የሲዳማኔት ኮሌጅ አምስተኛውን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር በሐዋሳ ኣዘጋጅቷል

በልዩ ልዩ ምክንያቶች በውድድሩ የማይሳተፉ ተቋማት ከማህበሩ ጋር
በመነጋገር ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው በመግለጫው ወቅት አጽንኦት
ተሰጥቶታል፤

በየዓመቱ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መካከል የሚካሄደው የስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 16እስከ 30 በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ እንደሚካሄደ ተገለጸ።
የውድድሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለማወቅ እንደተቻለው ፌስቲቫሉን የሲዳማኔት ኮሌጅ ያዘጋጃል። የግል ከፍተኛ ተቋማት ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር አብነት ግርማይ እንደተናገሩት፣ የዘንድሮው ውድድር በአስር የስፖርት ዓይነቶች በሁለቱም ጾታዎች ይካሄዳል።
በውድድሩ 25 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚሳተፉና ከ2ሺ 500 እስከ 3ሺ የሚደርሱ ስፖርተኞች እንደሚካፈሉ ተናግረዋል።
በውድድሩ የሚካፈሉ ተቋማት በብዛት የሚገኙት ከአዲስ አበባ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች ብቻ ስለመሆናቸው፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት ጋር ውድድሩን ለማካሄድ ስላለመቻሉና ሌሎች ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ዶክተር አብነት፣ «ውድድሩን በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ለማካሄድ ፍላጎትና እቅድ ቢኖረንም የተቋማቱ ፍላጎት ማጣት ነው በሦስቱ ክልሎች ብቻ እንዲወሰን የተደረገው። ያም ሆኖ ከትግራይ ክልል ሁለት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ይሳተፋሉ። ከመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት ጋር በጋራ ውድድሩን ለማካሄድ እስካሁን ብዙ ሙከራ አድርገናል። አሁን ጥሩ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ ውጤቱን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል» ብለዋል።
ውድድሩን በየዓመቱ ከማካሄድ በዘለለ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ተቋማት እንዲካፈሉና ውድድሩንም ለማዘጋጀት እንዲችሉ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር አብነት ጨምረው ገልጸዋል።
ውድድሩን የሚያዘጋጀው የሲዳማ ኔት ኮሌጅ ባለቤት አቶ መላኩ አበራ፣ በበኩላቸው ይህንን ውድድር ለማዘጋጀት በመመረጣቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ውድድሩንም እስካሁን ከተካሄዱት ፌስቲቫሎች ሁሉ የተሻለ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
«በተለይም ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሜዳዎችን ለማግኘት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተቋማቱን ሜዳዎች እንድንጠቀም ፈቅደውልናል። የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርም የሀዋሳን ስታዲየም የምንጠቀምበትን እድል ፈጥሮልናል። ውድድሮችን ተከታትለው ለሚዘግቡ ጋዜጠኞችና ውድድሩን ለመመልከት ወደ ሜዳዎቹ ለሚመጡ ተመልካቾች ደግሞ የመግቢያ ችግር እንዳይፈጠርባቸው ዝግጅታችንን በሙሉ አጠናቅቀናል» ሲሉ ተናግረዋል።
አላግባብ ተጫዋቾች ማሰለፍና የሥነምግባር ጉድለት ችግርን በተመለከተ የተጠየቁት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ሲመልሱም «እስካሁን በጣም የከፋ ችግር አልገጠመንም። ሊጠቀስ የሚችለው ችግር የገጠመን በሁለተኛው ውድድራችን ነበር። በወቅቱ የሥነ ምግባር ችግር ያሳዩ ተጫዋቾችን ያሰለፈ ተቋም ከውድድሩ እንዲታገድ ተደርጓል። ዘንድሮ ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም፤ ምክንያቱም የስፖርተኞች ሥነምግባር ጉድለትና አላግባብ ተጫዋች ማሰለፍ የሚያስከትለውን ቅጣት የሚቀበለው ተቋሙ ስለሆነ። ይህንን ደግሞ በመተዳደሪያ ደንባችን አስፍረነዋል» ሲሉ ተናግረዋል።
በአምስተኛው የግል ከፍተኛ ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል ላይ የሚካሄዱ የስፖርት ዓይነቶች አስር ሲሆኑ እነርሱም እግር ኳስ፣ ማዳ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና፣ ዳርት፣ ቼዝ፣ ባድሜንተን፣ አትሌቲክስ፣ መረብ ኳስና ቅርጫት ኳስ ናቸው። በዚህ ፌስቲቫል ላይ የሚገኙ እንግዶች የጸጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው ከክልሉና ከከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን የውድድሩ አዘጋጅ ኮሌጅ ባለቤት አቶ መላኩ አበራ ተናግረዋል።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/sport/7343-2014-01-10-08-34-33

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር