POWr Social Media Icons

Saturday, April 27, 2013

ሀዋሳ ሚያዚያ 19/2005 የብሄር ብሄረሰቦችን ባህልና የቱሪስት መስህቦችን የማስተዋወቅ አላማ ያደረገዉ ሁለተኛዉ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በዓል በተለያዩ ፕሮግራሞች በሀዋሳ ከተማ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማው አስተዳደርና አርቲስቶች ገለጹ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ይህንኑ በዓል አስመልከቶ የከተማው አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና ታዋቂ አርቲስቶች ትናንት በሀዋሳ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል ። ከግንቦት 9 እስክ 11/2005 በሚካሄደዉ የሙዚቃ ቀን በዓል ላይ የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡ የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባና የባህል ፣ቱሪዝምና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ምህረት ገነነ እንዳስታወቁት ሀዋሳ የበርካታ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማዕከል እንደመሆኗ ባህላቸውን፣ እሴታቸውንና ለማስተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በአሉ ከፍተኛ ፋይዳ ያለዉ ነዉ ። ፕሮግራሙ ከማዝናናት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፋይዳው ክፍተኛ በመሆኑ በተለይ የክልሉና የሀዋሳን ሁለንታናዊ ገጽታንና የእድገት እንቅስቃሴ ለሌላው በማሳየትና ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚያግዝ በመታመኑ ፕሮግራሙን ለማሳካት አስፈላጊዉ ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታዉቀዋል ። ታዋቂ የሀገራቸን አርቲስቶች ባለፈው አመት አዲስ አበባ ላይ ያከበሩት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ በሀዋሳ ለማክበር ፕሮግራም ይዘው ሲመጡ በደስታ ተቀብለው ለማስተናገድ ባለሀብቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካለትን ያሳተፉ አብይ፣ ንዑሳንና ኮሚቴዎችን አቋቁመው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሀገራችን ታዋቂ አርቲስቶች መካከል አቶ ተስፋ አለም ታምራትና አቶ ይገረም ደጀኔ በበኩላቸው " ዝክረ ሀዋሳ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን" በሚል መሪ ቃል ለሶስት ቀናት በሚከበረው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በዓል ላይ የእግር ጉዞ፣ የቱሪስት መስህቦች ጉብኝት ይካሂዳል ብለዋል ። መዚቃና ፋይዳውን አስመልከቶ የፓናል ውይይት በትምህርት ቤቶች የሚከሄድ ሲሆን በመጨረሻም አንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን የሚሳተፉበት ትልቅ የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡ በፕሮግራሞቹ ላይ ተዋንያን፣ ድምጻዉያን፣ ጋዜጠኞች፣ ስፖርተኞች፣ የግጥምና የዜማ ደራሲያን፣ ኮሚዲያን፣ የውጪ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ሰአሊያን ፣ የቲያትር፣ የኦዶቭዥዋል፣ የፊልም ባለሙያዎች ማህበራት ጨምሮ 200 የሚሆኑ ታዋቂ ሰዎች መጋበዛቸውን ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ የሙዚቃ ቀን በአል ላይ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ሙዚቃና የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ አመጋገብ፣ አለባበስን ያካተቱ ትርኢቶችም እንደሚቀርቡም አስረድተዋል፡፡