POWr Social Media Icons

Friday, July 12, 2013

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5 /2005 (ዋኢማ) -የደቡብ ክልል ምክር ቤት 4ኛ ዙር 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የ2005 በጀት ዓመት አፈጻጸምን ያደመጠ ሲሆን ፥ በ2006 በጀት አመት ጠቋሚ እቅድ ላይ በመወያየት በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳሉት ፥ በክልሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ይቀርብበት የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም ታይቷል።

በክልሉ ሁሉን አቀፍ የቀበሌ መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም ዝቀተኛ አፈጻጸም የታየበት ሲሆን ፥ ቀሪ ስራዎችን በጊዜ ለማጠናቀቅም ተጨማሪ ተቋራጮችን ወደ ስራ አስገብቶ እየተሰራ መሆኑም ነው በሪፖርቱ የቀረበው።

ምክር ቤቱ በክልሉ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይ በክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አማካኝነት የቀረቡ ሪፖርቶችንና የተሰሩ ስራዎችንም አድምጧል።
ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት በሚቀየው ጉባኤ የ2006 አመት በጀትን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪም በነገው ዕለት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር እንደሚሾም ይጠበቃል  ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2005(ዋኢማ) - ኢትዮጵያ ከሐዋሳ ወደ ሞጆ ለሚወስደው ፈጣን (ኤክሰፕረስ)መንገድ ግንባታ ከደቡብ ኮሪያ የጠየቀችውን 700 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአፋጣኝ እንዲለቀቅ የአገሪቱ ፓርላማው አፈ ጉባዔ ግፊት እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠየቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ የተመራውን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንዳሉት በሁለቱ አገሮች መካከል በደም የተሳሰረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በኢኮኖሚና በንግድ መስኮችም ማጠናከር አስፈላጊ ነው። 

ደቡብ ኮሪያ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ረገድ ያላትን ሰፊ አቅም በመጠቀም በቴክኖሎጂና በዕውቀት ሽግግር ለኢትዮጵያ የሚቻላትን ትብብር እንድታደርግ ጠይቀዋል። አቶ ኃይለማርያም ከሐዋሳ ወደ ሞጆ ለሚወስደው ፈጣን መንገድ ወይም ኤክሰፕረስ መንገድ ግንባታና የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ የጠየቀችው ገንዘብ በፍጥነት እንዲለቀቅ የፓርላማው አፈ ጉባዔ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

ከደቡብ ኮሪያ የሚገኘው ብድር አነስተኛ ወለድና በረዥም ጊዜ የሚከፈልበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የኮሪያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ የአገሪቱ ፓርላማ የግፊትና የማግባባት ጥረት እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ ኃይለማርያም የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጊሁን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ኦሽንያ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አረጋ ኃይሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች ምክር ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት፣የአገሮቹ የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር የበለጠ እንዲሻሻልና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር የመንግስታቸው ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል። 

ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የላቀ ግምት እንደምትሰጠው የተናገሩት አፈ ጉባዔው፣ የአገራቸው ባለሃብቶች በቆዳ፣በጨርቃጨረቅ፣በኤሌክትሮኒክስና በሌሎችም መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ግፊት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። 

በሁለቱ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

አገራቸው በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለኢትዮጵያ ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሴዑል በረራ እያደረገ በመሆኑ ደቡብ ኮሪያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል። 

እንደ ኢዜአ ዘገባ አፈ-ጉባኤ ካንግ ቻንግ ሂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደቡብ ኮሪያን እንዲጎበኙ ያቀረቡት ግበዣም ተቀባይነት ማግኘቱን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። 
http://www.waltainfo.com/index.php/2011-09-07-11-53-43/9166-2013-07-11-20-46-43

ቁጠባ የታደጋቸው

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ አራት ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የአንዳንዶቹን ኢኮኖሚ አቅም የማጠናከሩ ሥራ ፍሬያማ ውጤት አስገኝቷል፡፡
በወንዶገነት፣ በይርጋዓለም፣ በአለታ ወንዶና በጩኮ ከተሞች ነዋሪ የሆኑት የእነዚህ ወገኖች ኢኮኖሚ አቅም ሊያንሰራራ የቻለው በቁጠባ ላይ መሠረት ያደረገ ሥልጠና ተሰጥቷቸው በራስ አገዝ የቁጠባ ቡድን እንዲደራጁ፣ ቁጠባ እንዲጀምሩና በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ ነው፡፡ 

በዚህ መልኩ ከተንቀሳቀሱት ወገኖች መካከል በአለታ ወንዶ ከተማ ልዩ ስሙ ዲላ ሠፈር ነዋሪ የሆነው ባሕሩ አወቀ ይገኝበታል፡፡ ባሕሩ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፣ እናቱንና የባለቤቱን እህት ጨምሮ የስድስት ቤተሰቦች አስተዳዳሪ ነው፡፡ “እኔ፣ ባለቤቴና ሌሎች ሁለት ጐረቤቶቼ ሆነን በሳምንት አሥር ብር መቆጠብ ጀመርን፡፡ ቁጠባችን እያደገ መጥቶ ከላዩ ላይ 300 ብር አንስቼ ብስክሌት ገዛሁና ማከራየት ጀመርኩ፤” ይላል፡፡ 

ከዚህም የሚያገኘውን ገቢ አጠራቅሞ መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ መደብር ከፍቶ ቀስ በቀስም የቁም ከብት የማደለብ፣ እንዲሁም በግልና በጋራ የከተማ ግብርና ሥራዎችን እንደተያያዘውና በአሁኑ ጊዜም ከ100 ሺሕ ብር በላይ በባንክ ተቀማጭ እንዳለውም አልሸሸገም፡፡ 

ከዚሁ ከተማ በሸመታና በጉልት ችርቻሮ ኑሮአቸውን ይመሩ የነበሩ 23 ሴቶችም በየወሩ ሦስት ብር፣ ከዛም አሥር ብር በባንክ መቆጠብ እንደጀመሩ፣ ቁጠባቸውም ወደ 260 ብር ከፍ እንዳለና ይህንኑ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው በመቀጠል የቁጠባ መጠናቸው ወደ 15 ሺሕ ብር፣ ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ 34 ሺሕ ብር ከፍ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በዚህም ስኳርና ዘይት የማከፋፈል ሥራ ጀመሩ፡፡ ይህንንም የጀመሩት “ስኳርና ዘይት አከፋፋዮች የራስ አገዝ ማኅበር” በሚል መጠሪያ ተደራጅተው ነው፡፡ የማኅበሩ ፀሐፊ የሆኑት ወይዘሮ በላይነሽ እጅጉ እንደገለጹት፣ ለማከፋፈሉ ሥራ መነሻ የሚሆን መጠነኛ ገንዘብ ያገኙት ከኦሞ ፋይናንስ የብድርና ቁጠባ ተቋም በመበደር ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ብድራቸውንም መልሰዋል፡፡ ዘይትና ስኳር የሚያከፋፍሉበትን አዳራሽ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በነፃ እንዳገኙና ቁጠባቸውንም እንደተያያዙት ነው የተናገሩት፡፡ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው ለመቀጠልና ቢያንስ በክልል ደረጃ ስኳርና ዘይት አከፋፋይ የመሆን ራዕይ እንደሰነቁ ነው ከወይዘሮ በላይነሽ ማብራሪያ ለመረዳት የተቻለው፡፡ 

በጩኮ ከተማ ነዋሪ የሆነችው እመቤት ሀማሮ የተባለችውም ወጣት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ካጠናከሩት ወገኖች የምትጠቀስ ናት፡፡ እመቤት እስከ አሥረኛ ክፍል ድረስ ተምራ ውጤት ስላልመጣላት በሆቴል ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥራ ኑሮዋን መምራት ጀመረች፡፡ “አምስት ሆነን ቁጠባ ጀመርን፣ አራቱ ሲተዉት እኔ ብቻዬን ተያያዝኩት፡፡ በመካከሉ ሦስት ሺሕ ብር ተበደርኩና የፀጉር ሥራ ሥልጠና ተሰጠኝ፡፡ ባገኘሁትም ሥልጠናና በተሰጠኝ ብድር በመታገዝ የሴቶች ፀጉርና የውበት ሥራ የሚል ድርጅት አቋቋምኩ፤” ብላለች፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በ6,500 ብር ልዩ ልዩ ዓይነት የፀጉር መሥሪያ መሣሪያዎችን ገዝታ ድርጅቷን አጠናክራለች፡፡ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ባንክ አስቀምጣለች፣ ለአራት ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥራለች፣ ድርጅቷን ካቋቋመች ሦስት ዓመት እንደሆናትና በየዕለቱ የስምንትና የአሥር ሴቶችን ፀጉር እንደምታስውብ ከዚህም በቀን ቢያንስ 300 ብር፣ ገበያ ካለ ደግሞ እስከ 500 ብር ገቢ እንደምታገኝ ተናግራለች፡፡ 

