POWr Social Media Icons

Thursday, March 7, 2013

የካቲት 28/2005 የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በከተማው የተጀመሩ የልማት፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስኬት በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለፀ። የምክር ቤቱ ጉባኤ የአንድ መምሪያ ኃላፊ ሹመትና ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ተጠናቋል። ጉባኤው ትናንት ማምሻውን ሲጠናቀቅ የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባኤ አቶ ደምሴ ዳንጊሶ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በከተማው የተገኘውን ዕድገት ለማስቀጠል የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አባላት ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት መነሳት አለባቸው። የታየውን ውስንነት በማስወገድና የተከናወኑ መልካም ስራዎችን በማጠናከር ለበጀት ዓመቱ የተያዙ ዕቅዶችን በማጠናቀቅ በከተማው የተጀመሩ የልማት መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በተጠናከረ ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል። ጉባኤው በትናንት ውሎው በከተማው ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሰፍ የቀረበውን የ2005 የበጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመገምገም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ጉባኤው በተለያየ ምክንያት ወደ ሌላ ሴክተር መስሪያ ቤት በተዛወሩ መምሪያ ኃላፊ ምትክ አዲስ መምሪያ ኃላፊ ሾሟል።በዚሁ መሰረት ወይዘሮ ገነት ገረመውን የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ በማድረግ ሾሟል፡፡ ጉባኤው በሀዋሳ ከተማ ለሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል 57 ሚሊዮን 682 ሺህ 599 ብር ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ተጠናቋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ባለፈው ሐምሌ ለ2005 በጀት ዓመት በከተማው ለሚከናወኑ ተግባራት ማስፈጸሚያ 921 ሚሊዮን 958 ሺህ 298 ብር በጀት ማጽደቁ የሚታወስ ነው።http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=6132&K=1

የኬንያ ምርጫ ወዲህ የኢትዮጵያ ወዲያ


ኬንያ በአፍሪካ በተለይ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን የተረጋጋ ፖለቲካ ያላት ተብላ የምትደነቅ አገር ነበረች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007  የተካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ የተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ግን ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎችን ለሕልፈት ሲዳርግ፣ ከ600 ሺሕ የሚበልጡ ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ባለፈው ሰኞ የተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አጠቃላይ ሒደቱ ሰላማዊ የሚባል ቢሆንም፣ ከወዲሁ የሚያስፈራ ፍንጭ አሳይቷል፡፡

ምርጫው በአብዛኛው ሰላማዊ የሚሰኝ ቢሆንም፣ በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ አካባቢ ሞምባሳ ሪፐብሊካን ምክር ቤት (MRC) በመባል የሚታወቅ ተገንጣይ ቡድን በቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የ19 ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ ያለፈው ምርጫ የፈጠረው ጦስ ለኬንያውያን ያስፈራቸው መሆኑን በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ሲሆን፣ ምርጫው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የድምፅ አሰጣጥ ዘዴ ተከናውኗል፡፡ የብዙዎቹ  ሥጋት በዋና ተፎካካሪዎቹ መሀል ጎሳን መሠረት ባደረጉ የፖለቲካ ድጋፍና ድምፅ የማግኛ ሥልቶች ምክንያት፣ የምርጫ ውጤቱን አሜን ብሎ የሚቀበል ተፎካካሪ አይኖርም የሚል ነው፡፡ ይህ በድጋሚ ወደ ጎሳ ግጭት ሊመራል ይችላል በሚል፡፡

ኬንያና ኢትዮጵያ ወዴት?
ኢኮኖሚዋ በምሥራቅ አፍሪካ የተሻለ አቅም እንዳለው የምትታወቀው ኬንያ ፊታውራሪ በሆነችበት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (EAC) ኡጋንዳና ታንዛኒያን አስከትላ በአካባቢው በአንድ ፓስፖርት፣ በአንድ ዓይነት ገንዘብና በአንድ የተማከለ ሕገ መንግሥት የሚመራ የፖለቲካ ማኅበረሰብም ለመፍጠር ተስፋ ተጥሎባት ነበር፡፡ እንዳተባለውም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፍጥነት በመራመድ ከቀረጥ ነፃ የንግድ ልውውጥና ነፃ የሆነ የሰው ኃይል እንቅስቃሴ ፈጥራ ነበር፡፡

ሆኖም ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 50 ዓመታት የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን የሚደቁሰውና የፖለቲካ መረጋጋቱን ጥያቄ ውስጥ የከተተው ከአምስት ዓመት በፊት የተከናወነው አገር አቀፍ ምርጫ ነበር፡፡

ደርግን አሸንፎ ሥልጣን የያዘው የኢሕአዴግ መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ በተቀናቃኞቹ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከመፈተኑ ውጪ፣ እዚህ ግባ የሚባል በምርጫ የመንግሥትም የመሪም ለውጥ ለማየት ኢትዮጵያ አልታደለችም፡፡ በጎረቤት አገር ኬንያ በሚከናወነው ምርጫና በተከታታይ የመሪዎች ለውጥም ትቀና ነበር፡፡ አገሪቱን ሊያበጣብጥ ጥቂት የቀረውና ለሁለት መቶ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የ97ቱ ተጠቃሽ ምርጫም፣ ከዚህም በላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ መሪዎችን፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች›› እና ሠልፈኞችን ለእስር የዳረገ ነበር፡፡

ምርጫን በማያውቀው ኢሕገ መንግሥታዊ የኤርትራ ሥርዓት፣ መንግሥት አልባ በሆነችው ሶማሊያ፣ እስላማዊ መንግሥትን በመሠረተችውና የእርስ በርስ ግጭት የበዛባት በመጨረሻም ለሁለት የተከፈለችው ሱዳን፣ እንዲሁም ደግሞ በፖለቲካዋና በኢኮኖሚዋ እምብዛም ቀልብ የማትስበው ጂቡቲ የተከበበችው ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤት ኬንያ ዘላቂ የዲሞክራሲ ግንባታ እንድትማር ነበር የፖለቲካ ተንታኞች የሚጠቁሙት፡፡

በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ከተንሰራፋው ሙስና በስተቀር እምብዛም በመጥፎ የማትነሳው ኬንያ፣ የዲሞክራሲ ጭላንጭል ከታየበት የ97ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ሁለት ዓመት ዘግይታ ያካሄደችው ምርጫ ግን የዲሞክራሲዋን ጉዞ የሚቀለብስ ሆኗል፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ አቅቷት የኬንያ መሥራች አባቶች እነ ጆሞ ኬንያታና ዳንኤል አራፕ ሞይ መሥርተውት ያለፉት ሥርዓት አስተማማኝነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ብቻም ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከየትኛውም የአፍሪካ አገር የማይስተካከል የምርጫ ቀውስ ገጠማት፡፡

የምርጫውን አወዛጋቢ ውጤት ተከትሎም ለብዙ ዘመናት የተደበቀው የጎሳ ፖለቲካ በመቀስቀሱ፣ አገሪቱ ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ ነበር የገባችው፡፡ በተፈጠረው ቀውስ ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በአፍሪካ የዲሞክራሲ መስፈርቶችን በማስቀመጥ ኬንያን ከመጀመርያ አገሮች ተርታ አስቀምጦ የነበረው ‹‹ሞ አብራሂሞ›› ፋውንዴሽን፣ የዲሞክራሲ ኢንዴክስን ጨምሮ የተለያዩ በዚሁ ጉዳይ ላይ ሪፖርት የሚያዘጋጁ ድርጅቶችም ኬንያን በ‹‹ከሸፉ›› አገሮች (Failed State) ተርታ አስቀመጧት፡፡

ተፎካካሪዎቹ እነማን ናቸው? 
የኬንያ የፖለቲካ ፓርቲ አመሠራረትና አወቃቀር ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰላልም ይለያያልም፡፡ በብሔር ስም የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲ ባይኖርም (አዲሱ ሕገ መንግሥትም አይፈቅድላቸውም)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ለፓርቲያቸው ዋነኛ የድምፅ ድጋፍ የሚያገኙት ከፓርቲው መሪ ጎሳ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአሁኑ ምርጫ ከቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋናነት በአምስት ዋና ዋና ቅንጅቶች የተጣመሩ ናቸው፡፡ ከስብስቦቹ መካከል አንደኛው ቅንጅት ለሪፎርምና ለዲሞክራሲ ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት፣ ዋይፐር ፓርቲና ፎርድ ኬንያ የሚባሉትን ዋና ዋናዎቹን አቅፎ በውስጡ ይዟል፡፡

ሁለተኛው ጁብል የሚባለው ቅንጅት ሦስት ዋና ዋና ፓርቲዎችን አካቶ ይዟል፡፡ ንስር አሞራ ጥምረት የተባለውም ሁለት ጠንካራ ፓርቲዎችን አቅፏል፡፡ ፓምባዝኳ እንደዚሁ ከአራት በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጡ አካቷል፡፡ አማኒ ከአሊሻን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የፕሬዚዳንት ሙአይ ኪባኪ ዕውቁ ካኑን ጨምሮ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፈጠሩት ጥምረት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በአሁኑ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉት የጁብል አልያንስ ዋና መሥራች ኡሁሩ ኬንያታ በናሽናል አልያንስ ፓርቲያቸው በአንድ በኩል፣ የሪፎርምና የዲሞክራሲ ጥምረት ዋና መሥራች ራይላ ኦዲንጋ በዕውቁ ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት (ብርቱካናማ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ናቸው፡፡ ኡሁሩ ኬንያታ የመጀመርያው የኬንያው ፕሬዚዳንት ጀሞ ኬንያታ ልጅ ሲሆኑ፣ ከአምስት ዓመት በፊት የአገሪቱ የምርጫ ቀውስ ባመጣው የእርስ በርስ ግጭትና በወቅቱ ዜጎች ግድያ እንዲፈጸምባቸው ዋና ቀስቃሽ ተደርገው በዓለም አቀፉ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት ተከሰው ጉዳያቸውን በመታየት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሰውየው በኬንያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኩኩዩ ጎሳ ተወላጅ ሲሆኑ፣ ሜሩና ድምቡ የተባሉ ሌሎች የጎሳ ቡድኖችን አስከትለው አሁንም ምርጫውን በመምራት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ኡሁሩን ተከትለው ከፍተኛ የመራጮች ድምፅ በማግኘት ላይ ያሉት ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ፣ ቀደም ሲል ከፕሬዚዳንት ኪባኪ ጋር የካኑ ፓርቲ ጥምረት አባል ነበሩ፡፡ በኋላ ላይ በተፈጠረው መከፋፈል አዲስ ፓርቲ መሥርተው ባለፈው ምርጫ ሲቀርቡ ነበር ለእርስ በእርስ ግጭት የተዳረጉት፡፡

ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፍተኛ ሥልጣን እንዲሰጥ ሲሞግቱ የቆዩት ዝነኛው ኦዲንጋ፣ የምርጫ ቀውሱን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት በኬንያ ሁለት መሠረታዊ ለውጦች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ የተቀናቃኛቸው የፕሬዚዳንት ኪባኪ ሥልጣን በመቀነስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመጣጣኝ ሥልጣን የሚያስገኝ አዲስ ሕገ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔ እልባት ያገኘው በ2002 ዓ.ም. ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በቀድሞው የተመድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ሸምጋይነት በፕሬዚዳንት ኪባኪ ከሚመራው ካኑ ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት የፈጠሩ ሲሆን፣ እስካሁን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እየሠሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ምርጫ ፕሬዚዳንት ኪባኪ በገዛ በፈቃዳቸው ከውድድር ውጪ ሆነዋል፡፡

እነሱ ወዲህ እኛ ወዲያ
በ1997 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ለመጀመርያ ጊዜ የምርጫ ፈተና የገጠመው ሲሆን፣ ዋናዎቹ ተቀናቃኞች ግን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ ሁለት ዋና ዋና ጥምረት በመፍጠራቸው ነበር፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት፡፡ ክብደቱ ቢለያይም በ97 ምርጫ ማግስት የተፈጠረው ግርግር ከኬንያው የ1999 ዓ.ም. ምርጫ የሚመሳሰል ሲሆን፣ ምርጫውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሆነው ግን ከኬንያው በተቃራኒ ነበር፡፡ በኬንያ ጥምር መንግሥት በማቋቋም የሥልጣን ክፍፍል ሲደረግ፣ ኢሕአዴግ ለውጭ ተፅዕኖ አልበገርም በሚል የተቃዋሚ መሪዎችንና ከታቃዋሚዎች ጋር አብረዋል ያላቸውን ጋዜጠኞችንና አክቲቭስቶችን አሳሰረ፡፡ ፍርድ ቤትም አቀረባቸው፡፡ ከፍርድ በኋላ ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግም ምሕረት የሰጠ ሲሆን፣ ምርጫው በመንግሥት አወቃቀርም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ የለውጥ ማሻሻያ ለማድረግ ምንም ያልፈየደ ነበር፡፡

በኬንያ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጎ ለግጭት መነሻ የሆነው ጥያቄ ሲመለስ፣ በኢትዮጵያ በድኅረ 97 ምርጫ የተለያዩ ‹‹አፋኝ›› የሚባሉ ሕጎች (የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ) ፀደቁ፡፡ ኢሕአዴግም የአባላቱን ቁጥር ከ700 ሺሕ ወደ አምስት ሚሊዮን ከፍ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን ሙሉ ለሙሉ በመቆጣጠር ያለአንዳች ጠንካራ ፉክክር ቀጥሎ የመጣውን የ2002 ምርጫ 99.6 በመቶ ያሸነፈበት ነበር፡፡

በኬንያ የምርጫውን ቀውስ ተከትሎ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ የሚለውጡ ሁለቱ መሠረታዊ ፍፃሜዎች (የአዲስ ሕገ መንግሥትና የጥምር መንግሥት) መከናወን የአገሪቱ ሕዝብ ከፖለቲካ እንዳይርቅ ከፍተኛ ድርሻ የተጫወቱ ሲሆን፣ በተለይ አዲሱ ሕገ መንግሥት በዓለም በምርጫ ተራማጅ ከሚባሉ ሰነዶች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑን ጨምሮ በአገሪቱ ከምርጫ ገለልተኛ የሆኑት የዲሞክራሲ ተቋማት የሚፈጠሩበትን መንገድ ሲያመቻች፣ በ47 የአገሪቱ ክልሎች ለራስ አስተዳደር ሥልጣን የሚሰጥና ሴቶችና ሲቪል ማኅበረሰቦች በአገሪቱ ፓርላማ በቂ ውክልና እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡ በአዲሱ ሕገ መንግሥት መሠረት ፓርላማው ከየትኛውም ፆታ ከሁለት ሦስተኛ በላይ ሊኖረው አይችልም፡፡

በአሁኑ ምርጫ ኬንያውያን ከየትኛውም ጊዜ በላይ በነቂስ ወጥተው የመረጡ ሲሆን፣ የምርጫ ፉክክሩም በአመዛኙ በጎሳ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ካለፈው የበለጠ እንጂ ያነሰ አልነበረም፡፡ በሁለቱ ጎረቤት አገሮች በተከታታይ ምርጫዎች የተከሰተው ቀውስና ውዝግብ መሠረቱ ተመሳሳይ መልክ የነበረው ቢሆንም፣ በዘላቂነት ያስከተለው ውጤት ግን ለየቅል ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ በሁለቱም ወገን በኩል የነበረው ለድርድር የማይመች የፖለቲካ አቋም አንዱ ሌላውን ለመቅጣት ብቻ መሠረት ባደረገ አካሄድ አንዳች ድርድርና የሥልጣን ክፍፍል እንዳይደረግ ምክንያት የሆነ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ እንደሚሉት፣ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ምንም የትግል ፅናት የሌላቸውና ሥልጣንን በማናቸውም መንገድ ለመቆጣጠር የቋመጡ በመሆናቸው፣ እርስ በእርሳቸው ተሰባብረው ኅብረታቸውን ለውድቀት እነሱም በአብዛኛው ለስደት ተዳርገዋል፡፡

አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፖለቲካ ውስጥ የገቡት ሕዝብን ለማገልገል ሳይሆን፣ በጥላቻና በጥቅም ፈላጊነት ነበር ይላል፡፡ ለውድቀታቸውም ምክንያት መደበኛ ፖለቲከኞች (Full Timer) አለመሆናቸውን በማስረገጥ፡፡

በኢትዮጵያና በኬንያ የተከናወኑትን ሁለት ምርጫዎች በማነፃፀር ለሁለተኛ ዲግሪው መመረቂያ ጥናት ያደረገው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ ወጣት ሐጎስ ወልደኪዳን፣ የኬንያ ፖለቲካ አሁንም በሚያሳዝን ሁኔታ ከ‹‹ጎሳ ፖለቲካ›› ባለመውጣቱ መቼም አስተማማኝ አይሆንም ቢልም፣ በአገሪቱ ያሉት ፖለቲከኞች ጠንካራና በቀላሉ በማሰርና በማስፈራራት ከትግል የሚርቁ እንዳልሆኑ ያስረዳል፡፡

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ በኬንያ መንግሥት ላይ የፈጠሩትን ተፅዕኖም ያደንቃል፡፡ የተለያዩ የሥልጣን ማዕከላት የሚላቸው የሙያ ማኅበራት፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና ሌሎችም በጣም ጠንካራና በቀላሉ መፈራረስ የማይችሉ በመሆናቸውም የአገሪቱ ፖለቲካ በቀላሉ በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መሆን አይችልም ይላል፡፡

ስሙን መግለጽ ያልፈለገው የፖለቲካ ተንታኝ ግን በኢትዮጵያና በኬንያ የሚታየው ርዕዮተ ዓለም የፈጠረው ልዩነት እንደሆነ ይከራከራል፡፡ እሱ እንደሚለው የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዲሞክራሲ (አሁን ልማታዊ መንግሥት) በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ ዲሞክራሲን ወደ ጐን በማለት ልማትን ማምጣት መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግ ተቃራኒዎችን ከፖለቲካ በማጥፋት ሥልጣንን በአውራ ፓርቲነት መቆጣጠር ላይ ያተኩራል፡፡ ፓርላማውን ከሞላ ጎደል (ከአንድ ሰው በስተቀር) በምርጫ 2002 የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ፣ ይህንን አባባል የሚያረጋግጥ ይመስላል ብሎ፣ አሁን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ሲታዩ በቅርብ ጊዜ ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ያለው አይመስልም በማለት ሐሳቡን ያጠናክራል፡፡