በሲዳማ ዞን ዘንድሮ ከ197 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ይካሄዳል

ሀዋሳ ጥር 7/2006 በሲዳማ ዞን በዚህ አመት በህዝብ ተሳትፎ  ከ197 ሺ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ እንደሚካሄድ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡ 
በመምሪያው የግብርና ልማት እቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግብረ መልስ የስራ ሂደት ኦፊሰር አቶ ደርቤ በትራ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የተፋሰስ ልማት ስራውም  ችግኝ በመትከል ፣እርከንና የውሃ መፋሰሻ ቦዮችን በመስራት ተራራማ መሬቶችን ከጎርፍ ለመጠበቅ ነው፡፡ 
የዞኑ ህዝብ በየአካባቢው ባደረገው ውይይት የተፈጥሮ ሀብቱን በመንከባከብና በመጠበቅ ተጠቃሚ ለመሆን በ528 አካባቢዎች የተፋሰስ ልማት ለማከናወን  ቃል ገብቷል፡፡ 
በተፋሰስ ልማት ስራው ለመሳተፍ በዞኑ በ528 የገጠር ቀበሌዎች የሚኖር ከ400ሺህ በላይ ህዝብ በየአካባቢው በአንድ ለአምስት ተደራጅቶ ስራውን ለመጀመር መዘጋጀቱን አቶ ደርቤ አስረድተዋል፡፡ 
የልማት ስራውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄም በየአካባቢው ከ12ሺህ የሚበልጡ የአርሶ አደር የልማት ቡድኖች ተቋቁመው ስራን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡ 
በየአካባቢው በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ከሚሳተፈው ህዝብ መካከል ከ30 በመቶ በላይ ሴቶች እንደሚሆኑም ተመልክቷል፡፡ 
በተለይ ስነ አካላዊና ስነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ቴክኖሎጂ ውስጥ የአፈር ዓይነትና የመሬት ተዳፋታማነት የሚቀይሱ ከ48 ሺህ 600 በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮች ለስራው ተዘጋጅተዋል፡፡ 
በዞኑ ዘንድሮ ህዝቡን በማሳተፍ የሚካሄደው የተፋሰስ ልማትከ700 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት የስራ ሂደት ኦፊሰር አስታውቀዋል፡፡ 
ባለፈው አመት በህዝብ ተሳትፎ ከ200ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት መከናወኑም ተመልክቷል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር