POWr Social Media Icons

Thursday, April 11, 2013

አዳነ ግርማ ከምርጥ አስር አፍሪካዊ ተጫዋቾች ውስጥ በመካተት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ነው፤
 
ጆሴፍ ፔፕ ጋርዲዮላ የባርሴሎናን ክለብ ማሠልጠን እንደጀመረ የመጀመሪያ ስራው ያደረገው የክለቡን ነባር ተጫዋቾች በማሰናበት በምትካቸው በዝነኛው የክለቡ ማሠልጠኛ ማዕከል ( ላሜሲያ ) ያደጉ ተጫዋቾችን በዘመቻ መልክ ማሰባሰብን ነበር።
ከነዚህ ተመላሽ ካታሎናውያን መካከል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በፈረንሳዊው አርሴን ቬንገር ለሚሰለጥነው አርሴናል አምበልና የመሃል ሜዳ አንቀሳቃሽ የነበረው ሴስክ ፋብሪጋስ ቀዳሚው ነበር።
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ተጫዋቹን ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ለማስኮብለል ከተጠቀመባቸው አማራጮች መካከል አንዱ ራሱ በባርሴሎናና በስፔን ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት ይለብሰው የነበረውን የማሊያ ቁጥር ( አራት ቁጥር ) እንደሚሰጠው ቃል መግባት ይገኝበታል።
ሜክሲኮአዊው ራፋኤል ማርኬዝ ከባርሴሎና ጋር የነበረውን ኮንትራት አጠናቆ ወደ አሜሪካው ሜጄር ሶከር ሊግ ማምራቱን ተከትሎ ተሰቅሎ የቆየውን ማሊያ አውርዶ ለወጣቱ ጨዋታ አቀጣጣይ ሲሰጠው ተጫዋቹም በተደረገለት እንክብካቤ ከፍተኛ ደስታ ይሰማው ጀመር። ምክንያቱ ደግሞ በአርሴናል ይለብሰው የነበረውን አራት ቁጥር ማሊያ በአዲሱ ክለቡ ባርሴሎናም ለብሶ መጫወት ፍላጎቱ ስለነበር ነው።
ከላይ የገለጽኩት ሐሳብ ለዕለቱ መጣጥፌ መግቢያ ይሆን ዘንድ የተጠቀምኩት ሐሳብ ነው።
የዛሬው ጽሑፌ ማጠንጠኛ የሆነው ተጫዋች ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ውቢቷ ሐዋሳ ሲሆን የመጀመሪያ ክለቡም የከተማዋ ተወካይ የሆነው ሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ነው። በዚሁ ክለብ ከተከላካይነት እስከ አማካይ መስመር ባሉት ቦታዎች ላይ የተሰጡትን ሚናዎች በሚገባ እየተወጣ ማደጉ ለአሁኑ ሁለገብ ተጫዋችነቱ ( Versatile ለመሆኑ ) የመሰረት ድንጋይ ሆኖታል።
ኢትዮጵያዊውን ኃያል ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን የማሰልጠን ዕድል ከገጠማቸው አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት ሰርቢያዊው ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ በዚህ ወጣት ክህሎትና ችሎታ ተማረኩ። በወቅቱ በክለቡ የዋሊያዎቹ የፊት አውራሪ ሳላዲን ሰኢድን ጨምሮ ሌሎች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቢኖሩም አሰልጣኙ ይህንን የፈረጠመ ተክለ ሰውነት ባለቤት ተጫዋች ከአማካይነት ይልቅ ወደ ፊት መስመር አመዝኖ እንዲጫወት አደረጉት።
1999 .ም የመጨረሻ ወራት ከሞቃታማዋ የመዝናኛ ከተማ ወደ አፍሪካ መዲና ኃያል ክለብ የተዘዋወረው ወጣት ከፈረሰኞቹ ጋር አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችንና ሌሎች ድሎችን አጣጥሟል።በግሉም ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል።
የዚህ ጽሑፍ ባለታሪክ በክለቡም ሆነ በብሔራዊ ቡድን 19 ቁጥር ማሊያ ለባሹ አዳነ ግርማ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ እግር ኳስ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርገው የማሊያ ቁጥሩን አለመቀየሩ ሲሆን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ።
ሐዋሳ ከተማ ገብርኤል ሰፈር ተወልዶ ማደጉ ተጫዋቹ የማሊያ ቁጥሩን እንዲመርጥ እንዳደረገው በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህ ተጫዋች በስኮትላንዳዊው ኤፊም ኦኑራ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ወቅት ለዋሊያዎቹ መሰለፍ ቢጀምርም በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ግን በጣም ጎልቶ ወጥቷል።።
የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚወስደውን የአውሮፕላን ቲኬት ከመቁረጡ በፊት የነስቴፈን ሴስንሆን አገር ቤኒንንና ጎረቤታችንን ሱዳንን ማሸነፍ ግድ ይለው ነበር።ለዚህ ደግሞ የእንግሊዙ ሰንደርላንድ እግር ኳስ ክለብ ፈጣን አጥቂ የሆነውን ሴስንሆን አካቶ አዲስ አበባ የመጣው የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን ብሔራዊ ቡድን ግብ ሳይቆጠርበትም ሳያስቆጥርም ወደ አገሩ ተመለሰ።
ዋሊያዎቹ በዚህ ጨዋታ ባስመዘገቡት ውጤት የተከፋው ደጋፊ ሐዘኑ ቢበረታበትም የመልሱ ጨዋታ በአገሪቱ መዲና ፖርቶ ኖቮ ሲካሄድ 19 ቁጥር ለባሹ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣዩ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ አሳለፈች።
በካሜሩናዊው ዳኛ ጉልህ ስህተት እና በተከላካዮቻችን የትኩረት ማነስ ምክንያት ካርቱም ላይ አምስት ለሦስት ኢትዮጵያ ብትሸነፍም ብሔራዊ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች መካከል አንዷ በአዳነ ግርማ ግንባር ተገጭታ የተቆጠረች ነበረች።
የመልሱ ጨዋታ ከአንድ ወር በኋላ በአዲስ አበባ ሲደረግ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊያዎቹ ሁለት ማስቆጠር የግድ ይላቸው ነበር።በራዲሰን ብሉ ሆቴል የመሸገውና በውጤታማው አሰልጣኝ የመሐመድ ማዝዳ የሚሰለጥነው የሱዳን ቡድን በእድሜ ባለጸጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ ለሚያደርገው ጨዋታ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓትና ከዚያም በፊት ጀምሮ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ለማግኘት ያደረው ደጋፊ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ስዩም ከበደ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታ መከፋቱን መግለጽ ሲጀምርና ወደ ተስፋ መቁረጥ ሲገባ ይህ የደቡብ ልጅ የቡድኑን መንፈስ ያነሳሳች ግብ በማስቆጠር እንግዳውን ቡድን ጭንቀት ውስጥ አስገባው።ለዚች ግብ መገኘት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከበሬታ አስገኝቶለታል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘውና የቀድሞ የክለብ አጋሩ የነበረው ሳላዲን ሰኢድ ዋሊያዎቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው እርግጥ መሆኑን ያበሰረችዋን ወሳኝ ግብ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ የደደቢቱ አዲስ ሕንጻ አስተዋጽዖ እንዳለ ሆኖ አዳነ ግርማም ድርሻው ከፍተኛ ነበር።
ብሔራዊ ቡድኑ በአራት የማጣሪያ ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት ሰባት ሲያስቆጥር 19 ቁጥር ለባሹ አዳነ ግርማ ሦስት ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል።
የአውሮፓውያኑ 2011/2012 የውድድር ዘመን አፍሪካ ውስጥ ከሚጫወቱ አፍሪካውያን ኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ውስጥ ስሙ የሰፈረው የፈረሰኞቹ አጥቂ ከመጨረሻዎቹ አስር ምርጦች አንዱ በመሆን የመጀመሪያው የአገራችን ተጫዋች ሆኗል።
ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛው ዙር ሲያልፍ ወደ ማሊ ባማኮ በጉዳት ምክንያት ያልተጓዘው አዳነ ግርማ ከ19 ቁጥር ማሊያ ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ነው።1999.ም አስራ አንድ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ተወዳዳሪ ለሌለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የፈረመውና በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ብቸኛዋን የአገራችንን ግብ በዛምቢያ ላይ ያስቆጠረው ተጫዋች በ19 ቁጥር ማሊያው ታሪክ መስራቱን እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።
ሀዋሳ ሚያዚያ 2/2005 በሀዋሳ ከተማ 70 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የሚካሄደው የባህል ማዕከል ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የከተማ ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡ በማዘጋጃ ቤቱ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መብራቴ መለሰ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሀዋሳ መስቀል አደባባይ በ2003 ሀምሌ የተጀመረው የማዕከሉ ግንባታ ሁለገብ አዳራሽ፣ አንፊ ቲያትር ቤትና ሙዚየም አካቶ የሚይዝ ነው፡፡ በተለይ ቲያትር ቤቱን ይዞ 1500 መቀመጫ የሚኖረውና ለሁለገብ የስብሰባ አገልገሎት የሚውለው አዳራሽ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሲሆን በእስካሁን እንቅስቃሴ ከአጠቃላይ ስራው 80 በመቶው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ የቀሩት ጥቃቅን ስራዎችና የውሰጥ ድርጅት ማሟላት እስከ መጪው ሰኔ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አመልከተው ሁለተኛው ምዕራፍ የሆነውና በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው የሙዚየሙን ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁንና ስራው እሰከ መጪው አመት መግቢያ ድረስ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡ የባህል ማዕከሉ መገንባት ሀዋሳ የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ በኢንተርናሽናልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ስብሰባዎችን በብቃት በማስተናገድ የቱሪዝም ኮንፍራስ ከተማናቷን ከማሳደግ በሻገር የክልሉ ባህላዊ ቅርሶችና እሴቶችን አሰባስቦ ፣ ጠብቆና ተንከባክቦ ለማቆየት ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንደሚኖረው አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ማዕከሉ የቢዝነስና ማንጅመንት ፕላን ይኖሩታል ብለዋል፡፡ 
Source: http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=6846&K=1

አለመግባባት የሚያጦዘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

-    የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኪሳራው እንዲከፈለው ጠየቀ
-    ‹‹ነገሩ ግልፅ እንዲሆንልኝ መነጋገር እፈልጋለሁ›› እግር ኳስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከእንቅልፉ ተነሳ ሲባል መልሶ እያንቀላፋ፣ ተነቃቃ ሲባል እየደከመው ከረጅም ዓመታት በኋላ የለውጥ ጭላንጭል የታየበት ቢመስልም፣ ጊዜና ወቅት እየጠበቀ በሚፈጠር አለመግባባት እንደገና ወደ ጡዘት የሚያስገባ ምልክት እየተስተዋለበት ነው፡፡
የእግር ኳሱን ፋና የሚያጨልም ሰው (ጓዳ) ሠራሽ ቢሮክራሲ የበላይነት፣ የሥልጣን ማሳያ ሽኩቻ፣ ያለመግባባት ፍጥጫ ቀዝቃዛ ውኃ ሲቸልስበት ኖሯል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አሁንም እግር ኳሱ ቀና ቀና ማለት በጀመረበት ቅጽበት እንኳ የተቀየሩና የቀሩ አልመስል እያሉ ጉዞውን አስቸጋሪ እያደረጉበት ይገኛል፡፡

ከሰሞኑ የሚታየው ውዝግብም ኳሱ ከተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች ለዓመታት ተገልሎ የቆየበት ምክንየት ምን ነበር? የነበረውን ችግር ከሥር መሠረቱ ለመፍታት የተደረገው ጥረት ምንድነው? ዛሬስ ከዓመታት መገለል በኋላ ምን ዓይነት ለውጥና ዕድገት አምጥቶ ነው መድረኩን የተቀላቀለው? በሚሉትና ሌሎችም ተመሳሳይ የችግር አፈታት ሒደቶች ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ የሥልጣን ድርሻና የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሆኖ መታየቱ መንግሥትንም የሚያስተቸው መሆኑ አልቀረም፡፡

መንግሥት ‹‹ዘርፉ ከፖለቲካው ጨዋታ ውጭ እስከሆነ ድረስ ምንም ቢፈጠር ዝምታን ይመርጣል›› የሚለው የብዙዎች ትችት ወደ ኳሱም አካባቢ እየተዛመተ ስለመሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡

እነዚሁ አካላት መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እያከናወነ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ስፖርቱን እንደ አንድ የልማት ዘርፍ ቆጥሮ መንቀሳቀስ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁንና ተገቢውን ትኩረት ግን እየሰጠ ባለመሆኑ በተቋማት ‹‹መሪዎች ነን›› አማካይነት የዓለም አቀፍ ተቋማትን ሕጐች እንደ ሽፋን በመጠቀም የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚባክንበት ገጽታ መታየቱ ብቻ ሳይሆን፣ በስፖርቱ መሠረታዊ ዕድገት ላይም ተፅዕኖ እየፈጠረ ስለመምጣቱ ችግሩን በመጥቀስ ይተቻሉ፡፡

ከሰሞኑ ይኼው የእግር ኳስ ጡዘት ምናልባትም መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በእንጭጩ ሊቀጩት እንደሚገባ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ‹‹በምን ቸገረኝ›› የሚተው ከሆነ ግን በእግር ኳሱ ላይ የከፋ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል አለመግባባት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ተፈጥሯል፡፡ መነሻው ሁለቱ ተቋማት ይሁኑ እንጂ ይኼው ጉዳይ ወደ ሌሎችም ክልሎች መዳረሱ አልቀረም፡፡ 

ያለመግባባቱ መንስዔ፣ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ‹‹የአቻ ክልሎችን አደረጃጀትና አሠራር፣ እንዲሁም በአነስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ልማትና አጠቃቀም ዙርያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቃኘትና መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ለቀጣዩ ሥራችን ጠቃሚ ፍሬ ሐሳብ ለመቅሰም›› በሚል መነሻ መጋቢት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በሐዋሳ ሊያደርገው የነበረው የልምድ ልውውጥ ስብሰባ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ትዕዛዝ እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡

የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ስብሰባው የተቋረጠበት ምክንያት ግልፅ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በዕለቱ ከአቻ ክልሎች ጋር ሊደረግ የነበረው የልምድ ልውውጥ መድረክ ቀንና ሰዓቱ፣ እንዲሁም ቦታው ለክልሎች ከመገለጹ አስቀድሞ ጉዳዩ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ ቀርቦ እንዲፈቀድ ከተደረገ በኋላ ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም የፌዴሬሽኑ ተወካይ በልምድ ልውውጡ ላይ እንዲገኝ ጥያቄ ቀርቦ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ የተወከሉ መሆናቸው እንደተገለፀላቸውና ተወካዩም እንደተገኙ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው በክብር እንግድነት እንዲገኙ ጭምር የፌዴሬሽኑን ይሁንታ አግኝተው አሠልጣኙም እንደተገኙ፣ ከሁለቱ ተወካዮች በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አፈወርቅ አየለ ተሳታፊ እንደነበሩ ጭምር አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ አስረድተዋል፡፡

እንዲያ ከሆነ የክልከላው መንስዔ ምንድነው? ለሚለው አቶ ዘሪሁን፣ በዕለቱ ሊከናወን የታሰበው የልምድ ልውውጥ መድረክ፣ ‹‹ሕገወጥ ነው›› የሚለው የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ እስኪደርሳቸው ድረስ ስብሰባው እንዲቋረጥ የተደረገበት መንገድ ግልፅ እንዳልሆነላቸው ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የልምድ ልውውጥ መድረክ፣ ከሱማሌ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውጭ የተቀሩት ክልሎች ተገኝተዋል፡፡ የልምድ ልውውጡን ስብሰባ መቋረጥ ተከትሎ የጋምቤላ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ‹‹በአገራችን እግር ኳስ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ውይይት እንድናደርግ ወደ እዚህ የስብሰባ አዳራሽ የመጣነው ሕጋዊ ውክልና ተሰጥቶን ነው፡፡ ይሁንና ውይይቱ እንዳይካሔድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታግዷል፡፡ ክልከላው ደግሞ እኛን ካለማመን ሊሆን ይችላል›› ሲሉ ቅሬታቸውን የገለጹበት አጋጣሚም ነበር፡፡

ሌሎችም በተመሳሳይ የስብሰባው መቋረጥ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ገልጸው፣ የጋምቤላ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ‹‹ጥርጣሬ›› ሲሉ ላቀረቡት ቅሬታ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘውን የፌዴሬሽን አመራር መርጦ ካስቀመጣቸው አንዱ ባለድርሻ ይኼው አካል መሆኑን እንዴት ሊዘነጉት ቻሉ? ሲሉ በጥያቄ የታጀበ አስተያየትን ሰጥተዋል፡፡

በወቅቱ የተፈጠረውን ‹‹ግርታ›› ለማቀዝቀዝ በሚመስል መልኩ አስተያየቶቻቸውን የሰጡት የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መዘረዲን ሁሴንና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተወከሉት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ በየበኩላቸው፣ የልምድ ልውውጡ ስብሰባ ቢቋረጥም ክልሉ በእግር ኳሱ ረገድ እያደረገ ያለውን የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ዞሮ ዞሮ ይህም የልምድ ልውውጡ አንድ አካል በመሆኑ ተወካዮቹ ተዘዋውረው እንዲጐበኙ ጠይቀዋል፡፡ ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የጋምቤላ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ‹‹የእገዳ ትርጉም ሁለት ዓይነት ሳይሆን አንድ ዓይነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውይይቱ እንዳይደረግ አግዷል፡፡ ስለዚህ ጉብኝት ማድረግም የውይይቱ አንድ አካል በመሆኑ መደረግ የለበትም›› ሲሉ ተቃውመውታል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ተወካዮች የእሳቸውን ሐሳብ በመደገፍ ወደ ጉብኝቱ ሥፍራ ያልተንቀሳቀሱ እንደነበሩ ሁሉ፣ ምንም እንደማይሆኑ እምነት ወስደው ጉብኝት ያደረጉም ነበሩ፡፡

መሪዎች ነገሮችን የሚመለከቱበት የራሳቸው አተያይ እንደሚኖራቸው በመግለጽ የጋምቤላውን ተወካይ አቋምም እንደማይደግፉ የተናገሩት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ፣ በእግር ኳስ ላይ ውይይት ቢደረግ ያን ያህል ክፋት እንደሌለው፣ ነገር ግን ውይይቱ በጋራና ለጋራ ጥቅም በመግባባት ዓላማው ታምኖበት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲሉ ያከሉት አቶ ዘሪሁን፣ መሪዎች ሁኔታዎችን በተለያየ አቅጣጫ ተመልክተው ክልከላ ቢያደርጉ ስህተት ተብሎ ሊወሰድ እንደማይገባው ገልጸው፣ የስብሰባውን አጠቃላይ ሒደት በተመለከተ ግን ፈቃድ እንደተሰጠው፣ እሳቸውም በዚሁ መሠረት ተወክለው እንደመጡ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ ስለ ጉዳዩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ ያቀረበው ፈቃድ እንዲሰጠው ሳይሆን ተወካይ እንዲላክለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ስብሰባው እንዲደረግ የተሰጠ ፈቃድ የለም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራር በበኩላቸው፣ ስለስብሰባው መቋረጥ የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ መልስ ስለሰጡበት በድጋሚ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ ‹‹ስብሰባውን ለማድረግ ፈቃድ አልሰጠንም›› ለሚለው ለአቶ አሸናፊ አስተያየት የሰጡት መልስ፣ ክልሉ ያዘጋጀውን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ክልሉ ላቀረበው ጥያቄ ፌዴሬሽኑ የሰጠውን መልስ ተከትሎ በሁለተኛው ፓራግራፍ ላይ የሰፈረውን መልዕክት በማንበብ ይጀምራሉ፡፡

መልዕክቱም፣ ‹‹በውይይታችሁ ስለ ፌዴሬሽኖች አደረጃጀት፣ ጠንካራና ደካማ ጐን፣ ፌዴሬሽኖች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ሊኖራቸው ስለሚገባው አስተዋጽኦ ላይ እንድትወያዩ ለተሳታፊዎችም አበልና መስተንግዶ እንደምታደርጉላቸው ገልጻችኋል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አቶ ዘሪሁን ቃሚሶን የወከልን መሆኑን እንገልጻለን›› በማለት ለደብዳቤያቸው የሰጠው መልስ ትርጉሙ ለስብሰባው ሕጋዊ ይሁንታ መስጠት ካልሆነ፣ አሁን ወደ ኋላ ላይ እንደሚሉት ማለት ነውን? ሲሉ በጥያቄ ይመልሳሉ፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ የደረሳቸው የልምድ ልውውጡን ለማድረግ ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጣቸው መልስ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ ቁጥር 2/ኢ.እ.ፌ/አ.9/589 በቀን 17/07/05 ለደቡብ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአገሪቱ ከሚገኙ አቻ ፌዴሬሽኖች ጋር መጋቢት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. የልምድ ልውውጥ እንደምታደርጉ በቁጥር ደ/ክ/ፌ/12/05 በቀን 13/07/05 በተጻፈ ደብዳቤ ተወካይ እንድንልክላችሁ ጠይቃችኋል፡፡ በውይይታችሁም ስለከተማና ክልል መስተዳድር ፌዴሬሽኖች አደረጃጀት ጠንካራና ደካማ ጐን፣ ፌዴሬሽኖች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ሊኖራቸው በሚገባ አስተዋፅኦ ላይ እንደምትወያዩ ለተሳታፊዎችም የቆይታ አበልና መስተንግዶ እንደምታደርጉ ገልጻችኋል፡፡

በመሆኑም ፌዴሬሽኑን በመወከል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሴቶች ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲገኙ የተወከሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ በክብር እንግድነት የጋበዛችኋቸው አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውን በሹፌርነት ይዘው የሚመጡት አቶ ደረጀ ወንድሙ ስለሆኑ የሁለቱ ሰዎች ወጪ በእናንተ በኩል እንዲሸፈንላቸው እናሳስባለን›› የሚል ነው፡፡

‹‹ከፍተኛ ወጭ ተደርጐ፣ ተወካዮች ከየክልላቸው በሕጋዊ ደብዳቤ እንዲወከሉ ሆኖ ሁሉ ነገር ተጠናቆ ካበቃ በኋላ ስብሰባው ሊጀመር ሰዓታት ሲቀሩ፣ ፌዴሬሽኑ የክልከላ ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል ለፈቃድ በላከው ደብዳቤ አጀንዳዎቹን ጭምር አካትቶ መላኩ፣ ይህም ከፌዴሬሽኑ ዕውቅና ውጭ ነው ተብሎ ከታመነበት ደግሞ ያኔውኑ ተወካይም እንደማይልክ፣ ስብሰባውም ሕገ ወጥ ስለመሆኑ ለምን መልስ አልሰጠም ነበር›› የሚሉት አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበላይ እንደመሆኑ መጠን፣ ምንም እንኳ አካሔዱ አግባብ ነው ብለን ባናምንም የክልከላው ደብዳቤ እንደደረሰን ውሳኔውን አክብረን ስብሰባውን አቋርጠናል፡፡

ነገር ግን ፌዴሬሽኑ እስካሁን ድረስ ‹‹ሕገ ወጥ›› ያለበትን አጣርቶ ሊያሳውቀን ባለመቻው የተነሳ የክልላችን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጀመረውን የልምድ ልውውጥ ስብሰባ ማካሔድ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተጨማሪም በስብሰባው መቋረጥ የሞራል ካሳና ለስብሰባው ያወጣውን ሙሉ ወጭ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለሉ እግር ኳስ ጋር በመነጋገርና በመተባበር እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ መልስ እንዲሰጥ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሕግ አግባብ እንጠይቃለን›› የሚል ደብዳቤ ባለፈው ሐሙስ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መጻፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው አስከትለውም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄያቸውን ተከትሎ መልስ እንደሰጠ፣ ይኼውም በአድራሻ ለደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መዘረዲን ሁሴንና ቀጥሎ ለደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ባሉበት፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ሐዋሳ ላይ በክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት የምክክር ስብሰባ ማድረግ እንደሚፈልግ መግለጹን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽንና ለክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጻፈውን የደብዳቤ ይዘት አስመልክቶ ቀደም ሲል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራር በበኩላቸው፣ ‹‹በአጠቃላይ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንቅስቃሴ ግልፅ አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህ ይኼው ጉዳይ ግልፅ እንዲሆንልኝ በቅድሚያ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በተገኙበት ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ግልፅ ያልሆነው ባለፈው የተቋረጠው የስብሰባ አጀንዳ ነወይ? ለሚለው ኃላፊው፣ ‹‹ወደ እዚያ ጉዳይ መመለስ አልፈልግም›› ብለው የጠየቁት የምክክር መድረክ ‹‹በእግር ኳሱ ያለውን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ምን ያህል ያውቀዋል የሚለውን ማወቅ ስለፈለግሁ ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲቋረጥ ያደረገውን የስብሰባ ወጪ መክፈል እንደሚገባው የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠይቋል ስለሚባለው ኃላፊው፣ ‹‹የወጭውን ጉዳይ በሚመለከት ገንዘቡ የመጣው ከየት ነው? በአጠቃላይ በነገሩ ዙሪያ ያለው ሁኔታ ምንድነው? የሚለው ሁሉ ግልፅ ስላልሆነልኝ ይህንኑም ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ተነጋግሬ መረዳት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