POWr Social Media Icons

Tuesday, June 25, 2013

የስታዲየሙ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 23 በመቶ ያህል የተጠናቀቀ ሲሆን ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፤

በቀድሞ አጠራሩ «ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲየም» በአሁኑ ደግሞ «አዲስ አበባ ስቴዲየም » የአፍሪካ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ የአገሪቱንና የክለቦችን ዓለም አቀፍ ውድድሮች የምታስተናግድበት ብቸኛው ስፍራ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ሠላሳ አምስት ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው የሚነገርለት የአዲስ አበባ ስቴዲየም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1940 እንደተገነባ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። ስታዲየሙ በአውሮፓውያኑ 1962፣ 1968ና 1976 የተካሄዱ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል። ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው ከእነዚህ ሦስት የአፍሪካ ዋንጫዎች መካከል ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ባለድልም ሆናበታለች።
አዲስ አበባ ስታዲየም የአፍሪካ የወጣቶች ሻምፒዮናና 16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም በብቃት ተስተናግደውበታል።
ይህ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውና በመዲናዋ በብቸኝነት ደከመኝ ሰለችኝ ሳይል ከአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች በተጨማሪ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት ስታዲየም «አንድ ለእናቱ » እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ ማብቂያ የተቃረበ ይመስላል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በባሕር ዳር፣ በመቀሌ፣ በነቀምትና በሐዋሳ ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ። ከእነዚህ ስታዲየሞች መካከል ግንባታው ከተጀመረ የአንድ ዓመት እድሜ ያስቆጠረው የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛል። የጋዜጣው ሪፖርተር በከተማዋ በነበረው ቆይታም ይህንን አስተውሏል።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለግንባታው በመደበው 548 ሚሊዮን ብር በሳትኮን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ ተቋራጭነትና በኤምኤች ኢንጂነሪንግ አማካሪነት በመሠራት ላይ የሚገኘው የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ 23 ነጥብ አምስት በመቶ ተጠናቅቋል።
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 40ሺ ተመልካቾችን በመቀመጫ እንደሚይዝ የሚጠበቅ ሲሆን ፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የኦሊምፒክ ደረጃ ያለው እንደሆነ የፕሮጄክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ጉተማ ለጋዜጣው ሪፖርተር ነግረውታል። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት የሐዋሳ ስታዲየም እግር ኳስን ጨምሮ የአስራ አንድ ስፖርቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ይዟል።
ግንባታው ያለበትን ደረጃ ሲገልጹም በአሁኑ ሰዓት የተመልካቾች መቀመጫ ሥራ መጠናቀቁንና ሌሎች ስራዎችም በፍጥነትና በጥራት እንዲሁም በወጣለት የጊዜ ገደብ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት ።
የሐዋሳ ስታዲየም ፕሮጄክት በስኬት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥትና ስፖርት ኮሚሽን በየቀኑ በግንባታው ስፍራ እየተገኙ የሞራል ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በወቅቱ በማቅረብ ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አቶ ያሬድ ገልጸዋል።
በሥራ ሂደቱ እስካሁን የጎላ ችግር እንዳላጋጠመ የሚገልጹት አቶ ያሬድ፤ የክልሉን መንግሥት፣ የክልሉን ስፖርት ኮሚሽን፣ የሥራ ተቋራጩንና የአማካሪውን ተባብሮና ተግባብቶ መስራት የስታዲየሙ ግንባታ ከታለመለት ጊዜ በፊት ሊጠናቀቅ እንደሚችል አመላካቾች እንደሆኑም አስረድተዋል።
የሐዋሳ ስታዲየም ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ አብነት ኃይሌ ድርጅታቸው ከስታዲየሙ ዲዛይን ጀምሮ በማማከር ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረው፤ ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜና የጥራት ደረጃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ድርጅታቸው በባሕርዳር፣ በነቀምትና በሐዋሳ ስታዲየሞች ግንባታ ላይ በአማካሪነት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የሐዋሳው ስታዲየም ከቀድሞዎቹ በርካታ ልምዶች የተቀሰሙበትና በርካታ አዳዲስ ነገሮች የተጨመሩበት መሆኑን ነው የሚናገሩት። ለአብነትም የሐዋሳው ስታዲየም የክብር እንግዶች መግቢያና መቀመጫ የተለየ እንዲሆን መደረጉን ይገልጻሉ።
የግንባታውን ጥራት በተመለከተም ለግንባታው የሚውሉትን ግብአቶች በቤተ ሙከራ ከመቆጣጠር አንስቶ የሚጠበቅበትን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ነው የሚገልፁት። ፕሮጄክቱ አሁን ባለው ፍጥነት የሚሄድ ከሆነ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በፊት ሊጠናቀቅ እንደሚችል በመግለጽም የአቶ ያሬድን ሃሳብ ይጋራሉ።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ መዘረዲን ሁሴን በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የሐዋሳ ስታዲየም ግንባታ በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በግንባታው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩ ችግሮቹን የሚፈቱና አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጡ የቴክኒክና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራውን በመምራት ላይ ይገኛል ባይ ናቸው።
ኮሚቴዎቹ ለግንባታው የሚውል የፋይናንስ እጥረትና የግብአት ችግሮች ሲከሰቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት ግንባታው በታቀደለት ጊዜ ወይም ከዚያ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት ለግንባታው መጠናቀቅ ለሥራ ተቋራጩም ሆነ ለአማካሪው ድርጅት የቅርብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈም በየጊዜው ክትትል እንደሚያደርግ አቶ መዘረዲን ተናግረዋል። ከግንባታ ግብአቶች ዋጋ ንረትና ተያያዥ ችግሮች ጋር በተያያዘ የስታዲየሙ ግንባታ ፈጽሞ እንደማይስተጓጎልም አረጋግጠዋል።
የስታዲየሙን ግንባታ ሲጎበኙ ካገኘናቸው መካከል ዶክተር ይልማ በርታ «ግንባታውን ሲመለከቱ ከፍተኛ የመደመም ስሜት ተሰምቶኛል » ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት የሐዋሳውን ስታዲየም ጨምሮ በክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙት ስታዲየሞች የአገሪቱ የስፖርት ዘርፍ እያደገ ነው የሚለው አባባል ማሳያ ናቸው ።
በመገንባት ላይ የሚገኙት አራት ታላቅ ስታዲየሞች ግንባታ በፍጥነት መካሄዳቸውና በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መገንባታቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ስቴዲየሞቹ ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ታላቅ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ እድል እንደሚፈጥርላትም አብራርተዋል።
በክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስቴዲየሞች መገንባታቸው ብቁና ጥራት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማፍራት ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በመሳተፍ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት መካከል አብዛኛዎቹ ሐዋሳ ከተማ የሚገኘው የኮረም ሜዳ ያፈራቸው ናቸው። ስታዲየሙ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከአሁን በተሻለ መልኩ በርካታ ተጫዋቾችን ለማፍራት እንደሚያስችለው ይጠበቃል።
በሲዳማ የጊዜ አቆጣጠር መሰረት የሳምንቱ ቀናት በስም አራትናቸው። እነሱም ቃዋዶ፣ ቃዋላንካ፣ ዴላ፣ዲኮ በሚል መጠሪያ ተለይተው የታወቃሉ። እንዲሁም አንድ ወር አጋና (ጨረቃ) እና ቱንሲቾ(ጨለማ) ተብሎ በሁለት ይከፈላል። እያንዳንዱ ወር በቋንቋው ተለይቶ የሚታወቅበት የራሱ መጠሪያ (ሥያሜ) ያለው ሲሆን ፤ ወራቱ አስራ ሁለት ናቸው። በነባሩ የሲዳማ ባህላዊ የጊዜ አቆጣጠር ውስጥ ጷግሜ ፎቃ የሚል ስያሜ ተሰጥቶቷል።
    በነባሩ የሲዳማ የጊዜ ቀመር አቆጣጠር መሰረት በዓመት ውስጥ ያሉት አስራ ሁለት ወራት በአራት ወቅቶች የተከፈሉ ናቸው። ከዚሁ አንጻር ወቅቶቹ አሮ(በጋ)፣ሀዋዶ(ክረምት)፣በዴሳ (በልግ) እና ቢራ (መኸር) የሚል መጠሪያ አላቸው። በባህሉና በጊዜ ቀመሩ መሰረት ሲዳማ የራሱ ዘመን መለወጫ ቀን አለው።ይህም ፍቼ በሚል መጠሪያ ይታወቃል።
     የዘመን መለወጫ( ፍቼ) በአል አከባበር
    ፍቼ በሲዳማ ባህል በዓመት አንዴ በድምቀት የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል ነው። በባህሉ መሰረት አከባበሩ እስከ ሁለት ሳምንት ይዘልቃል። የፍቼ በዓል ቅደም ተከተላዊ የአከባበር ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ለአከባበሩ መነሻና መድረሻ የሚሆኑ ክንውኖች አሉ። ከእነዚህ ክንውኖች የመጀመሪያው ላኦ(ምልከታ) ነው። ላኦ ፍቼ መቼ እንደሚውል አያንቶዎች (የስነክዋክብት ተመልካቾች አረጋውያን) የጨረቃንና የከዋክብትን አካሄድ ጥምረት ተመልክተው የሚለዩት ሲሆን፤ አያንቶዎች ፍቼ ቀኑ መቼ እንደሚውል በከዋክብት ምልከታ ከለዩ በኋላ ለጎሳ መሪዎች ይገልጻሉ። የጎሳ መሪዎች ቀኑ ተገልጾ ለህብረተሰቡ እንዲለፈፍ ሲያዙ በገበያ ስፍራዎች በላላዋ (በልፈፋ) ይገለጻል። ላላዋ (ልፈፋ) የጎሳ መሪዎች ስር ባሉ ስፍራዎች የሚከወን ሲሆን ፤ ለፋፊዎች በገያ ቀን የበግ ቆዳ ረዠም ዘንግ ላይ ሰቅለው በመያዝ ገበያ ውስጥ ለህብረተሰቡ ቀኑ (ፍቼ) መቼ እንደሚውል ያበስራሉ።
    ከልፈፋ ቀጥሎ ያለው ክዋኔ ሳፎተ ቄጤላ (የቡራኬ ባህላዊ ጭፈራ) ነው። በባህሉ መሰረት ጭሜሳዎች (ብቁ ብጹዕ አረጋውያን) ፍቼ ሲቃረብ ለአስራ አምስት ቀናት በመጾም፤ ፍቼ (ዕለተ ቀኑ )ዘጠኝ ቀን ሲቀረው ሳፎቴ ቄጣላ (የቡራኬ ቄጣላሥበመጨፈር በዕለቱ ጾም ይፈታሉ። ቀጣዩ ክዋኔ አዲቻ ቄጣላ  (እውነተኛ ቄጣላ) የሚባለው ሲሆን ከአረጋውያኑ የቡራኬ ቄጣላ ቀጥሎ ባሉት የገበያ ቀናት ጎልማሶችና ወጣቶች በገበያው ለፍቼ አራት ቀን እስከሚቀር ድረስ አዲቻ ቄጣላ (እውነተኛ ቄጣላ) የሚባለውን ጭፈራ ይያያዙታል።
    በዋነኛው በፍቼ እለተ ቀን የሚከናወነው የአከባበር ሂደት የሚጀምረው ፀሀይ ከመሃል አናት ዘንበል ካለች በኋላ (ከቀኑ ዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ሰዓት) ባለው ጊዜ የሚከናወን የሁሉቃ ስርአርት ነው። ለዚህም እያንዳንዱ አባወራ ከቤቱ ፊት ለፊት በሚገኝ ገላጣ መስክ ላይ ረዥም እርጥብ እነጨት ጫፉን መሬት ላይ በመውጋት ሁሉቃ (ቅስት) ሰርቶ በቅድሚያ እራሱ አባውራው በቅስቱ ውስጥ በመሹለክ ቤተሰቡንና ከብቱን በተራ ያሾልካል። ይህ ስርዓት  በባህሉ መሰረት ከዘመን ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው። ሁሉም በየቤቱ አስቀድሞ ለበአሉ ዝግጅት ስለሚያደርግ በፍቼ እለት ቀን ከአመሻሽ ጀምሮ ከአንዱ ቤት በመሄድ በአሉ ለሊቱን  በጋራ በመብላት ይከበራል። እለቱም ፈጣሪ በመባል ይታወቃል።
    በየቤቱ በዕለቱ የሚቀርበው ዓይነተኛ ምግብ ቡርሳሜ(በቅቤ የራሰ ቆጮ) እና ወተት ነው። የቡርሳሜ  (በቅቤ የራሰ ቆጮ) ማቅረቢያ ገበታ ቁመቱ አንድ ከንድ ስፋቱ ግማሽ ሜትር የሚሆን ከሸክላ የተሰራ ካብ ውስጥ ጎድጓዳ ሻፌታ  ነው። ከቤት ቤት በመሄድ በጋራ መብላቱ የሚጀምረው በቅድሚያ በአካባቢው በተለያዩ ማህበራዊ ደረጃዎች በባህሉ ትለቅ ወደሚባለው አረጋዊ ቤት በመሂድ ነው። ይህም ሳፎ(መጀመር) ይባላል።
    የአመጋገብ ሥርአቱ የሚጀምረው በእድሜ ወይንም በማህበራዊ ደረጃ ታላቅ የሆነ ሰው በሻፌታ ከተሞላ ቡርሳሜ(ምግብ) ቆንጥሮ በመበተን ፍቼ ዲርዲሮ እሊሺ (ፍቼ ከዘመን ዘመን  አድርሺን) በማለት ከባረከ  በኋላ ነው። በእንዲህ ከአንዱ ቤት ወደሌላው በመሄድ ሌሊቱን ሙሉ  የታረደ ሲበላ፤ የተረፈ ስጋ እቤት ውስጥ ካለ ስጋው ውጪ እንዲያድር ይደረጋል።ይህ የሚሆነው አዲስ ዓመት ለከብቶችም መልካም ዘመን እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው።
    ለፍቼ በአል ህብረተሰቡ ትልቅ ክበር ስላለው ቀደም ሲል በልዩ ልዩ ምክንያት የተጣለም  ካለ ፍቼ ሲቃረብ እርቅ ይካሄዳል። በባህሉ ተኳርፎ ወደ አዲሱ ዘመን መሸጋገር ነውር ነው። እንዲሁም በፍቼ ዕለተ ቀን ከቤት ውጪ ሌላጋ ማደር በባህሉ ስለማይደገፍ ለጉዳይ ወደተለያየ አካባቢ እርቆ የሄደ ሁሉ ለፍቼ ወደመኖሪያው ይሰበሰባል። የፍቼ ማግስት(ሁለተኛው ቀን) ጫምባላላ ይባላል። ጫምባላላ በቋንቋው እንኳን አደረረሳችሁ እንደማለት ሲሆን ፤ በባህሉ መሰረት በጫምባላላ እለት መሬት የማረስና እንጨት የመስበር ተግባር  አይከናወንም። በእለቱ ልጆች በእረኝነት ተግባርም ሆነ በሌላ በማንኛውም ሥራ አይሰማሩም። በጫምባላላ እለት ልጆች ተሰባስበው ከአንዱ ቤት ወደሌላው ቤት በጋራ በመሄድ ኤይዴ ጫምባላላ(እንኳን አደረሳችሁ) በማለት በየቤቱ ቡርሳሜ (በቅቤ የራሰ ቆጮ) እና ወተት እየተመገቡ እማውራዎች አናታቸው ላይ ቅቤ ይቀቧቸዋል። በእለቱ አባውራው ከብቶቹን ለእዚህ እለት ባዘጋጀው የለመለመ መሥክ አሰማርቶ ቦሌ(ከሀይቅ ዳርቻ የሚወጣ ጨዋማ አፈር ) የለመለመ መስክ ላይ በመነስነስ ከብቶቹን  አጥግቦ እያበላ ያውላል።
