POWr Social Media Icons

Monday, April 29, 2013

አዋሳ ሚያዚያ 21/2005 በደቡብ ክልል ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚካሄደው አርሶ አደሩን ያሳተፈ የግብርና ግብይት ማሻሻያ ፕሮግራምን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ በተጀመረው በዚሁ ፕሮግራም አፈጻጸም ላይ የሚመክር ክልል አቀፍ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት ለሰባት አመታት የተነደፈው ይኸው ፕሮግራም አርሶ አደሮች በግብርና ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆኑና ኑሮቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያደርግ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም አካል ነው፡፡ በኘሮግራሙ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከልም ተቋማዊ የአቅም ግንባታ፣ የገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ለድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ግዥ የሚሆን ብድር ለአርሶ አደሮች ማቅረብ እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከ1998 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ እስካሁን በክልሉ 14 ዞኖች በተመረጡ 40 ወረዳዎች በተለያዩ ሰብሎች ጥራት፣ አመራረት፣ የድህረ ምርት አያያዝና ግብይት ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ሰልጥነዋል፡፡ በገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች አማካኝነትም ከ100 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች እንዲሰለጥኑ መደረጉም አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም በገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋት በኩልም በሀዋሳ፣ በዲላ፣ በሶዶና በቦንጋ ከተሞች አራት የቡና ቅምሻና የጨረታ ማዕከላት ግንባታ ተካሄዷል ብለዋል፡፡ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ በተመለከተም 1ሺህ 512 የእሻት ቡና መፈልፈያና ማድረቂያ፣ የዝንጅብል ማጠቢያና ማድረቂያ፣ በሞተርና በእጅ የሚሰሩ የበቆሎ መፈልፈያ፣ በእንስሳት የሚጎተት ጋሪ ፣ የእንሰት መፋቂያን ጨምሮ ሌሎችን ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን መሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች፣ የአርሶ አደሩን ምርት ጥራትና የምርት ብክነት ለመጠበቅ፣ የጉልበት ጫና ለመቀነስና የገበሬው ምርት እሴት እንዲጨምር እንዲሁም ገቢው እንዲያድግ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም የፕሮግራሙ ስራዎች አርሶ አደሩን ባሳተፈ መልኩ ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ የፕሮግራሙ የእሰካሁኑ አፈጻጸም የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከክልል እስከ ወረዳ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የመስራት ጉዳይ አነስተኛ መሆን፣ በወቅቱ የብድር ስርጭት አፈጻጸም ሪፖርት አለማድረግ፣ የብድር ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ አለመለቀቅና ለተጠቃሚው በፍጥነት ያለማሰራጨት ፣ ከቴክኖሎጂ አመራረጥ አንጻር እሴት በሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ አለማተኮር የሚሉት እንደሚገኙበት በጉባኤው ላይ ተመልክቷል፡፡ በሀዋሳ ከተማ የተጀመረውና ለሶስት ቀናት በሚቆየው የፕሮግራሙ አፈጻጸም የምክክር ጉባኤ ላይ ከክልሉና ከ14ቱም ዞኖች የተወጣጡ የግብይትና የህብረት ስራ መምሪያ ሃላፊዎች፣ የስራ ሂደት አስተባባሪዎች፣ የየዞኑ አሰተዳደር አማካሪዎችና የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ በአፈጻጸም ላይ የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም ፕሮግራሙን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተሻሉ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችንና ስልቶችን እንደሚቀይሱም ተመልክቷል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7529&K=1

የአለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ለ4 አመታት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የጤና ትብብር ስትራቴጂ ይፋ አደረገ፡፡
ስትራቴጁ  የጤና አገልግሎት ማሻሻል፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን፣ የእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነስ፣ የስነተዋልዶ ጤናን ማሻሻል እንዲሁም የተደራጀ መረጃን ማሳደግ ትኩረት ያደርጋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሀን አድማሱ እንዳሉት ትብብሩ ሀገሪቱ ከቀረፀችው የጤና ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ የምእተ አመቱን ግብ ለማሳካት ከፈተኛ ፋይዳ አለው፡፡
ይህም የጤና ልማት ሰራዊትን በማደራጀት በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ሊዊስ ሳምቦ በበኩላቸው በሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎችን ከዳር ለማድረስ ድርጅቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መለስ ዋንጫ  የ17ኛው ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ሚያዝያ 19/2005 ሶስት ጨዋታ የተካሄዱ ሲሆን  ሐዋሳ ላይ ሐዋሳ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
 ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ32 ነጥብ ደደቢት ተከትሎ ፕሪምየር ሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል።
ሐዋሳ ከነማ በ30 ነጥብ  ሶሰተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርባምንጭ ከነማ በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ሽንፈትን በሲዳማ ከነማ  አስተናዷል። በሲዳማ ቡና 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በመሸነፉ።
አዳማ ከነማ አሁንም ከወራጅ ቀጠና መውጣት ሳይችል ቀርቷል በሜዳው በመብራት ኃይል 1 ለ 0 ተሸንፏል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መለስ ዋንጫ ጨዋታ ደደቢት በ36 ነጥብ እየመራ ነው ።


