POWr Social Media Icons

Thursday, July 18, 2013

የሲዳማ ብሔር ተወላጅ የሆኑት አቶ ደሴ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት ከቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ላይ የክልሉን መንግሥት ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡

አቶ ደሴ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማዕከል የሆነውን የደቡብ ክልል ኃላፊነት ሲረከቡ እንደተናገሩት፣ ለሕዝቡ እኩል የልማት ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከርና የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ምንም እንኳን በክልሉ ሴክተር መሥርያ ቤቶች ከዚህ ቀደም ባይሠሩም፣ ከ1996 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም የይርጋ ዓለም ከተማ ከንቲባ፣ ከ1998 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ፣ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ሰኔ ወር ድረስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ ከሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ አዲሱን ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ በባይሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በለውጥ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ደሴ፣ በአዲሱ ሹመት የተሻለ ለውጥ ያስመዘግባሉ ተብሎ እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዞን ደረጃም ሆነ በፌደራል ደረጃ የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ለዚህ ኃላፊነት እንዳበቃቸው በክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ከተሳታፉ ግለሰቦች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡ “አቶ ደሴ በተለይ በሲዳማ ዞን አስተዳዳሪነታቸው ወቅት ባሳዩት አመራር የተነሳ ክልሉን በፍትሐዊነት ያስተዳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤” ሲሉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል ሰባተኛ ጉባዔ ላይ ከተሳታፉ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል፣ የሳይንስና ቴከኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በአቶ ደሴ ላይ ትልቅ እምነት አሳድረዋል፡፡ “አዲስ ከተመረጡት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሠርተናል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሆነው ሳውቃቸው ጥሩ ዕውቀት ያላቸው፣ ሰው አክባሪና የሚሠሩት ጠንቅቀው የሚያውቁ እንደነበሩ እመሰክራለሁ፤” ብለዋል፡፡

ደቡብ ክልል አቶ ደሴን በማግኘቱ ዕድለኛ ነው የሚሉት ዶ/ር አሸብር ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ በሆነው ፓርላማ በነበራቸው ግንኙነት የሥራ ባልደረባና አጋር ሆነው ነበር ያሳለፉት፡፡ ከዚህ አኳያ የሲዳማ ብሔር አባል ቢሆኑም፣ ከዚህ ቀደም አቶ ዓባይ ፀሐዬ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እንደገለጹት አቶ ደሴም ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ካፋ፣ ጋሞ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እሳቸውም በዚያ ዓይነቱ መንገድ የተቀረፁ ናቸውና፡፡ ሁሉንም ብሔረሰቦች በእከኩልነት የሚያዩና ሁሉንም እንደራሳቸው ብሔር አድርገው ማየት የሚችሉ ሰፊና ምሉዕ ሰው ናቸው፤” በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

ዶ/ር አሸብር ቀድሞ ሲል በነበሩት ርዕሰ መስተዳድር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በአቶ ደሴ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ የራሳቸውንም ራዕይና ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህም በአጠቃላይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱን እንደሚያሳኩ ጥርጥር አይኖረውም ብለው፣ “ከምርጫው እነደተረዳሁትና የጉባዔውንም መንፈስ እንዳየሁት የሁሉም ሰው እምነት ይኼ ነው፤” በማለት አስተያየታቸውን አጠናቅረዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የክልሉ ሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ኢሕአዴግ አቶ ደሴን ለዚህ ኃላፊነት በማቅረቡ ምርጫው ትክክል ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከር የተሻለ ግንዛቤና ተነሳሽነት ያላቸው ናቸው ሲሉም ገልጸዋቸዋል፡፡

አቶ ደሴ ሥራቸውን በይፋ ሲጀምሩ እንደተናገሩት፣ በተያዘው የበጀት ዓመት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝልማት ዘርፍ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ከ200 ሺሕ በላይ ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ፡፡ በክልሉ በሚገኙ 14 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጐች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
photo http://www.flickr.com/photos/espsol/sets/72157632677473483/
አዋሳ ሐምሌ 11/2005 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ከ186ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም ትናንት ተጀመረ ። የወጣቶችን የስራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የፕሮግራሙ መጀመር ምክንያት በማድረግ በሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ ትናንት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃለፊ ውይዜሮ ሻሎ ሮርሳ እንደገለጹት የዞኑ ወጣቶች ባለፉት አራት ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደራጀ መንገድ በመሰማራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባሮችን ሲያከናዉኑ ቆይተዋል ። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ወጣቶቹ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን ለአካባቢው ልማት በማዋል መልካም ተግባሮችን ከማከናወናቸዉም ሌላ ከማህበረሰቡ የተለያዩ እሴቶችን የቀስሙበት እንደነበር አስታዉቀዋል ። በዘንድሮም ክረምት ከዞኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር እራሳቸውንና ህብረተሰቡን ጠቅመው የዞኑን ልማት በሚያፋጥኑ የልማት ተግባሮች ለመሰማራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ወይዜሮ ሻሎ አብራርቷል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አክልሉ አዱሎ በበኩላቸው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በከተማው ከተጀመረ ወዲህ ወጣቶች ለልማት ያላቸዉ ተነሳሽነትና ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ በቆይታቸዉ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የጤና፣ የአካባቢ ፅዳትና ውበት፣ የትራፊክ ደህንነት፣ አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት መደገፍ፣ ደም ልገሳን ጨምሮ በአስራ ሶስት ዓይነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ይሰማራሉ ። የደቡብ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት መስቀለ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዜጎች በተለይ ወጣቶች ሁለንተናዊ አቅማቸውን ለማህበረሰብና ለአካባቢው ደህንነትና ልማት በነጻ የሚያውሉበት የተቀደሰ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ የዞኑ ወጣቶች ቀደም ሲልም የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማዋል ተቆጥበው ልማት የሚያጠናክሩና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት ሲያከናወን መቆየታቸውን አመልከተዋል፡፡ በዚህም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልከተው ዘንድሮም በተመረጡና ፋይዳ ባላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልል ደረጃ ከ1ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ሙሉ ተሳታፊ በመሆን ካለፉት ዓመታት የተሻለ ዉጥት እንደሚያስመዘገቡ እምነታቸዉን ገልጠዋል ፡፡ ወጣቶቹ በዚህ ስራ ያሳዩትን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ለማጠናከር በየደረጃ የሚገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ፕሮግራሙ በይፋ ስጀመር ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዕረፍት የተመለሱና በዞኑ ባሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ በርካታ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን በዕለቱም ከ20ሺህ የሚበልጡ ችግኞች ተከላም ተከናውነዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=9838&K=1