POWr Social Media Icons

Wednesday, October 30, 2013

ካላ ደሴ ዳልኬ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት
ከኣንድ ወር በፊት በወላይታ ዞን በሁምቦ ወረዳ ኣባያ ቢሳሬ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የሲዳማ ተወላጆች ላይ በኣከባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ወንጀሎች እንደተፈጸሙባቸው እና ቤት ንብረታቸውን በእነዚሁ ሰዎች መቃጠሉን ብሎም ኣከባቢውን በኣስቸኳይ እንዲለቁ በምል የማስፈራሪያ ዛቻ እንደደረሳቸው በቪድዮ የተደገፈ መረጃ በማቅረብ የሲዳማ ዞን መንግስት እና የቦርቻ ወረዳ ኣስተዳደር መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጥሪ ማቅረባችን ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተራችን ጥቻ ወራና ታማኝ ምንጭ ጠቅሶ ከሃዋሳ እንደዘገበው፤ እነዚሁ በቤትንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው የሲዳማ ተወላጆች 18 ተወካዮችን መርጠው ወደ ሃዋሳ በመላክ ለደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ለካላ ደሴ ዳልኬ ኣቤቶታ ኣቅርበዋል።

የተጎጂዎቹን ተወካዮች በቢሮቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት ካላ ደሴ፤ በኣስቸኳይ ጉዳይ ኣጣሪ ቡድን በመሰዬም እና ቡድኑን ወደ ቀበሌው በመላክ የወንጀሉ መፈጸም ኣለመፈጸም እንድጣራ ማድረጋቸው ታውቋል።

ኣጣሪ ቡድኑ ባቀረበው ሪፖርት በሲዳማ ተወላጆች ላይ ወንጀል መፈጽሙን በማረጋገጡ፤ ካላ ደሴ ዳልኬ በኣከባቢው ነዋሪዎች የወደሙ ቤቶች እንድገነቡ እና በኣከባቢው ተወላጆች በሲዳማዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በኣስቸኳን እንዲቆሙ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት በኣከባቢው ያለውን ችግር የመፍታት ስራ በመሰራት ላይ ሲሆን፤ ህዝቡም በመረጋጋት ላይ ነው ተብሏል።


ኣዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ካላ ደሴ ዳልኬ ተጎጂዎቹ ያቀረቡትን ኣቤቶታ በመስማት እና በኣስቸኳይ መፍትሄ በማፈላለግ ሀላፊነታቸውን በመወጣታቸው እና ለተጎጂ የሲዳማ ተወላጆች ኣጋሪነታቸውን በማሳየታቸው መደሰታቸውን ተጎጂዎቹ መግለጻቸውን ሪፖርተራችን ጥቻ ወራና ዘግቧል።