ኢኮኖሚው ወድቋል፣ ሞቷል አይደለም እያልን ያለነው፡፡ ፈዟል ነው፡፡ በእውነት  ፈዟል፡፡ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ፣ ተግባር ላይ ሲውሉና ሲሳኩም አገርን በእጅጉ የሚጠቅሙ፣ በሐሳብና በፍላጎት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሥራቸው የተጀመረ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡
ነገር ግን በሚያስተማምን ሁኔታ በቂ በጀት እያገኙ ያሉ ፕሮጀክቶች አይደሉም፡፡ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ከተገኘ ጥሩ፣ ካልተገኘ ደግሞ ራሳችን እንፈጽማቸዋለን ብለን የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በራስ ተማምኖ መጓዝን የመሰለ የለም፡፡ እዚህ ላይ ስህተት የለም፡፡

ነገር ግን በራስ መተማመን በራስ ገንዘብን እውን ከማድረግ ጋር መያያዝ አለበት፡፡ ምርት እያደገ፣ ኤክስፖርት እያደገ፣ ግብር እያደገ፣ ወዘተ ሲሄድ ነው የውስጥ አቅም ሊጨምር የሚችለው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዕድገትና የአቅም መጎልበት ካልታየ ሊገኝ የታሰበው በጀት ላይገኝ ስለሚችል በዕቅዶች ላይ መጓተት ያስከትላል፡፡

የስኳር ፕሮጀክቶች በቂ በጀት እያገኙ አይደሉም፡፡ የምድር ባቡር ሥራው በበጀት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ መንግሥት ከግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶችና ከሌሎች ዓበይት ሥራዎችን ከሚሠሩ የግል ድርጅቶች ጋር ተዋውሎ ላሠራው ሥራ ለመክፈልም ሲቸገር እየታየ ነው፡፡ ሥራው ተሠርቷል ክፍያ ግን አልተፈጸመም፡፡  ሁሉም ችግር በገንዘብ  ባይመካኝም የገንዘብ እጥረት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

ባንኮች ለደንበኞቻቸው በተገቢው ደረጃ ብድር እየሰጡ አይደሉም፡፡ ያላግባብ የሚሰጥ ብድርን ማረምና ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እየታየ ያለው ችግር ጉድለትን የማስተካከል ሳይሆን ለተገቢው ብድር ብቁና ንቁ ሆኖ አለመገኘት ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ጉዳይም እንደዚሁ አስተማማኝ አይደለም፤ እጥረት አለበት፡፡ ሙስናም አለበት፡፡ የአቅም ማነስም አለበት፡፡ ውሸትም አለበት፡፡ ችግሩን በሀቅ፣ በግልጽና በድፍረት በመመርመር እንዴት እንፍታው ከማለት ይልቅ ‹‹በሽበሽ›› ነው እያሉ ማጭበርበር ይስተዋላል፡፡

መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር አደርጋለሁ ቢልም አሁንም ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ ነው፡፡ አሁንም ጥቁር ገበያው ተስፋፍቷል፡፡ እንዲያውም ከውጭ የሚመጣው የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ገንዘብም የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ከማሳደግ ይልቅ፣ በጥቁር ገበያ እየተመነዘረ ባንክ ሳይገባ እንዳለ ወደ ውጭ እየተጓዘ ነው ያለው፡፡ ከውጭ የመጣው ወደ ውጭ እየሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መተላለፊያ እንጂ መድረሻ መሆን አልቻለችም፡፡ የውጭ ምንዛሪ አሠራርን መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ አስቸኳይ ትኩረት ሰጥቶ ዕርምጃ ሊወስድበት ይገባል፡፡ ጥቁር ገበያ እንዲጠፋ በይፋ ፈቃድ ለውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እየሰጠ ባንክ ማስገባታቸውን ቢቆጣጠር ይበጃል፡፡ ለባንኮች ብቻ ኃላፊነትና ፈቃድ ሰጥቶ የውጭ ምንዛሪ ወደ ጥቁር ገበያ እንዳይገፋ መከላከል አለበት፡፡

ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎችና ሸቀጦችም ዋጋቸው በእጅጉ እየናረ ነው፡፡ በብዛት ስለማይገኙ ዋጋቸውም የማይቻል እየሆነ ነው፡፡ ኤክስፖርት በማብዛት ኢምፖርት ለመቀነስ ቢታቀድም፣ ለኢምፖርት እየወጣ ያለው ገንዘብ ግን በእጅጉ ብዙ ነው፡፡ ከግሽበት ጋር በተያያዘ ምክንያት፡፡

በዚህ ምክንያትም ኅብረተሰቡ በኑሮ ውድነት በእጅጉ እየተጨፈለቀ ነው፡፡  ኑሮን ለመግፋት ደመወዝ ትርጉም የለሽ እየሆነ ነው፡፡ ስለቅንጦት ዕቃዎች አይደለም እየተነጋገርን ያለነው፡፡ ወይ ቅንጦት? ጤፉም፣ በቆሎውም፣ ልብሱም፣ ትራንስፖርቱም፣ ወዘተ በእጅጉ ውድ ሆነው ነው የሕዝቡን ኑሮ እያንገዳገዱ ያሉት፡፡ 

