POWr Social Media Icons

Monday, February 11, 2013

ከአዲስ አበባ 250 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሻሸመኔ ከተማ ሲደርሱ ቀኙን ትተው ወደ ግራ ሲታጠፉ አንድ አረንጓዲያማ አካባቢ የሚያደርሰውን አስፋልት  ያገኛሉ፡፡
ከዚያም 11 ኪ.ሜ እንደተጓዙ በአገራችን የመጀመሪያው በደን የተሸፈነ ስፍራና በአገሪቱ ብቸኛው  የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ይደርሳሉ፡፡

ቀጥሎም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መዳረሻ ወደሆነው ዋቢሸበሌ መዝናኛ ሆቴል ከሦስት ኪ.ሜ ጉዞ በኋላ ያገኛሉ፡፡ በአሳብ ይዤአችሁ  የምወስዳችሁ ሥፍራ ወንዶ ገነት ይባላል፡፡ እነዚህን ከላይ የዘረዘርኳቸው ስፍራዎች ከ30 ዓመታት በፊት በነበሩበት ማራኪ የተፈጥሮ ውበታቸው ጋር ማየት በእርግጥ የማይቻል በመሆኑ የሰነድና የስው አስረጅ ካላገኙ የቀድሞውን ታሪክ ማወቅ አስቸጋሪ ይሆንቦታል፡፡ በአገሪቱ በደን ሽፋንና በተፈጥሮ መስህብ የማንንም ቀልብ የመግዛት አቅም የነበረው ስፍራ ዛሬ ትዝታ የመሆኑ ምስጢርና ተያያዥ የሥነ ምህዳር ችግሮች ሰለባ ሆኗል፡፡

ወንዶገነትና የአረንጓዴው ዘመቻ
በ1970ዎቹ መጀመሪያ በደርግ የሥልጣን ዘመን የአረንጓዴው ዘመቻ ደን ሠርቶ ማሳያ ማዕከል የነበረው ወንዶገነት ከተፈጥሮ ጫካ በተጨማሪ የባሕር ዛፍና ጥድ እንዲሁም ሌሎች ዛፎች የተሸፈነ እጅግ ማራኪ ስፍራ ነበረ፡፡ በወቅቱ  በስዊድናውያን ዕርዳታ የተቋቋመው የደን ኮሌጅ ዓላማም ከአካባቢው ባለፈ በአገሪቱ የደን ሀብትን ማስፋፋት ስለነበረ የወረዳው ዙርያ በዛፎች እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ ከነዚህም አካባቢዎች ዛሬ የጫት ማሳ ሆነው የቀሩትንና የቀድሞውን መላጌ ወንዶ ሥጋ ፋብሪካ (አሁኑ ኤልፎራ) የሚገኝባቸው ቀበሌዎችን ያካትታል፡፡ የደን ኮሌጅ ከሚገኝበት ሆሻ ከተማ ዙሪያውን ስድስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘውን ሌላ ትንሽ ከተማ ኬላና በለጬ አካባቢዎች እንዲሁም የወረዳው ዋና ከተማ ጩኮ (በቀድሞ ስሙ ባሻ) የላይኛው መረቦና ባጃ አካባቢዎች ታይቶ የማይጠገብ ደንና በአስገራሚ የዱር እንስሳት የተሞሉ ስፍራዎች ነበሩ፡፡ በአረንጓዴው ዘመቻ አረንጓዴ ሆነው የቆዩት ዛሬ በትዝታ የሚነሱ አካባቢዎች ሆነዋል፡፡

