አሁንም የፕሬስ ነፃነት ይከበር እንላለን!

ሕገ መንግሥቱ ለፕሬስ ነፃነት ዋስትና ሲሰጥ በአንቀጽ 29 በሚገባ በማብራራት በማናቸውም መንገድ ሕጋዊ ከለላ እንደሚደረግለት ደንግጓል፡፡
የሕገ መንግሥቱ  አንቀጽ 29 በሰባት ንዑስ አንቀሶች ታጅቦ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት አረጋግጧል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ ወርቃማ አንቀጽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ቀጥተኛ ግልባጭ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት ማንም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳብ የመግለጽ፣ በፕሬስና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም መረጃ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት መብቶችን ያጠቃልላል፡፡ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ተከልክሏል፡፡ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማራመድ ይቻላል፡፡ ለዚህም ሕጋዊ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል ይላል፡፡ 
ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ሥራ ላይ ከዋሉ 22 ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ በማለፍ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አይካድም፡፡ አሁንም በጎርባጣው ጎዳና ላይ እየተጓዙ ናቸው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች ይቀርቡባቸው የነበሩ ዓመታት አልፈው አሁን ውስን ጋዜጦችና መጽሔቶች ቀርተዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የግሉ ፕሬስ ፈተናዎች በሁለት ምክንያቶች ሥር ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ውጫዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ውስጣዊ ችግር ነው፡፡ 
የውጭውን ተፅዕኖ ስንፈትሽ ችግሩ ከመንግሥት ይጀምራል፡፡ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን ከማውጣት ባለፈ ለፕሬሱ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጽኦ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሕጎች ሲወጡም በፕሬስ ውስጥ የተሰማሩ ዜጎችን ፍላጎቶች፣ ችግሮችና ተጨባጭ እውነታዎች ስለማያገናዝቡ ጋዜጠኞችና መንግሥት ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ በአንዳንድ ሹማምንት የግሉ ፕሬስ እንደ ጠላት ተደርጎ ይፈረጃል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው ዕውቅና እየተዘነጋ መረጃ ይከለከላል፡፡ ጋዜጠኞች በረባውና ባልረባው ነገር ይታሰራሉ፡፡ ሕግ እየተጣሰ በሕገወጥ መንገድ ሲንገላቱ ጠያቂም ሆነ ተጠያቂ አካል የለም፡፡ ለሌሎች ወገኖች የሚሰጠው የታክስ ማበረታቻና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ለግሉ ፕሬስ ብርቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ የግሉ ፕሬስ ህልውና ላይ ጥላቸውን የሚያጠሉ ደስ የማይሉ ነገሮች ይታያሉ፡፡
ጋዜጠኞች እስከምን ድረስ ሊሳሳቱ ይችላሉ የሚባለው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው አሠራር ትኩረት አላገኘም፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል በመሆናቸው የሕግ ተጠያቂነት ቢኖርባቸውም፣ ከሕጋዊው መንገድ ይልቅ ሕገወጥ ማንገላታቱ ያይላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ተካሂዶ ማሻሻያ ይደረጋል ቢባልም ሲብስበት ነው የሚታየው፡፡ ቅጣት ማስተማርያ መሆን ሲገባው የበቀል አለንጋ ይመስላል፡፡ በአጠቃላይ ውጫዊው ሁኔታ በአጭሩ ይህንን ይመስላል፡፡ 