የገንዘብ ዝውውር ተዳክሟል፡፡ ገንዘብ የለኝም የሚል በዝቷል፡፡ ጨረታዎች እንደድሮው አይደሉም፡፡ ብዙ ተሳታፊዎችን አያገኙም፡፡ ሒሳቦች በወቅቱ እየተከፈሉና እየተዘጉ አይደሉም፡፡ በነገራችን ላይ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ባንኮች እንኳን ደንበኛ ካስቀመጠው ሒሳብ ለማውጣት ሲጠየቁ፣ እዚህ ቅርንጫፍ ገንዘብ ስለሌለ ከሌላ ቅርንጫፍ ውሰዱ ማለት ጀምረዋል፡፡ ያሳስባል፡፡ እንዴት ገንዘብ አይኖራቸውም?

ባንኮች ከሚያበድሩት 27 በመቶ ቦንድ እንዲገዙ የወጣው ፖሊሲም ባንኮች የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ውስን እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ ፈዘዝ እንዲል አድርጎታል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ እየተነጫነጨና እየተንገጫገጨ በመሆኑ የውስጥ ኢኮኖሚያችንን እንዲበረታታ አያደርገውም፡፡ ከውጭ ይገኝ የነበረውን ብድር ያስቀራል፡፡ ይገኝ የነበረውን ዕርዳታ ያጠፋል፡፡ ለጋሾችና አበዳሪዎችም ገንዘብ እያጡ ነውና፡፡ ይህም በቀላሉ የሚታይ ጫና አይደለም፡፡ ይቆነጥጣልና፡፡

በዚህ ላይ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር አለ፡፡ ብዙ ዕቅድ ይዘናል ብዙ ገንዘብ ያስፈልገናል ብሎ ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቁሮ ከመሥራት ይልቅ በዕቃ ግዥ ስም ለመስረቅ፣ በጨረታ ስም ጉቦ ለመቀበል፣ ሥራ ለማስፈጸም በእግር አትምጡ በእጅ እንጂ በማለት ባለው የገንዘብ ችግር ላይ ተጨማሪ የገንዘብ ችግር የሚፈጥሩ አሉ፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚያዳክሙ፣ ኢንቨስተሮችን የሚያሸሹ፣ የአገር ሀብትን ለግል ጥቅም ለማዋል የሚሯሯጡ ሞልተዋል፡፡ ግፋ ቢል የሚታሙ እንጂ ጠንከር ያለ ዕርምጃ የማይወሰድባቸው አሉ፡፡ በየጊዜው እየበዙና እየተበራከቱ የመጡ፡፡

እነዚህና ሌሎች በርካታ ነገሮች ናቸው ኢኮኖሚውንና ቢዝነሱን እያፈዘዙ ያሉት፡፡ እናነቃቃው፡፡

ከሁሉም በፊት ሀቅን በድፍረት መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የበጀት ችግር አለ ሲባል ኧረ የለም እያሉ መግለጫ መስጠት፣ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሲባል ኧረ በሽ በሽ ነው እያሉ መደስኮር ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ትዝብት ነው ትርፉ ተብሎም መታለፍ የለበትም፡፡

በድፍረት ሀቅን እንወቅ፣ እንቀበል፣ ትክክለኛ መፍትሔ እንድናገኝ፡፡
መንግሥትና ኅብረተሰቡ ስለኢኮኖሚና ቢዝነስ የሚነጋገሩበት አገራዊ ‹‹የኢኮኖሚ ፎረም›› ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ብቻዬን አጥንቼና አስቤ ብቻዬን መፍትሔ እሰጣለሁ ማለት የለበትም፡፡ የኅብረተሰቡን አቅምም መጠቀም አለበት፡፡ የባለሙያዎችንና የባለድርሻ አካላትን ዕውቀትም ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም በፎረሙ እነሱንም ያሳትፍ፡፡

በጋራ መንቀሳቀስ ከተቻለ፣ ኅብረተሰቡና መንግሥት በሀቅና በግልጽ በአገር ችግር ላይ ከተወያዩና መፍትሔ ከፈለጉ መልስ ይገኛል፡፡ ችግር ይፈታል፡፡ አሁንም በአስቸኳይ መደረግ ያለበት ይኼው ነው፡፡
ኢኮኖሚውና ቢዘነሱ ፈዟል! እናነቃቃው!
  http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/item/1638-%E1%8A%A2%E1%8A%AE%E1%8A%96%E1%88%9A%E1%8B%8D%E1%8A%93-%E1%89%A2%E1%8B%9D%E1%8A%90%E1%88%B1-%E1%8D%88%E1%8B%9F%E1%88%8D-%E1%8A%A5%E1%8A%93%E1%8A%90%E1%89%83%E1%89%83%E1%8B%8D-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%82