POWr Social Media Icons

Wednesday, September 11, 2013

የሲዳማ ክልል ጥያቄን ተከትሎ በዞኑ ብሎም በዓለም ኣቀፍ ደረጃ የተነሳውን ህዝባዊ ንቅናቄ ለመቀልበስ በኣቶ ሽፈራው ሽጉጤ የተመራው የክልሉ እና የዞኑ ኣስተዳደር በንጽሃን የሲዳማ ተወላጆች ላይ ያደረሰው የሰብኣዊ መብት ረገጣና እስር በሪፖርተር ጋዜጣ የ2005 ዓበይት የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ኣልተካተተም። ጋዜጣው በኣገሪቱ በተከሰቱ ኣበይት የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያቀረበውን ዘገባ ከታች ያንቡ፦
በ2005 ዓ.ም. የተከሰቱ ዓበይት የፖለቲካ ጉዳዮች በዋነኛነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሹመት፣ ከሙስሊሞች ጥያቄ መባባስ፣ ከሙስና ተጠርጣሪዎች የፍርድ ሒደት፣ ከመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ፈተናዎች፣ ከኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
የሥልጣን ሽግግርና የመንግሥት የመዋቅር ለውጥ
የቀድሞውን ሊቀመንበር ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ ኢሕአዴግ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ አቶ ኃይለ ማርያምን አዲሱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ በዚሁ የኢሕአዴግ ስብሰባ ፓርቲው የመንግሥት ኃላፊዎች የሆኑ አባላቱ የሥልጣን ዘመን በአሥር ዓመት መገደቡንና የዕድሜ ጣሪያውም 65 ዓመት መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ከሆኑ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይጠበቁ የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ፓርላማው በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጋቸው መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡
ሕወሓት በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት የመረጣቸው አቶ ዓባይ ወልዱና ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል የኢሕአዴግ የንደፈ ሐሳብ መጽሔት የሆነው አዲስ ራዕይ፣ በ2001 ዓ.ም. ሐምሌ ወር እትሙ ካስቀመጠው የመተካካት ፖሊሲና በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ከፍተኛ አመራሮችን የማሰናበት ዕቅድ ጋር አብሮ እንደማይሄድም የተዘገበው በወርኃ መስከረም ነበር፡፡ ወሩ ከመገባደዱ በፊት ኦሕዴድ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ጁነዲን ሳዶን የግል የሃይማኖት እምነታቸውን ከመንግሥት ሥራ ጋር በመቀላቀል ገምግሞ ከኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚነት አግሏቸዋል፡፡ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመንግሥትን መዋቅር መለዋወጥ የጀመሩት ኅዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት የመንግሥት ዘርፍ (ክላስተር) ያስተዋወቁ ሲሆን፣ የሦስቱን ዘርፎች የሥራ ኃላፊዎች ሹመትም በፓርላማው አፀድቀዋል፡፡ መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ደመቀ መኮንን የማኅበራዊ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙት ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤልና አቶ ሙክታር ከድር ደግሞ በቅደም ተከተል የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍንና የመልካም አስተዳደር ዘርፍን በበላይነት እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ዲፕሎማሲ፣ ደኅንነት፣ መከላከያና ከፍተኛና ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡ በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቶ ሙክታር ከድርን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርነት፣ የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ የአቶ ከበደ ጫኔን የንግድ ሚኒስትርነትና የዶ/ር ከሰተ ብርሃን አድማሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ሹመት በፓርላማው አፀድቀዋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙት የክላስተር ኃላፊዎች ጉዳይ የሕግ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አንድምታ ለወራት የመወያያ አጀንዳ ሆኖም አልፏል፡፡ 
ለወትሮው በዝምታ የአስፈጻሚውን ሰነዶች በማፅደቅ የሚታወቀው ፓርላማ ከጥር ወር ጀምሮ በተነቃቃ መንፈስ ሥራውን በሕጉ መሠረት ማከናወን ጀምሯል፡፡ በጥር ወር ፓርላማው በተጓተቱ መንገዶች ግንባታ ዙሪያ የትራንስፖርት ሚኒስትሩን አፋጧል፡፡ በሚያዚያ ወር ደግሞ የሴቶች፣ የሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ የፓርላማ አባላቱ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡ በግንቦት ወር በቀረቡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ሪፖርትና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ በጥናት ላይ የተመረኮዙ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ ከሥልጣናቸው የተነሱት ከፓርላማ ሪፖርት ሲመለሱ ነበር፡፡ ይሁንና ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የፓርላማ አባላት በንቃት የተሳተፉት የፌዴራል ዋናው ኦዲተር የ2004 ዓ.ም. ሪፖርት በቀረበበት የሚያዚያ ወር ነበር፡፡ ባልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብርና ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ በተከፈለው የ897.5 ሚሊዮን ብር ክፍያ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ አባላቱ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ 
ቀስ በቀስ እየተለወጠ የመጣው ኢሕአዴግ በየካቲት ወር ለአዲስ አበባ ምርጫ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን አቶ ድሪባ ኩማን፣ አቶ ተፈራ ደርበውን፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌንና አቶ ወርቅነህ ገበየሁን እንዲሁም ወ/ሮ አዜብ መስፍንን በዕጩነት ማቅረቡን ያስታወቀው፡፡ 
መጋቢት 14 በተጀመረውና በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው 9ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ሕወሓትና ኦሕዴድ ወሳኝ ነባር አመራሮችን የሸኙበትን አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር፡፡ ሕወሓት ከነባር አመራሮቹ መካከል አቶ ሥዩም መስፍን፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ዘርአይ አስገዶምና አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በገዛ ፈቃዳቸው ከማዕከላዊ ኮሚቴ ሲለቁ፣ ድርጅቱ ሕሽ ለማን፣ መሠረት ገብረ ማርያምን፣ መንግሥተ አብ ገብረ ኪዳንን፣ ደስታ በዛብህንና ንጉሠ ገብረን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አሰናብቷል፡፡ አቶ ፀጋዬ በርሔንና አቶ አባዲ ዘሙን ደግሞ ከሥራ አስፈጻሚነት አንስቷል፡፡ ብአዴን በበኩሉ አቶ ብርሃን ኃይሉንና አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንን ከሥራ አስፈጻሚነት ሲያነሳ፣ ድርጅቱን ከትጥቅ ትግሉ መጠናቀቅ በኋላ የተቀላቀለው ደኢሕዴግ በአመራሩ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አላደረገም፡፡
በሰኔ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ተንታኞች ገለጻ ከሆነ በዕለቱ ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጧቸው ማብራሪያና ምላሾች ወንበራቸውን በቶሎ እየለመዱት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ አስቀድሞ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነታቸው ጨምሮ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመንግሥትን መዋቅር እንደገና የማዋቀር ሥራቸውን በሰኔ ወር አጠናክረው የቀጠሉበት ሲሆን፣ ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. በርካታ አዲስ ተሿሚዎችን ለፓርላማው አቅርበው አፀድቀዋል፡፡ አቶ ሬድዋን ሁሴን በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት፣ አቶ ጌታቸው አምባዬ በፍትሕ ሚኒስትርነት፣ አቶ ሽፈራው ሸጉጤ በትምህርት ሚኒስትርነት፣ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በትራንስፖርት ሚኒስትርነት፣ አቶ አህመድ አብተውን በኢንዱስትሪ ሚኒስትርነት፣ አቶ መኮንን ማንያዘዋል አዲስ በተቋቋመው ብሔራዊ ፕላኒንግ ኮሚሽን ኮሚሽነርነት፣ አቶ በለጠ ታፈሰ አዲስ በተቋቋመው የአካባቢና የደን ሚኒስትርነት፣ አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ኩማ ደመቅሳ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በሐምሌ ወር ደግሞ አቶ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነዋል፡፡
የሙስሊሞች ጥያቄ
በመንግሥትና በኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ላይ ጥያቄያቸውን በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ያነሱ የተወሰኑ የሙስሊም ማኅበረሰቦች በ2005 ዓ.ም. ጥያቄያቸው ተጠናክሮ የቀጠለበት ዓመት ነበር፡፡ በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በአወሊያና በአንዋር መስጊድ ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ የተጠረጠሩትና በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሙስሊሞች መከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ለማቅረብ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ተፅዕኖ መፍጠራቸውን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳሳተ መሆኑን የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያስታወቀውና በሕጉ መሠረት መያዛቸውን የገለጸው በወርኃ መስከረም ነበር፡፡ 
የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ ከመስከረም 8 ቀን ጀምሮ በዝግ ችሎት እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይሁንና መንግሥትና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፍርድ ቤት በተያዘው ጉዳይ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን በዶክመንተሪ ፊልም፣ በሰላማዊ ሠልፍና በግልጽ የክርክር መድረክ ላይ ሐሳባቸውን እየገለጹ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቱ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ጫና ያገናዘበ አለመሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኢሕአዴግና መንግሥት ዶክመንተሪው በስፋት የተሠራጨውን የተሳሳተ መረጃ ለማስተካከል፣ ተጨማሪ የሽብር ተግባርን ለመከላከል ካለው ጠቀሜታ አኳያ፣ የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ከመሆኑ አኳያ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ ተመሳሳይ ዶክመንተሪ መሥራት የተለመደ በመሆኑ የፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር ገልጸው ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን፣ የመብት ጥሰት ጥያቄ በማቅረባቸው መታሰራቸውንና መከሰሳቸውን ሲገልጹ ነው የነበሩት፡፡ የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚዎቹ ስህተት የአንዳቸውን ድርጊት ትክክል እንደማያደርገው አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ 
ከሙስሊሞቹ መሠረታዊ ሦስት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የሆነው የአዲሱ የመጅሊስ ምክር ቤት ምርጫ መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ መጅሊሱ በምርጫው ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሙስሊሞች በመሳተፋቸው ምርጫው የተሳካ መሆኑን ቢጠቁምም፣ በምርጫው ዕጩ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ምሁራን በመንግሥት በመታሰራቸው የተነሳ የመራጩ ቁጥር በጥቂት ሺዎች ብቻ እንደነበር የገለጹ ተቃዋሚዎች ዓመቱን ሙሉ የአደባባይ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ከርመዋል፡፡ በጥቅምት ወር በደቡብ ወሎ ገርባ በተከሰተ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ›› በሚል ተደራጅተው የሽብር ዓላማን የሚያስፈጽም ኮሚቴ በማቋቋም በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት መንቀሳቀሳቸውን ያትታል፡፡
የተቃውሞ ሠልፉ ተሳታፊዎች በቅድሚያ መንግሥት አወሊያ እስላማዊ ትምህርት ቤትና መጅሊስን ጨምሮ በእስልምና ሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ እንዳይገባና የመጅሊስ ምርጫ እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን፣ ምርጫው ከተደረገ በኋላ የምርጫውን ፍትሐዊ አለመሆን በመቃወምና የታሰሩ ‹‹የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተወካዮች›› ይፈቱ፣ የአህባሽ አስተምህሮ በሙስሊሞች ላይ መጫን የለበትም በሚል ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ መንግሥት የተቃውሞ ሠልፉ ተሳታፊዎችን በአክራሪነትና በሽብርተኝነት በመክሰስ፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንፃር ተቃዋሚዎቹ አናሳ መሆናቸውንም ይገልጻል፡፡ መንግሥት በኦሮሚያ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኘው ኮፈሌ ከተማ ፖሊስ ለመግደል ሙከራ አድርገዋል ያላቸውን የሦስት ተቃዋሚዎች ሕይወት ማጥፋቱን አምኗል፡፡ መንግሥት በደሴ ከተማ ሼክ ኑሩ ይማም በአክራሪዎች መገደላቸውንም አስታውቆ ነበር፡፡ ነሐሴ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በተከበረው በኢድ አል ፈጥር በዓል ሠልፈኞቹ ግጭት በመፍጠራቸው በርካታ ሰዎችም ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ ከበዓሉ አንድ ሳምንት አስቀድሞ በዓርብ ተቃውሞ ሠልፍ ላይ አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ባንዲራን ሲያቃጥል የሚያሳይ ምሥል በኢቲቪ የተላለፈ ቢሆንም፣ የተቃውሞ ሠልፉ ተሳታፊዎች ግለሰቡ የመንግሥት ተወካይ መሆኑን በመግለጽ ተጠያቂ አይደለንም ብለዋል፡፡
መንግሥት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል ከሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር ከነሐሴ 21 እስከ 23 በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባካሄደውና ‹‹ሃይማኖቶች አብሮ የመኖር እሴት በማጎልበትና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንረባረባለን›› በሚል መሪ ቃል ስብሰባ በማድረግ፣ በስብሰባው መገባደጃ ጽንፈኝነትና አክራሪነትን ለመቃወም ትልቅ ሠልፍ በአዲስ አበባ በጠርቷል፡፡ መንግሥት የተወሰኑት ሙስሊሞች ጥያቄ የእምነት ጥያቄ ሳይሆን እምነትን ከለላ ያደረገ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑን በስብሰባውና በተቃውሞው ሠልፍ ላይ መንግሥት ገልጿል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሁሉም ቅሬታ አቅራቢዎች አክራሪ እንደሆኑ አድርጎ መንግሥት ማቅረቡ ዋጋ እንዳያስከፍለው ያላቸውን ሥጋት ሲገልጹ ነው ዓመቱ የተገባደደው፡፡ መንግሥት ግን አማኞችን ከአክራሪዎች ለመነጠል ችያለሁ ብሏል፡፡
የከባድ ሙስና ክሶች
በኅዳር ወር የሕዝቡ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ኃላፊነቱን በማይወጣ ባለሥልጣን ላይ ፓርላማው ዕርምጃ ለመውሰድ ግፊት እንደሚያደርግ ሲገልጹ ማንም ይህ ጉዳይ እስከየት ድረስ እንደሚጓዝ መገመት አይችልም ነበር፡፡ በታኅሳስ ወር ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክት ግዥዎችን እንደሚመረምር ማስታወቁና ጠቅላይ ማኒስትሩ ‹‹የመንግሥት ሌቦች››ን ሕዝቡ በማስረጃ ካጋለጠ በግላቸው ለመከታተል ቃል መግባታቸው በበዓለ ሲመታቸው ላይ በግብርና በታክስ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በመንግሥት የዕቃ ግዥ ላይ የሚፈጸሙ ሙስናዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊነታቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በኃላፊነት በመጠየቅ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ለውጥ ለማምጣት ቃል ከገቡት ጋር ሲጣመር፣ በታላቅ የሙስና ተግባሮች ላይ መንግሥት አንድ ነገር ለማድረግ ማሰቡን የጠቆመ ነበር፡፡ በዘጠነኛው የኢሕአዴግ ጉባዔም ላይ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የሙስና ጉዳይ አንድ አጀንዳ ነበር፡፡ 
በጥር ወር የዓለም ባንክ ጥናት የቴሌኮም ዘርፍ ለከፍተኛ ሙስና መጋለጡን የጠቆመ ሲሆን፣ የልማት አጋሮችም በወርኃ ሚያዚያ የኢትዮጵያ የፋይናንስ አስተዳደር ሊሻሻል እንደሚገባና የኦዲት ቁጥጥርና የግዥ ሥርዓቱ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውንም ጠቁመው ነበር፡፡ ይሁንና የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ጋር በመተባበር ሃያ አራት በከባድ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለሥልጣንና ነጋዴዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ የተገለጸው በግንቦት ወር ነበር፡፡ የባለሥልጣናቱና ታዋቂ ነጋዴዎቹ ቁጥር በኋላ ላይ የጨመረ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቱ ሒደት ከምስክሮቹ፣ ከሥነ ሥርዓት ሕግና ከማስረጃ አቀራረብ አኳያ ጥያቄዎች እየቀረቡበት ነው፡፡ ሒደቱ ተጨማሪ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመጥለፍ የአሁኑ የክስ ሒደት ከፖለቲካ ስሌት የፀዳ የፀረ ሙስና ትግል መሆኑን ሕዝቡን የማሳመን ሥራ እንደሚጠብቀው አስተያየት ሰጪዎች በስፋት ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ በግንቦት ወር ፓርላማው የገንዘብ ብክንትና ዝርክርክነት የሚታይባቸውን ተቋማት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ፣ በሰኔ ወር ደግሞ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያካትት በግሉ ዘርፍ ላይ ፀረ ሙስና ትግል ሊጀምር መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡
የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ፈተና
በወርኃ መስከረም ኢዴፓ፣ ሰማያዊና አንድነት ፓርቲዎች ኢሕአዴግ በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ ምኃዳሩን እንዲያሰፋ ጠይቀው ነበር፡፡ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ወደ ኢትዮጰያ ፖለቲካ መቀላቀሉን በዚሁ ወር ነበር ያስታወቀው፡፡ በመስከረም ወር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ጥያቄ ሲያቀርብ ኢዴፓ፣ ኢራፓና መድረክ ስምምነታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ወሩ የተጠናቀቀው የኦብኮ ሊቀመንበር በፍርድ ቤት የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸው ነው፡፡ በጥቅምት ወር ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁ ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም እንደሌላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትና የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት አቶ በቀለ ገርባና ሌሎቹ ስምንት ሰዎች በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ 
በኅዳር ወር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም. በሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫ ዙሪያ መወዛገብ መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡ ፓርቲዎቹ ለምርጫ ቦርድ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ በሚያዚያ ወር ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉም አስታውቀው ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ ላይ ሚስጥራዊ ያሉዋቸውን ሰነዶች ይፋ ያደረጉት በታኅሳስ ወር ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የኢሕአዴግ ዕጩ ሆነው የተወዳደሩበትን ሰነድ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለኢሕአዴግ የአባልነት መዋጮ የከፈሉበት ሰነድና አንድ ለአምስት የተባለው የኢሕአዴግ አደረጃጀት ለምርጫ ቅስቀሳ እየዋለ መሆኑን በማቅረብ ለቦርዱ ቅሬታ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በየካቲት ወር ኢዴፓ በአዲስ አበባ የምክር ቤት ምርጫ በአንድ ዕጩ ብቻ እንደሚወዳደር ያስታወቀ ሲሆን፣ በዚሁ ወር በኢሕአዴግ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለገሰው ሁለት ሚሊዮን ብር ውዝግብ አስነስቶ ነበር፡፡ በመጋቢት ወር ከተካሄደው ምርጫ ውጪ በጣሊያን ሐውልት የተሠራለትን ግራዚያኒን የተቃወሙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ታስረው ተፈትተዋል፡፡
በግንቦት ወር ደግሞ አንድነትና መድረክ የአካሄድ ልዩነት እንዳላቸው ይፋ ሆነ፡፡ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. የተካሄደው የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሠልፍ ከምርጫ 97 በኋላ የተካሄደው የመጀመሪያ ሰላማዊ ሠልፍ በመሆን ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ቁጥሩ ላይ በፓርቲውና በመንግሥት መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ ቢሆንም ሰላማዊ ሠልፉ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ በሰኔ ወር የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ፊርማ አሰባስቦ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን የማሰረዝ ዕቅድ እንዳለው ሲያስታውቅ፣ በነሐሴ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከ‹‹ጽንፈኞች›› ጋር እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉዋቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስጠንቅቀው ነበር፡፡ አንድነት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማስጠንቀቂያ ሕገ ወጥነት በመጠቆም ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ 
ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 26 ቀን በተካሄደው የሃይማኖት ጉባዔ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የራሱን ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ በመሞከሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለሰዓታት መታሰራቸውንና መደብደባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ መንግሥት ፓርቲው ሕገወጥ ስብሰባ ለማድረግ መሞከሩን አስታውቋል፡፡ ፓርቲው በበኩሉ ቀድሞ ስብሰባውን ማስታወቁን ገልጿል፡፡ ከነቅሬታዎቹ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጓቸውን ውይይትና ክርክሮች ኢቲቪ ለማስተናገድ የተሻለ ሥራ የሠራበትም ዓመት ነው፡፡ በሥራ ፈጠራ፣ በህዳሴ ግድቡና በፀረ ሽብረተኝነት ሕጉ ላይ የተደረጉት ክርክሮች የፓርቲዎቹን የፖሊሲና የስትራቴጂ ልዩነት ለሕዝቡ ለማሳየት ትልቅ ሚና ከመጫወታቸው አኳያ፣ በቀጣዩ ዓመት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተመሳሳይ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብዙዎች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ስኬቶች ለማስቀጠል ደፋ ቀና ሲሉ የቆዩበት ዓመት ነበር፡፡ በተለይ በግብፅ ጉዳይ ላይና በህዳሴው ግድቡ ግንባታ ዙሪያ ዓመቱ በከባድ ፈተናዎች ያለፉበት ነበር፡፡ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳንና ከጂቡቲ ጋር የተሳካ ግንኙነት የፈጠሩት አቶ ኃይለ ማርያም ከኤርትራ ጋር ግን ወደፊትም ወደ ኋላም ሳይሉ ዓመቱ ተጠናቋል፡፡ በወርኃ መስከረም አይኤምኤፍ የዓባይ ግድብ ግንባታ እንዲቀዛቀዝ የኢትዮጵያን መንግሥት አለማሳሰቡን ገልጾ ነበር፡፡ በዚሁ ወር ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ለማጥቃት ከሱዳን ጋር ተስማምታለች የሚለውንም ዘገባ አስተባብላለች፡፡ በመስከረም ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሰሜንና ደቡብ ሱዳንን የማደራደር የተሳካ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከ4,200 በላይ የሚሆኑ ወታደሮቿንም በአብዬ ግዛት አሰማርታለች፡፡
በጥቅምት ወር በአዲሲቷ የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባለች፡፡ በጥቅምት ወር በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት ያህል አቋርጣው የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከኳታር ጋር ቀጥላለች፡፡ በኅዳር ወር የምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ ሚኒስትሮች ስምምነትን የሱዳንና የኢትዮጵያ መሪዎች አፅድቀዋል፡፡ በዚሁ ወር ኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል በመሆን ተመርጣለች፡፡ በታኅሳስ ወር ከኦብነግ አንጃ ጋር ለመደራደር አዲስ አበባ ላይ ሙከራ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥረቱን እንዲያፋጥን ተሰናባቹ ዳይሬክተር ፓስካል ላሚ የጠየቁት በጥር ወር ነው፡፡ በጥር ወር ኢትዮጵያ የአፍሪካ የእርስ በርስ መገማገሚያ ሪፖርትን ተቀብላለች፡፡ 
በየካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከእንግሊዝ ጋር በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ኢትዮጵያን ለጎበኙት የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክ ክሌግ ገልጸው ነበር፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት በዚሁ በየካቲት ወር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በአንድ የሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ንግግር በመቆጣት ማብራሪያም ጠይቆ ነበር፡፡ በግንቦት ወር ይፋ የሚደረገው የህዳሴው ግድብ ሪፖርት ግንባታውን እንደማያስቆመውም መንግሥት በዚያው ወቅት አስታውቋል፡፡ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ላይ ከውጪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተካሄደውም በዚሁ በየካቲት ወር ነበር፡፡ በመጋቢት ወር መንግሥት መሠረታዊ መብቶችን እንዲያከብር የአውሮፓ ኅብረት የጠየቀ ሲሆን፣ ግብፅ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ እንዳይፀድቅ ዘመቻ ጀምራ ነበር፡፡ በሚያዚያ ወር ቻይና ለህዳሴው ግድብ 1.2 ቢሊዮን ብር ብድር የፈቀደች ሲሆን፣ በግንቦት ወር ደግሞ ለባቡር ፕሮጀክቶች ቻይና፣ ብራዚልና ህንድ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ብር ለኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡ 
በግንቦር ወር ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓልን አስተናግዳለች፡፡ በስብሰባው መጠናቀቂያ ላይ የኅብረቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ አፍሪካውያንን እያደነ መሆኑን ተችተው ነበር፡፡ በዚሁ በግንቦት ወር ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብን የፍሰት አቅጣጫ ለጊዜው መቀየሯን ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ የግብፅ ባሥልጣናት ድርጊቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞች የጦርነት ቅስቀሳ በቀጥታ የቴለቪዥን ሥርጭት እስከመዋልም ደርሶ ነበር፡፡ በሰኔ ወር ደግሞ ሱዳን የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ከግብፅ ፊቷን ስለማዞሯ ተሰምቷል፡፡ በወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሙሐመድ ሙርሲ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ማንኛውንም አማራጭ እንደምትወስድ አስፈራርተው ነር፡፡ በዚሁ ወር የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ለግብፅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ 
በሐምሌ ወር የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ቡድን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ፣ የቃሊቲን እስር ቤት እንዳይጎበኝ መከልከሉንም በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡ በዚሁ ወር ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ማሠልጠኛ በኢትዮጵያ ሊቋቋም እንደሆነም ተገልጾ ነበር፡፡ መንግሥት የህዳሴው ግድብ 23 በመቶ ወጪ በሕዝቡ መሸፈኑንም የገለጸው በዚሁ ወር ነበር፡፡ ከግብፅ ብጥብጥና መፈንቅለ መንግሥት ጋር ተደምሮ ግድቡ ያለችግር መከናወኑ የተፋሰሱ አገሮችም የማዕቀፉን ስምምነት የማስፈረም ሥራ መቀላጠፍ ለኢትዮጵያ እንደ ታላቅ ስኬት ተቆጥሮለታል፡፡ በነሐሴ ወር የሃይማኖት ብዝኃነቷን ለመጠበቅ ነፃነትን እንዳትጋፋ መጠንቀቅ እንደለባት ለኢትዮጵያ ምክር የለገሱት ተሰናባቹ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ናቸው፡፡   
በማደግ ላይ ባሉትም ሆነ በበለፀጉት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ የውኃ አቅርቦት መስተጓጎልና የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ያጋጥማል፡፡ መጠኑና ደግግሞሹ በእጅጉ ሊለያይ ይችላል እንጂ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ እያስነሳ ያሉ የአገልግሎት አቅርቦት መሳከርና መቋረጥ እያጋጠሙ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውኃ ለቀናት መጥፋት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ለሳምንትና ለወር ተቋርጦብናል የሚሉ አሉ፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በቀን ሦስቴና አራቴ ይቋረጣል፡፡ መደበኛ ስልኮች ይቋረጣሉ፣ ሞባይል ስልኮች አይሠሩም፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትም ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ የብሮደባንድ፣ የዋይፋይና የኢቪድዮ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የተለመደ ሆኗል፡፡
ለተፈጠሩት ችግሮች ከአቅም በላይ የሆኑና ያልተገመቱ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ግን ቀርበው በግልጽ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ እስኪስተካከሉ ለሚያጋጥሙ የአገልግሎት መቋረጦች መንግሥት ሕዝቡን  በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ 
በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት የበርካታ ፋብሪካዎች ማሽኖች እየተበላሹና ከባድ ኪሳራ እያስከተሉ ናቸው፡፡ ምርትም እየተቋረጠ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት በርካታ የቤት ዕቃዎች እየተቃጠሉና እየተበላሹ ናቸው፡፡ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖችና የኩሽና ዕቃዎች እየተቃጠሉ ቤተሶበችን ለከፍተኛ ኪሳራ እያደረጉ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ፡፡
በዚህ ሰዓት ኢንተርኔት ከፍቼ መልዕክቶችን አያለሁ የሚል ሐሳብ ተረት ተረት እየሆነ ነው፡፡ በዚህም በርካታ የቢዝነስ ሥራዎች እየተስተጓጎሉ ናቸው፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን በመቋረጡ ምክንያት በርካታ ቢዝነሶች እየተጎዱ ናቸው፡፡
ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ስልክ በሌሉበት ሕመምተኞችንና ሕፃናትን መንከባከብ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ችግር በቀና መንፈስ የሚረዳ ሕዝብ ማብራሪያ ሲያጣ እንዴት ነው ነገሩ የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ 
እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲኖሩ መንግሥት ተገፍቶ ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት ምክንያቱን አጣርቶ ለሕዝብ ማስረዳት አለበት፡፡  ‹‹ኤሌክትሪክ የተቋረጠው ዛፍ ስለወደቀ ነው›› የሚለው ፌዝ ይቅር፡፡ በእውነት ለሁሉም የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ምክንያቱ የዛፍ መውደቅ ነው? የሚወድቁ ዛፎች በኤሌክትሪክ መስመርና በትራንስፎርመር ላይ የሚያደርሱትን ለማወቅ በእውነት ‹‹አስማተኛ›› መሆን ይጠይቃል፡፡
ዛፍ ወድቆ ነው እየተባለ ከመሸፋፈን ይልቅ ሆን ተብሎ የሚፈጸም አሻጥር ካለ መመርመሩ ያስፈልጋል፡፡ በሙስና ምክንያት የማይሠሩ ትራንስፎርመሮች ተገዝተው እየፈነዱ ለመሆናቸው ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ 
ከኃይል ማመንጫዎች ጀምሮ የሚዘረጉት የማስተላለፊያ መስመሮች በጥናትና በባለሙያ መከናወናቸውን ማየትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ችግር ቢኖርም መንግሥት ምን እንዳጋጠመ በትክክል መርምሮና አውቆ ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት፡፡ ስለደረሰው ችግር ሕዝብ የማወቅ መብት አለው፡፡ መንግሥት የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ 
ለሕዝብ መረጃ ከመስጠት ባሻገርም ይቅርታ መጠየቅ የሚባል ጨዋ አሠራር አለ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለተፈጠረ ችግር ይቅርታ መጠየቅ ግዴታም ጨዋነትም ነው፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ይቅርታ ከመንግሥት ሲመጣ ሕዝባዊ ከበሬታ ያስገኛል እንጂ ምንም ጉዳት የለውም፡፡
እስኪሠራና እስኪስተካከል ድረስ ሕዝቡ እንዲታገስ ማሳሰቢያ መስጠት፣ እያደረሰ ላለው ኪሳራና መስተጓጎል መንግሥት ሕዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል መባል አለበት፡፡ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ሲፈጥር ነው የሚከበረውና የሚደመጠው፡፡ 
የቦሌ መንገድ ሲሠራ በተፈጠረው መዘጋጋት ምክንያት ሕዝብ ጥያቄ ያነሳ ነበር፡፡ መንገዱ ተሠርቶ ሲያልቅ ግን የተፈጠረው መዘጋጋት ለአገሩ እንደሆነ አምኖ፣ አሁን ደግሞ ለመጋቢ መንገዶች ግንባታ መንገድ ሲዘጋጋ የአጭር ጊዜ ችግር እንጂ በቀጣዩ ጥሩ ይሆናል እያለ በአዎንታ እየጠበቀ ነው፡፡ እየተባበረ ነው፡፡
ነገር ግን በኤሌክትሪክ፣ በውኃና በስልክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ሲፈጠር ዝም መባል የለበትም፡፡ ሕዝብ  በተለያዩ ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ሆኖ በትዕግሥት እንዲተባበር የችግሮችን ምክንያት የማወቅ መብቱ ይከበርለት፡፡ ለሚደርሰው  ችግርም ይቅርታ ይጠየቅ፡፡   
የጋራ ችግርን በጋራ ለመፍታት ሕዝባዊና መንግሥታዊ የትብብር መሠረት ይፈጥራልና፡፡ የአገልግሎቶች አሰጣጥ ሲቋረጥና ሲሳከር ከመንግሥት ማብራሪያና ይቅርታ ይጠበቃል!