POWr Social Media Icons

Wednesday, May 29, 2013

አዋሳ ግንቦት 21/2005 የግንቦት 20 የድል በዓል የሀገሪቱን ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አኩሪ የትግል ውጤት መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺፈራው ሽጉጤ ገለጹ፡፡ ፋና ብሮድ ካስት ኮርፖሬት ሻሸመኔ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 ከሲዳማ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር የግንቦት 20ን በዓል ትናንት በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ፕሮግራሞች አክብሯል፤ በሲዳምኛ ቋንቋ የሬዲዮ ስርጭት መጀመሩንም አብስሯል፡፡ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሺፈራው ሽጉጤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የዘንድሮው የግንቦት 20 በዓል ትግሉን በመምራት ለድል ያበቁት ታላቁ መሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በሞት በተለዩን ማግስት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ እሳቸውን ብናጣም የሀገራቸንን ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር ራዕያቸውንና የህዳሴ ጉዞችንን ለማሳካት ጠንካራ መሰረት በመጣል የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አኩሪ የትግል ውጤት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ ከጨለማው ዘመን በመውጣት በአሁኑ ወቅት የቡድንና የግለሰብ መብት ከመረጋገጡም በላይ በተለይ በትግል ወቅትና ከዚያም ወዲህ እንደሚዲያ የህዝብ ድምጽ በመሆን ሲያገለግል የቆየው የፋና ብሮድ ካስት ኮርፖሬት የግንቦት 20 ሌላው የድል ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፋና የስርጭት አድማሱን በማስፋት ተደራሽ ከሆነባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በሲዳምኛ ቋንቋ አሁን የጀመረው ፕሮግራም ቀጥሎ 17 ሚሊዮን ለሆነው የደቡብ ክልል ህዝብ በተመሳሳይ እንዲሰራ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንሚያደርግ በማረጋገጥ እሰካሁን ላደረገው አስተዋጾኦ አመስግነዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የሲዳማ ህዝብ እንደሌላው ጭቁን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የግንቦት 20 የድል ውጤት ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት በሲዳምኛ ቋንቋ የጀመረው ስርጭት በአካባቢው መልካም አስተደደርን ለማረጋገጥ፣ የብሄረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው በማመልከት ለስራው መቃናት የሚደርጉትን ደጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ሚለዮን አብራርተዋል፡፡ የፋና ብርድ ካሰት ኮርፖሬት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው ፋና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት በተለይም በጸረ ድህነት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ መደላደል እንዲኖረው ስርጭቱን አስፋፍቶ አሁን ዘጠኝ ቅርንጫፎች እንዳሉትና በቅርቡም በሚዛን አማን፣ በደብረ ብርሃንና በአሰላ ለመክፈት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በሻሸመኔ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 በኩል አሁን የጀመሩት የሲዳምኛ ቋንቋ የስርጭት ፕሮግረም ለማሳካት የክልሉና የዞኑ አስተዳድሮች ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሉዑል ገብሩ በበኩላቸው ከግንቦት 20 የድል ውጤቶች መካከል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የኤፍ ኤምና የማህብረሰብ ሬዲዮ ጣቢዎች እንዲከፈቱ ፍቃድ በመስጠትና በመከታተል እውን እንዲሆን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልከተው በቅርቡም በዲጂታል ሲስተም የቴሌቪዥን ፍቃድ የሚሰጥበት አሰራር እየተመቻቸ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተወካይ ዶክተር ንጉሴ መሸሻ የሀገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማጎልበት ሚዲያ ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው አመልክተው ዩኒቨርስቲውም በተለይ የብሄረሰቦችን ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሲዎችን ለማጎልበት በቅርቡ በሲዳምኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ድግሪ በመክፈት የጀመሩትን ፕሮግራም አስፋፍተው ለመቀጠል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ የግንቦት 20 በዓል " የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ የእርስ በርስ መስተጋበርና መቻቻል" በሚል መሪ ቃል ሲከበር በፋና ሻሸመኔ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 የሲዳምኛ ቋንቋ የስርጭት ፕሮግራም በይፋ መከፈቱ ተበስሯል፡፡ በዓሉን አስመልክቶም የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን የስነ ግጥምና ባህላዊ የኪነት ትረኢት ቀርበዋል፡፡ ለሲዳምኛ ቋንቋ የሬዲዮ ፕሮግራም መከፈት አስተዋጾኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የምስክር ወረቀትና ባህላዊ አልባሳት ተበርክቷል፡፡ በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=8272&K=1