በሲዳማ ዞን ከ13ሺህ በላይ ላሞችና ጊደሮችን የማዳቀል ስራ ተከናውኗል

አዋሳ ጥር 12/2006 በሲዳማ ዞን ባለፉት 6 ወራት ከ13ሺህ በላይ ላሞችና ጊደሮችን የውጭ ዝርያ ካላቸው ኮርማዎችና በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል ስራ መከናወኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ ፡፡
የማዳቀሉ ስራ የተከናወነው በሸበዲኖ፣በአለታ ጩኮ፣ በአለታ ወንዶና በዳሌ ወረዳዎች ሲሆን በቀጣይም በቀሪ የዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በተመሳሳይ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁም ተመልክቷል፡፡
በመምሪያ የግብርና ልማት እቅድ፣ ዝግጅት፣ ክትትልና ግብረ መልስ የስራ ሂደት ኦፊሰር አቶ ደርቤ በትራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት እንስሳቱን ማዳቀል ያስፈለገው  የወተትና የስጋ  ምርትና ምርታማነታቸውን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ነው፡፡
በዚህም አንዲት የአካባቢው ዝርያ ያላት ላም በቀን የምትሰጠውን ከሁለት እስከ ሶስት ሊትር ያልበለጠ የወተት ምርት ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ ያስችላል፡፡
በየወረዳዎቹ የሚገኙ አርሶ አደሮችን በአንድ ለአምስትና በልማት ቡድኖች በማቀናጀት በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ኦፊሰሩ የእንስሳት ዝርያ የማሻሻሉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ በኮርማና በሰው ሰራሽ ዘዴ የተዳቀሉ ከ6ሺህ በላይ ጥጆች መወለዳቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም  ባለፉት ስድስት ወራት የወተት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል 66ሺህ 890 ቶን ወተት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በዞኑ ሰፊ የእንስሳት ሃብት ቢኖርም በተለይ የወተትና ወተት ተዋፅኦ ምርት ዝቅተኛ በመሆኑ ይህንን ለማሻሻል በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የዝርያ ማሻሻሉ ስራ ለማስፋፋት መዘጋጀታቸውን የስራ ሂደቱ ኦፊሰር አመልክተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር