POWr Social Media Icons

Thursday, March 21, 2013

ሃዋሳ መጋቢት 11/2005 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን / 8ኛ ጉባኤ የድርጅቱን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትና የኦዲት ኮሚሽን በመምረጥና የአቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡ ጉባኤው አቶ ሀይማርያም ደሳለኝን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር፣አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ደግሞ በምክትል ሊቀመንበርነት እንዲመሩ በድጋሚ መርጧል። ንቅናቄውን በስራ አስፈጻሚነት የሚመሩም 15 አባላት መርጧል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን የሚወክሉ 45 አባላትም መርጧል። ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት በዛሬ ውሎው የድርጅቱ ኦዲት ኮሚሽን ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል ውስጥ ያከናወነውን ስራ በመገምገምና በሪፖርቱ ላይ በመወያየት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ ጉባኤው በቀጣይ ሁለት አመት በተለያዩ መስኮች ድርጅቱ በክልሉ በሚያከናውናቸው ስራዎች ዙሪያ በመወያየት አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡ ጉባኤው ቀደም ሲል 65 አባላት ያሉት የድርጅቱን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትና አምስት አባላት ያሉትን የኦዲት ኮሚቴ በመምረጥ ተጠናቋል፡፡

ደኢህዴን አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት መረጠ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን የንቅናቄው ሊቀመንበር አደርጎ መረጠ።
አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ደግሞ  በምክትል  ሊቀመንበርነት መርጧል ።
ጉባኤው ዛሬ ካካሄደው የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ  ጋርም ሰባት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባላትን ጨምሮ 15 የንቅናቄው ስራ አስፈፃሚ አባላትን መርጧል ።
በዚህም መሰረት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝንና አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ጨምሮ አቶ ሬድዋን ሁሴን ፣ አቶ መኩሪያ ሀይሌ ፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ፣ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ፣ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ ፣ አቶ ደሴ ዳልኬና አቶ ተስፋዬ በልጂጌ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ተደርገው ተመርጠዋል ።
እነዚህ  የኢህአዴግ  ስራ አስፈፃሚ  አባላትን ለሚያካትተው የደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደግሞ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ  ፣ አቶ መለሰ ዓለሙ ፣ ወይዘሮ ሙፍሪያት ካሚል ፣ አቶ ታገሰ ጫፎ ፣ አቶ ደበበ አበራና አቶ ሳኒ ረዲ በአባልነት ተመርጠዋል ።
በጉባኤው በአጠቃላይ 250 አባላትን በባህር ዳር ከተማ በሚካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት  መደበኛ  ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡ ሲሆን ፥  ከነዚህ መካከልም 45ቱ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው ።