POWr Social Media Icons

Friday, May 31, 2013

ሃዋሳ ግንቦት 23/2005 በሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ከ5 ሺህ በላይ ጎልማሶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አዝመራ አመኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በወረዳው በሚገኙ ከ35 በሚበልጡ ትምህርት ቤቶችና ጊዜያዊ የማሰተማሪያ ስፍራዎች ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ጎልማሶች ትምህርት እየተሰጠ ነው። በወረዳው ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶችን በመለየትና ለ96 አመቻቾች የማስተማር ስነዘዴ ስልጠና በመስጠት 5 ሺህ 947 ጎልማሶች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በደረጃ አንድና ሁለት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ጎልማሶች በተጨማሪ በቀበሌ አመራሮች በልማት ቡድኖችና በአንድ ለአምስት ትስስር አማካኝነት ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶች እየተለዩ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት በወረዳው የጎልማሶች ትምህርት ሽፋን ከ56 በመቶ በላይ እንደደረሰ አቶ አዝመራ ተናግረዋል። የጎልማሶች ትምህርትን በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን የወረዳው አስተዳደር ለአመቻቾች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና የማስተማሪያ መጽሀፍት ግዥ በመፈጸም ለሁሉም ጣቢያዎች እንዲዳረስ ማድረጉን አስታውቀዋል። በተጨማሪም አምስትና ስድስት ዓመት የሆናቸው 23 ሺህ 233 ህጻናት በ250 አመቻቾች የቅድመ መደበኛ ትምህርት በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጪ በተዘጋጁ የማስተማሪያ ስፍራዎች እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ልዩ ፍላጎት ያላቸውን አካል ጉዳተኞች በአካቶ የማስተማር ዘዴ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ 392 መስማትና ማየት የተሳናቸውና የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው ህጻናት በሰለጠኑ መምህራን እንዲማሩ መደረጉን አቶ አዝመራ ጠቁመዋል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ጋቤራ በበኩላቸው እንዳሉት አስተዳደሩ በወረዳው ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶችና የልዩ ፍላጎት ትምህርትን አጠናክሮ ለማከናወን እንዲቻል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። አስተዳደሩ በወረዳ ደረጃ ከተቋቋመው የአካል ጉዳተኞች ማህበር ጋር በመተባበር በለኩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማዕከል ተከፍቶ በሀዋሳ መምህራን ኮሌጅ በልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህራን አጭር ስልጠና በመስጠት እንዲያስተምሩ መደረጉን አስረድተዋል። በወረዳው የትምህርት ሽፋንን መቶ በመቶ በማድረስ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ጎልማሶች ሙሉ በሙሉ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ለማድረግና የልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚያስፈልጋቸውን አካል ጉዳተኞች ለይቶ በአካቶ የማስተማር ዘዴ ትምህርት ተጠቃሚ ለማድረግ የወረዳው አስተዳደር ከትምህርት ጽህፈት ቤቱ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=8346&K=1