የወንዶገነት የቀድሞ ደን ፀጋዎች ሲታወሱ
 ወንዶገነት ከሃያ አመታት በፊት በሰው ሠራሽ ደንና የተፈጥሮ ጫካዎች የተሸፈነ አካባቢ ስለነበረ ዱኩላ፣ ሚዳቆ፣ ቀበሮ፣ ከርከሮ፣ የጦጣና ዝንጅሮ መንጋዎች፣ እጅግ አስገራሚ ተፈጥሮ ያላቸው አዕዋፋት፣ ጅብና የነብር ዝሪያዎች ጥሪኝና ሌሎች የዱር እንስሳት በስፋት ይገኙበት ነበር፡፡ በተለይ በወረዳው ዋና ከተማ በባሻ አካባቢ የቀድሞው ሥጋ ፋብሪካ የእንስሳት እርድ ያደርግ በነበረ ጊዜ ተረፈ ምርት ለጅብ ይጣል ስለነበረ የቤት እንሳስትና ሰውን ያን ያህል አይተናኮልም፡፡ ዛሬ የጅብ መንጋ ጨለማን ትቶ በቀን  እየወጣ ሰውን መተንኮስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከወንዶገነት ጥቅጥቅ ደን ጋር ከሚነሱ ፀጋዎች ከያቅጣጫው የሚፈሱ ምንጮችና ወንዞች ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ ይሁንና ደኑ ሲመናመን የምንጮቹ ቁጥር መቀነስ፣ ወንዞቹ መጠን በእጅጉ ወርዶ በትዝታ ቀርተዋል፡፡ ይህን እውነታ ወንዶገነት ዋቢ ሸበሌ መዝናኛ ሆቴል በተለያዩ ጊዜያት የመጎበኘት ዕድል የነበረው ሰው ማስታወስ ይቻለዋል፡፡ ከወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተንስተው ወደ ወረዳው ድንበር እስከሚደርሱ ለጆሮ በሚሰብ ድምፅ የሚፈሱት የኪላ፣ ጩኮ፣ ቡሳ (ወዲሳ) አቦሳ ወንዞች የሚነሱባቸው ተራራማ አካባቢዎች በደን ፈንታ በጫት ተክል በመሸፈናቸው መጠናቸው በክረምት እንኳን ዝቅተኛ ነው፡፡ ላይኛው መርቦ ለኤልፎራ እርሻ የመስኖ አገልግሎት የሚሰጥ  ከበጃ ቀበሌ የሚነሳው ወዴሳ ወንዝ መጋቢ የቁላባ ወንዝ ነው፡፡ አካባቢዎቹ በጫት ምርት ገቢ የሚተዳደሩ በመሆናቸው በበጋ ከሌላ አዝመራ ይልቅ ለጫት መስኖ ይጠቀማሉ፡፡ የፈረቃ አጠቃቀም እምብዛም ባለመለመዱ አንዳንድ ጊዜ የፍጥጫ ምክንያት ይሆናል፡፡

የወንዶገነት የደን ልብሷ የት ገባ?
 የወረዳው ሕዝብ ቁጥር ዕድገትን ተከትሎ የመሬት እጥረት ቀዳሚው ለደን ጥፋት መንስኤ መሆኑን የወረዳው የልማት ሠራተኛ አቶ ሽንኮሩ ተሰማ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተላጨ ፀጉር እንኳን ይበቅላል፣ የወንዶገነት ደን ግን እንዳያቆጠቁጥ ሆኖ ነው የጠፋው፤ ሁለተኛው መንስኤ የጫት ዋጋ በየጊዜው እየናረ መሄድ የደን መሬቱ በጫት ማሳ መተካቱ ነው፤ ሌላው ይቅርና ለአካባቢው የምግብ ዋስትና ትልቅ ፋይዳ ያለውን የእንሰት እርሻ ጫት እየያዘው ነው፡፡›› በአንድ ወቅት የተከሰተው ሰደድ እሳት በተለይ ለዋናው ደን መራቆት አስተዋዕፆ እንዳለውም ባለሙያው ይጠቅሳሉ፡፡ የእርሻ መስፋፋትና የቤት መሥሪያ እንጨት ፍላጎት መጨመር ለወንዶገነት ደን መሳሳት ምክንያት ነው፡፡ ያለምትክ መቆረጡ አሉታዊ ሚና እንዳለው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የደኑ መመናመን ያስተከተለው የሥነ ምህዳር ተፅዕኖ
የሰው ልጆች መጠለያ ቤት እንደመሆኑ የዱር አራዊት ቤታቸው ደን መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ እናም መኖሪያቸውን ያጡ ብርቅዬ እንስሳት ከመጥፋት ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡ በእርግጥ ደኑ መኖሪያቸው ብቻም ሳይሆን የመኖ ምንጫቸውም ስለሆነ እነዚያ የሚማርክ ተፈጥሮ ያላቸው እንስሳት ታሪክ ሆነው እየቀሩ ነው፡፡ ወንዶገነት በደንና የተፈጥሮ ጫካ ተሸፍና በነበረች ጊዜ እንደዛሬው የውሃ እጥረት አልነበረባትም፡፡ ምክንያቱም ክረምቱ ወቅቱን ጠብቆ ይከሰታል፣ በበጋም እርጥበትና የወንዞች መጠን ከክረምቱ ብዙም አያንስም፡፡ መሰል ሁኔታ አካባቢው አረንጓዴና ለምለም ሆኖ እንዲቀጠል አድርገውት ነበር፡፡ በዛሬዋ ወንዶገነት በጋና ክረምት ተዘበራርቀዋል፡፡ ሚያዝያና ግንቦት ሐሩር ጥቅምትና ኅዳር ደግሞ የሐምሌና ነሐሴ ዝናብ ይከሰትበታል፡፡ ይህም የሥነ ምዳህር እና የአየር ንብረት ለውጥ መከሰቱን አመላካች ነው፡፡

ወንዶገነት ዋቢሸበሌ መዝናኛ ሆቴል አካባቢ /ወሻ ከተማ/ ነዋሪ የሆኑ አቶ መተኪያ ሰይፉ ከአስርና አስራ አምስት ዓመት በፊት ይመጡ የነበሩት የውጭና የአገር ውስጥ ጎቢኚዎች ቁጥርን ከዛሬው ጋር ማወዳደር አይቻልም ይላሉ፡፡ ‹‹በሳምንቱ የዕረፍት ቀናት እንኳን በጣት የሚቀጠሩ ቱሪስቶችን ማየት ዘበት ነው፤›› በማለት የሚገልጹት አቶ መተኪያ ‹‹አይፈረድባቸውም ዛሬ ምን ሊያዩ ይመጣሉ? ወንዶገነት ታሪካዊ የውበቷ መገለጫ የነበረው አረንጓዴ ሽፋን ላይበቅል ተላጭቷልና›› ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡

የቀድሞዋን ወንዶገነት ማየት ይቻል ይሆን?
በእርግጥ የወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሮ ጫካ ከመጥፋት ጋር አብረው ታሪክ የሆኑ በርካታ የዛፍ ዓይነቶች ነበሩ፡፡ እነሱን መተካት ምናልባት ለኮሌጁም የቀለለ አይመስልም፡፡ በርካታ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት ዛሬ የሉም፡፡ በጣም የሚገርመው ለወንዶገነት መታወቂያ በመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ለመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚቀርበው የአቮካዶ ዛፎች እንኳን ተገንድሰው አልቀዋል፡፡ በተለይ በኤልፎራ እርሻ ልማት ዙሪያ ያሉት የላኛው መርቦ ነዋሪዎች በጥፍጥና የሚታወቀው ምርት የአቮካዶ ዛፎችን ለማገዶ ሸጠው ጨርሰዋል፡፡ መሸጣቸው አልከፋም ደግመው አለመትከላቸው እንጅ፡፡ እና ይህ ዛፍ በብዛት የሚገኘው በኤልፎራ እርሻ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ኩባንያው ከአቮካዶ በተጨማሪ በርካታ የዛፍ ዓይነቶችን በመትከል የሥነ ምህዳር ሚዛን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በኮሌጅ አካባቢ የባሕር ዛፍ ደን ቢወገድም ሌሎች ዛፎች በስሱ አሉ፡፡ ጥቅጥቅ ደን የሚባል አይደለም፡፡ በመሠረቱ በረሃን እንኳን አረንጓዴና ለምለም ለሰውና ለአራዊት ምቹ ማድረግ እየተቻለ ነው፡፡ የቀድሞው ወንዶ ገነት ሙሉ በሙሉ ማምጣት ባይቻልም የሥነ ምህዳር ቀውሶች እንዳይበረክቱ የዛፍ ተከላ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ኃላፊነት ያለው የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅና ማኅበረሰብ ላይ ነው፡፡

ወንዶገነት ዛሬ እንደቀድሞዋ አይደለችም፡፡ የውበቷ አካል የሆኑ በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎቿ የሉምና፡፡ ምናልባትም ከሃያ ዓመት በፊት የነበረችው ወንዶገነት መልሶ ለማየት ሌላ የአረንጓዴ ዘመቻ ወይም የዛፍ ተከላ ፕሮጀክት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ምንጮችና ወንዞች እንዲሁም የደን ሥፍራዎች በቀድሞ ይዞታቸው ማየት ከባድ ነው፡፡ የዱር እንስሳት ተሰድደዋል፤ ዕፀዋት ከጫካ ጠፍተዋል፡፡ ይልቅ ኑሮው በጉድጓድ ውስጥ የተመሰረተው ጅብ ብቻ ነው ማታ ማታ ወደ ባሻ ከተማ ቄራ አካባቢ እየተሯሯጠ ሕይወቱን ያስቀጠለው፡፡ ወንዶገነት የደን ልብሷ ዛፎች መሆናቸው ቀርቶ በጫት እየተሸፈነ ይገኛል፡፡ ጫት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዓይነተኛ የገቢ ምንጭ ነውና፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንዶ ገነትን ሲጎበኟት ‹‹ወንዶ›› ትባል እንደነበረና ለምለምነቷን አይተው ‹‹ምን ወንዶ ብቻ ገነትም ነው እንጅ›› ማለታቸውን ተከትሎ ወንዶ ገነት መጠሪያዋ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዛሬ ያንን ስሟን ከነውበቷ ማየት ከባድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት ማቀዷ ምናልባት ለወንዶ ገነት ዳግም ትንሣኤ ሊያመጣ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚኖር ለደን ኮሌጁና ለአካባቢው ማኅበረሰብ መልካም ዜና ነው ማለት ይቻላል፡፡
በአስፋው ብርሃኑ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሳ
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/other-sections/social-affairs/social/item/666-%E1%8B%A8%E1%8B%88%E1%8A%95%E1%8B%B6%E1%8C%88%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8B%B0%E1%8A%95%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%B3%E1%88%B3%E1%89%A2-%E1%8B%A8%E1%88%A5%E1%8A%90-%E1%88%9D%E1%88%85%E1%8B%B3%E1%88%AD-%E1%89%80%E1%8B%8D%E1%88%B6%E1%89%BD