POWr Social Media Icons

Sunday, June 23, 2013

ውዝግብ ያስነሳው የአማራ ክልል ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ዓመት በኋላ ተስተካከለ

ኮሚሽኑ የአማራ ክልል ሕዝብን ይቅርታ ይጠይቅ ተባለ
•ኮሚሽኑ ስህተቱን የፈጠርኩት እኔ አይደለሁም ብሏል
በ2001 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው ሦስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት ከተገመተው በሁለት ሚሊዮን አንሶ በመገኘቱ የፈጠረውን ውዝግብና ኢተዓማኒነት ለመቅረፍ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሉ ሕዝብ ብዛት ላይ በድጋሚ ጥናት እንዲካሄድ በወቅቱ በወሰነው መሠረት ጥልቅ ጥናት ተካሂዶ፣ የክልሉ ሕዝብ ቁጥር በ2.1 ሚሊዮን ከፍ ብሎ እንዲስተካከል የሚያስችል የዕድገት ምጣኔ ተገኘ፡፡ 

የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በፓርላማው ውሳኔ መሠረት በሁለት ቆጠራዎች መካከል የሚደረግ ‹‹ኢንተር ሴንሳል›› ጥናት በ2004 ዓ.ም. በማካሄድ ያገኘውን ውጤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ አቅርቧል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በ1999 ዓ.ም. እና በቀጣዩ ቆጠራ አጋማሽ ላይ በተደረገው ጥልቅ ጥናት በተገኘው ውጤት መሠረት የአማራ ክልል ሕዝብ ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔ ከሌሎች ክልሎችና ከአገር አቀፍ ምጣኔው በታች 1.73 በመቶ መሆኑ ስህተት ነበር ብለዋል፡፡ ትክክለኛው የክልሉ የዕድገት ምጣኔም ከአገር አቀፍ ምጣኔው ጋር ተቀራራቢ የ2.3 በመቶ ዕድገት እንዳለው በጥናቱ መረጋገጡን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ 
በዚህ መሠረት በተስተካከለው የ2.3 ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔ ሲሰላም የአማራ ክልል ሕዝብ በ2004 ዓ.ም. 19.2 ሚሊዮን መሆኑን ጥናቱ ማመልከቱን፣ ከዚህ በኋላም በዚህ ምጣኔ መሠረት እንደሚሰላ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ 
ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ ከምክር ቤቱ የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ አንድ የአማራ ክልል ተወካይ የክልሉ ሕዝብ በተሳሳተ ምጣኔ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲሰላ በመቆየቱ፣ ከፌደራል መንግሥት የሚያገኘው የበጀት ድጐማ እንዲቀንስ ምክንያት በመሆናችሁ ልትጠየቁ ይገባል ሲሉ ጣታቸውን በኮሚሽኑ ኃላፊዎች ላይ ቀስረዋል፡፡ 
የፌደራል መንግሥት በየዓመቱ ለክልሎች ለሚያደርገው የበጀት ድጐማ የክልሎች ሕዝብ ብዛት አንዱ መለኪያ በመሆኑ ነው የምክር ቤቱ አባል ይህንን ጥያቄ ለማንሳት የተገደዱት፡፡ ‹‹ቀደም ሲል የክልሉ ሕዝብ ዓመታዊ ዕድገት ሲሰላበት በነበረው የ1.7 በመቶ ምጣኔና አሁን በቀረበው የ2.3 በመቶ ምጣኔ መካከል ያለው ልዩነት ሲሰላ፣ በዓመት 500 ሺሕ ሕዝብ በመሆኑ ስህተቱ በፈጠረው ልዩነት ሳቢያም የተጠቀሰውን ያህል ሕዝብ ያለ በጀት ቀርቷል፡፡ ቢያንስ የዘጠኝና የአሥር ወረዳዎች ሕዝብ ማግኘት የሚገባውን በጀት እንዳያገኝ ኮሚሽኑ አድርጓል፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ አባል ጠንከር ብለው ተናግረዋል፡፡ 
‹‹የተጠቀሰውን ያህል ሕዝብ ቁራሽ ዳቦ አሳጥታችኋል፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል ሕዝብን ይቅርታ ልትጠይቁ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ 
ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የጀመሩት ወ/ሮ ሳሚያም የተፈጠረው ስህተት በእርሳቸው ተቋም እንዳልሆነ፣ ችግሩ የመነጨው ከአገሪቱ የመረጃ ግብዓት እጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የ1999 ዓ.ም. የሕዝብና የቤት ቆጠራ ከመካሄዱ ከአሥር ዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረው ቆጠራ ውጤትና በሌሎች የሥነ ሕዝብ ናሙና ጥናቶች አማካይነት የክልሉ ሕዝብ ብዛት ተሰልቶ ሲተነበይና ውጤቱም ለተለያዩ ተግባራት በግብዓትነተ ሲውል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 
ሲሰላበት በነበረው የክልሉ ዓመታዊ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ መሠረት የአማራ ክልል ሕዝብ በ1999 ዓ.ም. 19 ሚሊዮን ይሆናል የሚል ትንበያ እንደነበር፣ ነገር ግን በዚያው ዓመት በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ የተገኘው ውጤት 17.1 ሚሊዮን መሆኑ ኮሚሽኑንም ግራ ያጋባ በመሆኑ፣ በተደጋጋሚ የፍተሻ ሥራ እንደተከናወነና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል፡፡ 
የውጭ ባለሙያዎችን ጭምር በማስመጣት መረጃዎች ተበትነው ቢገመገሙም፣ ለውጥ ባለመምጣቱ ችግሩ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ እንደተወሰነ አስረድተዋል፡፡ የውጭ ባለሙያዎች አምስት ነጥቦችን በመፍትሔ ሐሳብነት ሰጥተው የነበረ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥም ድጋሚ ቆጠራ መካሄድ የለበትም የሚል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 
ባለሙያዎቹ ለተፈጠረው ችግር በዋነኝነት የቀድሞው የዕድገት ምጣኔ ላይ በማተኮር በሰጡት ሐሳብ አገር አቀፍ የውስጥ ፍልሰት መረጃ መሥራት፣ የወሳኝ ሁነቶች መረጃ ማለትም የወሊድና ሞት አኅዝ፣ የሥነ ጤና መረጃ ዳሰሳና በሁለት ቆጠራዎች መካከል ጥናት ማድረግ የሚሉ መሆናቸውን፣ በዚህም መሠረት ይህንኑ ለምክር ቤቱ በማቅረብ ተጨማሪ ጥናት እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ተጨማሪ ጥናት ተካሂዶ በ2004 ዓ.ም. ማለትም የቀጣዩ ቆጠራ አጋማሽ ላይ ጥልቅ ዳሰሳ ተሠርቶ፣ የክልሉ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ 1.7 በመቶ ሳይሆን 2.3 መሆኑ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡ 
ይህ ጥልቅ ጥናት በ1999 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብ ቆጠራ ውጤት አይቀይረውም ያሉት ወ/ሮ ሳሚያ፣ በቆጠራው መሠረት የአማራ ሕዝብ ብዛት ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔው 1.7 በመቶ ሳይሆን 2.3 በመቶ መሆኑን ተጨማሪ ጥናቱ ያስገኘው መረጃ አረጋግጧል ብለዋል፡፡ በዚህም ምጣኔ ላለፉት አምስት ዓመታት የአማራ ክልል ሕዝብ ቁጥር ሲሰላ በ2004 ዓ.ም. 19.2 ሚሊዮን እንደደረሰ አስረድተዋል፡፡ 
ችግሩ የተፈጠረው የቀድሞው ትንበያ ሙሉ ባልሆነ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በመሠራቱ እንደሆነ ወ/ሮ ሳሚያ ተናግረዋል፡፡ 
የቀድሞው ትንበያ የተሠራው የውልደት ምጣኔን መሠረት በማድረግ እንደነበር፣ በወቅቱ የነበረው አገራዊ የውልደት ምጣኔና የአማራ ክልል የውልደት ምጣኔ ሲነፃፀር የአማራ ክልል በጣም ዝቅተኛ የነበረ መሆኑን በመረጃ አስደግፈው ያቀረቡ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት ሲተነበይ የነበረው ግን በ2.6 በመቶ ያድጋል በሚል መሆኑን፣ ነገር ግን የተደረገው ቆጠራ ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም ብለዋል፡፡ 
‹‹ትንበያ የሚደረገው ባለው መረጃ ነው በወቅቱ የነበረው ምጣኔ የተገኘው የውልደት ምጣኔን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አሁን ግን የፍልሰት፣ የሞትና የውልደት መረጃዎችን በግብዓትነት መጠቀም የሚያስችል አገራዊ አቅም በመፈጠሩ ስህተቱን ለማረም ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይቅርታ እንዲጠይቁ የቀረበውን ጥያቄ ስህተቱ የመነጨው በእነሱ ምክንያት አለመሆኑን በማሳየት አልፈውታል፡፡ 
የ1999 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ውዝግብ የተፈጠረው በአማራ ክልል ላይ ብቻ እንዳልነበር፣ የአዲስ አበባ የሕዝብ ብዛት 2.68 ሚሊዮን ሆኖ መገኘቱም በተለያዩ አካላት ተቀባይነት ሊያገኝ አለመቻሉን አስታውሰዋል፡፡ 
በመሆኑም አጋጣሚውን በመጠቀም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛትን በተመለከተ በተጠቀሱት አዳዲስ መረጃዎችና በቀጣዩ ቆጠራ አጋማሽ ላይ በተሠራ ጥልቅ ጥናት፣ የአዲስ አበባ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ከ1999 ዓ.ም. ውጤት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ በመረጋገጡ፣ በ2004 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት 2.99 ሚሊዮን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይም በ2004 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 82.2 ሚሊዮን እንደደረሰ አስረድተዋል፡፡ 
ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ በተለያዩ ተቋማት የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛትን እስከ አምስት ሚሊዮን አድርጐ የማየት ችግር አለ፡፡ በመሆኑም በዚህ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡ 
አዲስ አበባ ውስጥ የሕዝብ ቁጥር ከፍ ብሎ የሚታየው ውሎ ገብ ነዋሪዎች በየዕለቱ ከተለያዩ አካባቢዎች በአዲስ አበባ ውለው የሚመለሱ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ የቀረበውን ማብራሪያ ተከትሎ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በመግባባት መቀበል ይገባል ብለው በመጠየቃቸው በዚሁ መሠረት ፀድቋል፡፡