POWr Social Media Icons

Thursday, June 13, 2013

በጥረት የተገኘ ስኬት /ከበለጠ አድነዉ /ሃዋሳ ኢዜአ/
ቁጠባ የግለሰብን ኑሮ ከመቀየር ጀምሮ ለሀገር እድገት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ዛሬ በዓለማችን ላይ አንቱ ተብለው የሚጠቀሱ ባለሀብቶች ምንጫቸው ትንሿን ገንዘብ ብዙ እንድትሆን በተለያዩ የቆጠባ ዘዴዎች ቆጥበው ነው፡፡አሁን አሁን በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በሚቋቋሙ የብድርና ቁጠባ ተቋማት፣በባንክ፣በማህበራትና በሌሎችም የቆጠባ ዘዴዎች በመቆጠብ በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡በዚህም በርካታ ወገኖች ኑሯችውን ቀይረውበታል፡፡ ወይዘሮ አበባ ዘነበ ይባላሉ፡፡የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ባለቤታቸው ከብድርና ቁጠባ ተቋም ባገኙት 500 ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት ባህላዊ የአልባሳት ጥልፍ ሥራ ስኬታማ አያደረጋቸው ነው፡፡የጥልፍ ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ ስላደረጋቸው ዘመናዊ የጠረጴዛና የጥልፍ ስፌት ማሽኖችን ገዝተው የብሄረሰቦችን ልዩ ልዩ አልባሳት በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ወይዘሯዋ በራሳችን ባህላዊ አልባሳት መዋብ እንችላለን ብለው በመነሳሳት ሳይታከቱ በመስራታቸው ዛሬ ከከተማውና ከክልሉ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተው ለተለያዩ ስብሰባዎች፣ ለጉብኝትና ለበአላት የሚውሉ አልባሳት እንዲዘጋጅላቸው በርካታ ጥያቄዎች እየቀረበላቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ኢንባሲዎች ሳይቀሩ የየሀገራቸው የባህል ልበስ እንዲዘጋጅላቸው ጥያቄ እያቀረቡላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡የአካባቢው አስተዳደር የስራ ውጤታቸውን በማየት የመስሪያ ቦታ፣ የሙያና የምክር ድጋፍ በመስጠት የሚያደርግላቸው እገዛ ለስራቸው መሻሸል ከፍተኛ ብርታት ሆናቸዋል፡፡ ወይዘሮ አበባ በአሁኑ ወቅት ኑሮአቸውን ከመለወጣቸውም በላይ ካፒታላቸው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ለ30 ኢትዮጵያውይንም የስራ ዕድል መፍጠራቸው ተመልክቷል፡፡ስራቸውን ይበልጥ ለማስፋፋት አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው የሚያስፈልጋቸውን ማሽን ለመግዛት በቅርቡ ወደ ቻይና በመሄድ ለማሽኖቹ ከሚያስፈልገው ወጪ 30 በመቶ ክፍያ መፈፀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ታታሪዋ አበባ ከጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ መስክ ወደ መካከለኛ እንዱስትሪ መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጥ ከክልሉ ሞዴል ኢንተርፕራይዝ በመባል በርካታ የምስክር ወረቀቶች፣ሜዳልያዎችና ዋንጫዎች ተሸልመዋል፡፡በቅርቡ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ "የተዳፈኑ መዳፎች" በሚል በተዘጋጀው የኤስ ኤም ኤስ የህዝብ ምርጫ ተወዳድረው ካሸነፉ 8 ሴቶች መካከል አንዷ በመሆን ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ተሸልመዋል፡፡ ስራው አእምሮዬ ነፃ እንዲሆን አድርጎኛል የሚሉት ወይዘሮ አበባ ዛሬ ከጠባቂነት ተላቀው እራሳቸውን በመቻልና ኑሮቸውን በመለወጥ ለሌላም መትረፋቸውን ገልጸዋል፡፡ሌሎች ሴት እህቶቻቸውን ስራ ፈት ሆነው በቤት ውስጥ ከሚቀመጡ መንግስት ባመቻቸው የስራ ዕድሎችና ድጋፎች ተጠቅመው ስራን ሳይንቁ ተግተው ቢሰሩ በአጭር ጊዜ ባለሃብት መሆን እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡፡የወደፊት እቅዳቸውም ልክ እንደ ኮምቦልቻና ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ብቃት ያለው ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት ከራሳቸው አልፎ ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣት ታምራት ሃይለማርያም በዚሁ ሀዋሳ ታቦር ክፍለ ከተማ በ500 ብር የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት የጀመረው ሥራ ውጤታማ እያደረገው ነው፡፡የሚያመርታቸው የቆዳ ውጤቶች የሚያስተዋውቅበት መድረክ በተደጋጋሚ በከተማው አስተዳደር በኩል ተመቻችቶለታል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩ ወልዴም የሚሉት አላቸው፡፡በአሁኑ ወቅት በከተማው ከ32 ሺ የሚበልጡ ወጣቶችና ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የእራሳቸውን ኑሮ ከማሻሻል አልፈው ለከተማው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት የሚጥል ምርትና ህብት በማፍራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ወጣቶቹ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ድጋፎችን አያደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት 150 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በብድር፣ በማህበርና በግል እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ያገኙ ሲሆን የመሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም አስረድተዋል፡፡እንዲሁም የስልጠና፣ የንግድ ፍቃድ፣ የገበያ ትስስር በማመቻቸት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ማህበራትና ግለሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ መንግስት በከተማው ድህነትንና ስራ አጥነትን ለመቀነስ ባመቻቸው ፕሮግራም በመጠቀም ብዙዎቹ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወጥተው ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት በመሸጋገር የከተማውን ዕድገት እያፋጠኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