POWr Social Media Icons

Friday, May 17, 2013

አዋሳ ግንቦት 09/2005 ህብረተሰቡን በቀበሌ ደረጃ ለሚያገለግሉ ስራ አስኪያጆች የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስልጠና በአምስት ማዕከላት እየተካሄደ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳደርና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሀላፊ አስታወቁ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የቢሮው ሀላፊ አቶ ታገሰ ጫፎ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የፕሮግራሙ አላማ የመንግስት የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና የለውጥ ስራዎች ዋና ማስፈጸሚያው ህብረተሰቡ በቅርበት በሚገኝበት በቀበሌ ደረጃ በመሆኑ ይህንን እንዲመሩና እንዲያስተባበሩ የተቀጠሩ የቀበሌ ስራ አሲኪያጆች ያሉባቸውን የማስፈጸም ብቃት ክፍተቶችን በመለየት አቅማቸውን ለመገንባት ነው፡፡ ከሁሉም የክልሉ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ለተወጣጡ ከ3 ሺህ 600 ለሚበልጡ ስራ አስኪያጆች የተዘጋጀው የማስፈጸም አቅም ግንባታ የስልጠና ፕሮግራም ከግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሀዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕናና በሚዛን አማን ማዕከላት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ በተጠቀሱት አምስት ማዕከላት ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በተሀድሶ መስመርና በኢትዮጵያ ህዳሴ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በቀበሌ መረጃ አያያዝና አደረጃጀት፣ በቀበሌ ጽህፈት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ፣ የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ስነ ስርዓት፣ በውጤት ተኮር ስርዓትና የተቀናጀ ዕቅደ ዝግጅት ዙሪያ በባለሙያዎች ትምህርት እንደሚሰጥና የጋራ ውይይትም እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡ በየቀበሌው የሚኖረው ህብረተሰብ ከመንግስት የሚፈልገውን ማንኛውንም አገልግሎት ወደ ወረዳ፣ ዞንና ክልል መሄድ ሳይስፈልገው እዚያው ባለበት ቀበሌ መጠቀም እንዲችል በክልሉ ሁሉም የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ስራ አስኪያጆች ተቀጥረውና ጽህፈት ቤቶች ተከፍተው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ተደራጅተዋል፡፡ ታች በሚካሄዱት ሁሉም የስራ ዘርፎች ከዕቅድ አወጣጥ እስከ አተገባበር ድረስ ህብረተሰቡን አሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ አጠቃላይ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መነሻ ቀበሌ ነው ያሉት አቶ ታገሰ ይህንን የመፈተሽና የመገንባት ብሎም ችግር ሊሆኑ የሚችሉ ምንጮችን የማድረቅ ስራ ውጤታማ ለማድረግ በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የመልካም አስተዳደርና የለውጥ ስራዎች የሚያጠናክር አደረጃጀት እንዳለም ተናግረዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማትም የልማት ሰራዊት በመገንባት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን ለማሳካት በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ እስከ ታችኛው መዋቅር ቀልጣፋ አሰራርን ለማጎልበት ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ የቢሮው ምክትል ሃላፊና የሰው ሀብት ስራ አመራር ዋና የስራ ሂደት ባለቤት ወይዘሮ አዳነው ድልነሳው በበኩላቸው ስልጠናው የቀበሌ ስራ አስኪያጆችን የማብቃት ብቻ ሳይሆን የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም ጭምር ነው ብለዋል፡፡ ከስነ ምግባር ጉድለቶች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ከስሩ በማድረቅ መልካም አስተዳደርና ልማትን ለማፋጠን ሁሉም በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ በሀዋሳ የስልጠና ማዕከል ተሳታፊ ከሆኑ የሲዳማና የጌዴኦ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ የቀበሌ ስራ አስኪያጆች መካከል አቶ ዳንኤል ሾሬ፣ አቶ ክፍሌ ሀሜሶና አቶ ሙሉጌታ ዲዳሞ በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ቆይታቸው የማስፈጸም ብቃት ችግራቸውን በመገንዘብ ወደየመጡበት ሲመለሱ ለህብረተሰቡን ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጠቃሚ ዕውቀት፣ ከፍተኛ መነሳሳትና አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ አዘጋጅነት በአምስቱም ማዕከላት እየተካሄደ ባለው ስልጠና ላይ ከቀበሌ ስራ አስኪያጆች ሌላ፣ የየዞኑና የየወረዳው ሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎች መሳተፋቸውም ተመልክቷል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7891&K=1