“የበፊቱ ኑሮዬ እጅግ በጉስቁልና የታጀበና ለጤንነት መታወክ የሚዳርግ ነበር” ያለችው እመቤት፣ አሁን ግን ከዚህ ሁሉ የሰቆቃ ኑሮ ተላቅቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ወገኖች ተርታ ለመሰለፍ በሚያስችላት መስመር ላይ እንደምትገኝ አስረድታለች፡፡ ትዳር ባትይዝም ወላጆቿን እየረዳችና ወንድሞቿንም እያስተማረች እንደምትገኝ፣ የከተማ ቦታ እንደገዛችና በቅርቡም ዘመናዊ የሆነ መኖሪያ ቤት የመገንባት ዕቅድ እንዳላት አመልክታለች፡፡ 

በይርጋዓለም ከተማ አውቶብስ መናኸሪያ ውስጥ 31 የሚሆኑ ጫኝና አውራጆችም በመናኸሪያው ቅጥር ግቢ ውስጥ ካፍቴሪያና የገላ መታጠቢያ ሻወር ቤቶችን በማቋቋም ተጠቃሚ እንደሆኑ ነው የተገነዘብነው፡፡ ከእነዚህም መካከል 16 ጫኝና አውራጆች ካፌ ቤት፣ ሌሎች 15 ጫኝና አውራጆች ደግሞ ሻወር ቤት አቋቁመዋል፡፡ ካፌ ቤት ያቋቋሙት “ስኬት ጎዳና የአስተናጋጆች ማኅበር፣ እንዲሁም ሻወር ቤት የመሠረቱት ደግሞ “የነገ ተስፋ ማኅበር” በሚል መጠሪያ ተደራጅተው ነው፡፡

የስኬት ጎዳና አስተናጋጆች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ቁምላቸው ሞገስ እንዳብራሩት፣ ካፍቴሪያው የተቋቋመው በቅድሚያ እያንዳንዱ ጫኝና አውራጅ በየወሩ 50 ብር እንዲቆጥብ በማድረግ ሲሆን፣ በዚህም አንድ ዓመት ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ስምንት ሺሕ ብር ለመቆጠብ ተችሏል፡፡ በዚህና በብድር በተገኘ ገንዘብ የቡና ማፍያ ማሽን፣ አነስተኛ ፍሪጅና ሌሎች ቁሳቁሶች ገዝተዋል፤ ለካፍቴሪያ የዋለውም ቤት ከመንግሥት በነፃ አግኝተዋል፡፡ 

“የነገ ተስፋ ማኅበር” በሚል መጠሪያ የተደራጁት ጫኝና አውራጆች በ21 ሺሕ ብር ያቋቋሙት ሻወር ቤት ስምንት ክፍሎች ያሉት ሲሆን አገልግሎት የሚሰጠውም የማኅበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ ከዚህም አገልግሎት ማኅበሩ በቀን እስከ 70 ብር ገቢ ያገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማይክሮ ፋይናንስ አሥር ሺሕ ብር፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 14 ሺሕ ብር በድምሩ 24 ሺሕ ብር ቆጥቧል፡፡ 

ቀደም ሲል በቀን ሠራተኝነትና በሆቴል ቤት አስተናጋጅነት ተሰማርተው የነበሩት እነዚህ ወገኖች አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ባስቻላቸው ሥልጠና ላይ በንግድ አማራጮችና በቢዝነስ ቤዚክ ስኬል ማኔጅመንት ላይ ትኩረት ያደረገ መሠረታዊ ዕውቀት ቀስመዋል፡፡ ሥልጠናውን የሰጣቸውና በቡድን እያደራጀ የቁጠባ ባህልን እንዲለምዱ ያደረገው “ኮመን ቪዥን ፎር ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን” የተባለ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ 

የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዮናስ ዓለሙ እንደገለጹት፣ የተጠቀሱት ወገኖች ቁጠባ የጀመሩት በሥልጠናው ወቅት በሽልማትና በአበል መልክ ከተያዘላቸው ገንዘብ ውስጥ 95 ከመቶ ያህሉን እንዲቆጥቡ በማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ የቁጠባን ጠቃሚነት እንዲረዱ ከማድረግ ባሻገር አሁን ለደረሱበትም ደረጃ መሠረት ሆኖአቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት የትራንዛክሽን ፕሮግራም ለድርጅቱ የፋይናንስ፣ የማቴሪያልና የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት የበኩሉን እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