POWr Social Media Icons

Sunday, October 27, 2013

የሲዳማ ዞን ከምድር ወገብ በስተሰሜን አካባቢ ይገኛል። በሰሜናዊ ምስራቅና በደቡባዊ ምስራቅ የኦሮሚያ ክልል በደቡብ ጌዲኦ ዞንና የኦሮሚያ ክልል፣ በምእራብ በኩል ደግሞ የወላይታ ዞን ያዋስኑታል። ዞኑ በሶስት የአየር ንብረቶች የሚካተት ሲሆን 30በመቶ ደጋ፣ 60 በመቶ ወይና ደጋ፣10 በመቶ በቆላ ይሸፈናል። የዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 7ሺ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን በ19 የገጠር ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው። በ1999 .ም በተካሄደው የህዝብና የቤቶች ቆጠራ መሰረት በዞኑ የሚገኘው የሲዳማ ህዝብ ብዛት 3ነጥብ2ሚሊዮን እንደሚሆን ተገምቷል። የሲዳማ ብሄር በሰሜናዊ ምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው።
የሲዳማ ብሄር የራሱ የሆነ የጊዜ አቆጣጠር ቀመር ያለው ሲሆን ቀመሩን ተከትሎ የፍቼ የዘመን መለወጫ በዓል በድምቅት ይከበራል። የፍቼ በዓል የሚከበርበትን ቀን «አያንቶ» (የተመረጡ አዛውንቶችክዋክብት በጨረቃ ዙሪያ የሚያደርጉትን ኡደት በመቃኘት ይወስናሉ። በጎሳ መሪው (ሞቴውውሳኔ መሰረት የበዓሉ ቀን ከታወጀ በኋላ ሁሉም በየፊናው ዝግጅቱን ያጧጡፋል። በዓሉም እስከ ሁለት ሳምንታት ለሚደርስ ጊዜ በየአካባቢው በሚገኙ «ጉዱማይሌዎች» (አደባባዮችበድምቀት ይከበራል። ጉዱማይሌ በዞኑ በሚገኙ መንደራት ሁሉ የሚገኝ ሲሆን ትልቅ ክብር የሚሰጠው ቦታ ነው። አራስ የመታረሻ ጊዜዋ አብቅቶ ከመውጣቷ በፊት ከልጇ ጋር በቅድሚያ የምታየው ጉዱማይሌውን ነው። ሙሽሮች ከሰርጋቸው ማግስት ጀምሮ ጉዱማይሌን ሳያዩ ወደአዲሱ ኑሯቸው አይቀላቀሉም።
የሲዳማ ብሄር ተወላጆች እንደየእድሜያቸውና በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ መሰረት ባህላዊ ልብሶቻቸውን በመልበስና በማጌጥ በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል።
በፍቼ በዓል ላይ «ቄጣላ» የሚሰኘው ሥነስርዓት በአዋቂ ወንዶች ዘንድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚጨፈርበት ነው። «ሆሬ»ና «ፋሮ» ደግሞ የወጣት ወንዶችና ሴቶች የጋራ ጭፈራ ነው። በተለይ ያላገቡ ወጣቶች በነፃነት የሚጫወቱበት ባህላዊ የጭፈራ አይነት ነው። ሴቶች «ፋሮ» የሚባለው ጭፈራ ይበልጥ ስለሚያስደስታቸው ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ከዋዜማው ጀምሮ አገጭ ለአገጭ ተጠጋግተው ይጨፍራሉ። ፍቅራቸውንም ይገላለፁበታል።
የዘንድሮው የፍቼ ጫምባላላ በዓል ሀምሌ 29እና30 በሃዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል። ሀምሌ 29 ሃዋሳ ሀይቅ ዳር በሚገኘው «ጉዱማይሌ» ወይም አሞራ ገደል ተብሎ በሚታወቀው ቦታ «በሞራ ንባብ» የተጀመረው በአል በ«አያንቶዎች» ወይም የተመረጡ አዛውንቶች አማካኝነት በግ ታርዶ ሞራውን በማንበብ የዘመኑን ሁኔታ በመተንበይ ነበር የተጀመረው። በመቀጠልም ከፍቼ ጫምባላላ በዓል ጋር አብሮ በመካሄድ ላይ ያለው የሲዳማ የቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም ለ19ኛ ጊዜ በሲዳማ ባህል አዳራሽ ተካሂዷል። በሲዳምኛ ቋንቋና የሲዳምኛ ቋንቋን ለመጠቀም የሚያስችል ሶፍት ዌር፣ የፍቼ ጫምባላላ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት በሚመለከት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደ ርጎባቸዋል። አመሻሽ ላይ ደግሞ የዘመኑን መለወጥ የሚያበስረው የርችት ተኩስ ሥነሥርዓት በድምቀት ተከናውኗል።ያኔ ሲዳማዎች አዲሱን ዓመት በደስታና በፌሽታ መቀበላቸውን በይፋ አብስረዋል። በተጨማሪም ጣፋጩንና በብሄረሰቡ ዘንድ እጅግ ተወዳጁን ባህላዊ ምግብ «ቦርሳሜ»ን በፍቅር በጋራ በመመገብ የእለቱ ሥነሥርዓት እንደ ደመቀ ተጠናቋል።
ሐምሌ 29 የተከበረው የመሹለክ ሥነሥርዓት «ሁሉቃ» በመባል ይታወቃል። በተለይ በገጠር አካባቢ ከእንጨትና ከእርጥብ ቅጠላቅጠል እንደ በር በተሰራው መሸጋገሪያ ውስጥ ሰዎችና የቤት እንስሳት እንዲሻገሩ ይደረጋል። ይህም ወደ አዲስ ዓመት እንደተሸጋገሩ ተምሳሌታዊ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የነገሩን በዞኑ የባህል እንክብካቤ ባለሙያ አቶ መሃሪሁን መኮንን ናቸው።
በፍቼ ጫምባላላ በዓል ከብት አይታረድም ። ቀድሞ የታረደ ስጋ በቤት ውስጥ ካለም ከብቶች ወደ ቤት አይገቡም። ከቤት ውጪ ነው የሚያድሩት ። ምክንያቱ ደግሞ ዘመኑ የሚቀየረው ለእንስሳትም በመሆኑ ሊደሰቱ ይገባቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።
በሲዳማዎች ዘንድ 2006 .ም በይፋ ተጀምሯል። በእለቱም አባቶች ለልጆቻቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። የጎሳ መሪዎችም ለመንግሥትና ለህዝብ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። ሀምሌ 30 ማለዳ በሃዋሳ ሀይቅ ዳር በተዘጋጀው በዓል ላይ ከሁሉም የሲዳማ ዞኖች የተወከሉና ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው ነበር።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬን ጨምሮ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስና ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች በጎሳ መሪዎቹና በተከታዮቻቸው ምርቃትን ተቀብለዋል። ርእሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት ባዩት ነገር ሁሉ እጀግ በጣም መደሰታቸውን ተናግረዋል።
«ለሲዳማ ህዝብ ፍቼ ጫምባላላ ታላቅ በዓል ነው ። በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ስላደረጋችሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። ይህ አስደሳች በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ። ይህ ሊሆን የሚችለው ባህሉ ተጠብቆ ሲቆይ ብቻ በመሆኑ ባህላችንን መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። የሲዳማ ብሄረሰብ የመከባበር ባህል ለሌሎች በአርአያነቱ የሚጠቀስ በመሆኑ ወጣቱም ይህንን ባህላዊ እሴት በመጠበቅ አዲስ ዓመት በገባ ቁጥር አዲስ እቅድ በማውጣት መስራት ይጠበቅበታል። እቅዱን ለማሳካትም በትጋት መስራት አለበት። ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በርትቶ መስራት አለበት። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ በስራ የምንለወጥበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ» በማለት መልካም ምኞታቸውን ለበዓሉ ታዳሚ አስተላልፈዋል።
በዓሉም እስከ ሁለት ሳምንታት ለሚደርስ ጊዜ በየአካባቢው በሚገኙ «ጉዱማይሌዎች» (አደባባዮችስለሚከበር በቀጣዩ ቀን በግምት 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው መልጋ ወረዳ ወተራ ቀበሌ በመገኘት በዓሉን በድምቀት አከበርን። በዓሉ የሚከበረው ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ በመሆኑ የበዓሉ ታዳሚዎች ከየመንደሮቻቸው አረፋፍደው በመነሳት ነበር በዝግታ ወደ ጉዱማይሌው የደረሱት። «ሲዳማ ስሙ ጥሩ ነው። ሌሎችን አይነካም። ገና ከዚህ በላይ እንበዛለን» በማለት ከየአካባቢያቸው ተሰልፈው ዜማ፣ ምትና የመሳሰሉትን የሙዚቃ ስልቶች ጠብቀው እየጨፈሩ ነው ወደ ጉዱማይሌ የወጡት። ገና ከመንደራቸው ከመነሳታቸው በፊት በግ ታርዶና ሞራው በትላልቅ ሰዎች ተነቦ «ፈላ» የተሰኘውን ሥነ ስርዓት አክብረው ነው የሚወጡት። የቄጠላ በዓልን ከማክበራቸው በፊትም ግምባራቸውን ደም በመቀባት ዓመቱን ሙሉ መልካም ነገር እንዲገጥማቸው ይመኛሉ።
በቄጣላ ጭፈራ ላይ ከፊት ለፊት የሚታዩት አባቶች «ጎንፋ» የተሰኘውን ባህላዊ አልባሳት ለብሰው ጋሻ፣ ጦርና ገጀራ ወይም «ሆሎ» ይዘው ወጣቶችና ህፃናት በቅደም ተከተል ተሰልፈው ከሶስት አቅጣጫ ወደ ጉዱማሌው ወይም አደባባዩ በሚማርክ አኳኋን ነው የመጡት። ሰልፈኞቹ ምርቃት ሲደረግ «ይይይይይ» በማለት መልዕክት ለማዳመጥ ዝግጁ መሆናቸውን በሚያሰሙት ድምፅ ይገልፃሉ። ከዚያም የጎሳ መሪዎች ይመርቃሉ። የጎሳ መሪዎችና የወረዳው አስተዳዳሪ ያስተላለፉላቸውን መልዕክት በሚገባ ካዳመጡ በኋላ ወደየመጡበት በጭፈራ ይመለሳሉ። በቀደሙት ጊዜያት ነብር የገደሉ እንደ ጀግና ይቆጠሩ ስለነበር ዛሬም ጆሯቸውን ተበስተው ሎቲ አድርገውና ቅቤ ተቀብተው ከፊት በመሆን ለየት ባለ ክብር ይጨፍራሉ።
በጭፈራቸው የሚያንጸባርቁት «እኔ ለልማት የተዘጋጀሁ ነኝ ። ሌላውን ሰው አልነካም። ከመንግሥት የተላለፈውን መልእክት ተቀብያለሁ። ከዚህ ውጪ ሌላ መልእክት አልቀበልም» የሚል መልእክት ነው። «ወረዱ ሴኬ ላላምቦ፤ ካዮ ዳጎ» ማለት «ወረዳው ተገቢውን መልእክት አስተላ ልፎልኛል ሌላ መልእክት ከኔ አይጠበቅም» እንደማለት ነው።
በጎሳ መሪዎች የሚተላለፈው መልእክት ደግሞ «በሥነ ሥርዓት ጨፍሩ፣ ታላላቆቻችሁና ባለስልጣናት የሚሏችሁን ስሙ» የሚል ነበር።
የበዓሉን በስኬት መጠናቀቅ አስመልክተው የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ፍላቴ በሰጡን አስተያየት ፍቼ ጫምባላላ በትላልቅ አባቶች ዘንድ የሚመራ በዓል እንደመሆኑ መጠን ወጣቶች ባህሉን ጠንቅቅው እንዲያውቁት እየተደረገ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በብዛት የሚያከብሩት ወጣቶች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
«ወጣቱ የሽማግሌዎችን ምክር እየተቀበለ ነው። አዲሱ ትውልድ ባህሉን ይዞ እንዲያቆይም ግንዛቤ የማስጨበጥና ጉዳዩን የማስረዳት ሥራ በዚህ ዓመት ተጠናክሮ በመሰራቱ ውጤት ታይቶበታል። አባቶችም በየጉዱማይሌዎች ወጣቶችን እያስተማሩ ነው። «አያንቶዎች»ን የሚተካ ሰው ያስፈልጋልና እነሱን እንዲተኩ ወጣቶቹ ጥበቡን እንዲያውቁ እየተደረገ ነው። ባህሉ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ በተሰራው ስራም ጥሩ ውጤት ታይቷል። ባህሉን ለመጠበቅም ተነሳሽነቱን አሳይቷል። ይህ ተስፋ የሚሰጥና የሚያበረታታ ነው።»
አቶ ወርቅነህ ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብሄረሰብ እሴት ቢሆንም ለአገር የሚጠቅም ነውና ለገፅታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ፋይዳ እንዲውል የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት። የብሄር ብሄረሰቦችን መፈቃቀር የሚጨምር መልካም አጋጣሚ እንደሆነ በማከል።