POWr Social Media Icons

Wednesday, September 25, 2013

‹‹ልማታዊ መንግሥትን ከፌዴራል ሥርዓት ጋር ማጣጣም እጅግ አስቸጋሪ ተግባር ነው›› ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፓም
መስከረም 13 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ፋኩልቲ የእሸቱ ጮሌ አዳራሽ “Federalism and the Developmental State” በሚል ርዕስ በዕውቁ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፓም የቀረበው ጥናት “Perspectives of Diversity in Ethiopia” የተሰኘውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል፣ በፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግና በጎተ ኢንስቲትዩት የሚዘጋጀው የውይይት መድረክ አካል ነበር፡፡
ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ እንዲጀመር ፕሮግራም ለተያዘለት ፕሮግራም ታዳሚዎች ከ11 ሰዓት ጀምሮ ቦታ መያዝ ጀመሩ፡፡ የጥናቱ አቅራቢ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፓም በወጣትነት ዘመናቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኢትዮጵያ እንዲሁም በአፍሪካ ላይ የሚያተኩሩ ዘርፈ ብዙ መጻሕፍትንና የምርምር ሥራዎችን ያሳተሙ ስለሆኑ ብቻ አልነበረም፣ ይልቁንም የጥናታቸው ርዕስ የበርካታ ሰዎችን ስሜት የሳበ ነበር፡፡ 
ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ
ፌዴራሊዝም እንደ መንግሥት አወቃቀር በኢትዮጵያ የበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ሕጋዊ ይዞታ በመስጠትና በፈቃደኝነት ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዳመጣው በመግለጽ ነው ፕሮፌሰሩ ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ ልዩነቱ ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉት መንግሥታት ፌዴራሊዝምን ቢያንስ በባሕሪ ደረጃ የተቀበሉና የአካባቢ አገዛዞችን ዕውቅና ሳይሰጡ ኢትዮጵያን መምራት አስቸጋሪ ስለነበረባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 
በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ እ.ኤ.አ. ከ1855 ጀምሮ ኢትዮጵያን ከመሩት መንግሥታት መካከል የአሁኑ መንግሥትን በአገዛዝ ዓመታት ብዛት የሚቀድመው እ.ኤ.አ. ከ1941 እስከ 1974 የመራው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛው መንግሥት ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ የአሁኑ መንግሥት ለረዥም ዓመታት ሥልጣን ላይ መቆየቱ አንፃራዊ ስኬትን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ከልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ጋር ለማጣጣም ተግዳሮት እንደገጠመው ጠቁመዋል፡፡ 
በ1983 ዓ.ም. የተጀመረው የፌዴራል ሥርዓት አብዮታዊ እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ ከ1983 ዓ.ም. በፊት የነበሩት መንግሥታት ከተከተሉት የአመራር ዘይቤ ፈጽሞ የተለየ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ፌዴራሊዝም ርዕዮተ ዓለማዊ ምንጭ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚያደንቁት የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለምና በብሔር ጥያቄ ዙሪያ የሚያጠነጥነው የሌኒን ጽሑፍ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ አቶ መለስ ርዕዮተ ዓለሙ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ነበር ብለው እንደሚያምኑ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ በፌዴራሊዝም አዲሱ መንግሥት የሚፈለገውን የፖለቲካ ዒላማ ማሳካቱንም ያስታውሳሉ፡፡ በማዕከላዊነት ያስተዳድር የነበረው ደርግ አግሏቸው የነበሩ ብሔሮች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መምራታቸው በጣም የሚስብ ስትራቴጂ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ብሔሮች መካከል የነበረው ልዩነት አዲሱ መንግሥት በፈጠረው የእኩልነት ዕድል መቀየሩ በጣም ወሳኝ የሆነ ታሪካዊ ግብ እንደነበረው ፕሮፌሰር አስረድተዋል፡፡ 
በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ዘግይተው የተቀላቀሉት የደቡብና የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት ቢሮዎች ውስጥ ከራሳቸው ሕዝብ የመጡና የራሳቸውን ቋንቋ የሚናገሩ አመራሮችን ማየት በመቻላቸው ፌዴራሊዝም “አብዮታዊ” ነበር ለማለት ማስረጃ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይሁንና አዲሱ መንግሥት የገባው ቃልና ተግባሩ መካከል መመጣጠን እንደሌለ ፕሮፌሰር ክላፓም ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹በከፊል አንደኛው ምክንያት አዲሱ መንግሥት በተረከባት ኢትዮጵያና መፍጠር በሚፈልጋት ኢትዮጵያ መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሥርዓቱ መቻቻልን የሚፈልግ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ መቻቻል ጉልህ ቦታ ያለው ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘበት አጋጣሚ የርዕዮተ ዓለሙ ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ሶቭየት ኅብረትና ሌኒኒስታዊ የአንድ ፓርቲ ሥርዓቱ መውደቅም ለደካማው አፈጻጸም ከርዕዮተ ዓለም መጋጨት ጋር በተያያዘ አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ይላሉ፡፡ 
ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ
በሚሌኒየም በዓል አከባበር መላ አገሪቱ ወደ ልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ለመሸጋገር የወሰነችው በበርካታ ምክንያቶች ድምር ውጤት መሆኑን ፕሮፌሰር ክላፓም ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና አዲሱ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም የፌዴራል ሥርዓቱን ተክቷል ማለት እንደማይቻል ያመለክታሉ፡፡ 
ሁሉም መንግሥታት አስቀድመው ከገመቱት ውጪ የሆነ ነገር ሲያጋጥማቸው መደንገጣቸውና ለውጥ ማሰባቸው የተለመደ ቢሆንም፣ በ1990 ዓ.ም. የኤርትራ መንግሥት ባድመን ሲቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግሥት በደነገጠው መጠን የሌሎች መንግሥታት ድንጋጤ እንደማይነፃፀር ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ፡፡ 
የኤርትራ መንግሥት ወደ ጦርነቱ ሲገባ ኢትዮጵያ የጋራ አያያዥ ጉዳይ የሌላቸው የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች ስብስብ ብቻ መሆኗን በመተማመን እንደነበር የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በኤርትራ ድርጊት መቆጣቱ ኤርትራውያን ፈጽሞ ያልጠበቁትና ለመሸነፋቸውም ዋነኛው ምክንያት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና በጦርነቱ ወቅት የተስተዋለው የሕዝቡ የአንድነት ስሜት ለኢትዮጵያ መንግሥትም አስገራሚ እንደነበርና መንግሥት በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የተነሳ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶት ያልነበረውን የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ማንነት ማስተዋሉን ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ፡፡ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ምን እንደሆነችና ምን ልትሆን እንደሚገባት ለመንግሥት አዲስ ዕይታ እንደፈጠረለትም ፕሮፌሰሩ ይጠቁማሉ፡፡ 
ከጦርነቱ በተጨማሪ በ1993 ዓ.ም. በኢሕአዴግ በተለይም በሕወሓት የተከሰተው የመከፋፈል አደጋ በኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥትን ለመጀመር ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ፡፡ በአቶ መለስ ይመራ የነበረው ቡድን በጥቂት ብልጫ አሸናፊ ቢሆንም፣ የፓርቲውን የቀደመና የመጀመሪያ የቡድን አንድነት ያፈረሰ ስለነበር አሸናፊው ቡድን የራሱን የለውጥ ሐሳብ በአገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ላይ ለመጫን ነገሮች ቀላል እንደነበሩለት ፕሮፌሰር ክላፓም አመልክተዋል፡፡ 
ሦስተኛው ምክንያት የ1997 ዓ.ም. ምርጫ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ፡፡ በምርጫው ኢሕአዴግ አለኝ ብሎ ያስብ የነበረውን የሕዝብ ድጋፍ የፓርቲው ፕሮግራም እንዳላመጣ መረዳቱን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ዙሪያ የተደራጀው ቅንጅት ያገኘው አገር አቀፍ ድጋፍ ኢሕአዴግ ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን እንዲከልስ ማስገደዱን አስረድተዋል፡፡ 
ሌላው ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥትን ርዕዮተ ዓለም እንድትቀበል ያስቻለው ምክንያት የአቶ መለስ ዜናዊ የግል ባሕሪ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹መለስ በባድመ መያዝ ወቅትና በምርጫ 97 ወቅት ትልቅ ስህተት መሥራቱን አምኖ ነበር፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ባሉ የተግባር ተሞክሮዎች መለስ ስህተቶቹን መልሶ የማጤንና አስፈላጊ ሲሆን የመቀየር የተለየ ክህሎት ነበረው፡፡ የተፈጠሩ ስህተቶችንና ክፍተቶችን ለመድፈን ምንጊዜም ዝግጁ ነበር፡፡ ከላይ ለገለጽኳቸው ስህተቶች መለስ እንደ መፍትሔ ያቀረበው አገሪቷን በ‹‹ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት›› አቅጣጫ እንድትታደስ ማድረግ ነበር፡፡ የአዲሱ አቅጣጫ ዋነኛ ዓላማ በመንግሥት ሥር ያለውን የአገሪቷን ሀብት በሙሉ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሻሻል ማዋል ላይ ነው?›› ብለዋል፡፡
የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም መሠረቱ የተጣለው በማርክሲስታዊና ሌኒኒስታዊ ርዕዮተ ዓለምን በተከተሉ አገሮች ሳይሆን በካፒታሊስት አገሮች እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ ርዕዮተ ዓለሙ የተፋጠነ ልማት ለማምጣት ጠንካራ መንግሥት ያለውን መጠነ ሰፊ ሚና እንደሚቀበልም አመልክተዋል፡፡ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ከዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ አገሮች በአንፃራዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታና በወጪ ንግድ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚገደዱ አስረድተዋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በመንግሥትና በግል ዘርፉ አንፃራዊ ሚና ዙሪያና በልዩነቱ መስመር ዙሪያ መጠነ ሰፊ ክርክር እንደሚያደርጉም አስታውሰዋል፡፡ 
በልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም መንግሥታት ሕዝባዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ግዴታዎች ስላሉባቸው መሠረታዊ ልማት፣ ትምህርት፣ የመንገድ ግንባታ፣ ሆስፒታል፣ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠር ማዕቀፍ ለምሳሌም የምንዛሪ አስተዳደር ማቋቋም፣ የሠራተኞች ጉዳይ መቆጣጠር፣ ኢንቨስትመንት የሚስቡና ወጪ ንግድ ተኮር ምርቶችን የሚያመርቱ ኮርፖሬሽኖችን የማበረታታት ኃላፊነት እንደሚወስዱ ፕሮፌሰር ክላፓም ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና በተለይ የመንግሥት ኮርፖሬሽኖችን የመምራት ጉዳይ ላይ የተለያዩ ልማታዊ መንግሥታት የተለያዩ ባሕሪ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ስኬታማ ልማታዊ መንግሥታት ከግል ኮርፖሬሽኖች ጋር መሥራትን እንደሚመርጡም አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ስኬታማ አገሮች የግል ተቋማቱ የሚመሯቸው ኮርፖሬሽኖች ከማዕከላዊ የፖለቲካ አመራሩ ጋር ግንኙነት ቢኖራቸውም ኮርፖሬሽኖቹ ስኬታማ፣ ዘላቂና የወጪ ንግድ ተኮር እንዲሆኑና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያሸጋግሩ ጫና ያደርጉ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡ 
በበርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቦትስዋና እንደ ልማታዊ መንግሥት የምትታይ ቢሆንም፣ ፕሮፌሰር ክላፓም ግን በአፍሪካ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ከዚህ ቀደም አለመሞከሩን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃና በግብርና ላይ የተመሠረቱ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ልማታዊ መንግሥትን መሞከር አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ የእስያ አገሮች ርዕዮተ ዓለሙን ሲጀምሩት የተነሱት ከሰፋፊ የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ 
ልማታዊ መንግሥትን በርካታ ብሔሮችና ባሕሎች ባሉበት አገር መፍጠርም ተግዳሮቶች እንዳሉት የጠቀሱት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ የእስያ ታይገር አገሮች የነበራቸው ባሕላዊ አንድነት የአገር ሀብትን ለማንቀሳቀስ፣ የሕዝብን ስሜት ለመቀስቀስና ማኅበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር አመቺ እንደነበርም አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምን ከመቀበሉ በፊት ብዝኃነትን ከማበረታታትም በላይ ተቋማዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው አድርጎ እንደነበር የጠቆሙት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ ይህ የራሱ ተግዳሮት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ልማታዊ መንግሥት በተሳካ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከናወነ ግን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ፕሮፎሰር ክላፓም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አንደኛ የመንግሥትን ሥልጣን ያጠናክራል፡፡ ሁለተኛ ዜጎች ርዕዮተ ዓለሙ መጀመሪያ ላይ የሚፈጥራቸውን ለውጦች ከተቋቋሙ ተጨባጭ ጥቅሞች ያገኛሉ፡፡ ሦስተኛ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ስኬቶችን የመስማት ከፍተኛ ጉጉት ካላቸው የውጭ ለጋሽ ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ያስችላል፡፡ እርግጥ እነዚህ ተቋማት ከቀረፁት የዋሽንግተን ስምምነት አንፃር የኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ሞደል ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የራሱ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ያሉት መሆኑና እንደ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችን ማሳካት ዓይነት ውጤት ማስመዝገቡ በጣም የሚበረታታ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ፌዴራሊዝምና ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ
ኢሕአዴግ የመሠረተው የፌዴራል ሥርዓት ከልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ጋር በግልጽ የሚጋጭ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ክሳፓም፣ የፌዴራል ሥርዓቱ የመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ ከሥር እንዲነሳ የሚያበረታታ መሆኑንና በአንፃሩ ልማታዊ መንግሥት ቁልፍ የመንግሥት ውሳኔዎች በተለይም ከኢኮኖሚያዊ አመራር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በማዕከላዊ መንግሥት እንዲወሰን እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ግብርና ላይ ጥገኛ በሆነ አገር ማዕከላዊ መንግሥት ወሳኝ ዘርፎችን በቁጥጥሩ ሥር እንደሚያውልም ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ የመሬት ቁጥጥርና ክፍፍል ዋነኛው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እንኳን በሕገ መንግሥት ደረጃ መሬት ማከፋፈልን ለክልሎች የሰጠችው ኢትዮጵያ፣ ሌሎች የፌዴራል አገሮችም በመሬት ጉዳይ ላይ ወሳኝነትን ለክልሎች ይሰጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት የተመሠረተው በቀድሞው አገዛዝ በደል የደረሰባቸውን ክልሎችና ብሔሮች ለመካስ ቢሆንም፣ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ይህን ሒደት ለማዕከላዊ የፌዴራል መንግሥት በመስጠት ሊያናጋው ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ የአሁኑ መንግሥት ፌዴራሊዝም ይቀርፈዋል ያለውን ችግር መልሶ የመቆስቆስ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያመጣ ያሰጋል፡፡››
ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሒደት ለዜጎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የመንቀሳቀስ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ያስገነዘቡት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ በኢትዮጵያ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አጋጣሚ የሚፈጥሩ አካባቢዎች በፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አካባቢዎች አለመሆናቸው ሌላ ችግር እንዳለው አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት ፕሮግራሞችም በእነዚህ አካባቢዎች እንዳልተወሰኑ ጠቁመው፣ ዘመናዊ እርሻዎች ለዓለም አቀፍ ገበያ ምርት እንዲያመርቱ እየተደረገ ያለውና መሬታቸውን የተሻለ ምርታማ እንዲያደርጉ አጋጣሚ የተፈጠረላቸው አካባቢዎች፣ ወደ አገሪቱ ዘግይተው የተቀላቀሉና በአገሪቱ ቆላማ አካባቢና ዳርቻ ላይ የሚገኙ ጥቂት ነዋሪዎች ያሉባቸው እንደ ጋምቤላ ያሉ አካባቢዎች እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አካባቢዎቹን ‘ድንግል መሬቶች’ እያለ እንደሚጠራቸው የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ነባር ነዋሪዎቹ መሬቱን ለራሳቸው ጉዳይ መጠቀማቸውን እንኳን ዕውቅና እንዳልሰጠ ተችተዋል፡፡ ዘመናዊ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችም ልክ በንጉሡ ጊዜ ይደረግ እንደነበረው ለውጭ ባለሀብቶች መሰጠታቸውንም አስረድተዋል፡፡ መሬቶቹ ‘ጥቅም ላይ ያልዋሉ’ ወይም ‘በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ’ እንደሚባሉ ያስታወሱት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ አባባሉ የተሳሳተ መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ የሰፋፊ መሬቶች ፕሮጀክት በአፍሪካ ስኬታማ አለመሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ክላፓም፣ መሬቶቹ ለችግር የተጋለጡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ነዋሪዎች መብቶች ጋር የተጣጣሙ እንዳልሆኑም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ የ1987 ዓ.ም. የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሬት የማከፋፈል ሥልጣን የክልሎች መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይሁንና ለውጭ ባለሀብቶች መሬት የሚያከፋፍለው በአብዛኛው በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር የሚወከለው የፌዴራል መንግሥት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የመፍትሔ ሐሳቦች
ሁለቱን የሚጋጩ ርዕዮተ ዓለሞች ለማስታረቅ ፕሮፌሰር ክላፓም የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሰጡ ሲሆን፣ ዋነኛው ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊደረግ የሚገባው የምክክርና የአካባቢ ነዋሪዎች ተሳትፎ አለመረጋገጡ ላይ መንግሥት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የቀደመው የነባር ነዋሪዎች አኗኗርና መንግሥት በሚፈጥረው አዲስና እንግዳ የሆነ አኗኗር መካከል የሽግግር ጊዜ ሊኖር እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡ 
የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከአራቱ ክልሎች ብቻ በመሆናቸው በብሔሮች መካከል የመበላለጥና የሥልጣኔ ደረጃ ልዩነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ሁሉም በእኩልነት አባላት እንዲሆኑ ቢደረግ መልካም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 
የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ከልማታዊ መንግሥትጋር ማጣጣም በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጋር ለማሠለፍ የሚደረገው ጥረት የምርት ኃይሎችን እርስ በርስ በማስተሳሰር ብቻ ሊሳካ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህን ለመፈጸም ትስስሩ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ብሔርና ክልል ተኮር ከሆነው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ጋር ይጋጫል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ 
ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፓም የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት እንዲፈርስ ፍላጎት እንደሌላቸው ቢጠቁሙም፣ ውሳኔ አሰጣጡ ቅድሚያ ለክልሎች መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ይህ ግን በሒደት ወደ እኩልነት ላይ የተመረኮዘ አንድነት በማምራት ሊታገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በቅርቡ የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን መምጣትም አገሪቱ ወደዚህ አቅጣጫ እየሄደች መሆኑን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም ከወላይታ ብሔር መገኘታቸውና ፕሮቴስታንት መሆናቸው የሚያሳየው በቀድሞው ጊዜ የማይታሰቡ የብሔራዊ አመራር ዕድሎች ለሁሉም ዜጎች ዛሬ መፈጠራቸውን ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ከነችግሮቿ ዛሬም እንዳምንባት የሚያደርግ ክስተት ነው፤›› ብለዋል፡፡