POWr Social Media Icons

Saturday, October 26, 2013


የሕገ መንግሥቱን የበላይነት በሚመለከት ሰሞኑን ጠቃሚና ዓበይት ቃላት ከባለሥልጣናት አንደበት ሲነገሩ እየተደመጡ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥቱን በማክበር አርዓያ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ ፓርላማውም ይህን መቆጣጠር አለበት በማለት በአፅንኦት ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ 
የመንግሥት መሪና ሥልጣን የያዘው ገዥ ፓርቲ ሊቀመንበር እንደመሆናቸው መጠን፣ እንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም ሕገ መንግሥቱን እናክብር ቁጥጥር ሊደረግብንም ይገባል ማለታቸው ጎሽ! የሚያሰኝ ነው፡፡ 
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳም ተመሳሳይ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ፓርላማው ሕገ መንግሥቱ መከበሩን ሊቆጣጠር ይገባል ብለዋል፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲና እንደ መንግሥት መሪ በአርዓያነት ሕገ መንግሥቱን ሊተገብር ይገባል፣ ለሕጎች ተገዥ መሆን አለበት፡፡ ይህንን በተግባር ለመተርጎም የሚያዳግተው አይሆንም፣ አርዓያም ይሁን በማለት በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡ 
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንም በቅርቡ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ልዩ ስብሰባ እንዲዘጋጅ በማድረግ ለሁለት ቀናት በተደረገ ውይይት በአፅንኦት ያነሱት ጉዳይ አለ፡፡ መገናኛ ብዙኃን ስለሕገ መንግሥቱ ኅብረተሰቡን ማስተማር እንዳለባቸውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የማስተግበር የበላይ ኃላፊነት የተሰጠው ስለሆነ፣ በቅርብ እየተገናኙ ስህተትንና ጉድለትን እያሳዩ ሥራቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ በተግባር ሥራ ላይ ያልዋለ ሕገ መንግሥት ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋም አስረድተዋል፡፡
በአጭሩ  ሲታይ ከመንግሥት መሪ፣ ከገዥው ፓርቲ ኃላፊ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ከፌዴሬሽን ምክር አፈ ጉባዔ ሕገ መንግሥቱና ሕጎች እንዲከበሩ ልዩ ትኩረትና ልዩ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ 
እንደ አፋችሁ ያድርግልን!
መናገር ቀላል ነው፡፡ አንቀጽ መጥቀስ አያስቸግርም፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠትም የተለመደ ነው፡፡ ሁሌም ችግሩ ተግባርና ተግባር ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሕገ መንግሥታችን የሰፈሩ መብቶችና የሕጎቻችን ፍሬ ነገሮች በደብዳቤዎች ሲጣሱና ሲደረመሱ እየተስተዋሉ ናቸው፡፡ በትግል የተገኙና ብዙ ክርክር የተደረገባቸው አኩሪ የሕገ መንግሥት አንቀጾች በቴሌፎን፣ በኔትወርኪንግና በሙስና እየተጣሱ ናቸው፡፡ 
ስለሆነም በግልጽ አንድ ጥያቄ ጠረጴዛ ላይ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ 
ሕገ መንግሥት መከበር አለበትና ቁጥጥርም ይደረግ በሚለው ላይ ተቃውሞ የለንም፤ በዚህ ላይ ድጋፍ ነው ያለን፡፡ 
ግን ነገር ግን ፓርላማውም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም፣ ገዥው ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሕግ የሚጥሱ ባለሥልጣናት ሲያጋጥሟቸው ዕርምጃ ለመውሰድ ቆራጦች ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ 
የኢሕአዴግም የመንግሥትም ችግር እዚህ ላይ ነው፡፡ በቃል የሚናገረውንና በመርህ አምንበታለሁ የሚለውን በተግባር አያሳይም፡፡ ሕጎች በባለሥልጣናት ሲጣሱ ዕርምጃ ለመውሰድ ድፍረት ያንሰዋል፡፡ 
ሕገ መንግሥቱንና ሕጎችን የሚጥሱ ባለሥልጣናትና ኔትወርኮች እንዳሉ መንግሥት በሚገባ ያውቃል፡፡ እከሌን አትንኩ ብለው የሚያዙ፣ እኬን አስቁሙ ብለው ቴሌፎን የሚደውሉ፣ ሕገወጦች ሕግ ሲጥሱ እንዳትነኩት የሚሉ፣ በሕጋዊ መንገድ የሚሠራውን አስቁሙት የሚሉ፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ካላቸው ታዛዠነት በላይ፣ ለሕገ መንግሥትና ለሕግ ካላቸው ከበሬታ በላይ፣ ለባለገንዘብና ለኔትወርክ ተገዥና ታዛዥ የሆኑ ባለሥልጣናት እንዳሉና ቁጥራቸውም በርካታ እንደሆነ ኢሕአዴግ ያውቃል፣ መንግሥት ያውቃል፡፡
ታዲያ ለምን ዕርምጃ አይወስድም? ለምን ሕገ መንግሥት የሕጎች የበላይ ነው ብሎ ቁጥጥሩን ጠበቅ አያደርግም? ኔትወርኩ የተወሳሰበ ነው፡፡ አባላቱ ብዙ ናቸው፡፡ መንግሥትም ኢሕአዴግም ድፍረት ያንሳቸዋል፡፡ ችግሩ ይህ ነው፡፡ 
የመረጃና የማስረጃ ችግር የለም፡፡ ዓይን የሚያስፈጥጡ መረጃና ማስረጃዎች በየአደባባዩ አሉ፡፡ ሕግ እየተጣሰ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ማሳያ አለ፡፡ ግራ የተጋባው ሕዝብም መንግሥት ለምን ዝም ይላል በማለት በየጊዜው ትዝብቱንና ቅሬታውን እየገለጸ ነው፡፡ የፍትሕ ያለህ እያለም ነው፡፡ አንድ ዜጋ ሕግ ጥሰሃል እየተባለ ሲቀጣና ሲንገላታ፣ ሌላው ሲጨፍርና ሲጋልብ በአደባባይ እየታየ ነው፡፡ 
ስለዚህ መንግሥትና ምክር ቤቶቻችን ሁለት ነገሮችን ያቀናጁ፡፡ ሕገ መንግሥትና ሕግ መከበሩን ጥብቅ ቁጥጥር እናድርግ ማለታቸውና ደፈር ደፈር እያሉ መናገራቸው በርቱ ተበራቱ ያሰኛል፡፡ ሕዝብም ከጎናችሁ ነው፡፡ ከጎናችሁም ይሆናል እንላለን፡፡፡ 
ግን በተግባር አውሉት እንላለን፡፡ ሕግ መጣስ የለበትም ከሚለው ጎን ለጎን የጣሰ ይቀጣል፣ በሕግ ይጠየቃል ማለትም አለባቸው፣ በተግባርም ያሳዩት፡፡ 
ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡ ንግግሩ ጥሩ ነው፡፡ በተግባር አሳዩን፡፡ እንደ አፋችሁ ያድርግልን!
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/itemlist/user/58-%E1%89%A0%E1%8C%8B%E1%8B%9C%E1%8C%A3%E1%8B%8D%E1%88%AA%E1%8D%96%E1%88%AD%E1%89%B0%E1%88%AD

ሲዳማ ቡና 

ሙሉ ስም ፡ ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ 
ምስረታ ፡ 1999
ስታዲየም ፡  ይርጋለም ስታዲየም ሀዋሳ ስታዲየም
የክለቡ የወቅቱ አሰልጣኝ ፡ ታረቀኝ አሰፋ  ዳኜ

ክለቡ ያገኛቸው ክብሮች ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን 2001
ሲዳማ ቡና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ እየተሳተፈ ያለ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከተመሰረተ ጥቂት አመታት ብቻ ቢቆጠሩም በብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በፕሚየርሊጉም ጥሩ ተፎካካሪ እየሆነ ይገኛል፡፡

ምስረታ 

ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የተመሰረተው በ 1999 ዓ/ም ነበር በደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ሲዳማ ዞንን በመወከል ሥስት ክለቦች ይሳተፋሉ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ዳራ ከነማ ነበር፡፡ ዳራ በውድድሩ ለፍፃሜ በመድረስ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ይህም ክልሉን በመወከል ሀዋሳ ላይ ወደተካሄደው የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከተሳተፉ አራት ቡድኖች አንዱ ለመሆን አበቃው፡፡ በዚህ ውድድር ቀዳሚዎቹን አራት ደረጃዎች የሚይዙ ቡድኖች ወደ ብሔራዊ ሊግ ሲያልፉ ዳራም ሦስተኛ ደረጃን አግኝቶ ስለነበር ብሔራዊ ሊጉን ተቀላቀለ፡፡ እናም ዳራ ከተማን ብቻ ይወክል የነበረው ክለብ መላውን የሲዳማ ዞንን እንዲወከል በማሰብ ሲዳማ የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡

ሲዳማ ቡና በብሔራዊ ሊግ
ሲዳማ ቡና ሁለት አመት በብሔራዊ ሊግ አሳልፏል፡፡ በመጀመሪያው አመት ቆይታው በ 2000 አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡ በሁለተኛው አመት 2001 ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሔድ በምድብ ሁለት የነበረው ሲዳማ በመጨረሻው ጨዋታ ከአየር ሀይል ጋር ያለ ግብ በመለያየት ከምድቡ ከሜታ አቦ ቢራ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በዚህ ጨዋታ ቢሸነፍ ኖሮ ይህን ደረጃ አያገኝም፡፡ በቀጣይ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ ከየምድባቸው የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች የያዙ አራት ቡድኖች  መካከል የአንድ ዙር ውድድር ተደረገ፡፡ ሻሸመኔ ከነማ፤ ደደቢትንና ሜታአቦ ቢራን በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብ የሰበሰበው ሲዳማ ቡና የብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን ዓመቱን አጠናቀቀ፡፡ አጥቂውን ሰዳት የሱፍንና አሰልጣኙን ታረቀኝ አሰፋን በኮከብነት አስመርጧል፡፡

ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊግ
ሲዳማ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የ 2002 ፕሪሚየር ሊግ እንደመጀመሪያው ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከሻምፒዮኑ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ አቻ መለያየቱ መከላከያን በይርጋለም ላይ 4 ለ 2 ማሸነፍ ከጠንካራ ክለቦች ጋር ያሳየውን ፉክክር ያመለክታል፡፡

የሲዳማ ቡና መሰረት
ሲዳማ ቡና ከሌሎች ክለቦች በተለየ ሁኔታ የፋይናንስ ምንጪን የዞኑን ህዝብ በማድረግ ይታወቃል፡፡ በአለም እውቅና በተሰጠው ቡና ስም የተሰየመው ይኸው ክለብ በዞኑ ህብረተሰብ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ክለቡን በበላይነት የሚመራው የሲዳማ ዞን  ስፖርት ምክር ቤት ሲሆን  ክለቡ ሙሉ በሙሉ የሚንቀሳቀሰው ከሕብረተሰቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመታዊ መዋጮ ያደርጋል፡፡ በየአመቱ በሚካሔድ የገቢ ማሰባሰቢያም ውጤታማ ሆኗል፡፡ በ 2001 የብሔራዊ ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ከ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናም ሲዳማ ቡና በዚህ ረገድ ያለው ልምድ ለሌሎች ክለቦችም በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2006 ዓ/ም የጨዋታ መርሃ ግብር በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 16/2006 ዓ/ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ 5 ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የደደቢትና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ህዳር 7 ዋሊያዎቹ ከናይጀሪያ ጋር ላለባቸው ወሳኝ ጨዋታ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን በመጠራታቸው እንደተራዘመ ታውቋል፡፡
ከ10 በላይ ተጨዋቾችን ለዋሊያዎቹ ዝግጅት የተነጠቀው ቅዱስ ጊዮርጊስም ቅዳሜ ከሙገር ሲሚቶ ጋር የሚኖረው ጨዋታ ተራዝሟል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን በዚህ ዓመት የተቀላቀለው ዳሽን ቢራ በሜዳው ሐረር ቢራን የሚያስተናግድ ሲሆን እንደ ዳሽን ሁሉ በዚህ ዓመት ሊጉን የተቀላቀለው ወላይታ ዲቻ አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል፡፡
መብራት ሃይል በበኩሉ ወደ ሃዋሳ በማቅናት ሃዋሳ ከነማን እሁድ ሲገጥም መከላከያ ሲዳማ ቡናን እንዲሁም ኢትዮጵያ መድህን አርባ ምንጭን የሚያሰተናግዱበት ጨዋታ በመጀመሪያው ሳምንት ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ዓመት የተከሰተው የጨዋታዎች መቆራረጥ በዚህ ዓመትም ሊቀጥል እንደሚችል ቢሰጋም የውድድር መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው እነዚን ውድድሮች ከግምት በማስገባት መሆኑን ፌደሬሽኑ ገልጿል፡፡
በውድድር ዓመቱ ዋሊያዎቹ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያን ጨምሮ ለቻን አፍሪካ እንዲሁም ለሴካፋ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በ“ኢትዮ ምህዳር” ላይ የ300ሺ ብር ክስ አቀረበ

ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል “አዲስ አድማስ”ን መክሰሱ ይታወቃል
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም ታስሮ ወደ ሃዋሳ ተወስዶ ነበር
 “ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ “የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት አባል በሙስና እጅ ከፍንጅ ተያዘ” በሚል ርዕስ ካወጣው ዜና ጋር በተያያዘ ስሜ ጠፍቷል በማለት 300ሺ ብር ካሳ እንዲከፈለው ዩኒቨርስቲው ክስ ያቀረበ ሲሆን፣ ፍ/ቤት ብይን ለመስጠት ለሚቀጥለው ረቡዕ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ 
የጋዜጣው አሳታሚ፣ ዋና አዘጋጅ እና ስራ አስኪያጅ እያንዳንዳቸው 100ሺ ብር ካሳ ሊከፍሉኝ ይገባል በማለት ዩኒቨርስቲው ክስ ያቀረበው፣ በሃዋሳ ለሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲሆን ተከሳሾቹ ሰኞ እለት የመቃወሚያ መልስ አቅርበዋል፡፡ በእለቱ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም የሚል ብይን እንዲሰጥላቸው ተከሳሾቹ ቢጠይቁም፣ ዩኒቨርስቲው “የመልስ መልስ ለመስጠት ጊዜ ይሰጠኝ” በማለቱ ለሚቀጥለው ረቡዕ ተቀጥሯል፡፡
“ኢትዮ ምህዳር” ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ “የሃዋሣ ዩኒቨርስቲ የማናጅመንት አባል በሙስና እጅ ከፍንጅ ተያዙ” የሚል ዜና ያወጣው ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲው የፍትሐ ብሄር ክስ በካሳ ጥያቄ ላይ ያተኮረ ሆኗል። ዜናው ታትሞ በተሰራጨበት ወቅት ዩኒቨርስቲው በደብዳቤው ምላሽ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዩኒቨርስቲው ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በላከው ደብዳቤ፣ የሙስና ወንጀል መፈፀሙን እንዳልካደ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አስታወሰው፤ “በሙስና የተያዘው ግለሰብ የማናጅመንት አባል ሳይሆን የቡድን መሪ ስለሆነ ማረሚያ እንድታወጡ” የሚል ደብዳቤ ነው የደረሰን ብሏል፡፡
ይህንንም ማረሚያ በጋዜጣችን አስተናግደናል ብሏል - ዋና አዘጋጁ፡፡
ቀደም ሲል ዩኒቨርስቲው በ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት ለፖሊስ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበርና እንዳልተሳካለት የሚታወቅ ሲሆን፤ የፍትሐ ብሄር ክስ በመመስረት የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ሃዋሳ ሄደው እንዲከራከሩ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
የዩኒቨርስቲው ክስ በሃዋሳ ፍ/ቤት ውድቅ እንዲሆን ከተደረገ በኋላም እስከ ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ ይግባኝ በመጠየቅ ተከራክሮ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅም እንዲሁ ከሁለት ሳምንት በፊት ታስሮ ወደ ሃዋሳ ከተወሰደ በኋላ፣ ስትፈለግ ትመጣለህ ተብሎ መለቀቁ ይታወሳል፡፡
ምንጭ፦ ኣዲስ ኣድማስ ጋዜጣ 
ሥራው አልቆ አገልግሎት የጀመረው የሀዋሳው ባለ 5 ኮከብ ሆቴልና ሪዞርት ስለሆነ እሱን ላስቃኛችሁ። ሆቴሉ የተሠራው ከሀዋሳ ከተማ ዳር ነው፡፡ ከሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ፊት ለፊት፣ ወደ ይርጋዓለም፣ ዲላ፣ ሞያሌ፣ … ከተሞች በሚወስደው አውራ ጎዳና ቀኝ ጠርዝ ነው፡፡ ወደ ሆቴሉ ሲታጠፉ የባለቤቶቹ ስም የተጻፈበት እብነበረድ አለ፡፡ ከዚያ ጥቂት ሜትሮች እንደተራመዱ፣ የሆቴሉን ትልቅ ባለ ቅስት መግቢያ ያገኛሉ፡፡ በሩ ሰፊ በመሆኑ፣ ወደ ሆቴሉ የሚገቡና የሚወጡ መኪኖች መተላለፊያቸው የተለያየ ነው፡፡ 
ግቢው በጣም ሰፊ ሲሆን፣ አረንጓዴ ሳር፣ በየስፍራው የተተከሉ በርከት ያሉ ዛፎችና አበቦች ሲያዩ ሆቴል ሳይሆን ዘመናዊ መናፈሻ ውስጥ የገቡ ይመስልዎታል፡፡ መግቢያውን እንዳለፉ በስተግራ፣ ግራውንድ ቴኒስ መጫወቻ፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ እንግዳ መቀበያውን፣ አዳራሽ እንዲሁም ትንሽ ራቅ ብሎ ባርና ሬስቶራንቱን ያገኛሉ፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ራቅ ብሎ የመዋኛ ገንዳው ይታያል፡፡ 
እስካሁን ክፍሎቹን አላየሁም፡፡ በባርና ሬስቶራንቱ ጐን፣ ሰፊ ስፍራ አለ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የተሠራው የአስተዳደርና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሕንፃ ነው። መኝታ ክፍሎቹን የሚያገኙት ከዚያ ሕንፃ ጀርባና ጐን ነው፡፡ ሕንፃዎቹ ሁሉ የጐጆ ቤት ቅርፅ አላቸው። በመጀመሪያው ምዕራፍ የተሠሩት 32ቱ ክፍሎች ፎቅ የላቸውም፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚሠሩት 75 ክፍሎች ፎቅ ሲኖራቸው፣ ግንባታቸው ተጀምሮ መሠረቱ መውጣቱን ባለሀብቱ ተናግሯል፡፡ 
ገዛኸኝ፣ በሀዋሳ ከተማ የተሠራው ሆቴልና ሪዞርት፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሊኖረው የሚገባውን ፋሲሊቲ አሟልቶ በኢትዮጵያ የተሠራ የመጀመሪያው ሆቴል እንደሆነ ይናገራል፡፡ ክፍሎቹ በአራት ደረጃ የተከፈሉ ሲሆን ባለ አንድ፣ ባለ ሁለት አልጋ፣ ትዊንና ልዩ የቤተሰብ መቆያ ኤግስኩቲቭ ቪላ (ባንጋሎ) ናቸው፡፡ ቪላው ራሱን የቻለ የታጠረ ግቢ ሲኖረው፣ የደህንነት ጥበቃውም ልዩ ነው፡፡ ምግብ ማዘጋጃ ኪችን መመገቢያ ጠረጴዛ፣ የወላጆችና የልጆች መኝታ ክፍል፣ እሳት ማንደጃ፣ ግቢው ውስጥ ደግሞ መኪና ማቆሚያ፣ ካምፋየር ማዘጋጃ ስፍራ፣ የጓሮ ፍራፍሬ፣ ማንጐ፣ ፓፓያ፣ አቡካዶ፣ … አለው፡፡ እዚያ ያረፉ እንግዶች ፍሬዎቹን ቀጥፈው መብላትና መጭመቅ እንደሚችሉ ገዛኸኝ ገልጿል። ኪችኑ፣ በተሟላ ምግብ ማዘጋጃ ዕቃዎች የተሟላ ነው፡፡ 
የልጆች ክፍል፤ ሁለት አልጋ፣ ቁም ሳጥን፣ መታጠቢያ ገንዳ፣ መፀዳጃ፣ ሆቴል ቲቪ፣ … አለው። የወላጆች ክፍል ደግሞ ማስተር ቤድ፣ መታጠቢያ ገንዳና ጃኩዚ፣ ሆቴል ቲቪ፣ ስልክ፣ መፀዳጃ፣ ቁምሳጥን፣ የመልበሻ ጠረጴዛ፣ … ይዟል፡፡ ሳሎኑ፤ ቲቪ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ፍሪጅ፣ ስልክ፣ የምግብ ጠረጴዛ፣ … በአጠቃላይ አንድ ዘመናዊ ቪላ ሊኖሩት የሚገባውን ነገሮች አሟልቶ ይዟል፡፡ ክፍያው ታዲያ የተጋነነ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሆቴሉ በይፋ ተመርቆ እስኪከፈት ድረስ ጊዜያዊ ዋጋ ቢሆንም፣ በሥራ (በአዘቦት) ቀናት 79 ዶላር ወይም 1,469 ብር፣ ቅዳሜና እሁድ 99 ዶላር ወይም 1,841 ብር ነው፡፡ 

የክፍሎቹን ብዛት ያየን እንደሆነ 5 ትዊንስ፣ 15 ሲንግል፣ 10 ደብልና 2 ቪላ ናቸው፡፡ ሲንግሉ፣ ቀዝቃዛ ሻወር አለው፡፡ ደብሉ ጃኩዚ፣ ትዊኑ በረንዳ ላይ ዐረቢያን መጅሊስ አላቸው፡፡ ቲቪ፣ ስልክ፣ ሚኒባር፣ ካዝና፣ በሆቴሉ ስም የተሠሩ የተለያየ መጠን ያላቸው ፎጣዎች፣ ሳሙና፣ የፀጉር ሻምፑ፣ ሎሽን፣ የጥርስ ብሩሽና ሳሙና፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ መፀዳጃ ቤት፣ ቁም ሳጥን፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ ሶፋ፣ … በሁሉም ደረጃ ባሉ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ 
አልጋ የያዙ እንግዶች በተጓዳኝ የሚያገኟቸው ጥቅሞችም አሉ፡፡ ጂም የፀጉርና የጥፍር ውበት (ስፓ)፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ዋና፣ ከረንቦላ፣ ግራውንድ ቴኒስና ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቁርስ፣ .. ለሁሉም በነፃ ይሰጣል፡፡ 
ሆቴሉ የተሠራው ከውጭ በመጡ ዕቃዎች ሳይሆን ግቢው ውስጥ ባሉ ወርክሾፖች በተመረቱ ዕቃዎች ነው፡፡ “የራሳችን የእንጨት፣ የብረታ ብረት፣ የኮንስትራክሽን፣ ወርክሾፖች አሉን፡፡ የሚያማምሩ ዲዛይን ያላቸው ሞልዶች ከውጭ አስመጥተን ግቢ ውስጥ ያነጠፍናቸውና ለጣራ ክዳን የተጠቀምንባቸው ታይልሶች እዚሁ የተመረቱ ናቸው፡፡ እነዚህን የኮንስትራክሽን ዕቃዎች እዚህ ማምረታችን፣ የዋጋና የጥራት ልዩነት አለው፡፡ አንድ ብሎኬት ስታመርት፣ አሸዋውን፣ ሲሚንቶውን … በምትፈልገው የጥራት ደረጃ ቀላቅለህ ትሠራለህ፡፡ ከውጭ አገር ለምሳሌ ከቻይና ስታስመጣ፣ የጥራት ደረጃውን ሳታውቅና ሳታይ ትቀበላለህ፡፡ ለሆቴላችን ክፍሎች የገጠምናቸውን መስኮትና መዝጊያ ስታይ እዚህ አገር እንደዚህ ይሠራል ወይ? ብለህ በጣም ትገረማለህ። ጥራታቸው ከውጭ ከሚመጡት ስለሚበልጥ እዚህ ግቢ ተመረቱ ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ነገሮች ለሆቴላችን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት፣ ለአገራችንም ገበያ ቢቀርብ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ” በማለት በወርክሾፑ ስለሚመረቱት ቁሶች ጠቃሚነት ገልጿል፡፡ 
መዋኛው ትልቅ እንደሆነ አትሌት ገዛኸኝ ይናገራል። የራሱ ጃኩዚ ሲኖረው፣ 26 ሜትር ቁመትና ከ20.55 እስከ 85 ሜ. ጥልቀት አለው፡፡ “የሕፃናት መዋኛው ጥልቀት 90 ሳ.ሜ ስለሆነ ማንኛውም ሕፃን እንደ ልቡ መጫወት ይችላል” ትላለች፤ የገንዳው ሕይወት አድን ሠራተኛ፡፡ በማከልም፣ “ውሃው ያለውን ኬሚካል በፒኤች ለክተን፣ ክሎሪን ወይም አሲድ እንደጐደለው አውቀን የጐደለውን እንጨምርበታለን። ኬሚካል ስንጨምርበት ከስር ዝቃጭ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ጊዜ ቆሻሻውን በቫክዩም ስበን በማስወጣት እናፀዳለን” ብላለች፡፡ 
ውሃውን እያጣራ የሚመልስ (ሰርኩሌት የሚያደርግ) መሳሪያ ያለው ሲሆን እንግዶች ዋና ሲደክማቸው ወደ ዳር ተጠግተው፣ ውሃው ውስጥ ባለ መቀመጫ ላይ አረፍ በማለት የተለያዩ ለስላሳ መጠጦችና ፋስት ፉድ የሚስተናገዱበት ስዊሚንግ ባር አለ፡፡ 
ገዛኸኝ፣ ለሆቴሉ ግንባታ እስካሁን 200 ሚሊዮን ብር መውጣቱንና ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ ካፒታሉ በእጥፍ እንዲጨመረ ጠቅሶ ለ120 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል፡፡ “ከመንግሥት ዋነኛ እቅዶች አንዱ የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ፣ ከ250 እስከ 300 ለሚደርሱ በክልሉ ያሉ ዜጐች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ እኔም ትንሽም ቢሆንም በመንግሥት ዕቅድ ተሳትፌ የበኩሌን ድርሻ በማበርከቴ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡ 
ምንጭ፦http://gezahegnhotels.com/ እና http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=13148:%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%88%8C%E1%89%B6%E1%89%B9-%E1%89%A3%E1%88%88-5-%E1%8A%AE%E1%8A%A8%E1%89%A5-%E1%88%86%E1%89%B4%E1%88%8D%E1%8A%93-%E1%88%AA%E1%8B%9E%E1%88%AD%E1%89%B5&Itemid=240

የሲዳማ ዞን መንግስት የካቢኔ ሽግሽግ ኣድርጓል። የቀድሞ  የዞኑ ዋና  ኣስተዳደር ኣቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ወደ ደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊነት የተዛወሩ ሲሆን፤ በእሳቸው ቦታ የቀድሞ የዞኑ ድርጅት ፖለቲካ ሃላፊ ካላ ኣክልሉ ኣደላ የዞኑ ዋና ኣስተዳደር ሆነዋል። በተጨማሪም በዞኑ ፋይናንስ መምሪያ በዋና ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ  የቆዩት ኣቶ  በቀለ ታፎ ወደ ስቪል ስርቪስ መምሪያ  ሃላፊነት ተዛውረዋል።

በተመሳሳይ ዜና በሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደርም የካቢኔ ሽግሽግ የተደረገ ሲሆን፤ የከተማው ፍይናንስ መምሪያ  ኣዲስ ሃላፊ ተሹሞለታል።

በዞኑ ስለተላሄደው የካቢኔ ሽግሽግ እና በሽግሽጉ ዙሪያ የተሰበሰበ የህዝብ ኣስተያየት እንደደረሰን ለክቡራን ኣንባብያን እንደምናቀርብ መግለጽ እንወዳለን ወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