነበሩን እሴቶች ዛሬ ላይ ዋስትናቸውን ተነፍገዋል።" ጥራዝ ነጠቅ ንግግሮቻችን በኮፒ የተሞሉ ናቸው። ሀሳባችንን አሳክቶ ለመናገርና ለመጻፍ የግድ ትምህርት ቤት ገብተን የክህሎት ስልጠና መውሰድ ያለብን ይመስላል። ተምረን ማንበብና መጻፍ ያቃታቸው የምንባልበት ጊዜ እንዳይመጣ ሰጋሁ። 
ራቶር ጸሀፊው ሻምበል ዛሬም በተለምዶ ስራቸው ላይ ተጠምደዋል አምምሯቸው ቃላት ላማፍለቅ ብቅራቸው በወረቀት ላይ ይጽሁፍ ዝናብ ከማዝነብ አላቆመም በትምህርት ደራጃቸው ከ10ኛ ክፍል ያለዘለለ ቢሁንም ከኛ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ደጅ ከረገጥናው በተሻለ ብዕራቸው ሳይነጥፍ ሀሳባቸውን አሳክቶ ከመጻፍ አልቦዘኑም።
እኛ ግን ባለ አምስት አንቀጽ ዜና ለመጻፍ የፈጣሪን ምልጃ እንጠይቃለን ቢቸግር ጤፍ ብድር እንዲሉ የሰውን ሀሳብ እየዘረፍን የኛ ነው ማለት እንኳን አልከበደንም።
 የምንጽፋቸው ዜናዎች ሀተታና ትንታኔዎች በኩረጃና በኮፒ ፔስት የተሞሉ ሆነዋል። ወዴት እያመራን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው የምንጽፋቸው ጽሁፎች አንባቢ እያጡ እስከመቼ ኧረ ጎበዝ አንድ በሉ ስራዎቻችን ቢፈተሹ አይከፋም በሉ ለማንኛውም ወደ ተለመደው የኮፒ ፔስት ስራዬ ልግባ።  ቸር ይግጠመን።
http://www.ena.gov.et/index.php?option=com_k2&view=item&id=1464:%E1%8B%A8%E1%8A%AE%E1%8D%92-%E1%8D%94%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8C%89%E1%8B%B3%E1%8B%AD-%E1%8B%88%E1%8B%B4%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%8B%88%E1%88%B0%E1%8B%B0%E1%8A%95-%E1%8B%AD%E1%88%86%E1%8A%95?%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B3%E1%88%88-%E1%8B%B0%E1%89%A0%E1%88%8B-%E1%88%80%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8A%A2%E1%8B%9C%E1%8A%A0&Itemid=259&lang=am

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር