POWr Social Media Icons

Monday, February 18, 2013


በውብሸት ሙላት
የሕግ ቋንቋ በብዙ መልኩ የተቀዣበረ ነው፡፡ ቀዥባራነቱን አንዳንዶች እንደ ውበት ይወስዱታል፡፡ ሌሎች ደግሞ የሕግ ባለሙያዎች ብቻ እንደሚያውቁት የአስማት/የመተት ቋንቋ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ሌላም ሌላም ይሉታል፡፡ ለማንኛውም በእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች ዘንድ የግልጽ ቋንቋ ተሟጋቾች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የሕግ ማኅበረሰቡ ግልጽ ቋንቋ ይጠቀሙ ዘንድ የሚያበረታቱ፣ እንዲጠቀሙ የሚሞግቱ የቋንቋና የሕግ ባለሙያዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በአገራችን ግን ስለዚህ ጉዳይ ስለመነሳቱ ይህ ጸሐፊ አያውቅም፡፡ በመሆኑም ስለሕግ ቋንቋ አንዳንድ ነገሮችን አንስተን እንወያያለን፡፡

መነሻ ወግ
አንድ በዕድሜ ገፋ ካሉ የእግሊዝኛ ቋንቋ መምህርና ደራሲ ጋር እያወጋን ነው፡፡ በሕይወታቸው ሦስት ጊዜ የእንግሊዝኛ አንድ ጊዜ የአማርኛ የፍትሐ ብሔር ሕግ ኮድ (መጽሐፍ) ገዝተዋል፡፡ አራቱንም መጻሕፍት ለሕግ ባለሙያዎች ሰጥተዋቸዋል፡፡ የስጦታቸው ምክንያት በልገስና ስሜት ሳይሆን ከገዟቸው በኋላ ሲያነቧቸው ሊገቧቸው ስላልቻሉ በብስጭት ነው፡፡ በእልህ ገዟቸው በብስጭት ሰጧቸው፡፡ እስካሁን ለምን ያነበቧቸው እደማይገቧቸው ግልጽ አልሆነላቸውም፡፡

አንድ የጓደኛዬ ጓደኛ ከሚንስትር መለስ ባለ ደረጃ ቱባ ባለሥልጣን ነው፡፡ ከቱባ ባለሥልጣን ሚስቱ ጋር በመጣላቱ በፍች ትዳራቸውን ሊያፈርሱ ሆኖ በሚስቲቱ አመልካችነት ጉዳዩ ተጀምሮ የፍችው አቤቱታ መጥሪያ ይደርሰዋል፡፡ በአቤቱታው የመጀመሪያ ገጽ የክሱ መግለጫ በሚለው ክፍል ላይ እንዲህ የሚሉ ዓረፍተ ነገሮች ተቀምጠዋል፡፡ “1. በሕግ ችሎታ የለሽም አልተባልኩም፡፡ 2. ጉዳዩ በይርጋ አልታገደም፤” የሚሉ ዓረፍተ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ቱባ ባለሥልጣን ሚስቱ እንፋታ ብላ ባቀረበችው አቤቱታ ላይ ከላይ የተገለዱትን ዓረፍተ ነገሮች ሲያይ ምን እደሚገልጹ ግራ ይገባውና በጓደኛው በኩል ስልክ ደወለ፡፡ በሕግ ፊት ችሎታ የለሽም አልተባልኩም የሚለው ምን እንደሚገልጽና እርሱም ምን ብሎ መመለስ እንዳለበት፣ ይርጋ ማለት ምን እንደሆነ ካለማወቁ በተጨማሪም ጉዳዩ የሚለው ምን እደሚያመለክት፣ እንዲሁም ምኑን እደሚያግደው ወይም እንደማያግደው ሊገባው አልቻለም፡፡

ይህ የምታነቡት ድንጋጌ የተጻፈው በ1952 ዓ.ም. በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2 ላይ የተደነገገ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡- “የተጸነሰ ልጅ በሕይወት ከተወለደና የሚኖር ከሆነ የራሱ ጥቅም በሚያሻበት ጊዜ ሁሉ እንደተወለደ ይገመታል፡፡”  በእርግጠኝነት ከዚህ ድንጋጌ ውስጥ የማይታወቁ ቃላት ያሉ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ወደ ዓረፍተ ነገርነት ሲቀየር ግን ምናልባት ቀዳሚውንና ተከታይ  አንቀጾችን በማንበብ ፍንጭ ካላገኙ በስተቀር በራሱ መረዳት አዳጋች ነው፡፡ እዚህ ላይ የተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች ሲበዙና በአንድ ላይ ተጠቃለው ሲታተሙ ኮድ ይባላሉ፡፡ ኮድ የሚባልበት ምክንያት ሚስጥራዊ መሆንን ለማመልከት ይሆን? በእርግጥ ይህንን ለማመልከት ከሆነ የሕግን የራሱን ዓላማ ያጠፋዋል፡፡ ሕግ ስለሰው ልጆች መብትና ግዴታ ስለሆነ መብትና ግዴታ ደግሞ መገለጽ ያለበት ማንም ሰው ሊረዳው በሚችል ግልጽ ቋንቋ መሆን አለበት፡፡ ከላይ የተገለጹትን ሦስት ምሳሌዎች እንደ መግቢያ ካየን ወደ ዋናው የጽሑፋችን አስኳል እንግባ፡፡

ስለሕግ ቃላት፣ ሐረጋትና ዓረፍተ ነገሮች በትንሹ
አቶ አስፋው ዳምጤ ለረጅም ዓመታት ስለ አማርኛ ቃላት መጻፋቸውን አውቃለሁ፡፡ ሕግ ስለሚጠቀምባቸው ቃላት፣ ሐረጋትና ዓረፍተ ነገሮች ጉዳይ መጻፋቸውን ግን አላውቅም፡፡ አልጻፉም ግን አላልኩም አላውቅም እንጂ፡፡ በ1961 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሕግ መጽሔት ላይ አቶ ፋሲል አበበና እስታንሊ ዜድ ፊሸር የተባሉ ሁለት የሕግ ባለሙያዎች በሚል ርዕስ ስለቋንቋና ሕግ የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በዚያን ዘመን ስለሕግ ቃላት እያከናወነ የነበረውንና በወቅቱ ከወጡት ሕጎቻችን መካከል ከሁለቱ የሥነ ሥርዓት ሕጎች ምሳሌ በመውሰድ፣ ከትርጉም ጋር በተያያዘ ሁኔታ የተስተዋሉትን ችግሮች ከስድስት ገጽ ያልበለጠ ጽሑፍ አስነብበውናል፡፡

ሌላ ሰው መጻፉን ግን አላውቅም፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲዎቻችንም ቋንቋን ለተለየ አገልግሎት (Language for a specific purpose) ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ ቢሰጥም ለስም ብቻ እንጂ በተግባር ግን መደበኛ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ነው፡፡ ለአብነት “English for Lawyers” የሚባለውን ትምህርት ብንወስድ አስተማሪዎቹም ስለሕግ ቋንቋ ስለማያወቁ፣ እነሱም ስላልተማሩት ያው “Sophomore English” ዓይነት ብቻ በመሆን ተገድቧል፡፡

አማርኛ ለሕግ ባለሙያዎች ሲባል ግን ሰምቼ አላውቅም፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የሥርዓተ ትምህርታችን መግባቢያ እንግሊዝኛ ሆኖ የምንሠራበት ደግሞ በአብዛኛው በአማርኛ (በየክልሉ የሥራ ቋንቋዎች እንደተጠበቁ ሆኖ) ነው፡፡ የሕግ የአማርኛ ቋንቋ ደግሞ በመግቢያችን ላይ ባነሳናቸው ችግር ዓይነቶች የተተበተበ ነው፡፡ የፍርድ ቤት የሥራ ቋንቋቸው ከአማርኛ ውጭ ለሆኑት ክልሎችና ፍርድ ቤቶች ይህ ችግር የባሰ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ ለምን ቢሉ? አንድም በየዩኒቨርሲቲዎቻችን የሕግ ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዝኛ በመሆኑ (በእርግጥም መሰጠት ያለበት በእንግሊዝኛ ነው)፣ በፌደራል ደረጃ የሚወጡትና ቀድሞም ቢሆን የወጡት ሕጎች በእንግሊዝኛና በአማርኛ ብቻ በመሆኑ፣ በኦፊሴል ደረጃ ባልተተረጎሙ ሌሎች ቋንቋ መሥራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት ቀላል በመሆኑ ነው፡፡  ችግሩን ለመፍታት ደግሞ የሚደረግ ጥረት አላየንም፡፡ በሌሎች አገሮች ግን አንድም ከላይ እንደተገለጸው ቋንቋን ለተለየ ግልጋሎት በማስተማር፣ የግልጽ ቋንቋ ንቅናቄ ቡድንና ማኅበራት በመመሥረት የሕግ ቋንቋ ከተተበተበበት ችግር እንዲላቀቅ ጥረት እየተደረገ  ነው፡፡ ትንሽ የሕግ ቃላት፣ ሐረጋትና ዓረፍተ ነገሮች እንመልከት-የችግሩን ግዝፈት ለማየት፡፡

የሕግ ቃላት ስብስቴያዊነት
ስብስቴ የሚያመለክተው ጥንታዊነቱን ነው፡፡ ምንጩም ጋሽ ዘካርያስ ቀንዓ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተባባሪ ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡  የሕግ ቋንቋ የጥንትና ያረጁና ያፈጁ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የማይውሉ ቃላትን ይጠቀማል፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን ቃላት እንይ፡፡

የአሽሙር ማኅበር፣ የሪም መብት፣ የእጅ ክስ፣ ወለድ አግድ፣ አረቦን፣ ግዙፋዊ ሀልዎት፣ የይዞታ መድን፣ እጅ እልፊት፣ መሰየም፣ ወዘተ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ይህ ጉዳይ በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛም ጭምር መሆኑን ክሪሲ ማር የተባሉ ጸሐፊ “Language on Trial” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ለአሁኑ ዘመን ትውልድ አይሆኑም፡፡ በተለይም በእንግሊዝኛ ተምሮ፣ ሥራ ላይ እነዚህን በመሳሰሉ ቃላት የታጨቀ ሕግን በመጠቀም በሰው ልጅ መብትና ግዴታ ላይ ውሳኔ መስጠት፣ በተለይም ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ከአማርኛ ውጭ ለሆነ ሕግ ተርጓሚ ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ለነገሩማ ፍትሐ ብሔርና አንቀጽ የሚሉትን ቃላት እንኳን እስኪ አጢኗቸው፡፡ ምን ማለት ናቸው? ወደ ግዕዙ ብትሄዱ ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ አንቀጽን እንኳን ብታዩ ደጃፍ፣ መግቢያ፣ በር ማለት ነው፡፡ ታዲያ “Article” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል እንዴት አድርጎ ይተካዋል? ስለአንቀጽ ያነሳነውን ጉዳይ ከመዝጋታችን በፊት አንድ ነገር እንጨምር፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ የሚለው እንዲተካ የታሰበው “Title” የሚለውን ቃል ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ በሚከተለው ሁኔታ ተከፋፍሏል፡፡

መጽሐፍ (Book)፣ አንቀጽ (Title)፣ ምዕራፍ (Chapter)፣ ክፍል (Section)፣ ንዑስ ክፍል (Paragraph)፣ ቁጥር (Article) በሚል ፡፡ እንግዲህ በመደበኛው የአማርኛ አገባብ የምናውቀው “Title” ርዕስ፣ “Paragraph” አንቀጽ፣ ቁጥር ደግሞ “Number” ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ በምዕራፍ (Chapter)፣ በክፍል (Part) በአንቀጽ (Article) ተከፋፍሏል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ አንቀጽ፣ ክፍልና ቁጥር የሚለው ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተገለጸው ይለያል፡፡ በመሆኑም ወጥ በሆነ መልኩ አልተቀመጡም፡፡ ከዚህ የምንረዳው የሕግ ቋንቋ ግራ አጋቢነት እንዲህ እያለ ገና ከአርዕስት አከፋፈሉ ጀምሮ መሆኑን ነው፡፡ ወጥ የሆነ ትርጉም እንኳን ይዞ መጓዝ ተስኖታል፡፡ ይህ በመሆኑም አደናጋሪነቱ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡

ፍትሐ ብሔር የሚለውንም ብናይ በግዕዙ ፍትሕ፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ፍርድ ሲሆን ብሔር፣ ቦታ፣ ሠፈር፣ ግዛት፣ አገር፣ ሕዝብ፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ብታቀናጇቸው የምታገኙት ትርጉም ግን “Civil Code” የሚለውን የሚተካ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ወንጀልና ወንጀል ነክ ያልሆነ ለማለት እንጂ የሕዝብ ሕግ፣ የአገር ሕግ፣ ወዘተ የሚለውን ለማመልከት አይደለም፡፡ ያ ቢሆንማ የወንጀል ሕጉም፣ ሕገ መንግሥቱም ያው የአገር፣ የሕዝብ ሕግ አይደል? እዚሁ ላይ አንድ ነገር ላንሳ’ማ- “ሕገ መንግሥት” የሚለውን ሐረግ ልብ በሉልኝ እስኪ? እንዴት ቢታሰብ ነው “Constitution” መንግሥተ-ሕግ ብቻ የሚሆነው? የመንግሥትን ተግባር ብቻ የሚቆጣጠር አይደል፣ የመንግሥትና የሕዝብን ግንኙነት ብቻም አይደነግግ? ምናልባት በየትም አገር የአገራት መተዳደሪያ ደንብ በመሆኑና ሌሎች ሕጎች ከዚሁ ሕግ ሥር በመሆናችው የበላይ ሕግ፣ ወይም ግዕዝና አማርኛ በመቀላቃል ልዕለ ሕግ ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ሕጋችን እጅግ ባረጁ ቃላት የተሞላ ነው፡፡ አሁንም ሆነ ድሮ ሕግ የሚያወጣው አካል አባላት ብዙዎቹ የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሳያውቁ ያወጧቸዋል፡፡ እጃቸውን በማውጣትም ያፀድቋቸዋል፡፡ ችግሩ እጅግ የሚጎላው ደግሞ የኢንሹራንስ ፖሊሲ (ውሎች) ላይ ነው፡፡ እጃችሁ የገባውን ፖሊሲ አንብቡና በተለይ እንግሊዝኛውን መረዳት ከቻላችሁ ታዘቡኝ፡፡ ሼክስፒራዊ ናቸው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደንበኞቻቸውን የማታለል ሐሳብ ኖሯቸው አዘጋጇቸው ብዬ ግን አላሰብኩም! የሕግ መዝገበ ቃላት ብዙም ባለመኖሩ የሰው ልጅ ወሳኝ የሆነውን መብትና ግዴታ ለመግለጽ ታስበው ቢወጡም፣ ውሎቹም ቢዘጋጁም፣ የታሰበላቸውን ዓላማ ሳያሳኩ የሕግ ባለሙያዎች ብቻ የሚያውቋቸው የአስማት ቋንቋ ሆነው ይኼው አሉ፡፡

የቃላት ውሰት ጥንውት
ሕግ ከሌላ ቋንቋ በተለይም ከላቲንኛ፣ ከፈረንሳይኛና ከእግሊዝኛ ቃላትን ይዋሳል፡፡ በእርግጥ ቋንቋ በባሕሪው ቃላትን ከአንዱ ወደ አንዱ ይዋሳል፡፡ ነገር ግን እንደ ሕግ ውሰት የተጠናወተው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከሕክምና በስተቀር፡፡ ልዩነቱ ሕግ የሚያወራው ስለ መብትና ግዴታ ሆኖ፣ ሕግን አለማወቅ ብዙ ጊዜ መከላከያ የማይሆን፣ ከቅጣትም የማያድን መሆኑ እየታወቀና የሕግ በጋዜጣ መውጣት ሕዝብ እንዲያወቀው ሆኖ ሳለ፣ ከተለያዩ ቋንቋዎች በተለይም በሥርዓተ ትምህርታችን ውስጥ እንኳን ውስጥ የሌሉ ከአማርኛ ጋር በተለይ ዝምድና የሌላቸው ቃላት መጠቀም ተገቢ አይመስልም፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን ቃላት እንይ፡፡

ኖቫሲዮን፣ አክሲዮን፣ አንቲካ፣ ሱር ታክስ፣ ኤክሳይስ ታክስ፣ ኮንቲኔንታል ሸልፍ፣ ዶፒንግ፣ ኮሚሲዮን፣ ኮማንዲት፣ አፊዳቪት፣ ኮማንዲቴር፣ ፕሮሴቬርባል፣ ወዘተ…ጉድ ስሙልኝማ ለምሳሌ ሱር ታክስ አልከፈላችሁም ተብላችሁ በወንጀል ብትከሰሱ ምን ትላላችሁ? መክፈል ይኑርባችሁ ከምን ላይ ትከፍሉ ሳታውቁ ወንጀለኛ ብትባሉ ፍትሐዊ ነው ትላላችሁ? በእርግጥ ይህ የቃላት ውሰት ጥንውት ለአማርኛ ብቻ ሳይሆን እንግሊዝኛውም ላይ ያው ነው፡፡ እንደውም ሳይብስበት አይቀርም? ለምሳሌ “Petitory action, Pauliana action, Novation, Petitio Haereditatis, Bonus Pater Familias, Del credere, Flagrante Delicto etc…” በነገራችን ላይ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18(4)(ለ)፣ 41(8)  እና 54(6) ላይም “in lieu” (በምትኩ ለማለት) የሚል የጥንት የእንግሊዝኛ ቃል፣ ዘላን (Pastoralists) የሚል ስድብ አዘልና የቆዩ ቃላት፣  እጅ ከፍንጅ ለማለት (Flagrante Delicto) የሚል የላቲንኛ ቃል በመያዝ የቅርብ ጊዜና ለሁሉም ግልጽ መሆን ካለበት ሁኔታ ጋር የማይሄዱ ቃላትን በውስጡ ተሸክሟል፡፡

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ እሱም ለሕግ ባለሙያ አንዳንድ የላቲን ቃላት አለማወቅ ሕግ እዳለማወቅ ተደርጎ የሚቆጠር ይመስላል፡፡ ልክ ቄስ (የኦርቶዶክስ ክርስቲያን) የግዕዝ ቃላት ጣል ካላደረገ ቄስ የሆነ እንደማይመስለው ሁሉ ማለቴ ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ ባለበት ጊዜ ከአጠገቤ ካለ መደርደሪያ ላይ አንድ የሕግ መጽሔት አነሳሁና ነበብ ነበብ ሳደረግ እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አገኘሁ፡፡ ነፍሳቸውን ይማረውና እውቁ የሕግ ባለሙያና መምህሬ አቶ ዮሐንስ ኅሩይ ለጻፉት እንደ መግቢያ እንዲያገለግል በእሳቸው ወይም በሌላ ሰው የተጻፈ  ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡፡ “…neither considerations for public policy nor interpretation of the text in tota lege perspecta justify departure from it.” የሚል ነው፡፡ (Tota lege perspecta = looking at the whole of the law ማለት ነው፡፡) በመጀመሪያ ያለ የላቲን መዝገበ ቃለት እንዴት ሊታወቅ ይቻላል? ደግሞስ የአንድ ጽሑፍ ዋና ዓላማው መልእክትን በትክክል ማስተላለፍ አይደል? ግን የደብተራ ተንኮላዊ ጽሑፍ ከመሆን አመለጠ ትላላችሁ?

የቃላት እጨቃ
የሕግ ባለሙያዎችም ይሁኑ ሕግ አንድን ነገር ለመግለጽ ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸውን ቃላት በመደጋገም መጠቀምን ያዘወትራሉ፡፡ ይወዳሉም ማለት ይቻላል፡፡ ከእንግሊዝኛው ምሳሌ እንይ፡፡ “Null and void”, “rest, residue and remainder” የሕግ ባለሙያዎች በአብዛኛው ቃላት ካላንጋጉ፣ ወይም እየደጋገሙ ካልጻፉ የጻፋ የሚመስላቸው አይመስለኝም፡፡

ለተመሳሳይ ቃላት የተለያየ ትርጉም የመስጠት አባዜ
በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ታሪክ ብዙ ጊዜ በእንግሊዝኛ ይጻፉና (ከንግድ፣ ከፍትሐ ብሔርና ሌሎች በ1950ዎቹ በፈረንሳይኛ ከወጡት የተወሰኑ ኮዶች ውጭ) ከዚያም በአማርኛ ይተረጎማሉ፡፡ ተርጓሚዎቹ የሕግ ባለሙያ ካልሆኑ፣ ልክ ዋና ዋና ሕጎቻችን ላይ እንደሆነው ወጥ ትርጉም ላይኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ በፍትሐ ብሔር  ሕጉ ላይ ለ“possessory action” በዳኝነት የመጠየቅ ሥራ የእጅ ክስ በማለት ሲገልጻቸው፣ በእንግሊዝኛው ደግሞ “legal action” እና “action for possession” ይላቸዋል፡፡ በተለምዶ ደግሞ ሁከት ይወገድልኝ ክስ በማለት ይታወቃል፡፡ “Usufruct” የአላባ ጥቅም፣ የሪም መብት ሲል “Depreciation” ለሚለው ደግሞ አንዴ የእርጅና ቅናሽ ሲል አንዴ ደግሞ የዋጋ ጉድለት ይለዋል፡፡ “Goods” የሚለውን ደግሞ አንዴ ንብረቶች አንዴ ደግሞ ዕቃዎች ይለዋል፡፡ በመሆኑም ወጥ የሆነ የቃላት አጠቃቀም ባለመኖሩ ብዙ የሕግ ቃላት አምታች ትርጉም አላቸው፡፡ በአንድ የዕውቀት ዘውግ (ዲስፕሊን) ውስጥ የተለያዩ አውዳዊ ፍች (Contextual Meaning) ያላቸው ቃላት መኖራቸውን ያጤኗል፡፡ ልክ “goods” በንብረት ሕግ ትርጉሙ ንብረት ሲሆን፣ በግብርና በግዥ ሕግ ዕቃዎች፣ “Partner” የሚለውን የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የንግድ ሸሪክ ሲለው የንግድ ሕጉ ማኅበርተኛ እንደሚሏቸው ማለት ነው፡፡

የችግሩን መጠን ፍንትው አድርጎ ለማሳየት ከእነ አቶ ፋሲል አበበ ሥራ፣ ከፍትሐ ብሔርና ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ላይ በመውሰድ ከገለጹት የሚከተለውን እጠቅሳለሁ፡፡ “Jurisdiction” ለሚለው ”ሥልጣን”፣ “የፍርድ ቤት ሥልጣን”፣ “ክስ ለማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት” “Evidence” የሚለውን ደግሞ “የሥልጣን ማስረጃ”፣” “መረጃ”፣ “የሚያረጋግጥ ጽሑፍ”፣ “ምስክርነት” በማለት እንዲህ በተዘበራረቀ ሁኔታ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን፣ “Complaint, Accusation, Prosecution, Charge” ለሚሉት የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች “ክስ” በማለት አንድ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ታዲያ ሕገ መንግሥቱ “የዘሬን ብረሳ ያንዘርዝረኝ” በማለት ከእንዲህ ዓይነቱ የአተረጓጎም ስልት በመኮረጅ ይሆን እንዴ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ለሚሉት ሦስት ቃላትና ጽንሰ ሐሳቦች አንድ ትርጉም የሰጣቸው?

ከመደበኛ ትርጉማቸው ያፈነገጡ ቃላትን መጠቀም
ሕግ እንደሌሎቹ ዲሲፕሊኖች የራሱ የሆኑ ቃላት አሉት፡፡ ከእነዚህ ቃላት ውስጥ የተወሰኑትን አዘውትረን የምንጠቀምባቸው ሲሆን፣ በሕግ ዘንድ ግን የተለየ ትርጉም አላቸው፡፡ በእርግጥ የዚህ ዓይነቱን ችግር ለማቃለል በማሰብ አንዳንድ ሕጎች ሲወጡ ለአንዳንድ ቃላት ትርጉም ይሰጣል፡፡ በሁሉም ሕጎች ሁልጊዜም ትርጉም የሚሰጣት “ሰው” የምትለውን ቃል ጨምሮ፡፡ እዚህ ላይ አስተማሪያችን የነገረንን አንድ ገጠመኝ ላጫውታችሁ፡፡ አንድ የአኙዋ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነ ግለሰብ በአንድ ወቅት የፓርላማ አባል ነበርና ሁልጊዜም ሕግ ሲወጣ በአብዛኛው የሕጉ  አንቀጽ ሁለት የቃላት ትርጉም ስለሚይዝና ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ደግሞ ወለፈንዴ መስሎ ይሰማዋል፡፡ እናም ይህ አባል ሁልጊዜም ሰው ማለት በተፈጥሮና በሕግ የሰውነት መብት የተሰጣቸውን ያካትታል፤ ውኃ ማለት የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃን ይጨምራል፤ መሬት ማለት ምድሩን፣ ውኃውን እንዲሁም አየሩንም ይጨምራል የሚሉ ሐረጋት ሁልጊዜ እየተነሱ ሲሰለቹት ፓርላማውን ጥሎ ወደመጣበት ክልል ተመልሶ በመሄድ ሌላ ሥራ ይጀምራል፡፡ ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ለጓደኞቹ ሲናገር “ሰው ማለት ያው አኙዋ ነው፤ ውኃ ማለት ያው ባሮ ነው፤ መሬት ማለት ያው የጋምቤላ መሬት ነው፡፡ ምን ትርጉም ያስፈልጋቸዋል?” አለ አሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ ያጋጠመ አንድ ገጠመኝ ልጨምር ይኼንን ችግር የበለጠ ለማሳየት፡፡ የአንድ ከተማ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆነ ሰው ለአንድ ኢንቨስተር የክብር እንግዳ በመሆን ለፋብሪካ መትከያ የመሠረት ድንጋይ ይጥላል፡፡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት መሬት ደግሞ የአንድ ገበሬ ይዞታ ነው፡፡ ለዚያ ገበሬ በወቅቱ ካሳና የመሳሰሉት ጉዳዮች አልተፈጸሙለትም፡፡ እናም ይህ አርሶ አደር ከተማው ውስጥ ላለ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት (ብዙዎች እንደሚሉት የሁከት ፍርድ ቤት) የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርቦ የፍርድ ባለመብት ይሆናል፡፡ ታዲያ ያ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠው ባለሥልጣን ፍርድ ቤት ይሄድና ውሳኔ የሰጠውን/ችውን ዳኛ “ሁከት ማለት ምንድን ነው? እንዴት እኔ ሁከት እፈጥራለሁ? የመሠረት ድንጋይ መጣል እንዴት ሁከት ይሆናል? መጀመሪያ ሁከት ምን እንደሆነ የፍርድ ቤቱ በር ላይ ለጥፉ፤” በማለት ሌሎች ነገሮችንም አለ፡፡ ለዚህ ባሥልጣን ሁከት ማለት ምናልባት ጠብ፣ ጫጫታና የመሳሰሉት ነገሮች ያካተተ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በሕግ ግን ከዚህ በእጅጉ ይሰፋል፡፡ በመሆኑም ሕግ ከላይ የተገለጹት ዓይነት ቃላትን ስለሚጠቀም ማለትም በዘወትራዊ አገልግሎቱ ሌላ፣ በሕግ ደግሞ ሌላ ትርጉም መያዛቸው ለኅብረተሰቡ ጫና  መሆናቸው አይቀሬ የሆነ ችግር ነው፡፡

ከገመድ የረዘሙ ዓረፍተ ነገሮች የመጠቀም ልክፍት
አንድ የፍርድ መጽሐፍ አንስቼ ሳገላብጥ 96 ቃላት የያዘ ዓረፍተ ነገር አገኘሁ፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ የአዋጆች መግቢያ ግማሽ ይሁን አንድ ገጽ የሚጻፈው በአንድ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱም ላይ ተስተውሏል፡፡ የሕገ መንግሥታችን መግቢያ 150 ቃላት ባሉት 7 አንቀጽ (Paragraph) ሲኖሩት አንድ አንቀጽ የተዋቀረው ደግሞ መደበኛውን የሰዋሰው ሕግ በመጣስ ረጃጅም ሐረጋትን አንድ አንቀጽ በማድረግ ነው፡፡ አቶ ስዬ አብርሃ ተከሰውበት የነበረውን 1ኛው ክስ 145 አካባቢ ቃላት፣ 2ኛው ክስ ደግሞ ወደ 250 የሚጠጉ ቃላት የያዙ ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ የበለጡ ቃላት የያዙ ነጠላ ዓረፍተ ነገሮች ብዙ ይገኛሉ፡፡ ወገብ ቆራጭ ዓረፍተ ነገሮች የሕግ ቋንቋ መለያው ይመስላል፡፡

ለሥርዓተ ነጥብ ሕግጋት ተገዥ ያለመሆን
በቅርቡ አንድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ያወጣው መመርያ በሥራ ምክንያት እጄ ላይ ገብቶ እያነበብኩት እያለ አንድ ነገር አስገረመኝ፡፡ ረጃጅም ተደራራቢ ሐረጋት መጨረሻቸው ላይ በአራት ነጥብ ይገድባቸዋል፡፡ ዓረፍተ ነገሮቹ ግን አላላቁም፡፡ የሐረጋቱ መጨረሻም “ስለሆነ”፣ “በመሆኑ” ወዘተ የሚሉ ቃላት ናቸው፤ ነገር ግን በአራት ነጠብ ተደምድመዋል፡፡  የሥርዓተ ነጥብ ችግር ጎልቶ የሚታየው በፍርዶች ላይ ነው፡፡ ምናልባት በዳኞች በትክክል ጥቅም ላይ ይውላል የሚባል ሥርዓተ ነጥብ ካለ አራት ነጥብ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በመለስ የምስክሮች ቃል፣ ከተለያዩ ሕጎችና ጽሑፎች  የተላያዩ ሐሳቦች ሲጠቀሱ ትዕምርተ ጥቅስና የመሳሰሉት ነጥቦች ሥራ ላይ ሲውሉ አይስተዋልም፡፡ በሕግ አውጭ አካል ስላልፀደቀ የሥርዓተ ነጥብ ሕግጋት የአስገዳጅነት ባህርይ የላቸውም በማለት ይሆን?

ማጠቃለያ ወግ
አንድ ሪዳል የሚባል በአገረ እንግሊዝ ጠበቃና የሊድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆነ “ጁሪስፕሩደንስ” (ሕገ ፍልስፍና) በሚለው መጽሐፉ ላይ የመጀመሪያውን ምዕራፍ “I Hate Jurisprudence” (ሕገ ፍልስፍና ያስጠላኛል) ሲል ሰየመው፡፡ የምዕራፉም አጠቃላይ ይዘት ስለጁሪስፕሩደንስ የሕግ ቋንቋ አስቸጋሪነትና ለመረዳትም ያለውን አዳጋችነት በምሳሌ በማሳየት ነው፡፡ የአንድ ዓረፍተ ነገር ከፊሉን ብቻ በማንበብ ችግሩን የበለጠ መገንዘብ ይቻላል፡፡ “The predictive empiricism inherent in the neo-Thomist rejection of meta physics qua metaphysics typically charactersises the substantive epistemology so clearly demonstrated by Weberstrom’s implicit acceptance of the semantically normative assertions…’’ እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህ በእርግጥ እንኳንስ ለሕግ ሙያ ጨዋ/ጃሂል ለሆነው ኅብረተሰብ ይቅርና በሙያው ውስጥ ላሉትም አስቸጋሪ ነው፡፡ የሕግ ድርሰቶችም ይሁኑ ሕጎቹ ምን ያህል በተጠናገሩ ቃላት ወይም ዓረፍተ ነገሮች የተሞሉ እንደሆኑ ለማየት ሞክረናል፡፡ ስለሆነም የሕግ ቋንቋ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ለመሆኑ ብዙ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡ ከላይ የተገለጹት አብነቶች በቂ ይመስሉኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ይህ ችግር በአንድ ቋንቋ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በመሆኑም የሕግ አማርኛም የዚሁ ችግር ሰለባ መሆኑ ልዩ አያደርገውም፡፡ ዋናው ነገር ሕግ ቋንቋ ላይ የተንጠለጠለ ነውና በተቻለ መጠን ግልጽ፣ አጫጭርና ትክክለኛ ቃላትን መጠቀም የሚያስችል ተግባር ማከናወን አስፈላጊ ነው፡፡ የሕግ መዝገበ ቃላት በአማርኛና በሌሎች አገራዊ ቋንቋዎች ማሰናዳት ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ሕግ ስለመብትና ግዴታ የሚያትት ዲሲፕሊን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው መብትና ግዴታውን ሊያውቅ በሚያስችለው መልኩ መቀረፅና ፍርድ ቤቶችም በዚሁ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ያሻል፡፡ አለበለዚያ ግን በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንዳነሳነው ለአብዛኛው ሰው በማይገቡ መንገድ ማዘጋጀት ጉዳትም ጭምር አለው፡፡ በተለይም ሕግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም ወይም መከላከያ አይሆንም እያልን በማይታወቅ መንገድ ማዘጋጀት ያው አለማወቅን መጨመር ነው የሚመስለው፡፡ ከዚያ ውጭ “notwithstanding, herein under, a prior to, aforesaid” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ማዘውተር ድንጋሬን መጨመር ነው፡፡ በተጨማሪም የሕግ ቋንቋ የሕግ ባለሙያዎች ብቻ ይሆንና ለኅብረተሰቡ እንደ አስማት ቋንቋ ስለሚሆን ዓላማውን ስቶ የጠበቆች የእንጀራ ምንጭ ብቻ መሆኑ ተገቢ ስላልሆነ አስፈላጊው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው raswube@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ለሁለተኛ ጊዜ በአራት ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ 50 ሚሊዮን ማሳዎች በካዳስተር ካርታ የተደገፈ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሊሰጥ ነው፡፡
የካዳስተር ካርታ ሥራውን የሚያካሂዱት የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ናቸው፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ጌታሁን፣ የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሡልጣን መሐመድና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ነገር ግን የግብርና ሚኒስቴር ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በእጁ ባለማስገባቱ ሥራው እንዳልተጀመረ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር የሚያስፈልገውን ገንዘብ የዓለም ባንክ እንዲያቀርብለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የዓለም ባንክ ገንዘቡን በቅርቡ እንደሚለቅ ምንጮችም ገልጸዋል፡፡

ገንዘቡ እንደተለቀቀ ደኅንነት ኤጀንሲ ማሳዎቹን የአየር ፎቶ ያነሳል፡፡ ያነሳውንም ፎቶ ለካርታ ሥራ ኤጀንሲ ያስረክባል፡፡ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ የማሳዎቹን ካርታ እንደሚሠራና ለሚኒስቴሩ እንደሚያስረክብ ታውቋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት መንግሥት በየክልሉ በባህላዊ የአሠራር ዘዴ በመጀመርያ ደረጃ የገጠር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በማዘጋጀት 90 በመቶ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ማደሉ ታውቋል፡፡

ነገር ግን ቀደም ሲል የቀረበው ካርታ የተጠናከረ መረጃ የማይሰጥ በመሆኑና በመጀመርያ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ የነበሩበትን ክፍተቶች በማስተካከል እንደ አዲስ መረጃ የሚሰጥ ካርታ መስጠት እንደሚገባ ታምኖበታል፡፡ የገጠር መሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የካዳስተር የመሬት መረጃ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተኝቷል ተብሏል፡፡

አዲሱ ሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ የሚይዛቸውን መስፈርቶች በሚመለከት የግብርና ሚኒስቴር አራት ነጥቦችን ያስቀምጣል፡፡ የመጀመርያው የመሬቱ ትክክለኛ ስፋት፣ አቅጣጫና የሚገኝበትን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በቀላሉ መለየት በሚያስችል መንገድ ይዘጋጅ ይላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እያንዳንዱ የገጠር መሬት ይዞታ የሚለይበት ልዩ የማሳ መለያ ኮድ ይኖረዋል፡፡

ሦስተኛ ለገጠር መሬት ልውውጥና ማስተላለፍ አመቺ የሆነ መረጃ ሥርዓት ይዘረጋለታል፡፡ የመጨረሻው ነጥቡ ይዞታውን በሚያሳይ የካዳስተር ካርታ እያንዳንዱ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይኖረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ገንዘቡን እንዳገኘ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በድጋሚ ተመዝግበው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