    በባህላዊ የጊዜ አቆጣጠሩ መሰረት ፍቼ( ዋነኛው ዘመን መለወጫ እለተ ቀን) ከሳምንቱ ቀናት በዕለተ ቀዋዶ የሚውል ሲሆን፤ ጫምባላላ (የፍቼ ማግስት) ሁሌም የሚውለው ከሳምንቱ ቀናት በዕለተ ቃዋላንካ ነው።
   ከጫምባላላ ቀጥሎ ያለው የአከባበር ሂደት በጥቅሉ ሻሺጋ የሚባል ሲሆን፤ ሻሺጋ  በአሉን በጋራ በገበያ  እንዲሁም በጉዱማሌ (በባህላዊ አደባባይ) በድምቀት የማክበር ሂደት ነው። በአከባበሩ ከታዳጊ ወጣቶች ጀምሮ እስከ አረጋውያን ያለው ህብተረሰብ በቄጣላ(በጋራ ባህላዊ ጭፈራ) ልጃገረዶች ሀገሬ (ባሀላዊ ዘፈን) ያላገቡ  ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች በፋሮ (ባህላዊ ጭፈራ) የሚሳተፉበት ከመሆኑም በተጨማሪ  የፈረስ ግልቢያ የንጉስ ስረአት የሚታይበት ነው።
   ከላይ በጥቅሉ ከተገለጠው በተጨማሪ ሻሺጋ በውስጡ ፋቂቂቾና ፍቺፋሎ የተሰኙ አበይት የአከባበር ክንውኖችን  ያካትታል። ከዚሁ አንጻር ሻሺጋ በገበያ በድምቀት የሚከበርበት ሂደት እስከሚገባደድበት ዕለት ቆይቶ በሻሺጋ መገባደጃ ዕለት ባለው የገበያ ቀን ወጣት ወንድ ለሚወዳት ሴት ልጃገረድ ፍቂቂቾ በልጅ ይልክላታል።የመፋቂያው ተምሳሌት ወይም ትርጉም ወድጄሻለው ወዳጅ ሁኚኝ የሚል ነው። መፋቂያው የተላከላት ሴት ከማን እንደተላከላት ጠይቃ ላኪውን ካልፈቀደችው መፋቂያውን አትቀበልም። የተላከውን ልጅ መልስለት ትለዋለች። ተስፋ ሳይቆርጥ በመልክተኛው ልጅ በኩል የመማጠኛና ማማለያ  ቃላት መላልሶ ይልክላታል። ልቧ ከፈቀደ ትቀበለዋለች። አልያም የወዳጅነት ጥያቄውን ካልተቀበለች መፋቂያው ለላኪው ተመላሽ ይሆናል።
    የመፋቂያው ልውውጥ ጥያቄ አንዳንዴ መፋቂያሽን ላኪልኝ የሚል ሊሆን ይችላል። ፍቄበታለሁ ላንተ አይሆንም ልትለው ትችላለች ። ይሄኛው አባባል መፋቂያ የለኝም ከማለት የተሻለ ስለሆነ የፋቅሺበተን ያንቺ ጥርስ የነካውን ፈልጌ ነው ይላታል። ወስደህ ልትጥለው ነው ከልብህ አይደለም ካለችው እንደነፍሴ እይዘዋለሁ እያለ መልሶ ይልክባታል። አባባሉና ማንነቱ  ካማለላት መቼ ትመልስልኛለህ በማለት በአንዴ የእሽታ መልስ ላለመስጠት ትግደረደራለች። ቀኑን ነግሮ ሲልክባት የትጋ የሚል ጥያቄ ልታስከትል ትችላለች። ይሄኛው ጥያቄዋ የት እንገናኝ የማለት አይነት ነው። በእንዲህ ምልልሱ ከሰመረና መፋቂያውን እንዳትጥለው እንደነፍስህ  ያዘው ብላ ከላከችለት  የወዳጅነት ጥያቄው እሽታ አገኘ ማለት ነው።
    ቀጣዩ የአከባበር ሥርአት ፍቺፋሎ(ለፍቼ በአል በጋራ ወደአደባባይ  መውጣት) የሚል መጠሪያ ያለው ነው። የፍቺላሎ እለት የአካባቢው ህብረተሰብ በጎሳ በጎሳው ሆኖ  በቄጣላ (ባህላዊ ጭፈራ ) ወደጎዱማሌ  የፍቼ በአል በጋራ ወደሚከበርበት ባህላዊ አደባባይ በመውጣት ፤ በጉዱሌ ውስጥ ባለ ማዕከላዊ ስፍራ በጎሳ በጎሳው በየተራ ገብቶ በመቀመጥ በጎሳው አረጋውያን፣ በጎሳው መሪ እና በጎሳው የባህላዊ እምነት መሪዎች ተመርቆ ተመክሮ በተመሳሳይ ቄጣላ ( ባህላዊ ጭፈራ ) በአሉን የማክበር ስርአቱን ይያያዘዋል።
ፍቺ ፋሎ ቀደም ሲል ከላይ ከተጠቀሱ የበአሉ አከባበር ሂደቶች ሁሉ የላቀ ብዙ ጎሳዎች ጉዱማሌ በመውጣት በጋራ የሚያከብሩት ደማቅ የአከባበር ስርአት የሚታይበት የፍቼ በአል ማሳረጊያ ነው። ከዚሁ አንጻር በእለቱ ቄጣላ ( የጋራ ባህላዊ ጭፈራ) የፈረስ ጉግስ ግልቢያ ትርኢት፣ ሆሬ (የልጃገረዶች ባህላዊ ዘፈን) እና ፋሮ  (ልጃገረዶችና ያላገቡ ወጣት ወንዶች በጋራ የሚሳተፉበት ባህላዊ ጭፈራ ) የሚከወንበት ደማቅ የማሳረጊያ በአል  ነው። በዚህ እለት በርካታ ሙሽሮች አምረውና ደምቀው በባሎቻቸው እናቶችና በጎረቤት ሴቶች ታጅበው ወደጉዱማሌ ይወጣሉ። በባህሉ መሰረት አንዲት ሙሽራ የሙሽርነት ጊዜዋ የሚያበቃው ተሞሽራ ከቆየችበት በእንዲህ አምራና ደምቃ ወደ ጉዱማሌ በመውጣት ነው።

http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/society/2804-2013-06-24-07-43-51
በዘንድሮው የትምህርት ዓመት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ መምህራን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚሰጣቸው የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ፉአድ ኢብራሂም እንደተናገሩት የትምህርተ ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደርገው ጥረት የመምህራን የሞያ ብቃት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡
ምዘናው እጩ ተመራቂዎቹ ወደ ስራ ዓለም ከመግባታቸው በፊት እንዲሰጥ መደረጉ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተዘረጋውን ፓኬጅ ውጤታማ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡
በስራ ላይ ያሉት ነባር መምህራንም ምዘናውን እንዲወስዱ በማድረግ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት ተከታታይ የሞያ ስልጠና ይሰጣል ማለታቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ እንደገና ሊቋቋም ነው። የኤጀንሲው በአዲስ መልክ  መቋቋም ተልዕኮውን በላቀ ብቃት ለመወጣት ያስችለዋል የተባለ ሲሆን ተቋሙ  ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው ፥የሚመራውም በጠቅላይ ሚንስትሩ  በሚሾም ዳይሬክተር ጄኔራል   ይሆናል።
ጥራት ያለው መረጃና አስተማማኝ የደህንነት አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ለዚህ ተቋም ተሰቶታል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ሃገር የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ስራን በሃላፊነት በመምራት፤አስፈላጊ ሁኖ ከተገኘ ከውጭ ሃገር አቻ ተቋማት ጋር በትብብር መስራትና በጋራ ኦፕሬሽን ማካሄድም ለዚህ ተቋም ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።
በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ እድገትና የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችንና የመልካም አስተዳደር አሻጥሮችን ተከታትሎ መረጃና ማስረጃ በማስባሰብ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብም አዲስ የሚቋቋመው ተቋም በአዋጁ ሃላፊነት ተጥሎበታል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መስሪያ ቤቱን በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቶ ለዝርዝር እይታ ወደ ሚመለከታቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች መርቶታል።
መስሪያ ቤቱ እንደገና እንዲቋቋም መደረጉም በሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ድጋፍ  አግኝቷል ። ከዚህ በተጨማሪ በአዋጁ መሰረት የመረጃና የደህንነት ሙያ የስልጠናና የምርምር ተቋምም የሚቋቋም ይሆናል።