POWr Social Media Icons

Sunday, July 7, 2013

የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወደ ፌዴራል መንግሥት ሚኒስትርነት መምጣት በደቡብ ክልል ላይ ጊዜያዊ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለክልሉ ፕሬዚዳንትነት የስድስት ግለሰቦች ስሞች እየተነሱ ነው፡፡
ከእነዚህ መካከል ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነታቸው በመነሳት በኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ደሚቱ ሃንቢሳ የተተኩት አቶ ደሴ ዳልኬ አንደኛው ናቸው፡፡ ሌሎቹ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ማርቆስ ተክሌና በአሁኑ ወቅት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የሚያገለግሉት አራት ግለሰቦች ናቸው፡፡ 
እነሱም አቶ ታገሰ ጫፎ፣ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ፣ አቶ ሳኒ ረዲና አቶ ደበበ አሰፋ ናቸው፡፡ ግምት ከተሰጣቸው መካከል የበለጠ ከፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑ ጋር በተደጋጋሚ ስማቸው እየተጠራ የሚገኘው አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ሲሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ አቶ ደሴ ዳልኬ ሊሆኑ ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡
ባለፈው ሐሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የከፍተኛ መንግሥት ባለሥልጣናትን ሹመት በፓርላማ አፀድቀዋል፡፡ የአሥሩ አዲስ ተሿሚዎች ሹመት የፀደቀው በአንድ ድምፅ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ነው፡፡
ተሿሚዎቹ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ አማካይነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ረቡዕ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ኩማ ደመቅሳ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊስ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው መመደባቸው ተገልጿል፡፡ 
በቅርቡ በፓርላማ የትምህርት ሚኒስቴርን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች ከሚኒስትር ጀምሮ እስከታች ያሉ አመራሮችን የወቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ በአቶ ኃይለ ማርያም አዲስ ሹመትና ሽግሽግ ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው ተነስተዋል፡፡
‹‹ከሚኒስትር ጀምሮ ከፍተኛ አመራሮች መንጠባጠብ ይታይባቸዋል፡፡ መካከለኛ አመራሩ ደግሞ የለውጡን ሥራ መመርያና ትዕዛዝ ሰጥቶ ሪፖርት የመቀበል አሠራር አድርጐ የመቁጠር መሠረታዊ የአመለካከት ችግር አለበት፡፡ እንዲሁም ሥራውን በሚፈለገው ብቃት፣ መጠንና ጥረት ለመፈጸም የሚያስችል የአቅምና የክህሎት ችግር በመካከለኛ አመራሩ የሚስተዋል ነው፡፡ ሠራተኛው ደግሞ አዳዲስ አሠራሮችን ለመቀበል መጠራጠር፣ የጠባቂነት ስሜትና ከተለመደው አሠራር ያለመውጣት በዋናነት የሚስተዋል ችግር ነው፤›› በማለት በትምህርት ዘርፉ ለታዩ ችግሮች በምክንያትነት በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ 
ይህንን ባቀረቡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሥልጣን ሽግሽግና አዲስ ሹመቶችን ፓርላማው እንዲያፀድቅላቸው የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በመጀመሪያ ደረጃ አቶ ደመቀ መኮንን በተደራቢነት ከሚሠሩት የትምህርት ሚኒስቴር መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሰጡት ምክንያት አቶ ደመቀ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በመፈለጉ ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን ነው፡፡
የአቶ ደመቀን የትምህርት ሚኒስትርነት ቦታ እንዲይዙ የተደረጉት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን እስካሁን ሲሠሩ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው፡፡
አቶ ሽፈራው በተቋማዊ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው መሆኑን፣ የተሾሙበት ተቋምን በብቁ ሁኔታ መምራት እንደሚችሉ በቅርበት የሚያውቃቸው ይናገራሉ፡፡ 
የአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወደ ፌዴራል መንግሥት ሚኒስትርነት መምጣት በደቡብ ክልል ላይ ጊዜያዊ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለክልሉ ፕሬዚዳንትነት የስድስት ግለሰቦች ስሞች እየተነሱ ነው፡፡
ከእነዚህ መካከል ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነታቸው በመነሳት በኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ደሚቱ ሃንቢሳ የተተኩት አቶ ደሴ ዳልኬ አንደኛው ናቸው፡፡ ሌሎቹ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ማርቆስ ተክሌና በአሁኑ ወቅት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የሚያገለግሉት አራት ግለሰቦች ናቸው፡፡ 
እነሱም አቶ ታገሰ ጫፎ፣ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ፣ አቶ ሳኒ ረዲና አቶ ደበበ አሰፋ ናቸው፡፡ ግምት ከተሰጣቸው መካከል የበለጠ ከፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑ ጋር በተደጋጋሚ ስማቸው እየተጠራ የሚገኘው አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ሲሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ አቶ ደሴ ዳልኬ ሊሆኑ ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት የሚኒስትርነት ሥልጣን ያገኙት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዳይሬክተር ጄነራል የነበሩት አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ እንደሚሆኑ የሚጠበቁትን የትራንስፖርት ሚኒስትሩን አቶ ድሪባ ኩማን ተክተዋል፡፡
አቶ ወርቅነህ ለረጅም ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም በመቀጠልም የፌዴራል ፖሊስን ከሰባት ዓመት በላይ በኮሚሽነርነትና በዳይሬክተር ጄኔራልነት  አገልግለዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ረዥም ዓመታትን በደኅንነት ሥራ ላይ ያሳለፉ ከመሆናቸው አንፃር ውስብስብ የአስተዳደር ሥራንና የውጭ ዲፕሎማሲን በሚጠይቀው፣ እንዲሁም የሲቪል አቪዬሽንን በሚያካትተው የትራንስፖርት ሚኒስትር መሾማቸው በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ 
የአማራ ክልል ምክትል መስተዳድር የነበሩት አቶ አህመድ አብተው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩትና የኢሕአዴግ አባል ሳይሆኑ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ለረዥም ዓመታት የቆዩት ብቸኛው ግለሰብ አቶ መኮንን ማንያዘዋል እንደአዲስ ለተቋቋመው ብሔራዊ ፕላኒንግ ኮሚሽን በኮሚሽነርነት ተሹመዋል፡፡ 
አቶ በረከት ስምዖን በሚኒስትርነት ሲመሩት ለነበረው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አቶ ሬድዋን ሁሴን ሲሾሙ፣ አቶ ሬድዋን የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከመሆናቸው አንፃር ሹመቱ የተጣጣመ እንደሆነ ይነገራል፡፡ 
በሌላ በኩል በቅርቡ ለተቋቋመው የአካባቢና ደን ሚኒስቴር አቶ በለጠ ታፈረ ተሹመዋል፡፡ በፓርላማ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በመሆን የወ/ሮ አስቴር ማሞን ተክተዋል፡፡ 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ሹመትና ሽግሽግን ኢሕአዴግ ከጀመረው የመተካካት ሒደት ጋር የሚያገናኙት ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል አቅም ባላቸው ከመተካት ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ለረጅም ዓመታት የሠሩ ሰዎች ወደ አማካሪነት መመደባቸውን በመተካካቱ ሒደት ከመንግሥት ሥራ እየወጡ መሆኑን ማሳያ ነው የሚሉም ተሰምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም አቀፍ ገበያ እየራቀ መጥቶ፣ ከነጭራሹ ሊወጣ የተቃረበበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ተዋንያዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ ለዓለም ቡናን ያበረከተች አገር ከመሆኗ ባሻገር እጅግ ተወዳጅ የሆነ ቡና የምታመርት አገር ናት፡፡ ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች ይህንኑ የጣዕም ልዩነት በመረዳት የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በቢሮክራሲ ውጥንቅጦች ምክንያት ቡናውን ማግኘት እንዳልቻሉ እየተናገሩ ነው፡፡ 
በቡና ግብይት ላይ ያለው ውጣ ውረድ ከፍተኛና ገዥዎች የማይተማመኑበት ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ በጣዕሙ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ እያጣ መምጣቱ የሚያስቆጭ ወቅታዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የችግሩ ምንጮች በዋነኛነት የመንግሥት የቡና ግብይት አቀንቃኞቹ የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት እንደሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች ያምናሉ፡፡ 
የቡና ግብይት ተዋናዮች እንደሚሉት፣ የችግሩ ምንጮች በእነዚህ ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት የተወለዱ ችግሮች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የንግድ ሚኒስቴር የቡና ግብይት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች የቡና ግብይት ሁኔታን በሚገባ አለመረዳታቸው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሥራ ኃላፊዎች የግብይት ሁኔታውን ቢያውቁም፣ የመወሰን አቅም የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ አካላት ግን ያሉባቸውን የተወሰኑ ችግሮች ለማረም አልሞከሩም፤›› ይላሉ የተበሳጩት የቡና ግብይት ተዋናዮች፡፡ በምርት ገበያ በኩል አሉ ከሚባሉት ችግሮች መካከል አንዱ የቡና ልኬት (ሚዛን) ችግር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ባሉት ዓመታት በቡና ግዥ ሒደት የቡና ገለፋት በ20 በመቶ ታሳቢ ተደርጎ በግዥ ሒደት ቅናሽ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ባለው የምርት ገበያ የሽያጭ ሒደት ግን ቀድሞ የነበረው አሠራር እንዲቀር በመደረጉ፣ ቡና ከአቅራቢዎች ገዝተው የሚልኩ ኤክስፖርተሮች መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ 
በዘርፉ በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በዚህ ዓመት ወደ ዓለም ገበያ መላክ ከነበረበት ቡና መካከል ከ150 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና በአገር ውስጥ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቡና ውስጥ 60 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ነቀምት ከተማና ሲዳማ ዞን ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 
የተጠናቀቀውን የሰኔ ወር ጨምሮ ወደ ውጭ የተላከው ቡና 170 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ከዚህ ቡና የሚገኘው ገቢ 800 ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የተላከው ቡና መላክ ከነበረበት ከማነሱም በላይ ለቡናው የሚሰጠው ዋጋም በዓለም ተወዳጅ ቡና ላላት አገር የማይመጥን ነው በማለት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ኬንያ 40 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ልካ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ 170 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ልካ ያገኘችው ከ800 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም ይላሉ፡፡ 
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በ2005 በጀት ዓመት ከቡና ዘርፍ ለማግኘት ያቀደችውን 1.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳይሳካ ከማድረጉም በላይ፣ በቡና ዘርፍ ለሚተዳደሩት 21 ሚሊዮን ዜጐች ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ 
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የወጪ ንግድ ዕቃዎች ግንባር ቀደም ድርሻ የሚወስደው ቡና፣ በቶን አምስት ሺሕ ዶላር ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ባለው ገበያ ግን ከ2,400 እስከ 2,500 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ 
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ይገኛል ብሎ ያቀደው ገቢ፣ በዋጋ መውረድ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወራት በመንግሥት በኩል በቀረበ አዲስ የቡና አላላክ ሥርዓት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የቡና ዋጋ ቢወርድም ግን ከታቀደው የበለጠ ጭማሪ በመላክ ማካካስ ይቻል እንደነበር ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡
በሚቀጥለው የ2006 በጀት ዓመትም የቡና ዋጋ ወደነበረበት ላይመለስ እንደሚችል ሥጋታቸውን የሚገልጹ ቢኖሩም፣ መገመት ግን እንደሚያስቸግር የሚገልጹም አልታጡም፡፡ የሌሎች አገሮች የቡና ዋጋ ከኢትዮጵያ የተሻለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ቡና ጣዕም ከሌሎች የተሻለ ሆኖ በየጊዜው በዘርፉ በሚፈጠረው የአሠራር ሳንካዎች ምክንያት ዋጋውን እያጣ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡
መንግሥት አገር ውስጥ ቡና የመላክ ፈቃድ ያላቸው ኩባንያዎችን በሙሉ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ውጭ የሚልኩትን የቡና መጠን እንዲያሳውቁ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ከነጋዴዎቹ በሚሰበሰበው መረጃ ላይ ተመሥርቶ የራሱን ትንታኔ ከሠራ በኋላ በበጀት ዓመቱ የሚላከውን የቡና መጠንና የሚገኘውን ገቢ ያቅዳል፡፡ በዚህ መሠረት በዚህ ሳምንትና በሚቀጥለው ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት የቡና ነጋዴዎች በዓመቱ ለመላክ የሚያቅዱትን የቡና መጠን እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል፡፡ 
የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ማዕከል የሆነው ንግድ ሚኒስቴር፣ በቡና ነጋዴዎች ማኅበር የቀረቡለትን ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች በእስካሁኑ ቆይታ ማስተናገድ አልቻለም፡፡ ምላሽ ባለመስጠቱም በርካታ የቡና ነጋዴዎች ተስፋ እየቆረጡ ከመመጣታቸውም በላይ ችግሩ ለቡና ኮንትሮባንድ በሰፊው በር መክፈቱን እየተናገሩ ነው፡፡
የዘርፉ ተዋናዮች መርካቶን ‹‹ደረቅ ወደብ›› የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና በመርካቶ ለአገር ውስጥ ገበያ በሰፊው ቀርቧል፡፡ ‹‹መርካቶ ላይ ያለው ቡና አውሮፓም ሆነ አሜሪካ የለም፤›› ሲሉ የቡና ነጋዴዎች የኤክስፖርት ቡና መርካቶ ላይ በሰፊው ለግብይት መቅረቡን ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቡና በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያና ወደ ሱዳን እየተላከ በመሆኑ፣ የቡና መገኛና የቡና ጣዕም ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በሒደት ከዓለም ገበያ ውስጥ እየወጣች እንደሆነ የዘርፉ ተዋናዮች እምነት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምትታወቅበት ቡና ችግር ውስጥ በመግባቱ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም የቡና ግብይት እንድትወጣ እየተጫናት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አንዳች ማሻሻያ ካላደረገ፣ ነጋዴዎች ከቡና ግብይት ውስጥ ሊወጡ እንደሚችሉም እየገለጹ ነው፡፡