ውስጣዊው ችግር ሁሌም የምናነሳው ነው፡፡ የግሉ ፕሬስ የውስጥ ገመና ሲፈተሽ የሙያና የሥነ ምግባር ችግሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ የጋዜጠኝነት መሠረታዊ አስተምህሮዎች ተረስተው ጋዜጠኞች የፖለቲካ አቀንቃኝ ሆነው ሲሠሩ ማየት አንዱ ችግር ነው፡፡ ጋዜጠኝነትና የፖለቲካ አቀንቃኝነት በየትኛውም መንገድ አይገናኙም፡፡ ሌላው ጉዳይ የጋዜጠኝነት ሥራ ዓለም አቀፍ የሥነ ምግባር ደንቦችን የተከተለ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ረገድ ብዙ ህፀፆች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመመካከሪያና የመተራረሚያ መድረክ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል የፕሬስ ካውንስልና ጠንካራ ማኅበር አለመኖር፣ በሙያው ውስጥ ያሉ ጥልቅ ጉዳዮችን ለማየት ያለው ፍላጎት መቀዛቀዝና ሌሎች ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ውስጣዊው ችግር ለጊዜው እዚህ ላይ ይብቃ፡፡ 
ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ ወጣ ገባ እያሉ የሚታዩ አንዳንድ ድርጊቶች ደግሞ የአገሪቱን የግል ፕሬስ ሕልውና ብቻ ሳይሆን፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕግ ሳይቀር የሚጋፉ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተዘጋጀ ተብሎ የቀረበው አንድ ጥናት አሳሳቢነት አለው፡፡ ‹‹ሰባት መጽሔቶች በተከታታይ ሕትመቶቻቸው በአሉታዊና በተደጋጋሚ ያነሱዋቸው ጉዳዮች የአዝማሚያ ትንተና›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ 
በመጀመሪያ ደረጃ ማንም ተቋም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማካሄድ እንደሚችል እናምናለን፡፡ ነገር ግን ጥናቱ ለምን አስፈለገ? የጥናቱ ውጤት ለምን ዓላማ ይውላል? ጥናቱ ካስፈለገስ የጉዳዩ ባለቤቶች አስተያየት ተካቷል ወይ? የጥናቱ ውጤት ለማስተማሪያ፣ ለልምድ መለዋወጫ፣ ለትላልቅ ጥናቶች መነሻ ሐሳብ ለማቅረብ፣ ወዘተ ወይስ ለምን የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ 
‹‹… የአዝማሚያ ትንተና›› በሚለው ጥናት በቀረበው መግቢያ ላይ፣ ‹‹የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በአገራችን የሕትመት ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው መጽሔቶች በአገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማወቅ ነው፡፡ ለዚህም ሰባት የግል መጽሔቶች ማለትም አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁ እና ሊያ ከመስከረም 1 እስከ ኅዳር 30 ድረስ ባሉ ተከታታይ ሕትመቶቻቸው በተደጋጋሚ የዘገቧቸውን ጉዳዮች አዝማሚያ ጥናት ለማካሄድ ተሞክሯል፤›› ይላል፡፡ በሰባቱ መጽሔቶች በዓምዶቻቸው ወይም በቋሚ ርዕሶቻቸው ይዘት ላይ የሚያጠነጥነው ይህ ጥናት ሕገ መንግሥቱን፣ የአገሪቱን ነባራዊ የኢኮኖሚ ለውጦች፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን፣ ሽብርተኝነትና የመንግሥት ኃላፊዎችን በተመለከተ ያስነበቡዋቸውን ጽሑፎች በምን ዓይነት አቀራረብና በምን ያህል ድግግሞሽ እንዳወጡ ‹‹ዋና ዋና ግኝቶች›› በማለት በሰንጠረዥ ያስቀምጣል፡፡ 
በመሠረቱ የአዝማሚያ ጥናት ሲባል ምን ማለት ነው? የመጽሔቶቹ የሦስት ወራት ሥራዎች አንድ በአንድ ሲጠኑ የተቀመጡት መሥፈርቶች 
ምንድናቸው? የመንግሥት ኃላፊዎችን የግል ሰብዕና የሚነኩ፣ የአመፅ ጥሪዎችን የሚጠሩ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ፣ የፖለቲካ ሥርዓቱን የሚያጨልሙ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚክዱና ሕገ መንግሥቱን የሚያጣጥሉ የሚሉ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ እነዚህ ትላልቅ ጉዳዮች በሦስት ወራት ጥናት ተጠንተው ቀረቡ ሲባል ምን ማለት ነው? የጥናቱ ውጤት ለምን ዓላማ ይውላል? ለመሆኑ በሚዲያው ሥራ ውስጥ ያሉ ተቋማት ሊያቀርቧቸው ይገባሉ ወይ? የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ወይም የብሮድካስት ባለሥልጣን የሚዲያ ሞኒተሪንግ ሥራን በምን ውክልና ተቀበሉ? ከዚያስ በራሳቸው ሥር ባሉ የሚዲያ አውታሮች እንዴት ዘገባውን ሊለቁ ይችላሉ?
በሌላ በኩል ቀደም ሲል እንዳነሳነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት መሥራት የሚገባቸው የሚዲያ ተቋማት በሚያጠፉበት ጊዜ ሕግ ፊት መቅረብ ወይም ተጠያቂነት እንዳለባቸው ራሱን የቻለ ሕግ አለ፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ለምን እንዲሸማቀቁ ይደረጋል? ማንም ጥፋት ፈጽሟል ተብሎ የሚጠረጠር ግለሰብ ወይም አካል በአግባቡ ሕግ ፊት ቀርቦ መዳኘት ሲገባው፣ ስሜታዊ (Subjective) በሆነ መንገድ በተሠራ ጥናት ለምን ይሸማቀቃል? ይህ ደግሞ ወትሮም እንደነገሩ የሆነውን የግሉን ፕሬስ ይረብሸዋል፡፡
በተደጋጋሚ እንደሚባለው የአገሪቱ ሚዲያ ገና በመዳህ ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ባህል በሚገባ አልዳበረም፡፡ ለምሳሌ ‹‹መጽሔቶቹ በጋራ ያነሷቸው ተደጋጋሚ ጉዳዮች አዝማሚያ›› በሚል ንዑስ ርዕስ ከመጽሔቶቹ የተቀነጨቡ ርዕሶች በማጣቀሻነት ቀርበዋል፡፡ በመጽሔቶቹ ቀረቡ ለተባሉ መጣጥፎች የተሰጡ ርዕሶችንና የጽሑፎቹን ምልከታ በተመለከተ እዚህ ላይ አስተያየት መስጠት ባይቻልም፣ በአጠቃላይ የፕሬስ ነፃነትን የሚጋፉና የተለጠጡ ስሜቶችን የያዙ ስሜታዊ ነገሮች ሲመጡ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በአትኩሮት ሊመለከቱት ይገባል፡፡ 
በአገራችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥት ዋስትና ተሰጥቶታል ሲባል፣ ይህንን መብት በአንድም ሆነ በሌላ የሚጋፋ አካል ተጠያቂነት አለበት፡፡ እንዲያውም ሕገ መንግሥቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጣልቃ ገብነትን ይከላከላል፡፡ ተጠንቶ ቀረበ በተባለው ጉዳይ ላይ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ሲነሳ የሚመለከተው አካል ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ በሦስት ወራት በተደረገ ጥናት የገዘፉና አስፈሪ ጉዳዮች ተነስተው ለአደባባይ ሲበቁ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ መረዳት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 
እንደ ሚዲያ ተቋም አሁንም ደግመን የምናነሳው የፕሬስ ነፃነት ካልተከበረ የሕገ መንግሥቱ ዋስትና እንደተሸረሸረ እንቆጥረዋለን፡፡ ዜጎች በመሰላቸው መንገድ አመለካከታቸውን የማራመድ ወይም የመያዝ መብታቸው ሊከበር ይገባል፡፡ ማንም ከሕግ በላይ አይደለምና በጥፋት የሚጠረጠር ለሕግ ይቀርባል እንጂ፣ በመፍገምገም ላይ ያለውን ፕሬስ ስሜታዊነት በተጫጫነው ‹‹አዝማሚያ ትንተና›› በተባለ ጥናት ማሸማቀቅ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ስንል ለማንኛውም ጉዳይ ሕግና ሥርዓት ይኑረው ማለታችን ነው፡፡ በሕግ ፊት እኩል የሆኑ ዜጎች ሲያጠፉም በሕግ የመዳኘት ግዴታ አለባቸው፡፡ ጥፋተኛ ናቸው እስኪባሉም ድረስ ንፁኃን ተብለው እንደሚታሰቡ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ 
የፕሬስ ነፃነት ሲከበር የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሲከበር ዜጎች ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሐሳባቸውን በነፃነት ያንሸራሽራሉ፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሲከበር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ትልቅ ዋጋ ይኖራቸዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ሲከበር የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ይቀጥላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚከናወኑ ተግባራት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ ስለዚህ አሁንም የፕሬስ ነፃነት ይከበር እንላለን!  
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/itemlist/user/58-%E1%89%A0%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A3%E1%8B%8D%E1%88%AA%E1%8D%96%E1%88%AD%E1%89%B0%E1%88%AD 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር