POWr Social Media Icons

Tuesday, July 23, 2013

ሃዋሳ ሐምሌ 16/2005 በደቡብ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት አመት 83 ሺህ 140 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ ገለጸ፡፡ በቢሮው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መላኩ እንዳለ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ቡናው የቀረበው በክልሉ ቡና አምራች ከሆኑ የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ 380 የህብረት ስራ ማህበራትና ከ330 በሚበልጡ የግል ባለሃብቶች እንዲሁም የቡና ተክል ልማት ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡ በዘመኑ ለማዕከላዊ ገበያ ገበያ ከቀረበው ከዚሁ ቡና ውሰጥ 42 ሺህ 189 ቶን የታጠበና ቀሪው 40 ሺህ 951 ቶን ደግሞ ያልታጠበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በስራው ላይም 394 የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ክንውኑ የእቅዱን 68 በመቶ መሸፉኑንና ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ከዕቅዱ ሊያንስ የቻለው ህገ ወጥ የቡና ግብይትና ዝውውር መበራካት እንዲሁም የአለም ገበያ ዋጋ መቀነስና መዋዥቅ ጋር ተያይዞ ቡና አምራቹ ገበሬና አቅራቢው ወደፊት ዋጋው ይጨምራል በሚል በክምችት መያዙ አቶ መላኩ በምክንያትነት ከጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከክልል እስከ ቀበሌ በየደረጃው የተቋቋመው የቡና ጥራትና ንግድ ቁጥጥር አሰተባባሪ ግብረ ሀይል በማጠናከር ህገ ወጥ ንግድ እንዲቆም ለማድረግ በዘመኑ በተካሄደው እንቅሰቃሴ ጀንፈል፣ መርቡሽ፣ እሸት ቡና ጨምሮ ከ21 ሺህ 700 ኩንታል በላይ ቡና ከህገ ወጦች ተይዞ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በህጋዊ መንገድ በመሸጥ ለመንግስት ገቢ መሆኑን የስራ ሂደቱ ባለቤቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሃዋሳ ሐምሌ 16/2005 በኢትዮጵያ ገቢዎችና ግምሩክ ባለስልጣን የሀዋሳ ቅርንጫፍ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ መያዙን አስታወቀ። የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ፈቃደ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአራት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ክምችት ይገኝባቸዋል ተብሎ በተጠረጠሩ ከተሞች በተደረገ ፍተሻ 62 ሚሊዮን 400 ሺህ 986 ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ መድሀኒቶችና ሌሎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል። ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ አዳዲስ አልባሳት፣ አሮጌ ልባሽ ጨርቅና ጫማ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ዘይትና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶች፣ መድሀኒቶች፣ ትምባሆና የትንባሆ ውጤቶች ከፍተኛውን መጠን የያዙ መሆናቸውን አቶ ያሬድ ገልጸዋል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃ መጠን በገንዘብ ሲገመት ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው የተለያዩ ልባሽና አዳዲስ ጨርቆች መድሀኒቶችና የመዋቢያና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መያዛቸውንና ኮንትሮባንድ የመያዝ አቅም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል። የኮንትሮባንድ ወንጀልን ለመቆጣጠር በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ጥምር ኮሚቴ በክልል ደረጃና በክልሉ በሚገኙ አምስት ዞኖችና በምዕራብ አርሲ ዞንና በባሌ ዞን ደረጃ የፀረ ኮንትሮባንድ ጥምር ኮሚቴ ከተዋቀረ ወዲህ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መዳከሙን ገልጸዋል። በግማሽ ዓመቱ ኮንትሮባንድን በተመለከተ ለጽህፈት ቤቱ ከደረሱ ጥቆማዎች ውስጥ አብዛኞቹ ለውጤት መብቃታቸውንና በጥቆማዎቹ መሰረት በተሽከርካሪና በጋማ ከብት ተጭነው ወደ ሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶና ሆሳዕና ከተሞች ሊገቡ የነበሩ የተለያየ መጠን ያላቸው አዳዲስና ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች መያዛቸውን ተናግረዋል። ለኮንትሮባንድ ያዥና ጠቋሚ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ከ11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የውለታ ክፍያ መፈጸሙንና በህገወጥ መንገድ የኮንትሮ ባንድ ዕቃዎችን ጭነው ሲያጓጉዙ የተገኙ ተሽከርካሪዎችና የጋማ ከብቶች ባለንብረቶች ከ8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በቅጣት እንዲከፍሉ መደረጉን አቶ ያሬድ አስረድተዋል። በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ከተያዙት ዕቃዎች ውስጥ ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ለጅንአድ መተላለፉንና ከ9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ልባሽ ጨርቆች፣ ጫማዎችና ሀሽሽ በቃጠሎ እንዲወገድ መደረጉን አስታውቀዋል። በተጨማሪም ተገቢውን የጉምሩክ መመሪያ ተግባራዊ ሳያደርጉ በህገወጥ መንገድ የገቡ ተሽከርካሪዎች ተይዘው በውርስ ለመንግስት ገቢ መደረጋቸውን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=10049&K=1